የአገራችን ሕዝብ በዓለም ላይ አማኒያን ተብለው በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሱት አገሮች ፊታውራሪው ነው። በዓለም በርካታ የእምነት ተከታይ አላቸው ከሚባሉት እምነቶች ዋና ዋናዎቹም በዚህችው አገር ይገኛሉ። እንደ አማኝነታችን ምን አተረፍን? የሚለው ነገር ሲነሳ ግን አጠያያቂ እና ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ይታያል። እምነት ቆም ብሎ ማሰብን በሰው ልጅ ላይ አለመጨከንን ቢያስተምርም፣ እኛ ግን እንደ አማኝነታችን ይሄን አምላካዊ ትዕዛዝ ስንፈጽም አንታይም።
ሆኖም አማኝነታችን እርስ በርስ ከመናቆር ሊያወጣን በተገባ ነበር። እኛ ግን እርስ በእርስ የሚያቆራቁስ ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ይህ ሁኔታ ደግሞ በእምነት ተቋሞቻችን ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ፤ የአማኞችም ወደ ቤተ እምነቶች ዘወትር መሄድ ከእግር መመላለስ የዘለለ አይሆንም። ይህ ደግሞ በሌሎች የጎጥና ማንነት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ግጭቶችና ችግሮች አዲስ የመሸጋገሪያ አውድ እንዲሆን እያደረገው ይገኛል።
ምክንያቱም ዛሬ ላይ በየቦታው ሲያቆጠቁጥ የነበረው ማንነትን መሠረት ያደረገው ግጭት መቋጫ አላገኘም። የውስጥ ባንዳዎች፣ የውጭ ጠላቶች ይሄንን አውድ ደጋግመው ለእኩይ ዓላማቸው ሊያውሉት ሲሞክሩ ይታያል። ሆኖም የማንነቱ የግጭት አውድ ለውጭ ጠላቶችም ሆነ ለባንዳዎች የሚፈልጉትን ያህል እልቂት ስላላመጣ አቅጣጫቸውን እየቀየሩ ነው። ይህ ተቀያሪ የትኩረት አውድ ዜጎችን በእምነት ሰበዝ ማጋጨት ነው። ይሄንንም በየቦታው እየሞካከሩ ይገኛል።
በዚህ መልኩ የእምነት ሰበዝ እየተመዘዙ ሕዝብን ማጋጨት ደግሞ ችግሩ ብዙ ነው። ምክንያቱም የእምነት ሰበዝ ግጭት ቢመዘዝ ቢመዘዝ አያልቅም። በዚህ ዓይነቱ ግጭት የሚሳተፍ ማንም አይተርፍም፤ አያተርፍምም። የእምነት ተኮር ግጭት ሁሉም ተያይዞ ተጠላልፎ የሚወድቅበት እንደመሆኑም ቆም ብሎ ማሰብ እና ከዚህ ተግባር መታቀብ የተገባ ነው። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሃይማኖት ታከክ ግጭት አስመልክቶ በጎንደር ተሰብስቦ ነበር። የጉባኤው አባላት በጎንደር ከተማ በግጭቱ ምክንያት የተጎዱ ቤተሰቦችን በማፅናናት የደረሰውን የንብረት ጉዳት ተዘዋውረው ተመልክተዋል፤ ድርጊቱንም አውግዘዋል።
የጉባኤው ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንደተናገሩት፤ በጎንደር ከተማ በሃይማኖት ሽፋን የተፈጠረው ግጭት የእምነት ተቋማት ግጭት ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም። በግለሰቦችና ቡድኖች የተጀመረን ግጭት በሃይማኖት ተቋማት በማላከክ ሽፋን መስጠት ተገቢነት የለውም። የእምነት ግጭት ማሳያም ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። በየትኛውም ቤተ እምነት ውስጥ ግጭትን፣ መገዳደልንና አንዱ አንዱን እንዲያጠፋ የሚፈቅድ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ የለም። እናም በሌለ መሠረት ላይ ሆነው ነው ጠላቶቻችን በእምነት ተቋማትና አማኞች መካከል ግጭት የቀሰቀሱት። የእምነት ተቋማትንና አማኒያንን ተገን በማድረግ ግጭት በመቀስቀስ አፍራሽ ተልዕኮን ለማሳካት መሞከር ደግሞ በሕዝብና አገር ላይ ጥሎት ከሚያልፈው ጠባሳ በዘለለ የሚያስገኘው ትርፍ የለም። እናም በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያውያን ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ መሠረት ጠንካራ ትስስር የሚስተዋልበት ቢሆንም፣ ጠላቶቻችን ይህን ትስስር ለማስለል አልፎም ተርፎ ለመበጠስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። አንዳንዶች በተለያዩ ጊዜያት በአገራችን የታዩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በመመልከት የአገራችንን ዕጣ ፈንታ እንደ ሶሪያ ሊቢያና ጎረቤታችን ሶማሊያ ሲመለከቱት ይስተዋላል። የኢትዮጵያውያን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መሠረቶች ሲታዩ ይህ ሊሆን የሚችልበት ዕድል የለም፤ ጠላቶቻችን ግን ይህን ዕድል ለመፍጠር ያልከፈቱት ዘመቻ የለም። እንዲያም ሆኖ ግን ግጭቶች ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ ለየትኛውም አለመግባባትና ግጭት ዕድል ሊሰጥ ለሚችል ጉዳይ መዘናጋትና ቦታ መስጠት አይገባም። ጠብ ጫሪዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ይገባል።
የእምነት ግጭትን ከዳር ሆነው የሚለኩሱና የሚያቀጣጥሉ፣ ይሄን ተቀብለውም የሚያራግቡ አገራቸውን ከመጉዳት በቀር የትም እንደማያደርሳቸው መረዳትና ከኅሊናቸው ጋር መታረቅ ይኖርባቸዋል። ከእንዲህ ዓይነት አውሬያዊነት እንዲርቁ እንመክራቸዋለን። ሰው በመግደልም ሆነ የእምነት ተቋማትን በማውደም የሚያገኙት ጥቅም የለም፤ አትርፈናል የሚሉ ከሆነም ትርፋቸው በማኅበረሰቡ ውስጥ የማይሽር ቁስል ማስቀመጥ ይሆናል። ይሄ ደግሞ ምንም አይጠቅምም። ያስጠይቃል፤ በታሪክም ተወቃሽ ያደርጋል።
ሆን ተብሎ በእምነት ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ ግጭቶችን፣ ሞትና ማፈናቀሎችን፣ እንዲሁም የእምነት ተቋማትን ማውደምን ተመልክተናል። በዚህ ረገድ በእምነት ተቋማት ግጭት እንዲባባስ የሚሠሩ የየእምነቱ ጽንፈኞች እንዳሉም ይታወቃል፤ ከፊሎቹ ለሚፈጥሩት ግጭት ስፖንሰር አላቸው። ይሄን ከውጭ ሆነው ለሚደግፉ ኃይሎች ደግሞ በየትኛውም መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀሰቀስ ግጭት ደግሞ ሠርግና ምላሻቸው ነው።
ከእነዚህ ግጭት ናፋቂዎች ከፊሎቹ የየእምነቱን ማዕረግ ያደረጉ ናቸው። እነዚህ እንደ አማኝ የአማኝ ቋንቋ እየተናገሩ ሕዝቡን ግጭት ውስጥ ይከታሉ። ገሚሶቹም በምርጫ ወቅት ብቻ ብቅ የሚሉ ጎርፍ አመጣሽ ሊባሉ የሚችሉ ፓርቲዎች ናቸው። ጎርፍ አመጣሽ ያልኩት ምርጫ ሲመጣ ሲመጣ የሚቋቋሙ ምርጫው ሲወጣ ደግሞ የሚከስሙ ሆነው ድምፃቸውን የማያሰሙ፤ የራሳቸውን የፖለቲካ ሥራ በአግባቡ መሥራት የተሳናቸውና የገዥው ፓርቲ ክፍተቶችን የሚያራግቡ ናቸው።
እነዚህ ፓርቲዎች ድምፃቸውን አጥፍተው ቆይተው ግጭቶች ሲካሄዱ ተቆርቋሪ መስለው መግለጫ ይሰጣሉ። ግጭቱን በባሌም በሉት በቦሌ ቢስፋፋ እንደ ሠርግና ምላሽ አድርገው ይቆጥሩታል። በእዚህ ሁሉ ላይ ደግሞ ለፀቡ አሉባልታ እየነዙ በአማኞች መካከል ጦር ሊያማዝዙ የሚፈልጉ ጋዜጠኞችና የማህበራዊ ሚዲያዎችም አሉ። በመሆኑም ይሄ ሕገወጥነት የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ መፍትሄ ማግኘት ይኖርበታል። ጥፋትን በጥፋት ለመመለስ የሚሠሩ አደብ እንዲይዙ ማድረግ፤ ለተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሆኑም ሆኑ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትም ተለይተው በሕግ ተጠያቂ ሊደረጉ ያስፈልጋል።
ገዥው ፓርቲም ዜጋው ሁሉ መንግሥት አድርጎ የመረጠው ልማት ያመጣልናል ሰላም ያሰፍንልናል ብሎ እንጂ ሁከትና ሞት ሲፈበረክ ቆሞ እንዲመለከት አይደለም። ከነበሩት ፓርቲዎች የተሻለ ስለሆነ አሸነፈ፤ አሁንም አመራሩ በሰላሙ የተሻለ ሆኖ ይገኝ። ይህ ደግሞ አንድም የሚረጋገጠው የሕግ የበላይነትን ማስጠበቅ ላይ ነው። እዚህ ላይ ክፍተት እየታየ በመሆኑ ለይቶ ለመፍትሄው መሥራት ይኖርበታል። ምክንያቱም፤
‹‹ ፊት ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ››
እንደሚባለው አገርኛ ስነ ቃል ግጭት ከደረሰ በኋላ መግለጫ መስጠቱ ምንም አይፈይድም። የፀጥታ አካላቱ ቀዳሚ ሥራ አደጋ መተንተንና መገመት፤ አደጋን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተጠንቀቅ መቆም ካልሆነ በየጊዜው አደጋ መድረሱ የዘወትር ክስተት ይሆናል። ኢንቨስተር መሳብ፣ ቱሪስትም ሆነ ዳያስፖራ ወደ አገር መጥቶ ዶላር መመንዘርና መዘርዘር የሚቻለው ሰላማችን አስተማማኝ ሲሆን ነው። የአገር ውስጡም ባለሀብት መሥራትና ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችለው አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ሲኖር ነው።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16 ቀን 2014 ዓ.ም