የተወለዱት በ 1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አፍንጮ በር በሚባል አካባቢ ነው። ከአራት እህትና ወንድሞቻቸው መካከል ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ የሆኑት አቶ ክንፈሚካኤል ሀብተማርያም በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ውስጥ ለረጅም ዓመታት የፎቶግራፍ ባለሙያ በመሆን ያገለገሉ፤ በዚህ የስራ ቆይታቸው ደግሞ አብዛኞቹን የጦር ግንባር ውሎዎች በካሜራቸው ያስቀሩ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በርካታ የዓለም አገራትን የዞሩ በጠቅላላው ስራና ህይወት ብዙ ያስተማራቸው፤ ለሌላውም አርዓያ መሆን የሚችሉ አንጋፋ ባለሙያ ናቸው። እኛም ዛሬ ከህይወት ገጽታ አምዳችን ላይ የእኝህን ሰው ታሪክ ልናካፍል ወደናል።
አቶ ክንፈሚካኤል ሀብተማርያም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በቀጥታ ያመሩት ወደ ቄስ ትምህርት ነበር። በዛም ለአምስት ያህል ጊዜያት ዳዊትን በመድገም ነው ወደ መደበኛ ትምህርት የገቡት። መደበኛ ትምህርታቸውን በአመሃ ደስታ ትምህርት ቤት “ሀ ” ብለው የጀመሩ ሲሆን ቀጥሎም ጉስቋም ኋላም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች በመዘዋወር ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ችለዋል። በወቅቱ የመንግስት ለውጥ ማለትም የአፄ ሀይለስላሴ መንግስት ወድቆ ደርግ መንበረ ስልጣኑን የተቆናጠጠበት ጊዜ ነበርና የፖለቲካውን ትርምስ ለማምለጥ ብሎም ተምሮ እራስን ለመቻል በማሰብ ወደ ኢትዮጵያ ፈጣን ሙያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ገቡ። በሙያ ማሰልጠኛውም በኮንስትራክሽን መስክ ላይ ፕላን ማንበብ። ኤሌክትሪክ ስራና የእንጨት ሙያን ሰለጠኑ። መመረቂያቸው በደረሰ ጊዜ ግን ሌላ የህይወት አጋጣሚ ጠራቸውና ወደ ኮንሰትራክሽን ሙያው ሳይመለሱ ቀሩ።
እዚህ ላይ ይላሉ ” የኮንስትራክሽን ትምህርቴን እየተማርኩ ጎን ለጎን ፎቶ ቤት የከፈተ ጓደኛዬ ጋር እውል ነበር። በወቅቱም የፎቶግራፍ አነሳስ። ካሜራ አያያዝን አይ ነበር፤ እየቆየሁ ግን ለሙያው ከፍተኛ ፍቅር እያደረብኝ መጣ “።
ፎቶ ቤት መዋል ከፍተኛ የሆነ የፎቶግራፍ ፍቅር በውስጣቸው እንዲኖር ያደረጋቸው አቶ ክንፈሚካኤል በወቅቱ ፎቶ እንዴት እንደሚነሳ። እንዴት ተደርጎ ታጥቦ ለባለቤቱ እንደሚመለስ እንዲሁም ሰርጎች በሚበዙበት ወቅትም እራሳቸውን ችለው ሰርተው እንዲመጡ እድል ይሰጣቸው ጀመር፤ ይህ ደግሞ ሙያውን ለማዳበር ከፍተኛ እድል ፈጠረላቸው።
ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ፎቶ ቤት ተቀጥረው ስራን ለመስራት ያሰቡት፤ እንዳሰቡም አልቀሩም ስራውን ጀመሩ፤ ነገር ግን ፎቶ ቤት ተቀጥሮ መስራቱ ከእለት ፍጆታ ባለፈ ህይወትን ከፍ የሚያደርግ ገቢ ሊገኝበት እንደማይችል ተረዱ። በወቅቱም ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ችግርም አጋጥሟቸው ስለነበር ፊታቸውን ወደሌላ የስራ መሰክ ማዞርን መረጡ። የገንዘብ ችግራቸውንም ለማለፍ በተማሩበት የኮንሰትራክሽን ስራ ለመግፋት ፈለጉና ጀመሩት፤ ነገር ግን ያም አልነበረምና የእሳቸው እንጀራ በወቅቱ ወደ ማሰልጠኛ ተቋሙ ለቃለ ምልልስ የሄዱ የፕሬስ ድርጅት ባልደረባ ጓደኛቸው ቀድሞውንም የፎቶ ማንሳት ችሎታቸውንና ፍላጎታቸውን ይረዱ ስለነበር “አንተ እዚህ ምን ትሰራለህ ? ለምን እኛ መስሪያ ቤት ሄደህ አትቀጠርም? ” አሏቸው። ሃሳቡን ተቀብለው በፍጥነት ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በ1971 ዓ.ም መጡ።
” በወቅቱ ወደ ተቋሙ ስመጣ ሁሌም እስከ አሁንም ድረስ በምታወቅበት ዝነጣ ዘንጬ። ከረቫት አስሬ ነበር፤ የወቅቱ የስራ ኃላፊም ሲያዩኝ በጣም ደንግጠው” ስራው አለ ነገር ግን አንተን ሳይህ የእኛ ደመወዝ የሚበቃህ አይመስለኝም” አሉኝ፤ ስንት ነው ብዬ ስጠይቃቸው 153 ብር አሉኝ፤ በጣም ደስ ብሎኝ “የመንግስት ደመወዝና የቤተ ክህነት ምግብ ተለምኖ የሚበላ ነው” አልኳቸው በጣም ተገርመው በል እሺ አሉና፤ አንዳንድ በሙያው ዙሪያ ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመሩ። በወቅቱ ግን ሙያውን እንዲሁ ልወቀው ልስራበት እንጂ በእውቀት ያልተደገፈ ስለነበር የጠየቁኝን ጥያቄ መመለስ አልቻልኩም” ይላሉ አቶ ክንፈሚካኤል ወደ ፕሬስ የመጡበትን አጋጣሚ እያስታወሱ።
በወቅቱ እኛ የፈተኗቸው የስራ ኃላፊ ዝም ብለው ሊሸኟቸው ወይንም ደግሞ አይ ፈተናውን አላለፍክምና መስራት አትችልም ሊሏቸው አልፈቀዱም። ይልቁንም አንተ ወጣት ነህ የሙያው ፍቅርና የመስራት ፍላጎት ያለህ በመሆኑ ከእኛ ጋር እዚሁ ቆይተህ የነጻ አገልግሎት ትሰለጥናለህ በማለት የእንጀራ በራቸውን እንደከፈቱላቸው ይናገራሉ። አቶ ክንፈሚካኤልም እድሉን ማጣት ስላልፈለጉ ተስማምተው ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በወቅቱ አጠራሩ ከማስታወቂያ መምሪያ ጋር ስራቸውን ጀመሩ።
” ……..የሚገርመው ነገር ስልጠናውን እያገኘው ስራውን እየሰራሁ ሙሉ በሙሉ ስለሙያው ለማወቅ አጭር ጊዜ ብቻ ነበር የወሰደብኝ። ኃላፊው ጠይቀውኝ ያልመለስኳቸውን ጥያቄዎች ሁሉ በስራ ላይ አወቅኋቸው። በዚህም በጣም ደስ አለኝ ይበልጥ ወደሙያው ተሳብኩ የመስራት ፍላጎቴ ጉጉቴ ጨመረ ” ይላሉ ወቅቱን ሲያስታውሱት።
ተቋሙም የካሜራ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ማስታወቂያ አወጣ፤ ወጣቱ ክንፈሚካኤልና አንድ ሌላ ጓደኛቸው ፈተናውን ወስደው በጥሩ ሁኔታ አለፉና በ 153 ብር የወር ደመወዝ ስራው ጀመሩት። ለወጣቱ ክንፈሚካኤል ከአለቃቸው ዘንድ እንዲህ የሚል ሃሳብ ቀረበላቸው ” እኛ አንተን የቀጠርነህ ለጦር ሜዳ ነው ለዚህ ፈቃደኛ ነህ ወይ የሚል”፤ የወጣቱ ክንፈሚካኤል መልስም “ለአገሬ በሙያዬ እዘምታለሁ” የሚል ሆነ።
ወጣቱ ክንፈሚካኤል በወቅቱ አገሪቱ ከወያኔ ቡድን ጋር እያደረገች ያለውን ጦርነት በቅርበት ይከታተሉ ነበር ጦርነቱም እጅግ ስቧቸዋል ለአገራቸው ደጀን ለመሆንም በውስጣቸው ያለው የአገር ፍቅር ስሜት ሲኮረኩራቸውም ከርሟል፤ ይህንን እድል ሲያገኙ ደግሞ ምኞታቸው ምሉዕ ሆነላቸው እጅግ በጣም እንደተደሰቱ በአንደበታቸው ይናገራሉ።
“…….ወቅቱ ጦርነቱ የተፋፋመበት እነ ከረንና ሌሎች አካባቢዎች የተለቀቁበት ስለነበር ሬዲዮው ሁሉ የድል ዜና ነው የሚያሰማው ፕሮግራሞች ሁሉ የጦር ሜዳ ናቸው፤ ይህ ደግሞ በጣም ልብ የሚያሞቅ ከመሆኑ የተነሳ እኔና ጓደኛዬ ድምጹን በቴፕ ካሴት እየቀዳን ደጋግመን እንሰማው ነበር፤ ይህ ደግሞ ውስጤ የጦር ሜዳ ቃና እንዲቀር በቃ ምን ልበልሽ አዲስ አበባ ተቀመጥኩ እንጂ ልቤም መንፈሴም ሁሉ ነገሬ ጦር ሜዳ ነበር። ልክ ስራዬን ከተፈራረምኩ በኋላ ይህንን ስሰማ በጣም ደስ አለኝ” ይላሉ።
የሚያዚያ መጀመሪያ 1971 ዓ.ም የኮንትራት ቅጥራቸውን የተፈራረሙት ወጣቱ ክንፈሚካኤል በዛው ወር መጨረሻ በደስታና በሙሉ ልብ በአንቶኖቭ አውሮፕላን ተጭኖ ወደ አስመራ ሆነ ጉዞው።
እንግዲ ከከተማ ወጥተው የማያውቁት ጦር ሜዳንም በሬዲዮ እንጂ በአካል ያላዩት ወጣቱ ክንፈሚካኤል ገና አንቶኖቭ አውሮፕላኑ ላይ ሲወጡ ድምጹ የፈጠረባቸውን መረበሽና መደናገጥ ያስታውሳሉ። በጣም ለጆሯቸው ስለከበዳቸውም ሶፍት ጠቅጥቀው መጓዛቸውን ይናገራሉ። በጣም የሚያስቀው ነገር ደግሞ አስመራ ከተማ ደርሰው ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ የጠቀጠቁት ሶፍት ወደ ጆሯቸው ዘልቆ ገብቶ ብዙ ችግር መፍጠሩና በኋላም አንድ ሀምሳ አለቃ ወታደር እንዳወጣላቸው እየሳቁ ይናገራሉ።
ጦርነት ሲቪል ሆነ ወታደር ሁሉን የማይመርጥ ጠላትን ነቅቶ መጠበቅ የሚያስፈልገው ክስተት መሆኑ ስፍራው ላይ ሲደርሱ በቦታው ከነበሩ የጦር አመራሮች መልዕክት ተላለፈ፤ በሌላ በኩል ማንም ሰው የወታደር ልብስ ሳይለብስ በሲቪል ልብስ መንቀሳቀስም ከባድ መስዋዕትነት እንደሚያስከፍል ተነገረ። ይህንን ተከትሎም ለሁሉም የወታደር ልብስ ተሰጠ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወጣቱ የፎቶግራፍ ባለሙያ ከልብሱ ጋር አብሮ የሚሄድ ቀበቶ አልተሰጣቸውም። እርሳቸውም ነገሬ አላሉት ለምን አልተሰጠኝም ብለውም አልጠየቁም።
“…….በወቅቱ አስመራ ከተማ ሰዓት እላፊ ነበር። እኔ ደግሞ የወታደሩን ልብስ ለብሼ በከተማዋ እንቀሳቀሳለሁ በዚህ መካከል ፖሊስ ያዘኝና አስቆመኝ፤ ቀበቶ ለምን እንዳላደረኩ ጠየቀኝ። በወቅቱ ግን መልስ አልነበረኝም። ፖሊሱም ወደ ህግ አቀርበዋለሁ ምክንያቱም መንግስት የቀበቶ ችግር ሳይኖርበት ለምን ቀበቶ ማድረግ አልቻልክም በማለት ብዙ ችግር ተፈጠረ። አለማወቅ መሆኑን በመናገር ይቅርታ በመጠየቅና ሌላ ጓደኛዬም የራሱን ቀበቶ አውልቆ ሰጥቶኝ ወደ ካምፔ ሄድኩ” ይላሉ።
ኸረ ጦር ሜዳ እንዲህ ከባድ ከሆነማ ልመለስ አላሉም ? ብዬ ስጠይቃቸው? አቶ ክንፈሚካኤል “…..ማ እኔ ….. እኔ እኮ ተወልጄ ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ስለ አገር ፍቅርና ስለ ሃይማኖት ሲነገረኝ ስለ ባንዲራ ክብር ጠዋት ማታ ስመክር የኖርኩ ነኝ፤ በሃይማኖትና በአገሬ ምንም ቀልድ አላውቅም፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ ሁሌም ቢሆን ቁስሌ ነው” ነበር ያሉኝ ።
ጦር ሜዳን መቀላቀል ለብዙዎች ቀላል አይደለም አዎ ለአቶ ክንፈሚካኤልም ገና ከጅምሩ ቀላል አልሆነላቸውም፤ በተለይም ወታደራዊ ህግና ደንብን ማወቅ አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። በዚህ በኩል ያጋጠማቸውን ሲናገሩም ” ጦር ሜዳ በደረስኩ ትንሽ ቀናት ውስጥ አንድ ትልቅ ወታደራዊ ጀነራል ጋር በመሄድ ሪፖርት እንዳደርግ ተነገረኝ፤ እኔም የአካባቢውን በረሃማነት መቋቋም አቅቶኝ ስለነበር ብዙውን ጊዜ ከወገቤ በላይ ራቁቴን ነበር የምሆነው፤ ልክ እንደዛው እንዳለሁ ወደጀነራሉ “አቤት” ብዬ ሄድኩ በወቅቱ ግን የገጠመኝ ነገር እጅግ አስደንጋጭ ነበር፤ ጀነራሉ በጣም ከመደንገጣቸው የተነሳ ልክ እንዳዩኝ ምንድነው ብለው በከፍተኛ ቁጣ በትረ መኮንናቸውን በመወርወር አይኔን ሊመቱኝ ሲሉ ለጥቂት ተረፍኩ፤ ኋላ ላይ ግን አለቃ ፊት በተለይም ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ሲገባ ትልቅ ስነ ስርዓት እንደሚያስፈልግ ነግረው ሸኙኝ “በማለት የገጠማቸውን ያስታውሳሉ።
በባህሪያቸው ስራ ፈተው መቀመጥ የማይፈልጉት ወይም የማይወዱት አቶ ክንፈሚካኤልን ካስቸገራቸው የጦር ሜዳ ኑሮ መካከል ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ የታለ ጠመንጃህ የሚለው ጥያቄ ነበር፤ እርሳቸው ደግሞ ጥሎባቸው በፍጹም ጠመንጃ መያዝን አልፈለጉም፤ ነገር ግን ፖሊሶች እያስቆሙ ጋዜጠኛ መሆናቸውን እንኳን ቢገልጹላቸው በፍጹም ጠመንጃ መያዝ አለብህ ብለው በማስገደዳቸው በቃ ጠመንጃ ስጡኝ በማለት ጠየቁ ኋላም ጠመንጃው ተሰጥቷቸው ታጥቀው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ነገር ግን ለመንቀሳቀስ ብዙም ስላልተመቻቸው ብሎም ክብደቱን መቻል ስላቃታቸው ከጠመንጃው ጋር ብዙ መዝለቅን አልፈለጉም ወዲያው አስረከቡ።
ይህ አለማወቃቸው እንዲሁም ስራ ፈትቼ መቀመጥ የለብኝም የሚለው መንፈሳቸው ለሌላ ለዛውም ከባድ ለሆነ ስህተትና ከስህተትም በላይ ደግሞ ህይወትን ለማሳጣት በሚችል አደጋ ውስጥ ጨምሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፤ አቶ ክንፈሚካኤል ሲናገሩ “…… በአንድ ወቅት ናቅፋን ለመያዝ ጋሬጣ የሚሆኑትን በርካታ ተራሮች በድማሚት ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጦር ግንባር መሃንዲሶች ሲሄዱ በአጋጣሚ አንድ ቦታ ቆመው አገኘኋቸው፤ የት ልትሄዱ ነው ? ስላቸው ግንባር አሉኝ፤ እኔም አብሬያችሁ እሄዳለሁ በማለት መኪና ውስጥ ገባሁ። ቦታው ላይ የሚሰሩትን በሙሉ ሲሰሩ እኔም አንዴ በልቤ እየተደፋሁ ሌላ ጊዜም እነሱ የሚያደርጉትን ነገር ሁሉ እያደረኩ ቆየሁ በመጨረሻ አንድ ወታደር ወደእኔ መጣና ማንነቴን ጠየቀኝ መጀመሪያ ላይ በንግግር ሳንግባባ ሰውየው ትንሽ ቢናደድም በኋላ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር መምጣቴን ስነግረው ማነው እዚህ ቦታ እንድትገባ የፈቀደልህ? ሲልም ጠየቀኝ ማንንም ሳላስፈቅድ ወይም ሳልናገር መምጣቴን ተናገርኩ ወታደሩ ይበልጡኑ ተናደደ፤ አክሎም ቦታው የጨዋታ እንዳልሆነና በየደቂቃው በየሰከንዱ የሰው ልጅ ህይወት የሚገበርበት መሆኑን በመግለጽ ሁለተኛ መሰል ስህተት እንዳልሰራ አስጠንቅቆኝ ወደመጣሁበት ግብረ ሃይል እንድሄድ ሸኘኝ” ይህ በጣም ይገርመኛልም አልረሳውም ይላሉ።
አቶ ክንፈሚካኤል ወቅቱን ሲያስታውሱ በጣም ከሚቆጫቸው ነገር መካከል እሳቸውና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያነሷቸው ፎቶግራፎች ተንቀሳቃሽ ምስሎች (ቪዲዮዎች) ታሪክ ሆነው ለተቋማቱ መሰጠት አለመቻላቸው ነው።”………..በወቅቱ እኛ ከዚህ ፊልም ይዘን ሄደናል እዛ ስንደርስ የያዝነውን ፊልም አስረከብን፤ እንደገና ወደስራ ስንወጣ የሚስጥር ወረቀትና የፊልም መቆጣጠሪያ ይሰጠናል፤ በወቅቱም 20 ፊልም ቢሰጥ 15ቱን ከተጠቀምን 5ቱን በሰነድ ይመለሳል። ምናልባት እነዛ ምስሎች በየተቋማቱ ቢቀመጡ ስንት የአገር ታሪክ ይወጣቸው ነበር። ብዙ መረጃም እዛው ቀረ ይህ በጣም ይቆጨኛል ” ይላሉ።
አቶ ክንፈሚካኤል ከ 1971 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ጦርነቶች ላይ ተካፍለዋል፤ በ1971 ዓ.ም ናቅፋ በር። በ 1972 ዓ.ም አልጌና። 1973 ከ11 ኛ ክፍለ ጦር ጋር በገላዴን ጎህና በዴሜር ጆክ ላይ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የተማረኩትን ንብረቶች በሙሉ በፎቶ ካሜራቸው ታሪክ አድርገው ማኖር ችለዋል። የአቶ ክንፈሚካኤል የጦር ሜዳ ውሎ ይህ ብቻ አይደለም 1974 ሙሉን አመት ቀይ ኮከብ ዘመቻ ላይ ነው የቆዩት፤ በ 1978 ዓ.ም ናቅፋ ላይ ባህረ ነጋሽ ዘመቻን በታሪክ አስቀርተዋል። እነዚህ ሁሉ አልፈውም ቢሆን አገራችንም ከጦርነት አላረፈችምና እርሳቸውም ከጦር ሜዳ ጉዞ አልቦዘኑም። በ1992 ዓ.ም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሲቀሰቀስ ወደባድመና ቡሬ በመጓዝ ታሪክን መሰነድ ችለዋል።
“…….አገሬን እወዳለሁ ለባንዲራዬም እሞታለሁ ስል ምስክሮቼ እነዚህ የጦር ሜዳ ስራዎቼ ናቸው። በየትኛውም የጋዜጠኝነትም ሆኖ የፎቶ ሪፖርተርነት ታሪክ ውስጥ እንደ እኔ አገሩን ጦር ሜዳ ሄዶ ያገለገለ የለም፤ ስድስት ጊዜ ጦር ሜዳ መሄዴ በጣም ያኮራኛል፤ በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ምንም ዓይነት የመቁሰል አደጋ አልገጠመኝም፤ ይህ የሆነው ግን በእድልና በአጋጣሚ እንጂ ሁኔታዎች ምቹ ስለነበሩ ወይም ራሴን ስለጠበኩ አይደለም፤ በነገራችን ላይ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኛ ሞቷል፤ ከዛ በፊትም በ1972 ዓ.ም የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ አውሮፕላን ሲቃጠል አብሮ ተቃጥሏል ሌላም ሌላም ብዙ ታሪክ አለ ” ይላሉ።
“……የሚናፍቀኝ ሰላም ነው ለምሳሌ በ1976 ዓ.ም ላይ እኔ የነበርኩበት ጦር 505 አልጌና ላይ ሙሉ በሙሉ ነው የተደመሰሰው፤ ግብረ ሃይል ተደመሰሰ ሲባል ቀላል እንዳይመስልሽ በጣም ከባድ ነው፤ ብዙ ሰው በርካታ መሳሪያ ምን ቅጡ በጣም ያሳዝናል፤ በሶማሌ ጦርነትም ወቅት ብዙ አልቀናል፤ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ እያለቅን ነው። ነገር ግን ከጦርነት የምናተርፈው ወይም የምናገኘው አንዳችም ነገር የለም፤ አሁንም ቢሆን መንግስት የገባንበትን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እመኛለሁ። ምክንያቱም እነሱ ምንም ይሁኑ ምን አንድ ጊዜ በደም ተጋምደናል ይህንን ደግሞ መካድም ሆነ መሰረዝ በጣም ከባድ ነው። በመሆኑም ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ የሚያበቃበትን ጊዜ እናፍቃለሁ፤ በዚሁ ከቀጠልን ግን ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ግብጽና ሱዳን ጭዳ ነው የምንሆነው “ይላሉ።
አንጋፋው የፎቶ ሪፖርተር አቶ ክንፈሚካኤልም እነዚህ ሁሉ የጦር ሜዳ ተሳትፎዎችን ከማድረግ ባሻገር ከደርግ ጊዜ ጀምሮ ከአገሪቱ ቁንጮ ባለሰልጣናት ጋር አለምን የመዞር እድል ያገኙ ስለመሆናቸው በራሳቸው እንደበት ይናገራሉ።
“……እኔ እንግዲህ በፎቶ ጋዜጠኝነት ስራ ዘመኔ ከ 29 በላይ የአለም አገራትን የማየት እድሉን አግኝቻለሁ፤ አፍሪካ ውስጥ ከጅቡቱ በቀር ሰሜኑንም ደቡቡንም ምስራቁንም ሁሉንም አይቻለሁ፤ አንዳንዶቹ እንደውም ከአምስት ጊዜ በላይ አይቻቸዋለሁ። አሜሪካን ጣሊያን ፈረንሳይ እና ሌሎችም አገራትንም አይቻቸዋለሁ። ከዚህ በላይ ግን እንዲታወቅልኝ የምፈልገው እነዚህ ሁሉ አገሮች ሄጄ የስራ ግዳጄን ተወጥቼ ከመምጣት ባሻገር አንድም ቀን ጠፍቼ እቀራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፤ ልሞክረውም አልፈለኩም፤ ምክንያቱም አገሬን ከልቤ ማፍቀሬ ነው” በማለት ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያን ከናቅፋ ጀምረው እስከ ሞያሌ፤ ከሞያሌ በዶሎ በኩል ኬንያ ማንዴራ፤ ከማንዴራ ጉባ ድረስ በጠቅላላው በአራቱም መዓዘን የአገሪቱን ጠረፍ አካለዋል። በዚህ የስራ ጊዜያቸው ደግሞ ያሳደጓቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አብዝተው በፎቶ ሪፖርተርነት አገልግለዋል። ብዙ ታሪካዊና ዘመን የማይሽራቸውን ፎቶግራፎች ሰንደዋል። በዚህ ስራቸውም አንጋፋ የሚል ማዕረግን ያገኙ ታላቅ ባለሙያ ስለመሆናቸው ብዙዎች ይመሰክራሉ።
ስራቸውን ለመስራት በተንቀሳቀሱባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የተለያዩ አደጋዎች አጋጥሟቸዋል ለምሳሌ በሄሊኮፕተር ተከስክሰዋል። ባህርዳር ላይ በመኪና ተገልብጠዋል። በ1997 ዓ.ም በነበረው አገራዊ ምርጫ ወቅትም በደረሰባቸው አደጋ እግራቸው መሰበሩን ይናገራሉ። ይህ ግን ለአገሬ ለሙያዬ ፍቅርና ክብር የከፈልኩት ዋጋ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ ይላሉ።
አሜሪካን አገር ሄደው የሆነ የገጠሞት ነገር አለ ይባላልና ስለእሱ አጫውቱኝ ስላቸውም፤ በሳቅ በትዝታ የኋሊት እየሄዱ “…..አዎ አሜሪካን አገር ትልቅ ገጠመኝ አለኝ። አሜሪካን ኒውዮርክ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ነበር የሄድኩት በወቅቱ ስብሰባው ይካሄድ የነበረበት አዳራሽ ከስፋቱ የተነሳ ሰውን ከሰው መለየት ከባድ ነበር። እኔ የያዝኩት ካሜራ ደግሞ ሃያ ሚሊ ሜትር (የዓይን ብርሃናችንን) ያህል ብቻ የምትረዝም ናት፤ በዚህ ርዝመት ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝቶ ፎቶ ማንሳት እጅግ ፈታኝ ሆነ። መሪዎቹ ስብሰባቸውን ጨርሰው እስከሚወጡ ድረስ የረባ ስራ አልሰራሁም። ይህም በጣም አሳስቦኛል። ኋላም አብረውኝ ያሉት የሙያ ባልደረቦቼ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ወደሆኑት ግለሰብ ስልክ ፈልጌ እንድደውል አዘዙኝ፤ ተስማማሁና ስልክ ፍለጋ ሄድኩ፤ በወቅቱ ሰውየውንም በስልክ ካለማግኘቴም በላይ ስመጣ ሌላ ዱብዳ ገጠመኝ ” ይላሉ።
ስልክ ፍለጋ የሄዱት አቶ ክንፈሚካኤል ሲመለሱ ጓደኞቻቸውን በተዋቸው ቦታ ላይ አላገኟቸውም በተመደበላቸው መኪና ጥለዋቸው ሄደዋል። በዚህን ጊዜ በሰው አገር ወዴት ልሂድ የሚለው ድንጋጤ በከፍተኛ ሁኔታ ይይዛቸዋል።
“…….በወቅቱ ከጓደኞቼ የታዘዝኩትን ስልክ ፈልጎ የመደወል ሃላፊነት ለመወጣት ነበር የሄድኩት ስመጣ ግን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ንግግር ሊያደርጉ ነው በሚል ሁሉም ጥለውኝ ሄደዋል። በህይወቴ እንደዛ አይነት ድንጋጤ የደነገጥኩበትን ወቅት አላስታውሰም። ወዴት ልሂድ የሚለው ነገር ወጥሮ ያዘኝ ወይስ አገሩን ከዳ ጠፋ ልባል ነው። ብዬ ተጨነኩ በኋላም ከብዙ ማሰብ በኋላ በአካባቢው ያሉ ሰዎችን ምን ማድረግ እንዳለብኝ ጠየኳቸው። እነሱም ታክሲ ይዤ ወደተባለው ቦታ መሄድ እንደምችል አመላከቱኝ፤ በዛው መሰረት ሄድኩ ግን አላገኘኋቸውም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ንግግር አላደረጉም። ይባስ ብዬ እዛ ሳጣቸው እንባ አውጥቼ አለቀስኩ በኋላ ግን ጓደኞቼም ከሄዱበት መጥተው ትልቅ ይቅርታ ጠይቀውኝ አብረን መጣን” በማለት ኒውዮርክ ላይ የገጠማቸውንና እጅግ ያስደነገጣቸውን አጋጣሚ ይናገራሉ።
አንጋፋው የፎቶ ጋዜጠኛ አቶ ክንፈሚካኤል በሰዎች ዘንድ ከሚታወቁበት አንዱ እጅግ ዘንጣፋ ቁመና ያላቸው በዛው ልክ በበዓል በስራ ቀን አንድ አይነት አለባበስ የሚያዘወትሩ ዘናጭ መሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ በሚንቀሳቀሱባቸው (በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር) ከሌሎች በተለየ መልኩ እንዲታዩ የጠየቁትን የሚፈልጉትን ሁሉ በፍጥነት እንዲያገኙም ያግዛቸው ነበር ።
ቁመናዬ በጣም ይገርምሻል ብዙ ነገሮችን ለማሳካት ጠቅሞኛል፤ በእርግጥ በማህበራዊ ግንኙነቴ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖም ቀላል አይደለም ይላሉ። በተለይም የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ስገኝ ሁሉም ነገር ለእኔ ምቹ ነበር፤ ሌሎች ጋዜጠኞች የተከለከሉበት ቦታ ሁሉ ገብቼ ፎቶ ለማንሳትም አልቸገርም በማለት ያስታውሳሉ።
“……ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ ስራ የሄድኩት በደርግ ጊዜ ከነበሩት ጉምቱ ባለስልጣን ከአቶ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ጋር ነበር፤ የሄድነው ዚምቧቤ ሲሆን መሪ ሞቶ ለቀብር ነበር፤ ግን ከላይ ኒውዮርክ ላይ እንደገጠመኝ አይነት ሁኔታ አጋጠመኝ አዳራሹ በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ የእኔ ካሜራ እዛ ውስጥ ያለን ነገር በፎቶ ማስቀረት አቶ ፍቅረ ስላሴንም ማንሳት እንደማልችል ተረዳሁ፤ እሳቸውን ሳላነሳ ከመጣሁ ደግሞ በአለቆቼ ዘንድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ገመትኩ፤ በመሆኑም ቁመናዬን ዝነጣዬን መጠቀም አለብኝ ብዬ ወሰንኩና ካሜራዬን በኮት ኪሴ ውስጥ ደብቄ መሪዎች በሚገቡበት በር ቀጥ ብዬ ገባሁ እንኳን የት ነህ ብሎ ሊጠይቁኝ ቀርቶ ልክ እንደ አንድ አገር መሪ ተቀበሉኝ። የአዳራሹ በር ተዘግቶ ንግግር ከተጀመረ በኋላም ካሜራዬን በማውጣት የምፈልገውን ሁሉ በፎቶግራፍ አስቀርቼ በገባሁበት በር ወጣሁ። እናም ቁመናዬን ተጠቀምኩበት ማለት አይደል ” በማለት ይናገራሉ።
እዚሁ ላይ ግን ሌላ የገጠመኝን ነገር ላጫውትሽ የሚሉት አቶ ክንፈሚካኤል ይህ የቀብር ፕሮግራም ሳይጠናቀቅ ከተማዋ በቦንብ ፍንዳታ ራደች በዚህ ጊዜ መሪዎቹም ተሸበሩ ሁሉም ግራ ተጋባ በቶሎ መሪዎቹን ለማስወጣት ተፍ ተፍ ማለት ተጀመረ በዚህ ጊዜ እኔም ምን ልሆን ነው የሚል ስጋት ውስጥ ገባሁ በኋላ ግን አቶ ፍቅረስላሴ ወግደረስና ፕሮቶኮላቸው አምባሳደሮች ወደ መኪና ሲገቡ አየሁ እኔም በድፍረት ከእናንተ ጋር ነው የመጣሁት ጥላችሁኝ ልትሄዱ ነው ብዬ ስጣራ ሲያዩኝ እውነትም ከእነሱ ጋር የመጣሁ ባለስልጣን ነበር የመሰልኳቸው በል ቶሎ ወደመኪና ግባ ብለው ወደ አውሮፕላን ማረፊያ ወሰዱኝ። ከዛማ እኔን ማን ይቻለኝ በማለት በትልቅ ሳቅ ውስጥ ሆነው ሁኔታውን ያስታውሳሉ።
ይህንን በሶስት መንግስት ውስጥ ያለፈን ታሪካቸውን አልፎም የትወልድ ማስተማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ የስራ ዘመን ቆይታቸውን ደግሞ በመጽሃፍ መልክ አዘጋጅቶ ማቅረብ ህልማቸው ቢሆንም እስከ አሁን ግን ምቹ ሁኔታዎችን አላገኙም። ምናልባት ታሪኩ የሳበው ለትውልድ ቢተላለፍ ይጠቅማል የሚል አካል ካገኙም አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ነግረውኛል።
የህይወት ዘመናቸውን ከግማሽ በላይ ካገለገሉበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ “አናዱሉ” በተባለ የዜና አገልግሎት ተቋም ውስጥ ገብተው በፎቶ ሪፖርተርነት ለአንድ አመት ያህል መልካም የሚባል የስራ ጊዜና ብዙ ልምዶችን እንዳካበቱ ይናገራሉ።
አቶ ክንፈሚካኤል ጉረኛ ናቸው ከአለባበሳቸው ጀምሮ ለሚሏቸውም “…. እኔ ጉረኛ አይደለሁም፤ እንደውም በጓደኞቼ በሚቀርቡኝ ሰዎች ዘንድ ተጫዋች ተግባቢ ነኝ፤ ነገር ግን የሚመስለኝን የማደርግ ካልመሰለኝ የምተው በራሴ መንገድ የምሄድ ሰው ነኝ። ራስን መጠበቅ ንጹህ ሆኖ መታየት ከጉራ ከተቆጠረ ደግሞ ምንም ማድረግ አይቻልም”።
አቶ ክንፈሚካኤል ለስራቸው ለሙያቸው የከፈሉት መስዋዕትነት ብዙ ነው በዚህም የተነሳ አንዲት ልጅ ከመውለድ የዘለለ የቤተሰብ ህይወት የላቸውም።
ምስጋና
ከልጅነት እስከ እውቀት እድሜዬን ከሰጠሁበት የኢትዮጵያ ፕሬስ ደርጅት በጣም ታሪካዊ የሚባሉ ስራዎችን ከሰራሁበት ተቋሜ አወጣጤ ባያምርም አልናደድም። ምክንያቱም ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ታሪክ መስራትም ሆነ ለትውልድ ማቆየት የቻልኩት እዛ ተቋም ላይ በመስራቴና እድሉን በማግኘቴ ነው።
አሁን ደግሞ እንደ ቤቴ የምወደውን ተቋም መለስ ብዬ ሳየው እጅግ እደሰታለሁ አዳዲስና ወጣት አመራሮች መጥተውለታል ብዙ የለውጥ ስራዎች አሉ። ጋዜጣው ላይ የሚሰሩ ስራዎች ጥሩ ናቸው የፎቶ አጠቃቀም ከወትሮው እጅግ በጣም ተለይቷል ሳቢም ሆኗል። የእለቱን ሁነቶች እንደ ድሮው ነገላይ መጠበቅ ቀርቷል ቶሎ ቶሎ ዜናዎች በማህበራዊ ትስስር ገጹ ይለቀቃሉ እድሜ ሰጥቶኝ ይህንን የተቋሙን ለውጥ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።
እኔንና መሰሎቼንም ከተረሳንበት አስታውሰው ምንም ዓይነት ብጣቂ ወረቀት ሳናገኝ ከተሸኘንበት ጊዜ አስታውሰው የምስክር ወረቀት ሰጥተውናል ይህ በህይወቴ ከማልረሳቸው የደስታ ቀኖቼ እንደ አንዱ አድርጌ ይዤዋለሁ በማለት ይናገራሉ።
ከዚህ ውጪ ወጣት ጋዜጠኞችም ሆኑ ፎቶ ሪፖርተሮች በተለይም አገራችሁን ውደዱ የምትሰሩበትን ተቋም አክብሩ ስራችሁ ላይ ትጉ ሁኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች እጃችሁ የሚገቡ የአገርና የተቋም ሚስጥሮችን ጠብቁ። ከምንም በላይ ደግሞ ተቋማችሁን ወክላችሁ ወደስራ ስትሰማሩ የግል ንጽህናችሁን ጠብቁ በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም