አዲስ አበባ፡- ባለፉት ዓመታትበአገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ የተደረጉ የዩኒቨርሲቲ ማስፋፋት ዕቅዶች በሚፈለጉ የትምህርት መስኮች አለመሆናቸው በችግር መለየቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ ስህተቶች መታረም እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡
ዶክተር ሳሙኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የማስፋፋት ሥራው የሚፈለጉትን የትምህርት መስኮች የለየና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አለመሆኑ በአንዳንድ መስኮች ትርፍ ሰው በአንዳንዶቹ መስኮች ላይ ደግሞ ያነሰ የሰው ኃይል ተመርቆ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ ማስፋፊያ ሲደረግ የትምህርት ጥራት ችግር እንደሚገጥመው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ዘርፉ የቀጣይ የአገሪቱን መፃዒ ዕድል የመወሰን ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ መታረም የሚገባው ችግር እንደሆነም ታምኗል፡፡
ለሥራው የተደረገ ዝግጅት፣ የተመደበው ሀብት፣ የተመራበት አግባብና ተያያዥ ጉዳዮች ሁሉ ለክፍተቱ አሉታዊ አስተዋፅዖ ሳያበረክቱ እንዳላለፉም ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ እነዚህንም በቀጣይ በልዩ ትኩረት እያረሙ መሄድ ይገባልም ብለዋል፡፡ በተያያዘ በዩኒቨርሲቲዎቹ መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነትም ጥራቱ ላይ ለሚነሱ ጉድለቶች ተጠቃሽ ምክንያት ይሆናል፡፡ ዕድሜው ገና የሆነው ዩኒቨርሲቲ ስለ አጥር፣ ውሃ፣ ስለመብራትና በቅጥር ጊቢው ውስጥ ስላልተሟሉ ግብዓቶች ሲጨነቅ ረጅም ዓመታትን በመማር ማስተማሩ የቆየው ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ስለ ትምህርት ጥራት አብዝቶ ያስባል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተቋማቱ በርካታ የመማር ማስተማሩን አጋዥ ግብዓቶች ዕጥረት እንዳለ አምነዋል፡፡ በተመሳሳይ የመምህሩ ጥራት ላይ የሚነሱ ችግሮች መነሻ ምንጫቸውም ከሀብት ዕጥረት የመጣ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡ እየተቀጠረ ያለው ብቁ ሠራተኛ አይደለም፡፡ በዚህም ከመንግሥት የመክፈል አቅም ጋር በተያያዘ አንዳንድ ጊዜ መለስተኛ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በከፋ ሁኔታ አጠያያቂ አቅም ያለው መምህር ቅጥር ይፈፀማል፡፡
የሀብት ዕጥረቱ የሚያመጣቸው ብዙ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት ዶክተር ሳሙኤል፤ መጽሐፍትን ጨምሮ ሌሎች መማር ማስተማሩን የሚያግዙ ግብዓት ማሟላት በማንበብ፣ በማሰላሰል፣ በዕውቀት ላይ ተመርኩዞ ሃሳብ የሚሰጥ፣ የሚተችና የሚደግፍም ምክንያታዊ ትውልድን ለመፍጠር አስፈላጊነቱም የትየለሌ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ ለዚህም የተከለሰ ዕይታና መልሶ መመልከትን የሚፈልጉ በርካታ ውሳኔዎች አሉ፡፡ ለችግሮቹ አጠቃላይ መፍትሔ የሚሆነውም አገር ሠላም አድርጎ ኢኮኖሚው በፍጥነት ማሳደግ በፍትሃዊነት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንደሆነም አክለው ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2011
በፍዮሪ ተወልደ