በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የሚገኘው የሸቀጦች ዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት ለብዙዎች ፈተና እየሆነ መምጣቱ እየተነገረም እየታየም ያለ ሃቅ ነው። የእያንዳንዱ ሸቀጥ ዋጋም አይን ጨፍኖ ሲነቃ ያህል ሽቅብ እየወጣ ነው። የኑሮ ውድነቱን አባባሽ ምክንያቶች እንዳሉት ሁሉ አርተፊሻል የኑሮ ውድነት የሚፈጥሩ እንዳሉም መዘንጋት የለበትም። የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ደግሞ በአገሪቱ ያለው የሰላም እጦት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋሉ ያሉ የሸቀጦች ዋጋ መናር እንዲሁም በዩክሪንና ሩስያ መካከል ያለው ጦርነት ተጠቃሽ ነው። ይሁን እንጂ ይሄንን ዓለም አቀፍም ሆነ አገራዊ ምክንያት የሚያባበሱ፣ እጥረት እንዲፈጠር ምርት የሚደብቁ፣ ዋጋ ሲተምኑና ሲያስተምኑ የሚውሉ ደላሎችና ነጋዴዎች ደግሞ መኖራቸው ይታወቃል።
አዎ ዛሬ ላይ ኑሮ ከብዷል አይንን ጨፍኖ እስኪገለጥ ድረስ የኑሮው ሁኔታ የማይደረስበት ደረጃ ላይ እየደረሰ የእቃዎችም ዋጋ እያሻቀበ ነው። ትላንት አንድን እቃ ለመግዛት ያወጣነው ገንዘብ ዛሬ ላይ ምንም የማይገዛ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። ይህ ደግሞ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ራስ ምታት ሆኗል። የዋጋ ጭማሪው በተለይ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ሸማች በሆነባቸው የከተሞች አካባቢ የዜጎች እለታዊ ኑሮ እንዲከብድ አድርጓል።
ድሮ ድሮ ኑሮ ከባድ የሚሆነው ዝቅተኛ ገቢ ላለው የመንግስት ሰራተኛ እንዲሁም ከዛ በታች ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ይባል ነበር፣ ዛሬ ላይ ግን የመንግስት ሰራተኛውም ሌላውም የእለት ስራ የሚሰራውም ብቻ በአጠቃላይ ሁሉንም እየፈተነና እየተፈታተነ ነው። በቅርቡ በልቶ ማደር ብርቅ የሚሆን እስኪመስል ድረስ አስፈሪ ሆኗል።
ዛሬ ላይ የሚገኘው ገቢና ወጪ ፍጹም አይገናኝም “ገቢ በማንኪያ ወጪ ባካፋ” ይሉት አይነት ሆኗል። እና ወጪና ገቢ ካልተመጣጠነ ደግሞ ነገ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመቱ ቀላል ነው። የቤት ኪራይ፣ ቀለብ፣ የልጆች ትምህር ቤት፣ ልጆች ትምህር ቤት ሲሄዱ የሚይዙት ምሳ፣ ትራንስፖርት፣ ልብስ፣ ጫማ፣ የቤት ሰራተኛ፣ ውሃና መብራት ኧረ ምኑ ቅጡ የወጪው አይነት ተዘርዝሮ አያልቅም። ምን አለፋችሁ ሰው ሁሉ ወረድ ብዬ ልኑር ቢል እንኳን እነዚህ ወጪዎች እጅግ የናሩ በመሆናቸው በፍጹም ከወር ገቢ ጋር ተመጣጥነው ማኖር አያስችሉም። እዚህ ላይ አንድ የሚያስማማን ነገር እንዳለ አምናለሁ። የኑሮ ውድነቱ ዓለም አቀፍ ነው የሚለው። ከውጭ የምናስገባው እቃ የዶላር እጥረት አጋጠሞታል የሚለው። ይሄ በሁሉም መልኩ ተቀባይነት ያለው ነው። ነገር ግን በአገራችን መሬት በወንዛችን መስኖ የለማው ሽንኩርት በኪሎ 50 ብር የደረሰው ለምንድነው የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል። ሀይባይ ተቆጣጣሪስ አለ ብለን እንድንጠይቅም ያደርጋል። ለነገሩማ በቅናሽ ዋጋ ምርቶችን የሚያቀርብልን የሸማቾች ማህበር ነበረን፣ የሸማቾችን መብት የሚያስከብር መንግስታዊ ተቃሟም ተቋቁሞ ነበር አሁን ግን የት ይሆን ያሉት ከማለት አገልግሎት ሲሰጡ አይታዩም። መንግስትም ክትትል ቁጥጥር ቅጣትና እርምጃ የሚባሉ ቃላቶች የታከቱት ይመስላል፤ ሁሉም እንዳሻቸው ሆነዋል ልበል?
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግም መንግሥት በቅርቡ ያደረገው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ በኑሮ ውድነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳረፈ ነው። ይህንን ደግሞ ነዋሪዎች እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የሚናገሩት ሀቅ ነው።
የበርካታ አገራት ፈተና የሆነው የኑሮ ውድነት በያዝነው አውሮፖውያኑ 2022 በርካታ የዓለማችን አገራት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አጋጥሟቸዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው ወር በዩናትድ ኪንግደም በ30 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የኑሮ ውድነት በ7 በመቶ ጨምሮ ተመዝግቧል። ኬንያውያንም በምግብ ዘይት፣ በእህል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ጭማሪ እጅጉን እየተማረሩ ስለመሆኑ ያትታል። የእኛን ሁኔታ ግን ለየት የሚያደርገው ኢኮኖሚያችን ዓለም አቀፉን ጫና በአገር ውስጥ ያለው ጦርነት ወደኋላም ሳብ ካልን ኮሮና ቫይረስ እያደረሰበት ያለውን ተጽዕኖ መቋቋም አለመቻሉ ነው። ህብረተሰቡ ቀድሞም ቢሆን ሕይወቱን ይገፋ የነበረው ከእጅ ወደአፍ በሚባል አይነት ሁኔታ ስለነበር አሁን ላይ እንደዚህ ያለውን መዓት መሸከም የሚችልበት ጫንቃ አጣ።
ከቀናት በፊት የብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ፤ አሁንም በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እየገጠመን እንደሆነ አትቷል። ይህ የሆነው ደግሞ ከዋጋ ግሽበት ጋር በተገናኘ ሲሆን፥ ከአምናው የሚያዝያ ወር ጋር ሲነጻጸር የዋጋ ግሽበቱ 36 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱንም ምክር ቤቱ መናገሩ የሚታወስ ነው። ነገሩን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ደግሞ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት እየተመዘገበ ያለው የምግብ ነክ ሸቀጦች ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ምን ያህሉን ሰው ፈተና ውስጥ እንደሚጨምረን ቤት ይቁጠረው።
የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ምን እርምጃ መወሰድ አለበት? የሚለው ደግሞ የሁሉም የሁላችንም ጥያቄ ነው፤ አዎ የዋጋ ግሽበቱን ተከትሎ እየመጣ ያለው የኑሮ ውድነት በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት እንደ ህዝብ መቀጠላችን ጥያቄ ምልክት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ አልያም ለመቆጣጠር፤ በተለይም ምርት በማከማቸት ዋጋ እንዲንር ምክንያት በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ በሚወሰድ እርምጃ፣ በሸማች እና አምራች መካከል በመግባት የኑሮ ውድነት የሚያስከትሉ ነጋዴዎች ላይ በቂ እርምጃ አልተወሰደም የሚሉ ቅሬታዎች ይነሱበታል።
በመሆኑም መንግስት በአሁኑ ወቅት ሊወስድ ይገባል ብዬ የማምነው ምንልባትም ባለሙያዎችም የሚያምኑበት መንገድ የምርት ዋጋ ከፍ የሚለው ፍላጎት ከአቅርቦት ሲያንስ በመሆኑ መሠረታዊ አቅርቦቶች በገበያ እንዲኖሩ መደገፍ፤ ተጨባጭ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ በአንድ ሌሊት የምርቶች ዋጋ የሚጨምርበት አጋጣሚ መቆጣጠር ፤ ትላንት የነበረ ዕቃ በአንድ ሌሊት ጠፍቶ አደረ ሲባል ምርቱን ደበቀው ዋጋውን ከፍ አድርገው መሸጥ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን በመገንዘብ ከፍ ያለ እርምጃ መውሰድ፤ በሌላ በኩል በምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚነሳውን የአገሪቱ የወጪና የገቢ ንግድን ማጣጣሚያ መንገድን በጥሞና ሰምቶ ተግባራዊ ማድረግ።
ከዚያ ባለፈ ግን እንደ አንድ አገር ህዝቦች እርስ በእርሳችን መረዳዳት ነጋዴውም ቢሆን ነግዶ አትርፎ የሚበላው ሰው ሲኖር መሆኑን ተገንዝቦ በተቻለ መጠን ተመጣጣኝ የሆነ ዋጋን ማቅረብ። በክልሎች መካከልም ያለው ግንኙነት የመረዳዳት እርስ በእርስ የመደጋገፍ አንዱ የሌለውን ሌላው ካለው በመረዳዳት ይህንን ጊዜ ተባብሮ ማለፍና በተለይም እንድንወድቅ የሚመኙልንን ጠላቶቻችንን ማሳፈር ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው። አበቃሁ!
በእምነት
አዲስ ዘመን ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም