የዛሬው የዘመን እንግዳችን አንጋፋ ከሚባሉት የኪነ-ጥበብ ሰዎች አንዱ ነው። በርካታ ደራሲያን የፈጠራ ችሎታቸውን ጨምቀው የከተቧቸውን ድርሰቶች በመድረክ ላይ ሁለንተናዊ ህይወት በመስጠት አንቱ ወደሚሰኝበት ከፍታ የደረሰ የጥበብ ሰው ነው። በተለይም በፀጋዬ ገብረመድህን ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› ሥራ የተመልካቹን መንፈስ በመግዛት ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል። ይህ የኪነ-ጥበብ ሰው ተስፋዬ ሲማ ይባላል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቲያትር ጥበባት ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። እንደተመረቀ የቲያትር ክፍል ኃላፊ በመሆን አርሲ ክፍለሀገር ሰርቷል። አልቆየም እንጂ የባህል መምሪያ ኃላፊ በመሆንም ቦረና ነገሌ ሄዶ የጥበብ አዝመራውን ጀባ ብሏል። በአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት ቢሮ የኪነ-ጥበብ ዋና ክፍል ኃላፊ በመሆንም ከአገር እስከሚወጣ ድረስ የወጣትነት ጉልበትና ላቡን አንጠፍጥፎ አገልግሏል።
ለአምስት ተከታታይ ዓመታት በቲያትርና በስነ-ፅሁፍ ዘርፍ ትምህርት ቤት በመክፈት የቲያትር አፃፃፍ አዘገጃጀት እንዲሁም የአተዋወን ብቃትን በማስተማር ዛሬ በየቴአትር ቤቱ፣ በፊልም ኢንዱስትሪው ስም ያላቸውን በርካታ የጥበብ ሰዎች አፍርቷል። በአዲስ አበባ ከተማ የቲያትርና የሙዚቃ ክበቦች እንዲመሰረቱና እንዲጠናከሩ በማድረግም ሞያዊ አሻራውን አስቀምጧል። በብሔራዊ፣ በአገርፍቅር፣ በአዲስ አበባ የቲያትርና ባህል አዳራሽ፣ በራስ ቲያትር በትወና እና በአዘጋጅነት ምርጥ ስራዎቹን ለተመልካች አቅርቧል። በሬዲዮ ድራማና በቴሌቪዥን በፊልም ስራዎቹም ብቃት ያለው ችሎታውን አሳይቶናል። በኋላም በእነዚህ ምርጥ ስራዎቹ የተመልካችን ቀልብ በመሳቡ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የተፃፈውን “ፍቅር በአሜሪካ” ቲያትርን በመያዝ አሜሪካን ገባ።
ዓላማው ያዘጋጀውን ቲያትር አቅርቦ እንደጨረሰ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ቢሆንም በወቅቱ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ያስነሳውን ‹‹ሀሁ ወይም ፐፑ›› የተሰኘው የፀጋዬ ገብረመድህን ድርሰት በመተወንና በማዘጋጀት በማቅረቡ በወያኔ መንግስት ጥርስ ውስጥ ገባ። እንዲሁም በባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የተመሰረተውን ቅዳሜ ቅኔ የጥበብ ማህበር መሪ በመሆኑ በሚሰራበትም ሆነ በማንኛውም ቲያትር ቤት ምንም አይነት ስራ እንዳይሰራ እገዳ ተጣለበት። በዚህ ምክንያት የሚወደውን ሙያ በመተው ለስራ በሄደባት አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቆ ወደአገሩ ሳይመለስ እንደወጣ ቀረ። ይሁንና በስደት በቆየባቸው ዓመታት በተለይም ላለፉት 22 ዓመታት ከጣይቱ የኪነ-ጥበብና የትምህርት ማዕከል ጋር በመሆን በርካታ ቲያትሮችን በመፃፍ፣ በማዘጋጀትና በመተወን መላውን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ፣ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከሌሎች በርካታ አንጋፋና ወጣት ባለሙያዎች ጋር በመሆን የጥበብ ስራዎችን ለህዝብ ያቀረበ ብርቱ የኪነ ጥበብ ባለሙያ ነው።
በትምህርት ቤቱ “ሰቃዩ ” እየተባለ የሚቆላመጠው ተስፋዬ በአሜሪካ ቆይታው ከጥበቡ ጎን በፋርማሲ ሙያ ተምሮ ላለፉት 19 ዓመታት ሳሚት በተሰኘ ኦክላንድ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል አገልግሏል። ነገርግን የወያኔ ወኪሎች ከግብፃዊ አለቃው ጋር ተመሳጥረው ለኢትዮጵያ በተባለ ጉዳይ ፈጥኖ የሚደርስውን ተስፋዬ ሲማን ከስራው አፈናቀሉት። ይህ የጥበብ ሰው ይህ ሁሉ ችግር ሲደርስበት ከዓላማው ሸብረክ ሳይል የኢትዮጵያን ህልውና የደፈረውን ወያኔ ኢትዮጵያን በጦርነት ሲያምስ በሰሜኑ መከላከያ ላይ አሰቃቂ ድንገተኛ ጥቃት ሲፈፅም “እኔም መከላከያ ነኝ” በማለት የወታደራዊ ልብሱን ለብሶ በዓለም አደባባይ ላይ ስለሃገሩ ክብር ሞግቷል።
ዓለም አቀፍ ወረርሽኙ ኮቪድ 19 በወገን ላይ ብዙ እልቂት እንዳያስከትል በተደረገው ዘመቻና የህዳሴ ግድቡን በአስቸኳይ ጨርሶ ለውጤት እንዲበቃ ለማድረግም ሲያስተባብርና ገንዘብ በማሰባሰብ አገራዊና ጥበባዊ ግዴታውን የተወጣ ድንቅ ኢትዮጵያዊ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ39 በላይ የዙም ገንዘብ ማሰባሰብ ላይ በመሳተፍ፣ ፕሮግራሙን በመምራት ጥበባዊና ታሪካዊ ዝግጅት በማቅረብ፣ ወገንን በመለመንና በማስተባበር ለኮቪድ፣ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ለአገር መከላከያና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሆን በሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ አሰባስቧል::
ይህ ብቻ ሳይሆን ከአምባሳደር ፍፁም አረጋና አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ጋር በመሆን ባለፉት አራት ወራት ብቻ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰበሰብና ለወገን ፈጥኖ ለመድረስ ከጦር ሜዳው ያልተናነሰ ብርቱ ጥረት አድርጓል። ‹‹አርበኛው የጥበብ ሰው›› በሚል መጠሪያ በዳያስፖራው የሚሞገሰው ይህ የጥበብ ሰው አሁንም ለወገኑ ለመድረስ ከሰሞኑ ወደ እናት አገሩ ብቅ ብሏል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የዛሬው እንግዳ በማድረግ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል።
አዲስ ዘመን፡- ወደ ኪነ-ጥበቡ ዓለም የገባህበትን አጋጣሚ አስታውሰንና ውይይታችንን እንጀምር?
አርቲስት ተስፋዬ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ ለኪነ-ጥበብ ልዩ የሆነ ፍቅርና ክብር ነበረኝ። ሆኖም ግን ተመልካችና አድማጭ እንጂ ተሳታፊ እሆናለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁም የሳይንስ ተማሪ ነበርኩኝ። ከፍተኛ ትምህርት ስገባም አንደኛ ምርጫዬ የነበረው የተፈጥሮ ሳይንስ ነበር። ይሁንና ጋዜጣ ላይ ስሜ ተመድቦ ያገኘሁት ማህበራዊ ሳይንስ ላይ ነው። በመሆኑም በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ከነበሩት ትምህርት ክፍሎች የተሻለ ነው ብዬ ስላሰብኩኝ ቲያትር ለመማር አመለከትኩት። እናም በዚያ መንገድ ገባሁ በኋላ ግን ሙያውን ይበልጥ እየወደድኩት መጣሁ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ በኪነ-ጥበቡ ዓለም ከፍተኛ ስም በነበራቸው በእነ መንግስቱ ለማ፣ ደበበ ሰይፉ፣ አቦነህ አሻግሬ እና ፕሮፌሰር ተስፋዬ ገሰሰ እጅ በመማሬ ራሴን እንደዕድለኛ ነው የምቆጥረው። ምክንያቱም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የሚቻለኝን ያህል በጥበብ ጎልብቼ እንድወጣ የእነዚህ ሰዎች ድርሻ ከፍተኛ ነበርና።
በነገራችን ላይ ገና የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ ነው ራስ ቲያትር ሥራዎቼን ማቅረብ የጀመርኩት። የሶስተኛ ዓመት ተማሪ ሆኜ ደግሞ የቴሌቪዥን ድራማ አቀረብኩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ አምስት ኪሎ ግቢ በሚታየው የቲያትር አዳራሽ በርካታ ቲያትሮችን አቅርቤያለሁ። የደራሲ ፍሰሃ በላይ እና የሌሎች በርካታ አንጋፋ ደራሲያንን ስራዎችንም እሰራ ነበር። በትምህርት ቤት ቆይታዬ በተግባርናም በንድፈ ሃሳብም ጥሩ ተማሪ ስለነበርኩ በማዕረግ ነው የተመረኩት፤ ዲግሪዬንም ከፕሬዚዳንት መንግስቱ ሃይለማርያም እጅ የመቀበል እድሉን አግኝቻለሁ። ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁኝ በኋላ የትነው የምንገባው? የሚል ጭንቀት አልነበረብንም። በዚህም ሳይማር ያስተማረኝን ወገን ላመሰግን እወዳለሁ። ምክንያቱም በነፃ ተምረን እንደጨረስን ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ነው የተቀበለን። እኔ የደረሰኝ አርሲ ክፍለሃገር አሰላ ከተማ ውስጥ ነበር፤ እዚያም ለአንድ ዓመት ያህል የቲያትር ኤክሰፐርት ሆኜ ሰርቻለሁ። ከአንድ ዓመት በኋላ ዝውውር ስጠይቅ በመምሪያ ኃላፊነት ወደ ቦረና ነገሌ ነው የተላኩት። ይሁንና ለአንድ ቀን ብቻ ቆይቼ ነው ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ የመጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- የቲያትር ባለሙያዎችን ወደ ማሰልጠን ሥራውስ እንዴት ገባህ?
አርቲስት ተስፋዬ፡- ቦረና እያለሁ በአጋጣሚ አሞኝ ስለነበር የአዲስ አበባ ዝውውሩ ተሳካልኝ። እናም የአዲስ አበባ አስተዳደር የባህልና ስፖርት ቢሮ የኪነ-ጥበባት ዋና ክፍል ኃላፊ ሆኜ ተመደብኩኝ። እዚያ እንደተመደብኩኝ መጀመሪያ ያደረኩት ነገር ወደ ትምህርት ቤቶች መሄድ እና የሚኒሚዲያ ክበቦችን ማደራጀትና ማጠናከር ነው። በመቀጠልም ከክቡር ዶክተር ተስፋዬ አበበ ጋር በመሆን አማተሮችን በስፋት አሰልጥነናል። ይህም ስራ ከፍተኛ ቅቡልነት በማግኘቱ በክረምት በርካታ ፍላጎት የነበራቸውን ወጣቶችን ማሰልጠን ጀመርን። እነ ቴድሮስ ተክለአረጋይና ሱራፌል ወንድሙ ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎቼ መካከል ናቸው። ሁለተኛው ዙር ላይ ደግሞ እነ ሽመልስ አበራ፣ ቴዎድሮስ ለገሰ፣ ሀረገወይን አሰፋ፣ እመቤት ወልደገብርኤልንና አዜብ ወርቁን የመሳሳሉ ታላላቅ አርቲስቶችን ማፍራት ችለናል። እስከ አራተኛ ዙር በዚህ መልኩ ነው የቀጠለው። በተለይ ሁለተኛ ዙር ካስተማርኩኝ በኋላ ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ጋዜጠኞችን በማምጣት የሬዲዮ ባለሙያዎችን፤ የቲያትር ባለሙያዎችን ደራሲያንንና የተለያዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታላላቅ ሰዎች በመጋበዝ የተለያዩ ስልጠናዎችን ይሰጥዋቸው ነበር።
በዚያን ወቅት ስንሰራቸው የነበሩ አብዛኞቹ ስራዎች የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ሥራዎችን ነበር። ያም ሆኖ ግን ‹‹ሎሬት ፀጋዬ ተማሪዎችን አይቀበልም›› የሚል ነገር ይነሳ ነበር፤ ስለሆነም ለምን አልጋብዘውም ብዬ አሰብኩኝ። በወቅቱ የባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስትሩ አማካሪ ነበረ። በቀጥታ ቢሮው አንኳኩቼ ገባሁና ተማሪዎቼ የሰሩትን ስራ እንዲያይልን ጋበዝኩት። ቀና ብሎ በመገረም አየኝና ለመምጣት ተስማማ። በቃሉ መሰረት ዝግጅታችን ላይ ታደመ። ያ ትልቅ ሰው የአማተር ልጆችን ስራ ለማየት መምጣቱ ለብዙዎች ግርምት ነው የፈጠረው። በዚህ ብቻ አልበቃም፤ በልጆቹ ስራ በመደነቁ እገዛ እንድናገኝና ሚኒስትሩ ባሉበት በብሔራዊ ቲያትር ሥራችን እንዲታይልን አደረገ። ልጆቹም በየቲያትር ቤቱ የመቀጠር ዕድል ተፈጠረላቸው። በእንዲህ አይነት መልኩ አራት ዙር ካስተማርን በኋላ ግን የመምሪያ ኃላፊው ተነስቶ ሌላ ሰው ሲመጣ ያኔ ሁሉንም ነገር ዘጋብኝ። ምክንያቱን በውል ባላውቀውም አንድም ከጋሽ ፀጋዬ ጋር ግኑኝነታችን በጣም ስለጠነከረ ሥልጠናው እንዲቆም ተደረገ።
ያም ቢሆን ግን ዘርፉን የሚረከብ ትውልድ የማስቀጠል ሥራችንን ተስፋ ቆርጠን አልተውነውም። አሁን ላይ ጦቢያ ጃዝ እንደሚያዘጋጀው ሁሉ በዚያ ወቅት እኛም ቅዳሜ ቅኔ ብለን የተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎችን እናቀርብ ነበር። በንግድ ስራ ትምህርት ቤት የግጥም ጉባኤ ካካሄድን በኋላ ግን ያኔ ትንሽ ችግር ተፈጠረና መንግስትም ከለከለን። ከዚያ በኋላ የመጠመድ ነገር እየጎላ መጣ። አምስተኛው ዙር ያስተማርኩት በግል ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። በዚያም ጊዜ እነ ግሩም ዘነበንና ቢኒያም ወርቁን የመሳሳሉ ድንቅ ሙያተኞችን ማውጣት ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- ለኪነ-ጥበብ ካለህ ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በርካታ ባለሙያዎችን ለማፍራት ብዙ ዋጋ ከፍለህ ከስኬት ደርሰሃል፤ እንዲያው የስኬት ሚስጥር ምን እንደሆነ ብትነግረን?
አርቲስት ተስፋዬ፡- በግሌ ያለኝንና ያገኘሁትን ነገር መስጠት እወዳለሁ። አገርን የመውደድ ስሜትና ወገኖችን መርዳት በእኛ ጊዜ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። በዚያ ላይ ደግሞ በአስተዳደጌም አገሬን እንድወድ ተደርጌ የተቀረፅኩኝ በመሆኑ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው መምህራን የሰጡኝ ትምህርት ለእኔ እንደ አዲስ ተቀብዬው የተጓዝኩበት በመሆኑ ነው ውጤታማ መሆን የቻልኩት ብዬ አምናለሁ። በተለይም ከነ ሎሬት ፀጋዬ ሥር እንደልጅ ቁጭ ብዬ ተሞክሮ መቅሰሜ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ትልቅ አቅም ሰጥቶኛል ብዬ አምናለሁ። ከዚህም ባሻገር የወጣትነት ጉልበትና እውቀት አፍኜ መቀመጥ የለብኝም ብዬ አምን ስለነበር ልክ አንደእኔ ሁሉ ሌሎች ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች እድሉን እንዲያገኙና እንዲወጡ የበኩሌን ጥረት በማድረግም ጭምር ነው።
እንዳልሽው ለቲያትር ባለኝ ጥልቅ ፍቅር ሰዎች ቀዳዳውን አግኝተው መውጣት እንዲችሉ የሰራሁት ስራ በአብዛኛው ስኬታማ ነበር ማለት እችላለሁ። በእርግጥ በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩብን፤ ሆኖም የማሰለጥናቸው ልጆች ለጥበቡ ያላቸው ፍቅርና ተገዢነት፤ ትጋት ያለኝን እውቀትና አቅም በአግባቡ እንዳወጣው እረድቶኛል ብዬ አስባለሁ። ይሁንና የነገውን ወጣት ለማፍራት ከወዲሁ
ስለታየኝ ነው እንደዚያ ዋጋ የከፈልኩት አልልሽም፤ ግን ደግሞ የእኔን ስሜት ወይም የእኔን ኃላፊነት መወጣቴን ብቻ ነው የማስበው። በዚህም የኢትዮጵያን ኪነ-ጥበብ የሚሸከሙ ትላልቅ ሰዎችን ማፍራት ችያለሁ። አሁን ላይ ብዙዎቹ ከፍተኛ ሥፍራ ላይ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ ቲያትር እየተዳከመ ስለመምጣቱ ይነሳል፤ ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው ብለህ ታስባለህ? ዘርፉንስ ለማሳደግ ምን መሰራት አለበት?
አርቲስት ተስፋዬ፡- ወደፖለቲካው መስመር ካልገፋሽኝ በስተቀር በአንድ አገር ውስጥ የጥበብ መኖር የሕዝብን ስነልቦና እንደሚቀይር ግልፅ ነው። ምክንያቱም ኪነ-ጥበብ ብቻውን የህዝብ አዕምሮ ለመቀየር ከፍተኛ ኃይል ነው ያለው። አንድ ሺ ካድሬ ተሰብስቦ ከሚሰብከው ፕሮፖጋንዳ በላይ አንድ ቲያትር ትልቅ ኃይል አለው። አገርን የሚያሳድገው የመንግስታት መለዋወጥ ሳይሆን የህዝብ አዕምሮ መለወጥ ነው። አንድ መሪ የሚያደርጋቸው ነገሮች በኪነ-ጥበብ እስካልታገዘ ድረስ ህዝብና መንግስት መገናኘት ሲገባቸው አይገናኙም ማለት ነው። ኪነ-ጥበብ በማገናኘት የሚኖረው ሚና እጅግ በጣም ትልቅ ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ዘርፉን ወደ አንድ ደረጃ ማሻገር ያልተቻለው ኢትዮጵያዊነት እንዲሞት ሲደረግ ጥበብም አብሮ እንዲሞት ተደርጓል። ጥበብ ከኢትዮጵያ መፍረስ ጋር አብሮ እየዘቀጠ እንዲሄድ ተሰርቷል። ለዚህ ነው በተቻለ መጠን መቶኛው በዓል ሲከበር ቲያትር ደግሞ እንዲያንሰራራ ሁላችንም መብታችንን ጮኸን ማስከበር አለብን ብለን በአንድ ድምፅ የተስማማነው።
በነገራችን ላይ በንጉሱም ሆነ በደርግ ዘመን ቲያትር ቤቶች እንዲስፋፋ ተደርገው እንደነበር ይታወቃል። ለዚህም ነው እነዚያን የመሳሰሉ ትልልቅ ሰዎችን ማፍራት የተቻለው። ያ ጊዜ ወርቃማው ጊዜ ነው የሚባለው። ከዚያ በኋላ ግን እየተዳከመ ነው የመጣው። እኔ ልጆቼን አስተምሬ ስጨርስ ጠርተውኝ ‹‹አንተ የምታስተምረው በኢህአዴግ ላይ ሰልፍ ልታስነሳ ነው ያሉኝ›› እንደዚህ እያደረጉ ነው እያጠላለፉ እነሎሬት ፀጋዬን የመሳሳሉ ታላላቅ ባለሙያዎች ላይ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩት። በሌላ በኩል ራስ ቲያትር ይሰራል ተባለ ግን እስካሁን አልተሰራም፤ ብሔራዊ ቲያትር ህንፃው በአዲስ መልክ ይገነባል ተባለ ግን አልተገነባም። አሁን ደግሞ ማዘጋጃ ቤት እንዲሁ ቅሬታ የሚያስነሳ ነገር ተከስቶ ነበር። ያንን ተከትሎ ነው አርቲስት ደበበ እሸቱ ቲያትር ቤቱ ከዚህ በኋላ ለባለሙያዎቹ የማይሰጥ ከሆነ ከሙያው እንደሚወጣ የተናገረው።
ከዚያ በኋላ ግን መንግስትም ጥሩና የሚያስደስት ምላሽ ሰጥቷል። እኔ በበኩሌ ውስጥ ያለውን ፖለቲካ ባላውቅም በጣም ነው የተደሰትኩት። አሁን ለባለሙያዎቹ የቲያትር ቤቱ ባለሙያዎቹ ቁልፉ ተሰጥቷቸው ‹‹ሜዳውም፤ፈረሱም ይኸው›› ተብለዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያን በፊት ወደነበረችበት ከፍታ እናደርሳታለን ከተባለ ጥበቡን ማሳደግ ያስፈልጋል። ባለሙያውም መታገል አለበት። የመንግስት አመራሩም ለጥበቡ ማደግ በሩን መክፈት ይገባዋል። ያ ሲሆን ነው ችግሮቻችን በጥበብ የምንሻገረው፤ በመተሳሰብ አገርንና ዘርፉን የምናሳድገው።
አዲስ ዘመን፡- ብዙ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ከአገር ከወጡ በኋላ ጥበቡን እርግፍ አድርገው ይተውታል፤ አንተ ግን በአሜሪካ ቆይታ ከኪነ-ጥበቡ ሳትርቅ የመቆየትህ ሚስጥር ምንድን ነው?
አርቲስት ተስፋዬ፡- እንደነገርኩሽ እኔ ከዚህ ስሄድም ቲያትር ለማሳየት ነው። ሆኖም ግን አልተሳካልኝም፤ ሙሉ ቡድኑም አልሄደም። እኔ በነበረብኝ ችግር ምክንያት ቀድሜ መውጣት ነበረብኝ። እዛ እንደሄድኩኝ የፖለቲካ ጥገኝነት ነው የጠየኩት። ወቅቱ ደግሞ ከመስከረም 11ዱ የአሜሪካ ሽብር ጥቃት በፊት ስለነበር ወዲያውኑ ነው ጥያቄዬ ተቀባይነት ያገኘው። በእርግጥም እዚህ ስራዬን እንዳልሰራ ታግቼ ነበር። በቀን አራት ጊዜ እንድፈርም፤ ግን ምንም ስራ እንዳልሰራ አግደውኝ ነበር። የትኛውም አይነት ፋይል እኔ ጋር አይመጣም፤ ማሰልጠንም ተከልክዬ ነበር። በቲያትር ቤቶችም ላይ አፈና ይካሄድ ጀመር። አንድ ቀን ግን አንድ የኢህአዴግ ባለስልጣን የሚሰራ ቲያትር ስላለ እንዳዘጋጅ ጠየቀኝ፤ እኔ ግን በመስሪያ ቤቴ መታገዴን ብነግረውም ዝም ብዬ እንድመጣ አዘዘኝ። እውነትም እሱ ጋር ሄጄ ዳይሬክት ካደረኩኝ ከሶስት ቀን በኋላ ስመለስ ሁሉም ዝቅ ብሎ ሰላም አለኝ። አንዳንዶቹ እንዳውም ሊያቅፉኝ ሁሉ ፈለጉ። በመሰረቱ እንደዚህ አይነት ነገር እጅግ በጣም ያበሽቀኛል። እኔ ከዩኒቨርሲቲ ወጥቼ ለሰባት ዓመታት የሰራሁት ስራና ግልጋሎት ከምንም ሳይቆጠር ሲያስጠምደኝ፤ አንድ ካድሬ ስለጠራኝና ልቀቁት ስላለ ብቻ የዚህን ያህል ሊያከብሩኝ አይገባም። ከዚያ በኋላ እንዳውም ጠርተውኝ ከጋሽ ፀጋዬ ጋር ያለህን ግንኙነት አቁም አሉኝ። በአጋጣሚ ደግሞ ቪዛ ሳገኝ እዚህ አገር ተመልሼ ብመጣም የማያሰራኝ ባለመኖሩ እዛው ለመቅረት ወሰንኩኝ። ምክንያቱም ማስተማር እወዳለሁ። እንዳልኩሽ የመኖሪያ ፍቃዴ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስተካከለለኝ።
የምኖረው ካሊፎርኒያ ኦክላንድ ከተማ ውስጥ ነበር፤ እዛ ጥቂት እንደሰራሁ ወዲያውኑ ዋሽንግተን ዲሲ ሄጄ ከተሾመ ምትኩ ጋር የመስራት እድሉ ገጠመኝ። በመቀጠልም የፕሮፌሰር አስራት ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ተሳተፍኩኝ። በተመሳሳይ ለጋሽ ፀጋዬ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ከነ አለምፀሃይ ወዳጆ እና ከነ ተመስገን አፈወርቅ ጋር መስራት ጀመርን። በኋላም የጣይቱ የባህል ማዕከል ተቋቋመ። ከ250 በላይ የሚሆኑ ቲያትሮችን በመላው አሜሪካ በመዘዋወር አቅርበናል። በቅርቡም ‹‹የቲዎድሮስ ራዕይ›› የተሰኘው የጌትነት እንየው ቲያትርን ከጣይቱ ማዕከል ጋር እየተዘዋወርን እየሰራን ነበር። መላውን አሜሪካና አውሮፓ በአውሮፕላን፤ በመርከብ፤ በአውቶብስ እየተዘዋወርን አሳይተናል።
ላለፉት 19ኛ ዓመታት በዚህ ሙያ ሰርቻለሁ። አገራዊ ጥሪው ከመምጣቱ በፊት በታላቁ ህዳሴ ግድቡ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ በዙምና በአካልም በመገኘት ሰርቻለሁ። ኮቪድ ሲከሰትም ለቲያትር ባለሙያዎች ገንዘብ አሰባስበን ልከናል። ከዚያ በኋላ ጦርነቱ መከሰቱን ተከትሎ የህዝቦች መፈናቀል እጅግ በጣም ስሜቴን ስለነካውና እድሉንም ስላገኘሁ ከአምባሳደር ፍፁም አረጋ እና ከአምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሤ ጋር በመሆን ከ25 ስቴት ያላነሰ ሥራዬን ሙሉ ለሙሉ አቁሜ እየተጓዝኩኝ ገንዘብ የማሰባሰቡን ስራ በመስራት ላይ እገኛለሁ።
በሳምንት ሁለት ቀን በአውሮፕላን ከቦታ ቦታ እየተጓጓዝኩ ቅስቀሳ አደርጋለሁ፤ በዙም ውይይቶችን አደርጋለሁ። እስካሁን ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የማሰባሰብ እድሉ ገጥሞኛል። ህዝብ በማንቀሳቀስ ሰልፎችን በመምራት፤ ንግግሮችን በማድረግ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን በመስራት የበኩሌን ሚና ለመጫወት ሞክሪያለሁ። በተለይም የሎሬት ፀጋዬን ስራዎችን በማቅረብ መላው ኢትዮጵያዊ ለአገሩና ለወገኑ እንዲደርስ ከፍተኛ ስራ ሰርቻለሁ። አሜሪካ የሚኖረው ደጉ ኢትዮጵያዊም እጅ ከምን ስለው አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ያለውን ሁሉ ሳይሰስት ነው የሚለግሰው። በተለይ ከገና በፊት በነበረው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መድረኮች ዲያስፖራው በከፍተኛ ደረጃ ነበር ሲንቀሳቀስ የነበረው። ከአምባሳደር ፍፁም ጋር ጠዋት ለሶስት ሰዓታት ብዙ ገንዘብ ሰብስበን ከሰዓት ሌላ ከተማ በአውሮፕላን እንሄዳለን። አንድ ጊዜ እንዳውም ቨርጂኒያ የአስር ደቂቃ ልዩነት ባለው ቦታ ላይ በሁለት አዳራሽ ስብሰባ አካሂደን ከፍተኛ ገንዘብ አሰባስበናል፤ ጨረታም አጫርተን ድጋፍ አግኝተናል። እዚህ ከመምጣቴ በፊትም ካሊፎርኒያና ዲሲ ላይ ዝግጅቶች ነበሩ።
በአጠቃላይ በዚህ ደረጃ ቁርጠኛ ሆኜ እንድሰራ ያረገኝ አንድ የኪነ-ጥበብ ሰው ለአገርና ለወገኑ ያለው ከበሬታ ትልቅ በመሆኑ ነው። ‹‹የጥበብ ሰው ነኝ›› ማለት ራስን አሳልፎ ለሌሎች መስጠት ማለት ነው። ይህንን ነገር ስለተረዳሁ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ እኛ ዘርፉን የተቀላቀልንበት ወቅት ጥሩ ዘመን ነበር። ዩኒቨርሲቲ ስንማር መንግስት አላስከፈለንም። ተመርቀን ስራ ከጀመርንም በኋላ የሚከፈለን ብዙ አልነበረም፤ ግን ብዙ የህዝብ ፍቅር ነበረን። ስለዚህ ብዙዎቻችን የዚህች አገር ውለታ ያለብን በመሆኑ ‹‹አገሬ ምን አደረገችልኝ›› ሳይሆን ‹‹እኔ ለአገሬ ምን ላድርግላት ይገባል›› ልንል ነው የሚገባን። በተለይ በእድሜ እየበሰልሽ ስትሄጂ ህሊናሽ የሚፈተነው በዚህ አይነቱ ጉዳይ ላይ ነው። ራስን ብቻ ለማሳደግ የሚደረግ ሩጫ የንፉጎች ኑሮ ነው። ከዚህ አልፎ ተርፎ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ስራ መስራት ያስፈልጋል። አሜሪካ የሚኖረው ዳያስፖራ ከገንዘብ ባለፈ በቁሳቁስም በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል። በቅርቡም ቆቦ ለሚገኙና ባሎቻቸው በጦርነቱ ለሞቱባቸው 140 ለሚሆኑ ሴቶች ትልቅ ትራክተርና ሁለት መካከለኛ ትራክተሮች ተጭነው ተልከዋል።
አዲስ ዘመን፡- ውጭ ከሄድክ በኋላ በአገሪቱ የነበረውን የፖለቲካ ችግር በሥራዎችህ ስትታገል ነበር። በተለይ ‹‹ጀምበር ጠልቆብሃል›› የሚለው መነባነብህ በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ውጥረት በገሃድ የሚያሳይ ነው። ከዚህ አንፃር ታደርገው የነበረው ትግል ምንያህል ውጤት አምጥቷል ብለህ ታምናለህ?
አርቲስት ተስፋዬ፡- እንደአንድ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደአንድ የጥበብ ሰው የበኩሌን አስተዋፅኦ እንዳደረኩ ነው የሚሰማኝ። ልክ በፍቅርና በመሰል ጉዳዮች ላይ እንደምሰራው ሁሉ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መስራት እንዳለብኝ አምናለሁ። ኢትዮጵያ ለእኔ ሁሉንም ነገሬ ናት። ኢትዮጵያ ለእኔ በምናብ አለም የምትታይ የሕዝቦች ስብስብ ናት። እጅግ በጣም ታላቅ የሆነች አገር ናት። በተለይ በጥልቀት ለመረመረና ታሪክን ላወቀና ለተገነዘበ ከማንም አገር የምትበልጥ እጅግ ትልቅ አገር ናት። አሁን ያለው ትውልድ የውጭ ጸሐፍያን ሳይቀሩ የፃፏቸውን መጽሓፍት ሲመለከቱ ኢትዮጵያዊ ለመሆን ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ይገነዘባሉ ብዬ ነው የማስበው። አንድ ቀን ግን ወደነበርንበት የከፍታ ማማ እንደምንደርስ ተስፋ አለኝ። አገሬ ላይ የማኩረፍ ፍላጎት የለኝም፤ በቅርቡ እስረኞች ተፈቱ ተብሎ ብዙዎች ሲያኮርፉ እኔ አላኮረፍኩም። ምክንያቱም መንግስት የራሱ ድርሻ አለው። እሱ በሚመለከተው መንገድ ባንመለከትም ስራውን እንዲሰራ መተው አለብን።
አንቺ ያነሳሽው ጀምበር ጠልቆብሃል በሚለው ስራዬ የኮረኔል ደመቀን ጀግንነት ለማንሳት ነው የሞከርኩት። እሱ ያኔ የከፈለው መስዋዕትነት ከፍተኛ ነው። ለእኔ ይህ ሰው ጀግና ብቻ ሳይሆን ዳግማዊ ቲዎድሮስ ነበር። አሁንም ለመጣው ለውጥ በተለይ አማራ ክልል የነበረውን ብርቱ ተጋድሎ የመራው ይህ ሰው ነው። በዚያ ፕሮግራም እሱን ለማወደስ ነው በሰው አገር ባንዲራችንን እያውለበለብን የዘከርነው። እኔም የወታደር ልብስ ለብሼ መነባንቡን በማቅረብ ለእሱ ያለኝን ፍቅርና እክብሮት ለመግለፅ የሞከርኩት። አሁን እንደተከሰተው ችግር አይነት አጋጣሚው ሲገኝ ለአገሬና ለወገኔ ያለኝን ፍቅር በተግባር ለመግለፅ ነው የምሞክረው።
በቅርቡ እንዳውም ላስቬጋስ ላይ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተን ዝግጅቱ ሊጀመር ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው የሆቴሉ ሰዎች ፕሮግራሙን ማካሄድ እንዳማንችል ነገሩን። ምክንያቱም ጁንታዎቹ ለአገሬው ሰዎች እኛ ገንዘብ የምንሰበስበው ለጦርነት እንደሆነ አሳምነዋቸው ይመስለኛል። ለእኛ ግን ምክንያቱ አልተነገረንም። ይህንን ሁኔታ ለመላው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ መልዕክቱ እንዲደርሰው ተደረገ። ያን ጊዜ ስራ ለመሄድ ያሰበው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በቁጭት ስራ ቀርቶ ወዲያውኑ ትልቅ መጋዘን ተከራይቶ፤ አፅድቶና አስውቦ እንዳውም ከታሰበው በላይ የሞቀና የደመቀ ፕሮግራም ነው ያካሄድነው። በግምት ከ1ሺ200 ሰዎች በላይ ነው የታደሙበት። በአንድ ቀን ገንዘብ ለመስጠት ሲባል ብቻ ያንን ያህል ሽሚያ ሲካሄድ አላየሁም። በእርግጥ ሎስአንጀለስ በአንድ ሌሊት ብቻ 640ሺ ብር ነው መሰብሰብ የቻልነው። ከኩርፊያውም በኋላም እንደመጀመሪያውም ባይሆን ዳያስፖራው ለአገሩ የተጠየቀውን ሁሉ እያደረገ ነው ያለው። አሁንም የሚቀበለኝ አጣሁ እንጂ በግምት 500ሺ ብር የሚያወጣ ሁለት ሻንጣ መድሃኒት ይዤ ነው የመጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለማስቆም ዳያስፖራው ምን እያከናወነ ነው?
አርቲስት ተስፋዬ፡- እርግጥ ነው ኤች.አር 6600 እጅግ በጣም አደገኛ ሰነድ ነው። አንዳንድ በመንግስት ላይ ያኮረፉ ሰዎች ለጊዜውም ቢሆን ቢደግፉትም አሁን ላይ ግን አብዛኛው ዳያስፖራ እውነታው ስለተገነዘበ ማዕቀቡ እንዳይፀድቅ ብዙ ታግሏል። እየታገለም ይገኛል። እንደግፋለን የሚሉትም ቢሆን መንግስትን የሚጥል ስለመሰላቸው ነው እንጂ ከመንግስት በላይ ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ መሆኑን ተገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ለሚገኙ ወላጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ መላክ እና እዚያ እናት አባት ማስመጣት አይቻልም። ከዚህ ቀደምም ለግድቡ ገንዘብ እንዳይሰበሰብ ታግዶ በነበረበት ጊዜ ዳያስፖራው ቦንድ እንዳይገዛ ተደርጓል። አሁንም በተመሳሳይ ዳያስፖራው አገሩንና ወገንን እንዳይደግፍ ነው የሚያደርገው። እንዳልኩሽ ማዕቀፉን ደግፈው አቋማቸውን ያሳዩ አንዳንድ ሰዎች ባለማወቅ ነው ይህንን ሲያደርጉ የነበሩት። የዚህን ሰነድ አደገኛነት ካስረዳናቸውና በአገር ሊኮረፍ እንደማይቻል ከተገነዘቡ በኋላ ብዙዎቹ አቋማቸውን ቀይረዋል።
በቅርቡ እኛ በምንኖርበት ከተማ ላይ የአሜሪካ መንግስት ሶስተኛ ሰውና አፈጉባኤ የሆነችው ናንሲ ፔሎሲ በመጣችበት ወቅት መረጃው አስቀድሞ ስለነበረን በቀጥታ ደብዳቤያችን እንዲደርሳት አድርገናል። ከዚህም ባሻገር ሬቬረንድ ብራውን የተባለው ጥቁር የማህበረሰብ አንቂን ይዘነው ነው የሄድነው። የሚገርምሽ ፓርኪንግ ስራ ላይ የተሰማሩ ኢትዮጵያኖች ሳይቀሩ መረጃ በመሰብሰብና በማቀበል ረገድ ከፍተኛ ሚና ነው እየተጫወቱ ያሉት። አሁን ላይ በተለይ የትግራይ ተወላጅ የሆነው የቺፍ ስታፉ መነሳት ብዙ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ። የቴዎድሮስ አድሃኖም ነገርም ወደ ውድቀት የሚሄድ በመሆኑ አሁን ለኢትዮጵያ ጥሩ በር የሚከፍት ይመስለኛል። ሁላችንም በርትተን ለአገራችን ዘብ መቆም አለብን። ምክንያቱም በአገር ኩርፊያ የለም። አሁን ላይ በእርግጥ አብዛኛው ዲያስፖራ እየነቃ ነው ያለው። አሁንም ስለአገራቸው የሚያለቅሱ የሚጮሁ አሉ። በየስራ ድርሻቸው ሆነው ለአገራቸው ዘብ የቆሙ የሚሞግቱ አንቂዎች አሉን። ወደፊትም እንቅስቃሴው እየተጠናከረ ሲመጣ ጫናውን ለማስቆም እንችላለን። በቅርቡ በሚካደው በአሜሪካ ምርጫ ዳያስፖራ ድምፁን ተጠቅሞ ኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና ለማስቆም እየሰራ ነው። ደግሞም ዲያስፖራዎቻችን የምርጫውን ውጤት የማስቀየር አቅም ስላላቸው የአሜሪካ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ስሊዚህ ያኮረፉትን ብቻ ሳይሆን የሚዋዥቁትንም ሳይቀር በማሳመን እንደቀድሞው ጫናውን እንዲታገሉ ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አርቲስት ተስፋዬ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል