የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዎ ጉተሬዝ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በተጀመረበት ሰሞን በሰጡት መግለጫ የኒውክሌር ጦርነት ሊቀሰቀስ እንደሚችል፤ በዚህም መላው የሰው ልጅ ላይ አደጋ እንደተደቀነና በአስቸኳይ ጦርነቱ ቆሞ በሰላማዊ ድርድር እንዲቋጭ ጥሪ አድርገዋል። ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ፈረንሳይ፣ ሕንድ፣ እስራኤል፣ ፓኪስታን፣ ራሽያ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና አሜሪካ በአጠቃላይ 13 ሺህ 80 የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጥቀዋል ቢባልም፤ 90 በመቶው ማለትም 11 ሺህ የአሜሪካና የራሽያ ነው። ከዚህ ውስጥ ሁለቱ አገራት እኩል ድርሻ እንዳላቸው ይገለጻል። ይፋ ያልሆኑ መረጃዎች ግን በአለማችን የሚገኘውን የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ብዛትን እስከ 20 ሺህ ያደርሱታል።
የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት
የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /ኔቶ/ የተመሰረተበት መርህ የማዕዘን ድንጋይ በአንቀጽ 5 ላይ የተደነገገው ከአባል አገራቱ አንዱ ቢጠቃ በጋራ መከላከል/collective defence/የሚለው ነው። የሕብረቱ አባል የሆኑ 30 አገራት እንደተጠቁ ስለሚቆጠር በአንድነት የመሰለፍ ግዴታ አለባቸው። የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት አካል የነበሩት እነ ላቲቪያ፣ ሉቲኒያና እስቶኒያ ዛሬ ሉዓላዊና የኔቶ አባል ስለሆኑ አንዳቸው በራሽያ ጥቃት ቢደርስባቸው በቀላሉ የ3ኛው የአለም ጦርነት ለዛውም በኒውክሌር የጦር መሳሪያና በሳይበር ታግዞ ሊቀሰቀስ ይችላል። ይህ ደግሞ የአለም መጨረሻ አርማጌዶን ሆነ ማለት ነው።
አንድ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የማጥፋት አቅም ሲኖረው በአካባቢና ህይወት ባላቸው ሌሎች ፍጥረታት ላይ ዘላቂ ጠንቅ የማምጣት ጉልበት አለው። ለዚህ ነው አለም የራሽያን እና የዩክሬንን ጦርነት እያወገዘው ያለው። በነገራችን ላይ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦርነት ላይ የዋለው በ2ኛው የአለም ጦርነት ሲሆን፤ ጥቅም ላይ ያዋለችውም አሜሪካ ነች፡፡ በወቅቱም ጃፓንን ለማጥቃት ተጠቅማበታለች። በዚህም 2ኛውን የአለም ጦርነት መቋጨት ቢቻልም ወደ 226 ሺህ የሚጠጉ ባብዛኛው ሰላማዊ ሰዎችን በመፍጀት ዛሬ ድረስ ጠባሳው ሳይሽር አለ።
የCNN Global Public Square /GPS/አዘጋጅ ፋሪድ ዘካሪያ እና ሌሎችም እንደሚሉት፤ የራሺያ ዩክሬን ጦርነት የድህረ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመንን ወደቀደመው ቆፈን የመለሰ ነው፡፡ ዳግማዊ ቀዝቃዛው ጦርነትም ተቀስቅሷል። የድህረ ቀዝቃዛው ዘመን 30 አመታት እያለፈባቸውና እየጨረሱ ነው። በእነዚህ አመታት ቻይና ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ኃያልነቷን አረጋግጣለች። ኢኮኖሚዋ በአለማችን በሀብት ደረጃቸው ከ3ኛ እስከ 6ኛ የሚገኙትን አገራት ድምር አክሏል። የራሽያ ተፅዕኖም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በማስታወስ የአለም ሁኔታ እየተለዋወጠ መሆኑን ፋሪድ በማስረጃ ይሞግታል።
ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ራሽያውያንን የናዚ አቀንቃኝ ከሆነው የኪየቭ መንግስት ጭቆና ለመታደግ ያሉትን ልዩ ዘመቻ ሲያስጀምሩ፤ ውሳኔው ለሌሎች ያስተላለፈው መልዕክት የሚመስለኝ የኒውክሌር የጦር መሳሪያን በአንደኝነት የታጠቀች አገር ገዥ ስለሆነ የሁሉንም ትኩረት የሳቡ መሆናቸውን ነውር። እንደተሰጋው የንግግሩን ማሳረጊያም፤ “ጣልቃ ለመግባት የሚሞክር አገር ካለ፤ በታሪኩ አይቶትና ሰምቶት የማያውቅ የራሽያ መብረቃዊ የአጸፋ ምላሽ ይከተለዋል፤ “ ካሉ በኋላ በመቀጠል፤ ኒውክሌርን እናንተም ብትታጠቁት የእኛ ግን ከእናንተው የላቀ ስለሆነ አርፋችሁ ተቀመጡ በማለት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
እንደተፈራውም መልዕክቱ አለምን ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ብርክ አስያዘ። የሰው ልጅ ያለ ልዩነት በቃ ሲፈራ የኖረው የኒውክሌር ጦርነት መባቻ ላይ ተደረሰ ማለት ነው ብሎ እንዲጠይቅ ተገደደ። ሕዝበ አዳም የፕሬዚዳንት ፑቲንን ማስፈራሪያ በቅጡ አንስቶ ሳይጥል፤ ለማብሰልሰያ በቂ ጊዜ ሳያገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ ከቀናት በኋላ ብቅ ብለው፤ “ 3ኛው የአለም ጦርነት የሚቀሰቀስ ከሆነ እንደቀደሙት ሁለት የአለም ጦርነቶች አይነት ሳይሆን የኒውክሌር ጦርነት ነው የሚሆነው፤ “ ሲሉ የፑቲንን ማስፈራሪያ ደገሙት፤ አጸኑት።
ይህ የፕሬዚዳንት ፑቲን ማስጠንቀቂያ አለምን ከአጽናፊ እስከ አጽናፍ በድንጋጤ ክው ከማድረጉ ባሻገር ላልተጠበቀው አደጋ እንዲዘጋጅ ከጥልቅ የንጋት እንቅልፉ አባኖታል። የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የታጠቁ አገራትም ሙከራ ባያደርጉም መዘጋጀታቸው አይቀርም። መጨረሻው ምን እንደሚሆን መገመት ቢያዳግትም አሜሪካ ይሄን በመፍራትና ራሽያን ላለመተንኮስ የአገር አቋራጭ ባልስቲክ ሚሳይሏን ሙከራ ለማራዘም፤ በዩክሬን ከበረራ ነጻ የአየር ክልል ለማስፈን እንደማትንቀሳቀስ ደጋግማ ቃሏን ሰጥታለች። ሁኔታዎች በዚህ ስለመቀጠል አለመቀጠላቸው እርግጠኛ መሆን ግን አይቻልም።
የታዋቂው የ”ፎሪን አፊርስ”መጽሔት ጸሐፊዎች ኤማ አሽፎርድና ጆሹዋ ሽፍሪንሰን በዚያ ሰሞን ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ፤ ራሽያ የአሜሪካንና የምዕራባውያንን ጫና መቋቋም ቢሳናትና ተስፋ በመቁረጥ የኔቶ አባል በሆነ አንድ አገር የሳይበር ጥቃት ብትፈጽም እንኳ በሌሎች አገራት ጭምር እንደተፈጸመ ስለሚቆጠር የአባል አገራቱን በቀላሉ ስቦ ወደ ጦርነቱ ሊያስገባ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ያጋባሉ። ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የራሽያ አራት የጦር አውሮፕላኖች የስዊድንን የአየር ክልል ጥሰው ገብተው እንደነበር የሚናገሩ አሉ፤ በሰላም ጊዜ እንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች በመነጋገር ሊፈቱ ይችላሉ። እንደአሁኑ ባለ ቀውጢ ሰዓት ግን በተለይ የኔቶ አባል አገራትንም ሆነ የራሽያን የአየር ክልል መጣስ የተፈራውን ጦርነት ሊጠራ ይችላል። በነገራችን ላይ በገለልተኝነትና በአፍቃሪ ሰላምነት የሚታወቁት ስዊድንና ፊንላንድ የኔቶ አባል ለመሆን ማመልከቻ አስገብተዋል።
አሜሪካና ምዕራባውያን ዩክሬን አለንልሽ፤ ከጎንሽ ነን ሲሏት ከርመው ጦርነቱ ሲጀመር እና ከተሞቿ ወደ ፍርስራሽነት ሲቀየሩና ወደ ድንጋይ ዘመን ሲመለሱ ምንም ባለማድረጋቸው በምንተ እፍረት የጦር መሳሪያ እርዳታውን እያጎረፉት ነው። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ እርዳታው የሚገባው የኔቶ አባል በሆኑ የጎረቤት አገራት አማካኝነት ስለሆነና ራሽያም እየገጠማት ያለውን ጫና ለመቀልበስ የዩክሬን ተባባሪ በምትላቸው አገራት ላይ ጥቃት ከፍታ ጦርነቱን ልታሰፋው ትችላለች የሚለው ሌላው ስጋት ነው።
“ፎሪን አፊርስ” እስካሁን የሁሉም ኔቶ አባል አገራት እያሳዩት ያለው ሕብረት አስገራሚ ቢሆንም ዩክሬንን በጦር መሳሪያ መርዳትና ማስታጠቅ ላይ አጠንክረው እየወተወቱ ያሉት ግን የራሽያ ጎረቤቶች እነ ፖላንደ፣ እስቶኒያ፣ ላቲቪያና ሉቲኒያ መሆናቸው ለራሽያ ብቀላ ካጋለጣቸው፤ የኔቶ አባል አገር ስለሆኑ ወደ 3ኛው የአለም ጦርነት ሊወስዳቸው ይችላል ሲል ስጋቱን ያጋራል። ሌላው ራሽያ ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ከተቆጣጠረችና መንግስት ከለወጠች ጦርነቱ ጎረቤት አገራትን መሰረት ወዳደረገ የሽምቅ ውጊያ ስለሚቀየር፤ በእነዚህ አገራት የሚገኙ የዩክሬን የአማጽያኑን ማሰልጠኛና ወታደራዊ ካምፖችን ካጠቃች ኔቶን ጎትቶ ወደ ጦርነቱ ያስገባል ይላል- “ፎሪን አፊርስ”።
የኔቶና የራሽያ ግጭት ተባብሶ በኒውክሌር የታገዘ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ የታሪክ ልሒቃን ግን ኒውክሌር አልባ 3ኛው የአለም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል እያሉ ነው። ራሽያና ቻይና በ1960ዎቹ፤ ሕንድና ፓኪስታን በ1999 ዓ.ም ካርጊሊ ላይ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ታጥቀው እያለ ነገር ግን ጥቅም ላይ ሳያውሉ ተዋግተዋል በማለት ታሪክን በዋቢነት ይጠቅሳሉ። (በነገራችን ላይ ሁሉም የዘመን አቆጣጠሮች እንደ አውሮፓውያን ናቸው፤)
ይሁንና ጦርነቱ ሊሰፋና አለማቀፍ ሊሆን የሚችለው ሁሉም የጦርነቱ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተሳታፊዎች ከፍ ብሎ ለማሳየት የተሞከሩ ስጋቶችን በጥበብና በማስተዋል ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ አንዳቸው የተሳሳተ ውሳኔ ካሳለፉ ነው። የራሽያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬንን የመውረር ውሳኔ አልያም የአውሮፓ ሕብረትንና ኔቶን የመቀላቀል የዩክሬን ውሳኔ ስህተት ይሁን አይሁን አከራካሪ ቢሆንም፤ የማናቸው ውሳኔ ስህተት እንደነበር ወደፊት ታሪክና ትውልድ ያልተዛባ ፍርድ ይሰጣል። የ3ኛው የአለም ጦርነት ለዛውም በኒውክሌር የጦር መሳሪያና በሳይበር ታግዞ ሊቀሰቀስ 11ኛው ሰዓት ላይ መገኘቱ ግን እርግጥ የሆነ ይመስላል።
ጦርነቱ በእርግጥ ከተቀሰቀሰ ደግሞ የአለም መጨረሻ፣ ምጽዓት ወይም አርማጌዶን ሆነ ማለት ነው። ለዚህ ነው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የራሽያና የዩክሬን ጦርነት የሁለቱ አገራት ወይም የራሽያና የምዕራባውያን የውክልና/proxy/ጦርነት ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ጦርነት ነው ያሉት። ለዚህ ነው ጦርነቱን ሁሉም በጥፍሩ ቆሞ በአንክሮ የሚከታተለው። ኢኮኖሚያዊ ዳፋው ከወዲሁ በነዳጁ፣ በብረቱ፣ በስንዴውና በዘይቱ አገራችንን ጨምሮ በአለም ላይ ተገልጧል። ራሽያ ኔቶ እንደ ክፉ ድንበርተኛ በምስራቅ በኩል ሲገፋ ሲገፋ እንደ አምባዬና ምሽጌ የማያትን ዩክሬንን በመጠቅለል የህልውናዬና የደህንነቴ ስጋት እየሆነብኝ፤ በዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዜሌኒስኪ የሚመራው መንግስትም የአውሮፓ ሕብረት አባል በመሆን ለእኩይ አላማው አብሮ እያደመብኝ ነው በሚል በስጋት የተጀመረው ጦርነት 4ኛ ወሩን ይዟል።
የጦርነት ታሪክ አጥኝ ልሒቃን ገና ከአሁኑ ከ2ኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ የተከሰተ ጦርነት ብለውታል። ጦርነቱንም የ2014 ዓም ተከታይ አድርገው ይወስዱታል። ዩክሬናውያን የክብር አብዮት ብለው ባቀጣጠሉት የጎዳና ላይ ነውጥ የአገሪቱን ከአውሮፓ ሕብረት መቀላቀል የሚቃወሙትንና ለሞስኮ ያደሩትን ፕሬዚዳንት ከስልጣን ያባርራሉ። መፈንቅለ መንግስት በምትለው በዚህ ለውጥ የተበሳጨችው ራሽያ በ2014 ዓ.ም የወደብ ከተማ የሆነችውን ክሬሚያን ጦር አዝምታ ጠቀለለች። በራሽያ የሚደገፉ ተገንጣይ አማጽያን ደግሞ የዩክሬንን ደቡባዊ ምስራቅ አካል የሆነችውን ዶንባስ ተቆጣጠሩ።
በ2021 ደግሞ ራሽያ ጦሯን ወደ ዩክሬን ድንበር በስፋት አስጠጋች። በዚህ የተነሳም ቀጣናዊ ውጥረት ነገሰ። ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ የዩክሬንን ሉዓላዊ አገርነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት በዘወርዋራ የራሽያ አካል ናት አሉ። ኔቶም የራሽያ የደህንነት ስጋት መሆኑን ገለጹ። በአናቱ ዩክሬን አውሮፓ ሕብረትን እንደማትቀላቀል መተማመኛ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። ምዕራባውያንም ሆኑ ዩክሬን ሉዓላዊ አገር ስለሆነች ሕብረቱን የመቀላቀል የማይገሰስ መብት እንዳለት ቆፍጠን ብለው ገለጹ።
ፑቲንም ዩክሬን የራሽያኛ ተናጋሪዎች ላይ ዘር ማጥፋት እየፈጸመች መሆኑን በመግለጽ ክስ አቀረቡ፤ የኒውክሌርና የባዮሎጅካል የጦር መሳሪያ ባለቤት ልትሆን ስለመሆኑም ተናገሩ፤ ዩክሬንም ይሄን ክስ አስተባበለች፡፡ አሜሪካና ኔቶም የዩክሬን ሀሳብ ተጋሩ። ራሽያም እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ኧረ በፍጹም እያለች ስታስተባብል ቆየች፡፡ በመጨረሻም የካቲት 21 ቀን 2022 ዓም በራሽያ የሚደገፉ አማጽያን በኃይል ለተቆጣጠሯቸው የዶኔስክና ሉሀንስክ ሪፐብሊኮች እውቅና ሰጠች። በበነጋው የራሽያ ፌደሬሽን ምክር ቤት ጦሩ እነዚህን አካባቢዎች እንዲቆጣጠር በሙሉ ድምጽ ወሰነ። የካቲት 24 ቀን 2022 ዓም የዩክሬንን ጦር ለማሽመድመድና ከናዚ ለማጽዳት ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን ፑቲን ይፋ አደረጉ።
የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎም በሚሳይልና በአየር ድብደባ የታገዘ ጥቃት ተከፈተ። እግረኛው የራሽያ ጦርም በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ዩክሬን ገሰገሰ። ይሄን ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮልዲሚየር ዜለንስኪ የአስቸኳይ ጊዜና ክተት አወጀ። ራሽያ ከቤላሩስና ከዶንባስ አቅጣጫ ከባድ ወታደራዊ ጥቃት ከፈተች። ሆኖም ዩክሬናውያን ያልጠበቀችው የመከላከልና መልሶ የማጥቃት ውጊያ ገጥሟትም ነበር።
ከዚህም ባለፈ በፑቲን ላይ ከዋሽንግተን እስከ ብራስልስ፤ ከቶሮንቶ እስከ ፓሪስ፤ ከለንደን እስከ ሲውዲን የውግዘት ውርጅብኝ ተዥጎደጎደ። ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና ሲንጋፖር ሳትቀር ፑቲንን አይንህን ለአፈር አሉት። የምዕራባውያን ቀኝ እጅ የሆነው የመንግስታቱ ድርጅት ኢኤስ_11/1 የተባለ ውሳኔ አሳለፈ። አሜሪካና ምዕራባውያን ተናበውና ተቀናጅተው የሞስኮው የሽርክና ገበያ ላይ ኢኮኖሚ ማዕቀብ ጣሉ። የራሽያው መገበያያ ሩብል ተጽዕኖ ላይ ወድቆ የነበረ ቢሆንም አሁን ማንሰራራት መጀመሩ እየተዘገበ ነው። ከ300 በላይ ኩባንያዎች ከሞስኮ ወጡ።
ራሽያም 51 የምዕራባውያን ኩባንያዎች ላይ አጸፋዊ ማዕቀብ ጣለች። በተደጋጋሚ ከምዕራባውያኑ የሚጣል ማዕቀብና ጫና ትንኮሳን ሊያስከትል በማሰብ በፕሬዚዳንቷ አማካኝነት የካቲት 27 ቀን 2022 ዓ.ም የኒውክሌር ጦሩ በተጠንቀቅ እንዲቆምና እንዲጠባበቅ ትዕዛዝ ሰጠች፡፡ በዚህም አለም በእውኑም ሆነ በሕልሙ ያላሰበው የኒውክሌር ጦርነት ደጁ ላይ ቆሞ እያንኳኳ መሆኑን ተረዳ። አውሮፓ ከ1990ዎቹ የዩጎዝላቪያ ቀውስ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩክሬናውያን ተፈናቃዮች እየተጥለቀለቀች ነው። እስካሁን ወደ 6 ሚሊየን የሚጠጉ ዩክሬናውያን ከአገር ውጭ፤ ወደ 8ሚሊየን የሚጠጉ ደግሞ በአገር ውስጥ ተፈናቅለዋል። ጦርነቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የተፈናቃዮች ቁጥር በእጅጉ ሊያሻቅብ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችና ሰላማዊ ሰዎች ሞተዋል።
ታዋቂው የታሪክ ሊቅ ፓል ኬኔዲ “The Rise and Fall of the Great Powers,” በሚለው መጽሐፉ፤ አገራት ባልተፈለገ ጦርነት ዘው ብለው እየገቡ ራሳቸውን ለበረታ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየዳረጉ እድሜያቸውን ያሳጥራሉ ሲል ይገልጻል። አሁንም እየሆነ ያለው ይሄ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በጦርነቱ ራሽያ ዩክሬንን ልታንበረከክ ትችላለች። በሒደቱ ግን እሷም ከመጎዳት አትድንም። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን፤ ከኒውክሌር ጦርነት ስጋት ነጻ የሆነ አለም ለሁሉም ታስፈልጋለች!
ቸር ይግጠመን፤ አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም