በኢትዮጵያ ዋጋቸው ጣሪያ ነክቶ አልቀመስ ካሉ ዘርፎች መካከል የቤት ግብይት አንዱ ነው። በተለይ በከተሞች እንኳንስ ጥሩ ቤት መግዛት፣ ቤት መከራየትም ለአብዛኛው ዜጋ ቅንጦት ሆኖ እየተስተዋለ ነው። የዚህ ችግር መሠረታዊ ምክንያት የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን እንደሆነ ቢገለፅም ይህን አለመመጣጠን የሚፈጥሩ ሌሎች መንስኤዎች አሉ።
ከእነዚህም መካከል አንዱ የዘርፉ ግብይት በፍትሐዊ የገበያ ሥርዓት እንዲከናወን የሚያስችል የተቀናጀና ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት አለመኖሩ እንደሆነ ይጠቀሳል። ይህ የመረጃ ክፍተት ደግሞ የዘርፉ ግብይትና አስተዳደር መደበኛ ባልሆነ ሥርዓትና ተዋንያን (Informal System) እንዲመራ አድርጎታል። የቤት ፍላጎትና አቅርቦት የተመጣጠነ ካለመሆኑም በተጨማሪ በቤት ግብይት ሥርዓት ውስጥ በቂ የሆነ መረጃ አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል።
‹‹እፎይ ፕላስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የተባለው ተቋም ይህን ችግር በማቃለል የቤት ግብይትን የሚያዘምን መላ ይዞ ወደ ገበያው መቅረቡን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። ድርጅቱ ይፋ ያደረገው ቴክኖሎጂ ‹‹እፎይፕላስ ዶት ኮም (efoyplus.com)›› የተሰኘ የድረ-ገፅ አገልግሎት ነው። ዋና ትኩረቱን በቤት ግብይት (ኪራይ፣ ሽያጭና ግዢ) ላይ አድርጎ በገበያ ላይ ያሉትን የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን የሚያስከትሉ ተግዳሮቶችን የመቀነስ እንዲሁም የኢትዮጵያን የግብይት ሥርዓት የተሳለጠና ውጤታማ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል። የእፎይ ፕላስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ዘመነ የሰጡንን ማብራሪያ ይዘን ቀርበናል።
የቴክኖሎጂው ምንነትና አገልግሎት አሰጣጥ
የቤት ግዢና ሽያጭ ገበያው በዓመት እስከ 400 ቢሊዮን ብር ግብይት የሚከናወንበት እንደሆነ የገበያ ዳሰሳ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከዚህ ግብይት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆነው የሚከናወነው መደበኛ ባልሆኑ የዘርፉ ተዋንያን (ባለንብረቶች፣ አሻሻጮች/ደላላዎች) አማካኝነት ነው። በኪራይ የሚከናወነው ግብይት ደግሞ ከዚህም የበለጠ ነው። ይህን ያህል ግዙፍ ገንዘብ የሚዘዋወርበት ገበያ ግን በሚገባው ልክ በሥርዓት እየተመራ አይደለም።
የቤት ፍላጎትና አቅርቦት መመጣጠን ስላልቻለ የቤት እጥረት ይስተዋላል። በኪራይም ሆነ በግዥና ሽያጭ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት አለ። ይህ ችግር እንዲፈጠር ዋነኛ መንስዔ የሆነው አንድ የተማከለ የግብይት ማዕከልና የመረጃ ፍሰት አለመኖሩ ነው። ይህም አብዛኛው የዘርፉ ግብይትና አስተዳደር መደበኛ ባልሆኑ ተዋንያን እጅ እንዲወድቅ ምክንያት ሆኗል።
በቤት ግብይት ዘርፍ የሚዘዋወረው ይህ ግዙፍ ገንዘብ በሚመጥነው ቴክኖሎጂ የተደገፈ ባለመሆኑ እፎይፕላስ (efoyplus.com) ይህን አሠራር ለማዘመን መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል። ቴክኖሎጂው ጊዜውን የጠበቀና ሰዎች በቀጥታ እንዲገበያዩ ማድረግ የሚያስችል ቀላል ዘዴ ነው።
ይህ የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ሰዎች በኮምፒዩተራቸው ወይም በስልካቸው አማካኝነት መጠቀም የሚችሉት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የኦንላይን/ድረ ገፅ ተደራሽነት የሌላቸው አካላት ደግሞ በ9793 የጥሪ ማዕከል (Call Center) አማካኝነት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ቴክኖሎጂ ነው። በጥሪ ማዕከሉ በኩል አገልግሎቱን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ዝርዝር መረጃዎችንና ፍላጎቶቻቸውን በማስመዝገብ የግዢና የሽያጭ ፍላጎታቸውን ማሳካት ይችላሉ።
በአጠቃላይ ቴክኖሎጂው የሚከራይና የሚሸጥ ቤት አቅራቢዎችን ከፈላጊዎች ጋር የማገናኘት፣ የግንባታ ዕቃዎችን የመሸጥና የመግዛት እንዲሁም ቤትን በመግዛትና በመሸጥ ሂደት የውክልና አገልግሎት የመስጠት ተግባራትንም ያከናውናል። አገልግሎት ፈላጊዎች በአቅራቢያቸው የሚገኝ የሰለጠነ አሻሻጭ ከፈለጉም በጥሪ ማዕከሉ በኩል እንዲያገኙም የሚያስችል አሠራርም አለው። አሻሻጮቹም ለአገልግሎት ፈላጊዎች ምክርና እርዳታ ይሰጧቸዋል።
በአገሪቱ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እያደረጉና በኢኮኖሚው ውስጥ ችግር እየፈጠሩ ከሚገኙ መካከል አንዱ በቤት ግዥና ሽያጭ ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረትና ተገቢ ያልሆነ የገበያ አመራር ነው። በዚህ ዘርፍ በዝርዝርና ሥርዓት ባለው መልኩ የተጠናቀረ መረጃ የለም። እፎይፕላስ ይህን ችግር ታሳቢ በማድረግ የዘርፉን መረጃዎች ወደ ቴክኖሎጂው ቋት እንዲገቡ በማድረግ አገልግሎት ፈላጊዎች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ ይጥራል። በዚህ መንገድ በገበያው ላይ አማራጭ ቤቶችን ማቅረብና ያሉትንም ማስተዋወቅ የሚቻልበት መድረክ ይፈጠራል።
ብዙ አሻሻጮች የዋጋ ንረትን በማባባስ ረገድ አስተዋፅኦ አላቸው፤ በተጨማሪም ቁጥራቸው ጥቂት በማይባሉ ባለሀብቶችም ክፍያቸውን ይከለከላሉ። ይህ የሆነው ደግሞ አሻሻጮቹ ኢ-መደበኛ ሆነው ስለሚሠሩ ነው። እፎይፕላስ የቤት ግዢና ሽያጭ ገበያው በመረጃና በሕጋዊ አሠራር ላይ ተመስርቶ እንዲከናወን የማድረግ ዓላማ ያለው በመሆኑ፣ አሻሻጮች (ደላላዎች) ስልጠና እንዲያገኙና ሥራቸውን በፍትሐዊ መንገድ እንዲሠሩ የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል። አሻሻጮች ተገቢውን ስልጠና አግኝተውና መረጃ ኖሯቸው የሚሠሩ ከሆነ ጥቅማቸውን ያስከብራሉ፤ ገበያውም በሥርዓት እንዲመራ ሚና ይኖራቸዋል። እፎይፕላስ ይህን እውን የሚያደርጉና አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ደረጃዎች (Standards) ያዘጋጃል።
ቴክኖሎጂውን የማበልፀግ ሥራ ከተጀመረ ቆይቷል። ሃሳቡ የተወጠነው ከሦስት ዓመታት በፊት ነው። ሥራው ከሃሳብነት ተሻግሮ ለትግበራ ከበቃ በኋላም ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፤ አስተያየቶች ተሰብስበዋል፤ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል። በሙከራ ከቆየና ዓላማውን ለማሳካት የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ካደረገ በኋላ ይፋ ተደርጎ ለአገልግሎት በቅቷል። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተመዘገበ ሕጋዊ ድርጅት ነው።
የቴክኖሎጂው ልዩ ገፅታዎች
ቴክኖሎጂው መሰል አገልግሎቶችን ከሚሰጡ ተቋማትና አሠራሮች የሚለዩት ባህርያት አሉት። ከእነዚህ ባህርያት መካከል አንዱ ቴክኖሎጂው ሻጭና ገዢን በቀጥታ ማገናኘት መቻሉ ነው። ለዚህ የሚጠየቀው የአገልግሎት ክፍያ (Service Fee) ዝቅተኛ ነው። አሁን ገበያው ላይ ባለው አሠራር አሻሻጮች ከቤት ኪራይ 10 በመቶ፣ ከሽያጭ ደግሞ ሁለት በመቶ ክፍያ ይቀበላሉ። አሻሻጮች የሚቀበሉት ይህ ክፍያ በእፎይፕላስ ቴክኖሎጂ የአገልግሎት ክፍያ (Service Fee) የሚባል ሲሆን የሽያጭ ክፍያውም ከአንድ በመቶ በታች ነው።
ለእያንዳንዱ ቤት የሚጠየቀው የክፍያ መጠን እንደቤቱ ዓይነትና እንደገዢው/ሻጩ ፍላጎት የሚወሰን ቢሆንም ሁሉም ክፍያዎች ከአንድ በመቶ በታች ናቸው። ግዢና ሽያጭ የሚከናወንባቸው ቤቶች የንግድ አልያም የመኖሪያ (Residential Houses) ሊሆኑ ይችላሉ። የመኖሪያ ቤቶችም ደግሞ የቅንጦት (Luxury) አልያም የጋራ መኖሪያ (Condominium) ሊሆኑ ይችላሉ። የአገልግሎት ክፍያ የሚጠየቀው በአገልግሎት ፈላጊው ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ነው። አብዛኛው የመኖሪያ ቤት ፈላጊ ኅብረተሰብ መደገፍ ያለበት ስለሆነ አገልግሎቱ በነፃ የሚሰጥ ይሆናል። ሻጩ ለድረ ገፁ ለሚያቀርበው የቤቱ መረጃዎች ድርጅቱ ክፍያ አይጠይቅም። ሽያጭ በሚፈፅምበት ወቅት አሁን ከሚከፈለው ሩብ እንኳ የማይሆን የአገልግሎት ክፍያ ይቀበላል። በዚህም ገዢና ሻጭ እስከ 200ሺ ብር ያተርፋሉ።
ቴክኖሎጂው የሚጠቀማቸው መተግበሪያዎች ቀላልና ሁሉም ሰው በሚረዳው መንገድ የተሠሩ ናቸው። በአማርኛ፣ በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው።
ቴክኖሎጂው ቀጥተኛ የሆነ የፋይናንስ ትስስር ለመፍጠርም ያስችላል። ቤት መግዛት የሚፈልግ ሰው ብድር ከፈለገ በዚሁ መተግበሪያ ላይ በቀጥታ የብድር ሂሳብ ቁጥር መክፈት ይችላል። ድርጅቱ የብድር ጥያቄውን ከድርጅቱ ጋር በትብብር ለመስራት ትስስር ለፈጠሩ ባንኮች ይልካል። ይህ ሁኔታ በተለይም ለዳያስፖራው ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
ለአገራዊ ኢኮኖሚው የሚኖረው በጎ አስተዋፅኦ
እፎይፕላስ ቴክኖሎጂ ለአገራዊ ምጣኔ ሀብት መሻሻል የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። በዋናነት በቤት ግዥኛ ሽያጭ ዘርፍ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት ያስችላል። ቴክኖሎጂው ለቤት ግብይት መረጃ ትኩረት ይሰጣል። ግብይቱ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ደግሞ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት ይቀንሳል። የግብይት ሂደቱም ፈጣን ይሆናል። የግብይት ሂደት ፈጣን ሲሆን የምጣኔ ሀብት እድገትም ይጨምራል። ለአጠቃላይ አገራዊ የዋጋ ንረት አስተዋፅኦ ካላቸው ነገሮች አንዱ በቤት ግብይት ዘርፍ ያለው የዋጋ መጨመር በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ያለውን ዋጋ መቆጣጠር ለጠቅላላው የዋጋ ንረት ቅነሳ ሚና ይኖረዋል።
በቤት ግብይት ሂደት ውስጥ ከድርጅቱ ጋር በትብብር የሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት (ከካርታ፣ ከውልና ማስረጃ፣ ከፍርድ ቤት ጋር የተገናኙ) አሉ። ይህ ትብብርም በግብይት ሂደት ውስጥ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለመቀነስና ለመቆጣጠር ያስችላል።
ግብይቶች ሕጋዊ፣ ግልጽና ፍትሐዊ ሲሆኑ መንግሥት ከግብር የሚያገኘውን ጥቅም ያስከብራል። መንግሥት ከግብር የሚያገኘው ገቢ ለአገር ልማት የሚውል በመሆኑ በሂደቱ አገርና ሕዝብ ተጠቃሚ ይሆናሉ ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በቀን፣ በወርና በዓመት የተመዘገበው የግብይት ብዛት በመነሳት ጥናቶችን የማካሄድ እቅድ ስላለ በቴክኖሎጂው የትግበራ ሂደት የሚገኙ ውጤቶች ለፖሊሲ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ይሆናል ተብሎም ይታመናል።
በትግበራው የተገኙ ውጤቶች
እፎይፕላስ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ይፋ ከተደረገ በኋላ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ግብይት ለመፈፀምና አገልግሎቱን ለማግኘት ጥያቄ ያቀረቡ ግለሰቦችና ተቋማት ቁጥራቸው በየቀኑ እየጨመረ ነው። ይህም ዳያስፖራው ኅብረተሰብ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገሩ በመላክ ገንዘቡን ሀብት በማፍራት ላይ እንዲያውለው ያስችለዋል። ብዙ አሻሻጮችም (Agents) ከድርጅቱ ጋር አብረው ለመሥራት ፍላጎት አሳይተዋል።
እፎይፕላስ የተማከለ የመረጃ ቋት አደራጅቷል። ብዙ ሪል ስቴቶች (Real Estates) ከእፎይፕላስ (efoyplus.com) የመረጃ ቋት ጋር ትስስር ፈጥረዋል። በቀጣይም የቀሩት ሪል ስቴቶች ወደ ቴክኖሎጂው የመረጃ ቋት እንዲገቡ ይደረጋል። ድርጅቶቹ መረጃዎቻቸውን ወደ መረጃ ቋቱ ሲያስገቡ አማራጭ ቤቶቻቸውን፣ ከዚህ ቀደም ያላቸውን የአፈፃፀም ብቃት እንዲሁም ወደፊት ያሏቸውን የፕሮጀክት አማራጮች በተመለከተ መረጃዎችን ለኅብረተሰቡ ያቀርባሉ። በዚህም የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ግብይት እንዲኖር ምቹ ዕድል ይፈጠራል።
በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን አለመመጣጠን ለማስተካከል የቤት ገንቢዎች ድርሻ ወሳኝ በመሆኑ የእነርሱ በቴክኖሎጂው መታቀፍ ችግሩን ለማቃለል ትልቅ ሚና ይኖረዋል። ገንቢዎች ስለድርጅታቸው ሥራዎች በቂ መረጃዎችን ስለማያቀርቡ ከኅብረተሰቡ ጋር በሚፈለገው መጠን ተገናኝተዋል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። እፎይፕላስ ገንቢዎች በቂ መረጃ እንዲያቀርቡ ያደርጋል። የመረጃ ፍሰቱ ፈጣን ከሆነ ደግሞ ግብይትና የገንዘብ ፍሰቱም ፈጣን ይሆናል።
ሌሎች አገልግሎቶችና እቅዶች
እፎይፕላስ በቤት ግብይት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮች ቅድሚያ የሚሹ በመሆናቸው ቀዳሚ ትኩረቱን በዚህ ጉዳይ ላይ ቢያደርግም ከቤት ግብይት በተጨማሪ ሌሎች የዘርፉን ተግባራት የማከናወን እቅድም አለው። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የሀብት አስተዳደር (Asset Management) ሥራ አንዱ ነው። ግብይት ከፈፀሙና ግንባታ ካከናወኑ በኋላ የሀብት አስተዳደር ሥራ እንዲከናወንላቸው ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦችና ተቋማት አገልግሎቱን የመስጠት እቅድ አለው።
በቤት ግዥና ሽያጭ ዘርፍ ጥናቶችን በማካሄድ ለመንግሥት ፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት ለማቅረብም ይሠራል። የገበያ ትስስር መፍጠርም ሌላው ተግባር ነው። የቤት ዋጋ ሊቀንስ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ የግንባታ ግብዓቶችን አቅራቢዎችንና ፈላጊዎችን በማገናኘት ነው። ለአሻሻጮች ስልጠና በመስጠት ባለሙያዎቹ ዘመናዊና ፍትሐዊ በሆነ ግብይት ውስጥ እንዲሳተፉና ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር ለማድረግ ጥረት ያደርጋል።
የእፎይፕላስ ዋነኛው ፍላጎትና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈጣንና የሰለጠነ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ነው። ለዚህ ደግሞ የተቀናጀ የመረጃ ሥርዓት ያስፈልጋል። የእፎይፕላስ ቴክኖሎጂ መነሻም ይኸው ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ለ25 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት በሚያከናውናቸው የማስፋፊያ ተግባራት ደግሞ እስከ 200 ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅዷል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም