ሴት ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ከሚያስቀሩ ምክንያቶች አንዱ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ እጦት ነው። በቅርብ ዓመታት በዚሁ ዙርያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ካሉ ሴቶች 22 ሚሊዮን የሚሆኑት የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም።
ችግሩ በአፍሪካ በተለይም በእኛ አገር ይጉላ እንጂ በአውሮፓና በምራባውያኑ ሴቶች ዘንድ መኖሩን ጥናቶች ይጠቁማሉ። ለአብነት በዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኙ ሴቶች መካከል 10 በመቶው የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ የመግዛት አቅም እንደሌላቸው ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከነዚሁ ሴቶች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች አቅም የንፅሕና መጠበቂያውን መግዛት የሚችል ቢሆንም በበቂ ሁኔታ የሚያስገዛ እንዳልሆነ ጥናቱ ያመላክታል። ጭራሹኑም 19 በመቶው በዋጋ ውድነት ምክንያት ጥራት የሌላቸውንና የማይመቹ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያዎችን እንደሚጠቀሙም በጥናቱ ተጠቅሷል። ዕድሜያቸው ከ14 እስከ 21 ዓመት ከሆኑ ሴቶች መካከል 71 በመቶ የወር አበባ መገልገያዎችን ከየመድኃኒት ቤቶችና መደብሮች ለመግዛት የሚሸማቀቁና የሚፈሩበት ሁኔታም መኖሩ በጥናቱ ተመላክቷል።
ወደ እኛ አገር ስንመጣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያዘጋጀውን አንድ ጥናት ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ግንዛቤ እንደሌላቸው፣ ሲመጣባቸው እንደሚያፍሩ፣ ንጽህና መጠበቂያውን መግዣ አቅም እንደሌላቸው በዚህ ምክንያትም አብዝተው ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩና እንደሚያቋርጡ አመላክቷል። የዛሬ ጽሑፋችንም በዚሁ ዙርያ ያተኮረና በመድረኩ የተገኙ የእቴጌ መነን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎችን ተሞክሮ ያካተተ ነው።
ተማሪዎቹ ትምህርት ቤታቸው እያንዳንዱ 10 ፍሬ የሚይዝ በወር ሁለት እሽግ የንጽህና መጠበቂያ (ፓድ) እንደሚሰጣቸውና እጥረት እንደማያጋጥማቸው ይናገራሉ። ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሴት ተማሪዎች እንዲህ እንደነሱ ትምህርት ቤት የንጽሕና መጠበቂያ መስጠትና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንዳለበትም ገልፀዋል።
ተማሪ ሀዊ ሰብስቤ ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ያየችው በ13 ዓመቷ ሲሆን ያኔ ሰባተኛ ክፍል ነበረች። የቤተሰቡ የበኩር ልጅ እሷ በመሆኗ ቀደም ብላ ስለ ወር አበባም ሆነ በዚሁ ወቅት መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄዎች የምታውቀው ምንም ነገር አልነበረም። በዚህ ጉዳይ ከእናቷ ጋርም አውርታ አታውቅም። ከመምጣቱ በፊት ራሷን እያመማትና ሆዷን እየቆረጣት ነበር። መኝታ ክፍሏ ውስጥ ተኝታ ነው ድንገት የመጣባት። አንሶላዋ በደም ተነክሮ ስታየው ደነገጠች። ዘላ ከአልጋዋ ላይ ስትወርድ በእግሯ ደም ሲወርድ እግሯ የተቆረጠ ሁሉ መሰላት። ፈሳሹ የሚወጣው ከእግሯ አለመሆኑን ስታይ እፍረት ተሰማት። በዚህ መካከል ወደ መኝታ ክፍሏ ከመጣችው እናቷ ለመደበቅም ሞከረች። ሆኖም እናቷ የሆነችውን በግልፅ በማየቷ ነገረቻትና ስለ ሁኔታው ተረዳች። እናቷ ለአባቷ ነገረችውናም አባትና እናቷ በቃ ልጃችን አደግሽ ትልቅ ሰው ሆንሽልን ብለው በማሳሳቅ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያና ቁሳቁሶችን እንዲሁም ሊያስፈልጋት ይችላል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ገዝተው ሰጧት።
ከዚህ በኋላ በአምስት ዓመት ዕድሜ የምትበልጣት ጓደኛዋ እንደነገረቻት በቤተሰቧ ውስጥ ግልፅነት ባለመኖሩና በመፍራቷ እስከ አሁን ለወላጆቿም ሆነ ለእህትና ወንድሞቿ የወር አበባ እያየች መሆኗን አልተናገረችም። ንጽህና መጠበቂያው የሚታደልበት ትምህርት ቤት ከመግባቷ በፊት የነበረችበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለች ትጠቀም የነበረው በነጠላና በተለያየ አሮጌ ጨርቅ ነበር። ይሄ ደግሞ በአካሏ ላይ ጉዳት ያስከትል እንደነበር ትናገራለች። ቤተሰቦቿ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው በመሆናቸው እሱንም እንደልብ ስለማታገኝ እያጠበች መጠቀም ግድ ይላታል። ቤት ውስጥ አጥባ እንዳታሰጣው ስለሚታይባት እርጥቡን አድርጋው ትመጣና ስትቀመጥ እርጥበቱ ቀሚሷን የሚያበላሽበት ሁኔታ እንደነበር አውግታለች።
ተማሪ ዮስቲና ተጋረድ የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው የሰባተኛ ክፍል ትምህርቷን ልታገባድድ ሁለት ወራቶች ሲቀራት ነው። የመጣባት በአጋጣሚ ቤት ውስጥ ሆና ስለነበር ፈጥና ለእናቷ ነው የነገረቻት። ተማሪዋ እንደገለፀችልን ታላቅ እህቷን ታይ ስለነበር በአየችበት ወቅት ትልቅ የሆነች ሆኖ ስለተሰማት ደስ ብሏት ነው የነገረቻት። አሁንም ቢሆን ውጪ ገጥሟት አያውቅም።
ነገር ግን የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ ትምህርት ቤት እያሉ የሚመጣባቸው ሴት ተማሪዎች ታውቃለች። ልብሳቸው በፈሳሹ የተበላሸባቸውም ገጥሟታል። ሴት ተማሪዎች ብዙ ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሲገጥማቸው ያፍራሉ። በአንዳንድ ትምህርት ቤት በዚህ ዓይነት ወቅት ለተማሪ የሚሰጥ የንጽሕና መጠበቂ ቢኖርም ደፍረው አይጠይቁም። ሆኖም ወደ ቤታቸው ሄደው ልብስ ቀይረውና ታጥበው ይመጣሉ። በተለይ ልብሷን የነካው ከሆነ ስለሚያፍሩ ሳይነግሯት እንዳላየ ሆነውም ያልፋሉ። ኮታቸውን ወይም ሹራባቸውን አውልቀው እንድትሸፍንበት የሚሰጡ ወንድ ተማሪዎችም አሉ። ፈሳሹ የሚበዛባቸው መውጫ ቀኑ የሚረዝምባቸው ተማሪዎች እጅግ ሲቸገሩ አስተውላለች። ለነዚህ ዓይነት ተማሪዎች ምን አልባት አሁን ላይ በትምህርት ቤታቸው አማካኝነት በወር የሚሰጠው ሁለት እሽግ የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ላይበቃቸው ይችላል።
ከዚህ በፊት የምትማርበት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪም ሆና የሚታጠበው ይሰጥ ስለነበር እሷ በወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ በኩል ተቸግራ አታውቅም ።
የእቴጌ መነን የሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ አናቶል መርድ 17 ዓመቷ ነው። አናቶል የወር አበባ ማየት የጀመረችው በ14 ዓመቷ ነው። ሁለት ታላላቅ እህቶች አሏት። እህቶቿ ቀደም ሲል ስለ ወር አበባ ይነግሯት ነበርና ጥሩ ግንዛቤ ነበራት። በተለይ እሷ የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ባየችበት ወቅት 10ኛ ክፍል የነበረችው እህቷ ብዙ ሴት ተማሪዎች በወር አበባ ወቅት ንጽሕና መጠበቂያ በማጣት እንደሚቸገሩ አንዳንዶቹም ቀድሞ ግንዛቤው እንደሌላቸውና እሷም የነዚህ ተማሪዎች ዕጣ እንዳይገጥማት በዚህ ላይ ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ስለ ወር አበባ ታሳውቃት ነበር። ቀደም ብላ ከእህቶቿ በመስማቷ ግንዛቤ ቢኖራትም ብዙ ጓደኞቿ እውቀቱ አልነበራቸውም። ግንዛቤውን ይይዙ የነበረው ግራ ተጋብተው እንደነበርም ታስታውሳለች። ብዙዎቹም ትምህርቱን ይከታተሉ የነበረው በእፍረት ተሸብበው ፊታቸው ላይ ላብ ቸፈ እያለ ሳይቀር መሆኑም ትዝ ይላታል። እነዚህ የጾታ አጋሮቿ ስለ ወር አበባ ቀደም ብለው ግንዛቤ ያላቸው ሲሆኑ እሷም ትምህርቱን በምትከታተልበት ወቅት ተመሳሳይ ስሜት እንደነበራት አትዘነጋውም። በዚህ ትምህርት ሰዓት ወንድ ተማሪዎች በፊናቸው ይስቁና ያላግጡ የነበረበትንም ሁኔታ ታዝባለች። ያም ሆነ ይህ የአገራችን ኢትዮጵያ ዋና መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩና የተወለዱ ሴት ተማሪዎች ስለ ወር አበባ እንደ እሷ የተሻለ ግንዛቤ ያላቸው ለመሆናቸው በተለያየ ምክንያት ከተለያዩ የገጠር አካባቢዎች መጥተው ከነሱ ጋር በመጀመሪያ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት በአንድ ክፍል ሲማሩ ከነበሩ ሴት ተማሪዎች ጋር በማነፃፀር ማየት ችላለች።
በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ ያገኘናትና ተሞክሮዋን ያካፈለችን አደራ ባርክልኝ ተወልዳ ያደገችው በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን መርጦ ለማርያም የምትባል የገጠር ከተማ ውስጥ ነው። አደራ እንደነገረችን የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ የታያት ደብል ደብል መታ በ14 ዓመቷ የደረሰችበት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነበር። ‹‹ስለ ወር አበባ ቀደም ብሎ ምንም ዓይነት ግንዛቤ አልነበረኝም ብል ይሻላል›› ስትል ትውስታዋን ትጀምራለች። ምክንያቱም እሷ ተወልዳ ባደገችበት አካባቢ ስለ ወር አበባ ከወላጅ ጋር ማውራት ነውርና እጅግ አሳፋሪ ነው። ሌላው ቀርቶ አዋቂ ልጅ ፊት አያወራም። ያወራ ልጅ ቢገኝ አዋቂ ሲያወራ ማዳመጥ ልጅን እንደባለጌ ስለሚያስቆጥረው ይገሰጽና ይባረራል። ሰባተኛ ክፍል ሆና በተወሰነ መልኩ የተማረችውም ቢሆን አስተማሪውም ሆነ ተማሪው ነውረኛ ጉዳይ አድርጎ ስለሚቆጥረው ነካ ነካ አድርጎ የማስተማርና ከልብ ያለማዳመጥ ሁኔታ በመኖሩ ተዘንግቷታል። እንደምታስታውሰው ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣባት ክፍል ውስጥ በትምህርት ላይ ሳለች ነበር። ሞቃትና ፈሳሽ ነገር ሲሰማት ክፉኛ ደንግጣለች። እራሷን እንደምንም አረጋግታ ፈሳሹ ምን ሊሆን እንደሚችል ስታስብ ራሷን ስታ ሽንቷን የለቀቀችው መሰላት። ሆኖም ፈሳሹ ሲጨምር ያለ ውስጥ ሱሪ የለበሰችውን የውስጥ ልብስ አልፎ ወደ ቀሚሷ መዝለቁን ስታስተውል ድንጋጤው ወደ ብርክ ተለውጦ መንቀጥቀጥ ጀመረች። ‹‹ስለ ክብረ ንጽሕናም ሆነ ስለ ወር አበባ ባላውቅም ክብረ ንጽሕናየን ያጣሁ ሁሉ መስሎኝ ነበር›› አደራ በዚህ ምክንያት የክፍሉ ተማሪ አይደለም የትምህርት ቤቱ ተማሪ ወጥቶ እስከሚያልቅና በወር አበባ ፈሳሽ የረጠበው ቀሚሷ ከወንበሩ ጋር እስኪጣበቅ ከተቀመጠችበት ወንበር ላይ አልተነሳችም። ሰርክ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት አብራት ለምትሄደውና ከአጠገቧ ለምትቀመጠው ጓደኛዋ እንኳን የሆነችውን አልነገረቻትም። እንዲያውም ከወንበሬ ከተነሳሁ የሆንኩትን ታይብኛለች በሚል እጅግ ፈርታና ተሸማቅቃ ነበር። ምን እንደሆነችና ለምን ከተቀመጠችበት እንደማትነሳና ወደ ቤት እንደማይሄዱ በጥያቄ ስትወተውታት ቆይታ ምላሽ ስታጣ ያመማት ስለመሰላት ወደ ቤቷ ሄዳለች። አደራ ሹራቧን አውልቃ ፈሳሽ የነካው ቀሚሷ ላይ በማሸረጥ ወደ ቤቷ ብትሄድም የሆነችውን ለቤተሰቦቿ ለመንገር አልደፈረችም። የወር አበባዋ መፍሰሱን እስኪያቆም ትምህርት ቤት አልሄደችም። አመመኝ በማለት ጓዳ ውስጥ ተደብቃ ነው የሰነበተችው።
በአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተርና የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ መለሰ ድንቁ ያቀረቡትን ጥናት ዋቢ አድርገው እንደገለፁት በወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ እጦት ምክንያት በርካታ ሴቶች ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ። በራስ መተማመናቸው ይቀንሳል። ራሳቸውን የሚያገሉበትም ሁኔታ አለ። ትኩረት የሚሰጡት ከወር አበባ ጋር ተያይዞ ለሚገጥማቸው ችግር እንጂ ለትምህርት ባለመሆኑ በክፍል ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ ይቀንሳል። ውጤታማም አይሆኑም። ትምህርት አቋርጠው ያለ አስተማሪ ፈቃድ ከክፍል ውስጥ ይወጣሉ። በአጠቃላይ በዚሁ በወር አበባ ምክንያት አንዲት ሴት ተማሪ በወር ከአንድ እስከ አራት ቀን ትቀራለች። ይሄ በዓመት ሲሰላ ከ22 እስከ 40 ቀን ይደርሳል። በመሆኑም ጥናቱ እነዚህንና ሌሎች ምክንያቶችን መሠረት አድርጎ ለሁሉም ለመንግሥት ትምህርት ቤት ሴት ተማሪዎች የወር አበባ ንፅሕና መጠበቂያ በጀት ተይዞለት መሰጠት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል። እንደሌሎቹ ሁሉ በግዢ ሥርዓቱ በጀት ሊያዝለት ይገባል ብለዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2014