ደብረብርሃን፡- ላለፉት 50 ዓመታት ምንም ቅያሬ ሳያደርጉ ‹‹ጓጉንቸር›› በተባለው ቁልፍ ቤታቸውን ሲቆልፉ መቆየታቸውን የሚናገሩት የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ የሆኑት እማማ ባዩሽ ቅጣው ናቸው።
እንደ እማማ ባዩሽ አባባል፤ ጓጉንቸር የተባለው የቤት ቁልፋቸው ጠንካራ እና ታማኝ አገልጋያቸው ነው። ከጓጉንቸሩ ጋር እስከ ህልፍተ ቀን ድረስ የመቆየት እቅድ ያላቸው ሲሆን፤ እርሳቸው ዓለምን ሲሰናበቱ ልጃቸው ቁልፉን እንዲጠቀም ጥንቃቄ በተሞላው መንገድ እንደሚይዙትም ነው የሚናገሩት።
«ጓጉንቸር» የተባለውን ቁልፍ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ከአንድ ጎረቤታቸው እንደተበረከተላቸው አስታውሰው፤ እስከዛሬ ድረስ መቆየቱ ከአያያዜ ጥንቃቄ የተሞላበት በመሆኑና እቃውም ጠንካራ ስለሆነ ነው ብለዋል።
በ90ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አዛውንቷ፤ ሁለት ልጆች ያላቸው ሲሆን መጀመሪያ ልጃቸው በደርግ ዘመን በውትድርና ብላቴ በሚባል ስፍራ ሲያገለግል እንደነበርና፤ እስካሁንም የውሃ ሽታ ሆኖባቸው በአካል እንዳላገኙት ይናገራሉ። ሁለተኛ ልጃቸው ደግሞ የአዕምሮ ታማሚ ሲሆን፤ ከእራሳቸው ጋር ይኖራል። ሆኖም ይህን ቁልፍ እኔ ቀድሜ ዓለምን ከተሰናበትኩ ልጄ ታማሚ ቢሆንም ይጠቀምበታል ብለዋል።
የእማማ ባዩሽ ጎረቤታሞች በበኩላቸው፤ «ጓጉንቸር» የተባለውን ቁልፍ ለዘመናት እንደሚያውቁትና በረጅም ጨርቅ አንጠልጥለው እንደሚይዙት የዓይን አማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 14/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር