ዛሬ ስለ ለውጥ ሕግ እናወራለን። የለውጥ ሕግ የሕይወት ሕግ ነው። የሕይወት ሕግ ደግሞ የአጠቃላዩ እንቅስቃሴአችን ሕግ ነው። ሕይወት ሶስት ቀን ናት.. ትላንት ዛሬና ነገ ስል ተነስቻለሁ። ትላንት ዛሬን የምናደምቅበት ብዕራችን ነው ስል ቀጥያለሁ። ነገ ደግሞ ምን እንደሆነ የማናውቀው ለእያንዳንዳችን ባዳ ቀን ነው ስል ሰልሻለሁ። እኚህ ሶስት የጊዜ ፈረቃዎች በሕይወታችን ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ እየገለጥን እናያለን። ዓለም ሁለት ዓይነት ሰዎች አሏት፤ ከትላንት የሚማሩና ትላንትን የሚያማርሩ። ከትላንት የሚማሩ ሁሌም አሸናፊዎች ናቸው። የዚህን ዓለም ብርቱና ስኬታማ ሰዎች ብታስተውሉ በትላንት ተምረው ዛሬን መልካም ያደረጉ ናቸው። በእኛ አገር እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው። ትላንትን ለመማረሪያ እንጂ ለመማሪያ ስናደርገው አንታይም። የዛሬ ችግሮቻችንን ከትላንት አብራክ ውስጥ ጎርጉረን ያወጣናቸው ናቸው። በትላንት የዛልን፣ በትላንት የምንኖር ሕዝቦች ነን። ሰው ትላንትን መርሳት ካልቻለ ዛሬ አይኖረውም። ሰው መኖር የሚጀምረው ትላንትን መርሳት ሲችል ብቻ ነው።
ትላንት ከትዝታ ባለፈ በእኛ ሕይወት ላይ ሕላዊነት የለውም። አብዛኞቻችን በትላንት ዛሬን የምንኖር ነን። ለዛም ነው እንደ ሃገር ከስረን የቆምነው። ትላንት ለዛሬ የሚሆን ጉልበት የለውም። እንድንማርበትና ዛሬን መልካም እንድናደርግበት መጥቶ የሄደ እንጂ በቁጭትና በሮሮ እንድናስታውሰው ሆኖ የተፈጠረ አይደለም። እኛ ኢትዮጵያውያን ከትላንት ብንማር የሚያስተምሩን በርካታ ታሪኮች ነበሩን። ግን አንማርም፤ ዛሬን በትላንት መንፈስ የምንኖር ነን። በትላንት ጉያ ውስጥ የተደበቁ ብዙ የአንድነት ታሪኮች፣ ብዙ የመለያየት ታሪኮች አሉን። የሚጠቅመንን እየወሰድን የማይጠቅመንን መተው አናውቅበትም። ዛሬዎቻችን በትላንት ቁርሾ፣ በትላንት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የተጨማለቁ ናቸው። አዲስ ዛሬ መፍጠር አልቻልንም። ሰው ከትላንት ተምሮ አዲስ ዛሬን መፍጠር ካልቻለ ሕልውናውን አደጋ ላይ እየጣለ ነው የሚሄደው። ስህተት የሰውን ልጅ ካለወጠው በምንም አይለወጥም። ትላንት መጥቶ የሄደው እንድንማርበት ነው። በትላንት ችግሮቻችን መማር ካልቻለን የምድርን ትልቁን የለውጥ ሕግ ዘንግተናል ማለት ነው።
ለምን ስልጣኔ የራቀን ይመስላችኋል? ፊት ተፈጥረን ለምን ኋላ የቀረን ይመስላችኋል? ለዛሬ የሚሆን አዲስ ልብ ስለሌለን ነው። ችግሮቻችንን ችግር ፈጣሪ በሆነ ሀሳቦቻችን ለመፍታት ስለምንሞክር ነው። በመሠረቱ ችግር.. ችግር ፈጣሪ በሆነ ጭንቅላት አይፈታም። የመፍትሔ ስፍራው ምክንያታዊ አዕምሮ ነው። ጭንቅላታችን በትላንትና በአምና የፖለቲካ አስተሳሰብ ተመርዞ፣ በትላንት የታሪክ ቁርሾ ተይዞ ከፍ ማለትም ሆነ ለችግሮቻችን መፍትሔ መውለድ አንችልም። ለአስተዋይ ሰው በስህተት ውስጥ መፈጠር ልክ በሆነ ነገር ላይ ከመፈጠር የበለጠ አዋጭ ነው። ብዙዎቻችን ስህተት የሚያበላሸን እንጂ የሚሞርደን አይመስለንም። ለዚህም ነው በእውቀት ድርቀት የምንሰቃየው። ስህተት ዋጋ ቢስ የሚሆነው የማንማርበትና የማንለወጥበት ከሆነ ብቻ ነው። ዕውቀት የትም አለ፣ የሰው ልጅ የትም፣ በማንም ሊማር ይችላል። በስህተት ውስጥ የመማርን ያክል ዕውቀት ግን የትም አይገኝም። እንከን አልባ እውቀት አንድ ጊዜ ነው የሚቀርጸን የስህተት እውቀት ግን እድሜአችንን ሙሉ የሚከተለን ፍጹምናችን ነው። እኛ ግን ከስህተቶቻችን አንማርም። ትላንትን ዋና የችግሮቻችን ምንጭ አድርገን የምንገልጥ ነን። ስህተት ካልተማርንበት ሌሎች ችግሮችን እየፈጠረ የመከራ ሎሌ ነው የሚያደርገን። የሰው ልጅ ደግሞ ትላንትን እያስታወሰ እንዲቆዝም ሳይሆን በዛሬ በረከት ተደስቶ ተመስገን እያለ እንዲኖር ነው ሰው የሆነው።
በሕይወታችን የትኛውም ቦታ ላይ በስህተት ውስጥ ካላለፍን ምሉዕ አንሆንም። ሳንገዳገድ መቆም አንችልም። በአንድ ነገር ላይ የበላይ ስንሆንና ኃይልን ስንላበስ የትም ቦታ ላይ ያለአንዳች ተግዳሮት እንፈስሳለን። ይሄ ደግሞ በስህተት ውስጥ የመፈጠር ልዕልና ነው። አንዳንዶች በችግራቸው ሌላ ችግር ይፈጥራሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ በችግራቸው ነጋቸውን ብሩህ ያደርጋሉ። በችግራቸው ችግር የሚፈጥሩ ሰዎች የዕውቀት ባይተዋር ናቸው። በችግራቸው የሰላምን ግንብ ገንብተው የሚኖሩ እነሱ ደግሞ መለኛ ናቸው። እኛም ለድሀዋ ሃገራችን መለኛ መሆን ይጠበቅብናል። በችግራችን ላይ ሌላ ችግር ሳይሆን ችግሮቻችንን የምንሽርበት የመነጋገርና፣ የመወያየት ብልሀትን የእኛ ማድረግ ይጠበቅብናል። መንግሥት እንደ መንግሥት፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ከችግሩ ተምሮ ለሰላም የሚሆን አቅም፣ ለአንድነት የሚሆን ኃይል ማጎልበት አለበት። ጥበቦቻችን በትላንት አስተሳሰብ ታውረው የዛሬን በረከት ማየት ካልቻሉ እንደ ለመድነው ከጦርነትና ከመጠላላት አንወጣም። ጦርነትና እኔነት ባህላዊ ጨዋታችን እስኪመስሉ ድረስ ለዘመናት ኖረንባቸዋል። ኢትዮጵያዊነት መገዳደል እስኪመስል ድረስ ለዛውም ከወንድሞቻችን ጋር፣ ለዛውም እኛ ከምንላቸው ጋር ደም ተቃብተናል። ሰው በሰላም ዋርካ ስር መጠለል ሲገባው በመከራ ሮሮ ውስጥ መውደቁ ሁሌም ይደንቀኛል። ችግሮቻችን ብልህ እንዲያደርጉን እንጂ ሞኝ እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም።
ዓለም የስህተት መልክ ናት። ስህተት ነው እንዲህ ጠፍጥፎ ያበጃት። የአሁኑ ውብ መልኳ በስህተት ውስጥ የተፈጠረ ነው። ዓለም የብዙ ትውልዶች አስተሳሰብ፣ የብዙ ሀሳቦች የስህተት ነጸብራቅ ናት። በተለያየ ዘመን የመጡ አስተሳሰቦች፣ በተለያየ ዘመን የመጡ አመክንዮ ሀሳቦች አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ በመሆን የፈጠሯት ናት። እያጠፉ የሳሏት፣ እያደመቁ ያደበዘዟት የልክነትና የስህተት ቅይጥ። ዓለም እኮ ዛሬም ድረስ ተሠርታ አላለቀችም..ዛሬም ድረስ ተስላ አልተጠናቀቀችም። እኛም በብዙ ስህተት ውስጥ አልፈን ነው ዛሬን ያየንው። ስህተት ውስጥ ጥበብ አለ። ውድቀት ውስጥ መስፈንጠር አለ። እኛም ከትላንት እየተማርን፣ ካለፈው እየተረዳን ዛሬን በዋጋ መኖር ግድ ይለናል። ጠቢብ ሰው ማለት መከራ የማይደርስበት ማለት ሳይሆን ከመከራው ተምሮ አዲስ ዛሬን የሚፈጥር ማለት ነው። እኛስ ምን ዓይነቶች ነን?.. የሃገራችን አብዛኞቹ ችግሮች ከትላንት ማህጸን ውስጥ የሚመዘዙ ናቸው። ይህ ማለት ዛሬም ድረስ ከትላንት አስተሳሰብ አልወጣንም ማለት ነው። ይህ ማለት ዛሬም ድረስ እንደትላንቱ ነን ማለት ነው። እንደ ሃገር ከትላንት እኩይ አስተሳሰብ መለየት ይኖርብናል። እንደ ሕዝብ፣ እንደመንግሥት ትላንትን በይቅርታ የሚሻገር አዕምሮና ልብ ልናዳብር ይገባል እላለሁ።
ሰው በዕውቀት ሲዘመን፣ በስልጣኔ ሲቀድም ነገ ላይ በኩራት የሚያወራውን ታሪክ ዛሬ ይሠራል እንጂ በትላንት ጦስ ዛሬን አይኖርም። ዛሬ ለሁላችንም አዲስ ቀን ነው። ስለምንድነው በትላንት ነውር ዛሬአችንን የምናጨልመው? ስለምንድነው በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ሆነን የምንኖረው? ይሄ ሁላችንም ጠይቀን የምንመልሰው የጋራ ጥያቄአችን ነው። ከትላንት አስተሳሰብ ለመውጣት የዛሬን ዋጋ መረዳት ይኖርብናል። ከትላንት አስተሳሰብ ለመመለስ መንግሥትና ሕዝብ አዲስ ነገር መናፈቅ ይኖርባቸዋል። ከትላንት የጦርነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ የትላንትን ቁስል የሚያሽር የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ይኖርብናል። ትላንትን መማሪያ እንጂ መማረሪያ ያላደረገ ትውልድ ሃገራችን ያስፈልጋታል። እኛ ኢትዮጵያውያን ፖለቲካ ያመረቀዘው የብሔር ቁስል አለብን። እኔነትና ተረኝነት የወለደው የመገፋፋት ሕመም አለብን። ራስ ወዳድነትና ጎጠኝነት የጸነሰው የመጠላላት ነቀርሳ አለብን። ከነዚህ ደዌአችን ለመፈወስ ደግሞ ትላንትን ገሎ መቅበር አለብን። ከነዚህ ደዌአችን ለመዳን እንደ ትላንት ያልሆነ አዕምሮና መንፈስ ያስፈልገናል።
ሰው ወደ ትላንት ሲሳብ የዛሬን በረከት አይደርስበትም። ስልጣኔ ሊርበን ይገባል። እድገትና ዘመናዊነት ሊጠማን ይገባል። ይሄን ሁሉ ዘመን ኋላ ቀርተን እንኳን በሌሎች መቀደማችን አይቆጨንም። በማይጠቅመን ነገር ያባከንው ጊዜ ሊቆጨን ይገባል። አንድነት አጥተን የተገፋፋንባቸው ጊዜያቶች ሊያስቆጩን ይገባል። ትውልድ ካልተቆጨ፣ መንግሥት ካልተቆጨ፣ ሕዝብ ካልተቆጨ ከትላንት አስተሳሰብ መላቀቅ አይችሉም። የሃገራችን ሰላም ማጣት፣ የሕዝባችን ኋላ መቅረት፣ የፖለቲከኞቻችን አለመግባባት ሊቆጨን ይገባል። የትውልዱ ብሔር ተኮር አስተሳሰብ፣ በትላንት አስተሳሰብ ዛሬን መኖራችን ሊቆጨን ይገባል። የስኬት ሕግ አስተሳሰብን መሠረት ያደረገ ነው። የለውጥ ሕግ አምናን ሳይሆን ዘንድሮን፣ ትላንትን ሳይሆን ዛሬን የተንተራሰ ነው። እኛንም ሆነ ሌሎችን የምንቀይረው በአስተሳሰባችን ስንቀየር ነው። ሕይወታችንንም ሆነ ሃገራችንን የምንቀይረው ከማይጠቅሙን አፍራሽ አመለካከቶች ስንርቅ ነው። ዛሬ ላይ የሃገራችን መልክ ወያባ ነው። የእርቅና የይቅርታ ሀሳብ አጥታ ሃገራችን ጠውልጋለች። የውይይትና የተግባቦት መድረክ አጥቶ ሕዝባችን ተጎሳቁሏል። ዳገቱን እናልፍ ዘንድ አዲስ አስተሳሰብ ያስፈልገናል። ከነበርንበት ዝቅታ ከፍ እንል ዘንድ ዕውቀት መር የሕይወት ልምድ ግድ ይለናል።
ሕይወታችንን ከትላንት በመማር እናለምልም። ሃገራችንን ከትላንት በመማር እናሻግር። የዚህ ዓለም ከባዱ ጥፋት ትላንትን ዛሬ ላይ መድገም ነው። ሰው የትላንቱን ጉስቁልና ዛሬ ላይ ከደገመው፣ የትላንቱን ስህተት ዛሬ ላይ ከመለሰው እንደ ትላንቱ ሆኖ ከመኖር ባለፈ አዲስነት አይጎበኘውም። ነውር እየመሰላቸው መሳሳትን አጥብቀው የሚፈሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ስህተትን በመፍራት ተጠንቅቀው የሚረግጡ፣ ተጠንቅቀው የሚኖሩ፣ አድብተው የሚንቀሳቀሱ ብዙ ናቸው። እነኚህ ሰዎች ሳያውቁ ራሳቸውን ከጥበብ እያራቁት እንደሆነ ማን በነገራቸው እላለሁ። ስህተትን በመፍራት መናገር ያቆሙ፣ መጠየቅ እርም ያሉ፣ መሞከርና መጀመር የፈሩ ብዙ አሉ። ስህተት አያስፈራም የሚያስፈራው ከስህተት አለመማርና አንድ ዓይነት ሆኖ መኖር ነው። የሚያስፈራው በአንድ ጥፋት ሁልጊዜ እየተጸጸቱ መኖር፣ ሁልጊዜ እያለቀሱ መኖር ነው። የሚያስፈራው በአዲስ አስተሳሰብ ከዘመኑ ጋር አብሮ አለመራመድ ነው። የሚያስፈራው የዛሬን አዲስ ማለዳ በትላንት ጨለማ መሰወር ነው። የሚያስፈራው ሃገርን በአዲስ ልብ፣ ሕዝብን በአዲስ ተስፋ አለማሻገር ነው።
ሕይወት ትምህርት ቤት ናት። ጊዜ ደግሞ መምህራችን። እኛ ደግሞ ተማሪዎች። በዚህ የተፈጥሮ ሂደት ውስጥ ነን። በሕይወት ትምህርት ቤት ውስጥ ጊዜ ሲያስተምረን ጥሩ ተማሪ መሆን ግዴታችን ነው። ጊዜ ሲያስተምረን ጥሩ ተማሪ አለመሆን ማለት ለመውደቅና ለመሸነፍ መዘጋጀት ማለት ነው። ዓለም ደግሞ ለተሸናፊዎች ቦታ የላትም። ዓለም የባለራዕዮች ናት። ዓለም ራሳቸውን ለመቀየር ከሌሎች ጋር ለሚተባበሩ የተገለጠች ናት። ዓለም ተነጋግረው ለሚግባቡ ነፍሶች የተሰጠች ናት። ዓለም በትጋትና በጥረት ከፍ ለማለት ለተሰናዱ የተዘጋጀች ናት። የእኛ ጥሩ ተማሪ መሆን ጥሩ ሃገርና ጥሩ ትውልድ በመፍጠር ሂደት ላይ የአንበሳ ድርሻ አለው። ጥሩ የሕይወት ተማሪ መሆን ማለት ከትላንት ተላቆ ዛሬን ብቻ መኖር ነው። ጥሩ ተማሪ መሆን ማለት ከዘልማድ ወጥቶ እውቀት መር በሆነ እሳቤ ሃገርን ማራመድ ነው። ጥሩ ተማሪ መሆን ማለት ጥላቻን በይቅርታ መሻር ማለት ነው።
በየትኛውም የሕይወት ስፍራ ውስጥ ትልቅ ነገር ለማግኘት ስንነሳ የምናጣው ትንሽ ነገር ይኖራል። ዓላማችን ትልቁን ነገር ማግኘት እስከሆነ ድረስ የምናጣው ትንሽ ነገር ሊያስቆጨን አይገባም። ዓላማችን ሊሆን የሚገባው በትልቅ ሀሳብ ትልቅ ነገር ማግኘት ነው። በይቅርታ ማሸነፍ ነው። ዘመኑ በከሸፈ ሀሳብ የምንራመድበት ሳይሆን በታደሰ ሰውነት አንድነትን የምናጠናክርበት ነው። አሁን ላይ እየባከንን ነው። በትላንት ዛሬን መኖር አልቻልንም። እጃችን ላይ ያለውን ውድ ነገር በርካሽ እየቀየርን ነው። ወርቃችንን በጠጠር እየመነዘርን ነው። ቁራ ለማግኘት ርዕግባችንን እየሸጥን ነው። ምን እንደሚያስፈልገን ማወቅ አልቻልንም። የትላንት ስህተቶቻችንን ዛሬም በመድገም ላይ ነን። ለሰላም ስንደክም፣ ለአንድነት ስንበረታ አንታይም። ችግሮቻችን ሌላ ችግር ሲፈጥሩብን እንጂ ሰላም ሲያወርዱልን አናይም። ታድያ ከስህተቶቻችን መማር ለምን አቃተን? ይህ ለሁላችንም የቀረበ ጥያቄ ነው። አበቃሁ፤ ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም