ያረፍዳል.. አንድም ቀን በሰዓቱ ክፍል ገብቶ አያውቅም። ከመምህር እስከ ተማሪ በእሱ ኋላ መቅረት ብዙዎች ተዘባብተዋል። ‹ቆይ አንተ ስንት ሰዓት ከእንቅልፍህ ብትነሳ ነው ከተማሪ መጨረሻ ክፍል የምትደርሰው› ሲሉ ጓደኞቹ ስቀውበት ያውቃሉ።
ማርፈድ የስንፍና ምልክት ነው እየተባለ ባንዲራ ሲሰቀል ተማሪ ፊት ወጥቶ ተገርፎ ያውቃል። ከሁሉም የባሰው ደግሞ የስም ጠሪያቸው የመምህር ክብሩ ቁጣና ግርፊያ ነበር። በሕይወቱ ማድረግ ያቃተው አንድ ነገር ቢኖር ከመምህር ክብሩ ቀድሞ ክፍል መገኘትና አለመገረፍ ነው። በሕይወቱ ሮጦ ያልደረሰበት፣ ሮጦ ያልቀደመው ስም ጠሪያቸውን መምህር ክብሩን ነው።
ትንሽ መዳፉ፣ ትናንሽ ጣቶቹ የመምህር ክብሩን አርጬሜ ሳይቀምሱ ክፍል ገብቶ አያውቅም። አሳዛኝ ፊቱ በመምህር ክብሩ ቁጣ ሳያፍርና እንደ ድልህ ሳይቀላ ቀርቶ አያውቅም። አሳዛኝ አይኖቹ በዛ አርጩሜና በዛ ዲያቢሎሳዊ ቁጣ እንባ ሳያቀሩ ክፍል ገብተው አያውቅም። ንጹህ ልቡ በጓደኞቿ ሳይሳቅባት ክፍል ገብታ አታውቅም። እንጭጭ ነፍሱ ሳትጎሳቆል ክፍል ገብታ አታውቅም። በዚህ ሁሉ ውስጥ የረጋ ነው..የሰከነ። አያለቅስም። ግርፊያው ነፍሱ ድረስ ዘልቆ እየተሰማው እንኳን አይባባም።
ዛሬም አረፈደ..የደብተር ቦርሳውን ትከሻው ላይ እንዳንጠለጠለ ወደ ክፍላቸው በረረ። መምህር ክብሩ ቀድመውት ክፍል ገብተው ነበር። እንደልማዱ የስም ጠሪው አይን እየገረፈው በር ላይ ቆመ። አቤት ጽናት! ፊቱ አልተረበሸም፣ ነፍሱ አልተጨነቀችም። በዛ ጠዋት፣ እዛ ቦታ በመምህር ክብሩና በተማሪዎች ፊት እንደ እየሱስ ለፍርድ ሲቆም ደስ እያለው ለመሞት የተሰናዳ መሲህ ይመስል ነበር።
በር ላይ እንደቆመ መገረፍ የማይሰለቻቸውን አሳዛኝ እጆቹን አያቸው። በመምህር ክብሩ አርጩሜ ለአመታት ተገርፈዋል..ከእሱ በቀር ለማንም የማይታዩ የህመምና የጥዝጣዜ ሰንበሮች መዳፉ ላይ ነበሩ። አምስቱንም ጣቶቹን ያወየበ፣ የመምህር ክብሩን ፈርጣማ ክንድና የመግረፊያቸውን መልክ የቀለመ የጅራፍ ንቅሳት። ከትከሻው እየተንቆራጠጠ ህመሙን እንዲደብቁለት እጅጌውን ወደ መዳፉ እየሳበ ጣቶቹን አለበሳቸው። እነዛ እየሱሳዊ ጣቶች፣ እንደ ካህን መዳፍ የሚሳሙ እጆቹ ለግርፋት ተሰናዱ። እየሞተ ሊኖር ራሱን ለግርፊያ አሰናዳ።
መምህር ክብሩ አዩት። እነዛ አይኖች መዳፉ ላይ ከተነቀሱት የመከራ ሰንበሮች እኩል አይኖቹም ላይ ተነቅሰዋል።
ወዳለበት እየተራመደ ‹ቆይ አንተ መቼ ነው የሚገባህ? አንተን ስቀጠቅጥ የኔ ክንድ ዛለ…እንዴት ብገርፍህ ነው የሚገባህ? ሲሉ አንድ ጊዜ በጥፊ ደረገሙለት። እጆቹ ብቻ አይደሉም ጉንጮቹም ጥፊውን ለምደዋል..እንዲህ እንደዛሬው እየተራገሙ ይመጡና በደንዳሳ መዳፋቸው በጥፊ ያጠናግሩታል። በወጠምሻ መዳፋቸው አፈፍ አድርገው ከሊጦስጥራ እስከ ጎለጎታ ድረስ መስቀሉን ተሸክሞ በአይሁድ እንደተንገላታው እየሱስ እየረገሙና እየተሳደቡ እያንገላቱትም ወደ ተማሪዎቹ ፊት አቀረቡት።
‹ቆይ አንተ አይገባህም? እንዴት ብትገረፍ ነው የሚገባህ..አመቱን ሙሉ ገረፍኩህ..ግን ያው ነህ፣ መቼ ነው የምትሻሻለው?
ኤልሻዳይ ዝም አለ።
‹ንገረኝ ምን ይዘጋሃል..ሲሉ ጆሮ ግንዱ ላይ ሁለተኛውን ጥፊ አሳረፉበት።
የትንሹ ልጅ ዝምታ ይገርማል። ዝም አለ..እንደ እየሱስ..ለእርድ እንደተዘጋጀ በግ።
‹እንዳንተ አይነቱን ደንቆሮ በማስተማሬ አዝናለሁ›። ሲሉ ተቆጥተው ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጡትን ከእሱ ሌላ ማንም ተገርፎበት የማያውቀውን አርጩሜ አንስተው ጣቶቹ ላይ አሳረፏቸው። ጣቶቹ የአርጩሜውን ምት መቋቋም ተስኗቸው ተንቀጠቀጡ። ግራ ቀኙን እያፈራረቀ አስር ተገርፎ ወደ ቦታው ሄደ። ወደ ቦታው ሲሄድ እጆቹ እየተንቀጠቀጡ ነበር። ፊቱ ደም ለብሶ፣ አይኖቹ እንባ አቅርረው ነበር። ወደ ቦታው ሲሄድ ልቡ መቼም የማይወጣውን የመምህር ክብሩን መከራ አዝሎ ነበር። ነፍሱ በጓደኞቹ ሳቅ መግቢያ ቀዳዳ አጥታ ነበር። ጎስቁሎ ነበር..ግን አላለቀሰም። እንዳውም እንደዛ በክብር ተራምዶ አያውቅም።
መምህር ክብሩ ስለእሱና ተገርፈውና ተመክረው ስለማይገባቸው አንዳንድ ስለባለጌ ተማሪዎች አወሩ። የኤልሻዳይን ስም እየጠሩና ወደ እሱ እየጠቆሙ ሰው ባለጌ ሲሆን እንደ ኤልሻዳይ ነው። እሱን እንዳትሆኑ፣ እሱን ጓደኛችሁ እንዳታደርጉ፣ እሱ አመት ተገርፎ ያልገባው ሰነፍ ተማሪ ነው እያሉ ተማሪዎቻቸውን መከሩ። ሕይወት ቀጠለ ነገም ከዛ በኋላም ባለው ቀን ውስጥ የተቀየረ ነገር አልነበረም..መምህር ክብሩ ከመግረፍ፣ ኤልሻዳይም ከመገረፍ የዘለለ ታሪክ አልጻፉም። መምህር ክብሩ ከመግረፍ ባለፈ የኤልሻዳይን ኋላ መቅረት ትልቅ ጉዳይ አድርገው ነጋ ጠባ ክፍል በገቡ ቁጥር ለተማሪዎቻቸው ማስተማሪያ አደረጉት። የአመቱ መጨረሻ ላይ ኤልሻዳይ ሲወድቅ ሁሉም ተማሪዎች አለፉ። ኤልሻዳይ ከጓደኞቹ ኋላ ቀረ..በሚቀጥለው አመት እዛው ክፍል መምህር ክብሩ የነኤልሻዳይ ስም ጠሪ ሆነው ተመደቡ። በአዲስ ዓመት መምህር ክብሩ ለመግረፍ፣ ኤልሻዳይ ደግሞ በማያውቃቸው ተማሪዎች ፊት ለመገረፍ ዳግም ተገናኙ።
እንደተለመደው ሕይወት ቀጠለ..ሁሌ ጠዋት ኤልሻዳይ ክፍል በር ላይ ይቆማል። መምህር ክብሩም ይገርፉታል። መምህር ክብሩ አንድ ሰኞ ቀን ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ኤልሻዳይን ሲያስተዋውቁት እንዲህ ነበር ያሉት ‹እሱ ጓደኞቹ ሁሉ ትተውት ያለፉ ሰነፍ ተማሪ ነው፣ እናንተም ጥላችሁት እንደምትሄዱ አምናለሁ። ሰነፍና የማይገባው ተማሪ ነው› ነበር ያሉት።
አንድ ቀን ግን እንዲህ ሆነ.. መምህር ክብሩ ሁሌ ከቤት ወደ ትምህርት ቤት በሚመላለሱበት ብስክሌት ላይ ሆነው ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ። ከፊት ለፊታቸው ቦርሳውን ያነገተ አንድ ተማሪ አንድ አዛውንትን በዊልቸር እየገፋ መንገዱን ሲያቋርጥ ተመለከቱ። ኤልሻዳይ ነበር። ያ ለዘመናት የገረፉት፣ ያ ለዘመናት በተማሪዎች ፊት ያዋረዱት ትንሽዬ ልጅ ነበር። ያ ሲሰድቡትና ሲረግሙት ዝም የሚለው፣ በገቡበት ክፍል ሁሉ ስንፍናውን አውርተውለት የማይጠግቡት ታዳጊ ነበር። ለካ የሚያረፍደው እኚህን አባት አድርሶ ሲመለስ ነበር። ለካ ኋላ የሚቀረው እኚህን ሽማግሌ እየገፋ መለመኛቸው ጋ አድርሶ ሲመለስ ነበር።
ከብስክሌታቸው ላይ ወርደው መሬት ቁጭ ብለው አለቀሱ። የዛ ብላቴና ትንሽዬ ነፍስ ትልቅ ነፍሳቸውን አስጨነቀቻቸው። መሬት ቁጭ እንዳሉ አንድ ተማሪ በአጠገባቸው እየሮጠ ሲያልፍ አዩ..ቀና ሲሉ ኤልሻዳይ ነው። ወደ ትምህርት ቤት እየሮጠ አዩት..እግዜር እንኳን ይቅር ቢላቸው ራሳቸውን መቼም ይቅር እንደማይሉት ያውቃሉ። ቀድሟቸው ክፍል ገብቶ እንዲያገኙት ሲሉ ኋላ ቀሩ..
ክፍል ሲገቡ ኤልሻዳይን ቦታው ላይ አዩት። ወደተቀመጠበት ተራምደው እቅፍ አደረጉት..ሲያቅፉት እያለቀሱ ነበር። የበደሉትን ያክል ለዘላለም ሲያፈቅሩት ይኖራሉ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2014