ዛፍ በለጋነቱ ካልተቃና፤ ሰው በልጅነቱ የሰውነት እሴትን እንዲላበስ ካልተደረገ፤ ሁለቱም ካደጉና ከጠነከሩ በኋላ ለማቃናት የሚደረገው ጥረት ከንቱ ድካም ነው:: ምክንያቱም ዛፉም ይሰበራል፤ ሰው ሲሆን ደግሞ ከመቃናት ይልቅ እኩይ ባህሪው የበለጠ እየጎላ ይሄዳል:: የዛሬው አሸባሪ የሕወሓት ቡድንም የዚህ እውነት አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ቡድኑ ከሕዝቡ ይልቅ በውጭዎች ዳረጎት ተኮትኩቶ በተጣመመ መንገድ ማደጉ በዘመናት ጉዞው ከሰላም ይልቅ ጦርን፤ ከሃሳብ ይልቅ ጉልበትን፤ ከመረጋጋት ይልቅ ሽብርን፤ ከትብብርና አብሮነት ይልቅ መከፋፈልና መለያየትን፤ ከወንድማማችነት ይልቅ ጠላትነትን፤ ከመተማመን ይልቅ መጠራጠርን፤ ከፍቅር ይልቅ ፀብና መገዳደልን፤… መርጦ ከውልደቱ እስከ ሞቱ እየዳከረ ይገኛል:: ይሄን ተነግሮም፣ ተጽፎም ፈቅ የማይል የዚህን ቡድን የእኩይና የሴራ ምግባር ጉዞ መተረኩም ሆነ መጻፉ ውቅያኖስን በማንኪያ ይሉት አይነት ቢሆንም፤ እንደው ለትውስታ ያህል ያውም ቆሜለታለሁ በሚለው የትግራይ ሕዝብ ላይ ከፈጸማቸው የበዙ ግፎች ውስጥ እጅግ በጥቂቱ ለማንሳት ልሞክር::
የጥፋት ሀ…ሁ
ወቅቱ እዚህም እዚያም የተቃውሞ ድምጾች የሚሰሙበት ነበር፤ በ1960ዎቹ ከፍ ብሎ የሚደመጠው የተማሪዎች አመጽና ተቃውሞ በአብዮት ታግዞ የመሬት ላራሹን ጥያቄ የመለሰ ለውጥ አመጣ:: ይሁን እንጂ በለውጥ ውስጥ ሆኖ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ሲቻል፤ በአብዮት የመጣውን የሥርዓት ለውጥ በሌላ አብዮት የመለወጥ ተልዕኮን ይዘው ጥቂቶች ከትምህርት ቤት ወደ ጫካ አመሩ:: በተረካቸው እንዳሰፈሩትም አስራ አንድ ሆነው ነፍጥ አንግተው ደደቢት በረሃ ከተሙ:: እናም ነፍጥ አንግቶ ስለ ሰላም፤ ጫካ ገብቶ ስለ መነጋገር፤ ከሰው ተነጥሎ ስለ ፍቅርና አንድነት፤… ማሰብ አይቻልቸውምና የሴራ ጉዟቸውን፤ የተልዕኮ መንገዳቸውን ከዚሁ ሥፍራ አንድ ብለው ጀመሩ::
በሰላም ፈንታ ጦር ሲመዘዝ
በሴራ ተመስርቶ በሴራ ውስጥ ያደገውና በሴራ ኑሮውን እየመራ ያለው የሕወሓት ቡድን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ላለ ችግር ሁሉ መንስኤ ሆኖ የሚገለጽ ነው:: ግማሽ ምዕተ ዓመት የሚሆነው የሕወሓት የጥፋት ጉዞ ውስጥ በርካታ ጦርነቶች ተቀስቅሰዋል፤ ይሄን ተከትሎም በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷል:: ምናልባት እነዚህ ጦርነቶች የሕወሓት በጦርነት ውስጥ የተመሰረተ የኑሮ ዘይቤ ገፊ ምክንያት ባይሆንባቸው ኖሮ ላይከሰቱ፤ ወደ ጦርነት ሳይገባ ቀድሞ በንግግር ሊፈቱ የሚችሉበት እድል ስለመኖሩ የሚናገሩም ቀላል አይደሉም:: በዚህ ረገድ ከደርግ መንግስት ጋር በእነዚሁ ኃይሎች ፊታውራሪነት የተካሄደው ዓመታትን የዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት፤ በኋላም ከኤርትራ ጋር የተካሄደው አውዳሚ ጦርነት፤ እና ሌሎችም በንግግርና ድርድር ሊፈቱ ይችሉ እንደነበር የሚናገሩ በርካቶች ናቸው::
ለምሳሌ፣ የደርግ ስርዓት እውን መሆንን ተከትሎ ሕወሓት ነፍጥ አንግቶ ወደ ጫካ ከሚገባ ይልቅ፤ በውስጥ ሆኖ የሕዝብ ጥያቄዎች የሚመለሱበት ሂደት ላይ አብሮ በመስራትና በመነጋገር ጦርነትን ማስቀረት ይቻል ነበር የሚሉ አሉ:: ከኤርትራ ጋር የነበረውም ቢሆን ችግሩን በውይይት መፍታት ይቻላል የሚል ሰፊ ሙግት እንደነበር የድርጅቱ ነባር ታጋዮችና አመራሮች ሳይቀር ሲገልጹ ተሰምቷል:: በወቅቱ የእነዚህ ሰዎች ሀሳብ ተደምጦ ቢሆን ያ ሁሉ አውዳሚ ጦርነት ባልተካሄደ ነበር ሲሉ የሚቆጩም አሉ:: ጉዳዩን ቀረብ ብለው በደንብ የሚያውቁም በትግል ላይ እያሉም ከኢዲዩ እና ሌሎችም ድርጅቶች ጋር የተደረገው ጦርነት ሂደቱ ሕዝብን ያስቀደመ ቢሆን ኖሮ ምንም ለጦርነትና መገዳደል የሚያበቃ ምክንያት እንዳልነበረው ይገልጻሉ:: እነዚህንና ሌሎች መሰል ማሳያዎችን በማንሳትም የጦርነቶቹ ሁሉ ምክንያትም ማጠንጠኛም የሕወሓት ሴራ አዘል አፈጣጠር ስለመሆኑ ያስረዳሉ::
በግፍ የተቀጠፉ የተጋሩ ነፍሶች
የሕወሓት የጥፋት ቡድን የጦርነት እሳቤው እና ይገዳደሩኛል ያላቸውን የማጥፋት አባዜው በእርሱና በሌሎች ተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል ብቻ እንዳልነበረ የድርጅቱ ነባር ታጋዮችን ጨምሮ በርካቶች የሚናገሩት ሃቅ ሆኗል:: ይልቁንም ቡድኑን ለመቀላቀል በገፍ ወደ ጫካ የገቡና አብረውት ለመታገል የተቀላቀሉ፤ ነገር ግን የተሻለ ሃሳብና ራዕይ ያላቸውን ወጣቶች በመብራት እየታደኑ በግፍ የማስወገድ/የመግደል አካሄድንም ይከተል ነበር:: ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ለነጭ ሽብር አጸፋ የተጀመረው ቀይ ሽብር እርምጃ ከፍ ብሎ በተገለጠበት ወቅት በ1970 እና 71 ብዛት ያላቸው የትግራይ ልጆች ከአራቱም ማዕዘን ወደ በረሃ ገብተው እንደነበር በወቅቱ በድርጅቱ ውስጥ የነበሩ ታጋዮች ይናገራሉ::
እንደ የዐይን እማኞቹ አገላለጽ፤ ከእነዚህ ውስጥ 90 ከመቶው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፣ ወይም የሃይስኩል ተማሪ፣ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ትልልቅ ቦታ ላይ የሚሰሩ ነበሩ:: ወደ በረሃ ከወጡ ወጣቶች መካከል ከፍ ያለ ግንዛቤና ክህሎት የነበራቸው ዓድዋን ጨምሮ ከሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የተቀላቀሏቸው ወጣቶች ነበሩ:: ሆኖም የሕወሓት ቡድን በተለይ የስብሃት ኔትዎርክ ጽዳት በሚል ያንን በረሃ የወጣውን የተማረ ወጣት ሁሉ የተለየ ሃሳብ አለው በሚል እስር ቤት አስገባው:: ከኤርትራ ጭምር ቀይ ሽብርን ፈርተው በሺህ የሚቆጠሩ የተማሩ ወጣቶች ወደ በረሀ ገብተው ነበር። ይሄንን ያየ የስብሃት ነጋ ኔትዎርክ ጽዳት በሚለው አሰራሩ አውራጃ ሳይለይ የመጡትን በሙሉ እስር ቤት አስገባቸው:: ሆኖም ከእስር ቤቱ የወጣ አንድም ሰው አልነበረም:: ሁሉም ለትግል እንደወጡ እስር ቤት ታጉረው በዚህ የጥፋት ቡድን ሴራ ተጨፈጨፉ::
በዚህ መልኩ የተማሩ የትግራይ ወጣቶች ጥሪውን ተቀብለው ወደ በረሃ ለትግል በወጡ፣ የተሻለ ሃሳብ አላቸው፣ ከእኔ እሳቤ ጋር ላይራመዱ ስለሚችሉና ካሁኑ ደጋፊ ስላበዙ ነገ ሊገዳደሩኝ ይችላሉ፣ ወዘተ በሚል ተልካሻና የተንኮል እሳቤ፤ የሕወሓት ቡድን በትግል ወቅት በየምክንያቱ የሚገላቸውን ወጣቶችም ሆኑ ሌሎች ሰዎች ለራሳቸው መቀበሪያ ጉድጓድ ያስቆፍራቸው እንደነበር፤ በዚህም እሺ ብለው የሚቆፍሩ ታስረው ጉድጓዱ ውስጥ ከተጣሉ በኋላ በጥይት ተደብድበው ይገደሉና እዛው አፈር እንዲለብሱ ስለመደረጉ፤ አልቆፍርም ያሉ ደግሞ ሌሎች ጉድጓድ እንዲቆፍሩላቸው በማድረግ እጃቸው ታስሮ ጉድጓዱ ውስጥ ይጣሉና ከነሕይወታቸው አፈር ያለብሷቸው እንደነበር እማኞች ይናገራሉ::
በዚህ መሰል አሰቃቂ ትዕይንት በወር ውስጥ ከአምስት መቶ ያላነሰ ሰው እንደሚገደልም ነው የሚያስረዱት:: በዚህ መልኩ በተፈጸመ የግፍ ጭፍጨፋ በትግል ወቅት ሞተዋል ከሚባሉ 60 ሺህ የትግል ጓዶች የላቀ ቁጥር በሕወሓት የእኩይ እጆች ተገድለዋል፤ በዚህም ለትግል ብለው በወጡበት የቀሩ የትግራይ ወጣቶች፣ ምሁራንና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች እጅጉን የበዙ ናቸው:: እንደውም ደርግ፣ ኢህአፓ እና ኢዲዩን ጨምሮ በአምስቱ ግንባር ተዋግቶ ከተሰዋው ታጋይ በላይ፤ በሕወሓት አመራሮች በተለይም በስብሃት ኔትዎርክ የተገደለው ታጋይ እጅጉን የላቀ ስለመሆኑ በቁጭት የሚናገሩ ነባር ታጋዮች አሉ::
በዚህ መልኩ ከ1977 እስከ 1980 የዘለቀው ጭፍጨፋ፣ በ1977 ማለሊት በሚል በዓድዋ ልጆች የተመሰረተ ፓርቲ ሰዎችን ጨምሮ፤ ሌሎችንም በአብረን እንታገል ሽፋን በአንድ ቀን ሌሊት በልቶ የጨረሰ ቡድን ነበር:: በ1983 ወደ አዲስ አበባ ሲገቡም፣ በኋላ ይገዳደሩናል ያሏቸውን ታጋዮችንና ወታደራዊ አዛዦችን ሳይቀር በዚህ መልኩ አጽድተው ነበር በኔትዎርክ ተሳስረው የገቡት::
መቶ ሺዎች የወደቁበት፤ ጥቂቶች የነገሱበት
ብዙዎች ነጻነትን ሲናፍቁ ለባሰ ጭቆናና ድህነት፣ እንግልትና ጉስቁልና የተዳረጉበት፣ በነጻነት የዳቦ ስም 17 ዓመታትን በዘለቀው ጦርነት ብዙዎች ዋጋ ከፍለዋል:: ምንም እንኳን የውጭው ጣልቃ ገብነት ትልቁን ሚና ቢጫወትም ሕወሓት በትረ ሥልጣኑን እንዲጨብጥ አስችለዋል:: ይሁን እንጂ ይሄ ብዙ ሺዎችን ዋጋ ያስከፈለው የትግል ጉዞ ከድል ማግስት የጥቂቶችን ጥቅምና ፍላጎት ማስጠበቅ ላይ ተመስርቶ ብዙሃኑን የበይ ተመልካች በማድረግ የመከራ ሕይወት እንዲገፉ አስገድዷል:: ለምሳሌ፣ አካላቸውን የገበሩ ስልሳ ሺህ ታጋዮች ዛሬ በየቦታው ተበትነው ቀርተዋል፤ ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባና በየአካባቢው የተበተኑ 40ሺ ታጋዮች እንዳሉ ይነገራል::
እነዚህ ወገኖች ግን በስራ ወይም ሌላ የተሻለ ኑሮ አግኝተው ሳይሆን እውነቱን በቁጭት የሚናገሩት ነባር ታጋዮች “ከአስር ለማኞች አምስቱ ወይ ስድስቱ የሕወሓት ታጋይ ነበሩ ናቸው፤ በርካታ ታጋይ እህቶቻችን ደግሞ ስጋቸውን እየሸጡ ለመኖር ተገድደዋል፤” ሲሉ እንደሚገልጹት፤ በከፋው የልመና እና የሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ውስጥ ያሉ ናቸው:: በትግሉ ሂደት ዋጋ የከፈሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት የትግራይ ልጆች እንዲህ በየቦታው ተበትነው ለችግር ከመዳረጋቸው በተጓዳኝ፤ በትግራይ ክልል ውስጥም ቢሆን ከ20 ሺህ በላይ ታጋዮች ተበትነውና በየጎዳናው ወድቀው ለመኖር መገደዳቸውም የታወቀ ነበር:: ይህ ብቻም አይደል፣ ከ100 ሺ በላይ እናቶች ፍጹም ድህነት ውስጥ፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች ህክምና እንኳን በማያገኙበት ሁኔታ ውስጥ ለመኖር ፈርዶባቸዋል::
በክልሉ መኖር ያቃታቸው የሰማዕታት ልጆችም አገር ጥለው እየተሰደዱ በየመን፣ በሊቢያና በሌሎች አካባቢዎች በየባህሩ እየሰጠሙ ቀርተዋል:: ይህ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ የመስዋዕትነቱ ዋጋ በዚህ መልኩ ሲከፈለው፤ በዚህ ሕዝብ መስዋዕትነት ላይ ተረማምዶ ለስልጣን የበቃው የሕወሓት ቡድንና ኔትዎርኩ ግን 27 ዓመታት የስልጣን ዘመኑን ራሱን ሲያበለጽግ፣ የቡድኑን ኑሮ ሲያደላድል ለመኖሩ አያሌ ማሳያዎች ያነሳሉ::
ለዚህም ነው የትግራይ ሕዝብ በሴፍቲኔት ተቀይዶ እንዲኖር ሲፈረድበት፤ የሕወሓት ቀንደኛ ሰዎች በቤተሰብና በአካባቢ ተደራጅቶ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ አዲስ አበባ ውስጥ ከ600 ሺህ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚከራይ ህንጻ ባለቤት ለመሆን በቅተው የነበረው:: በጫካ እያሉ የትግራይ ህዝብ ለከፋ ረሃብ እንዲጋለጥ አድርገው በስሙ የለመኑትን ሰብዓዊ ድጋፍ ለግል ጥቅማቸው በማዋል እንደ ኢፈርት ያሉ ግዙፍ ድርጅቶችን ለቡድናቸው መንደላቀቂያ የገንዘብ ምንጭ፣ የሃብት ማፍሪያ አድርገው የመሰረቱት::
ጠቅላይነት/ አልጠግብ ባይነት
የሕወሓት ቡድን በሕዝብ ዋጋ ለሥልጣን የበቃ፤ በነጻነትና ዴሞክራሲ ምሎ ከፍ ያለ ቢሆንም፤ መጨረሻው ግን ሥልጣኑንም፣ ሃብቱንም (ብዙዎች እንደሚሉት “ሥልጣኑንም፣ ባንኩንም፣ ታንኩንም”) ጠቅልሉ በጥቂት የድርጅቱ ሰዎችና ኔትዎርኮቻቸው እጅ በማስገባት ፈላጭ ቆራጭነቱን አሳይቷል:: ቡድኑ በሕዝብ ዋጋ ታግዞ፤ በሴራና ሺዎችን በትግል ሜዳ በማጽዳት እሳቤው በግፍ ጨፍጭፎ አዲስ አበባ ከገባ በኋላም፤ የሕዝብን ዋጋ ዘንግቶ ኢትዮጵያን ይገዛት የነበረው የአንድ ቤተሰብ ወይም የዘር ሃረግ አባላት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው::
ለምሳሌ፣ ትግራይ ውስጥ በሁሉም ቦታ በዋናነት የስብሃት ቤተሰብ፣ ወረድ ሲል ደግሞ የኔትዎርኩ አባላት ነበሩ ሁሉን አድራጊዎችም፤ በሁሉም መስክ ተጠቃሚዎችም:: በዚህም ከ27 ዓመታት የሥልጣንና የሃብት ዙፋኑ የሕዝብ ማዕበል ገፍቶ እስኪያወርደው ድረስ፤ ሙሉ ሥልጣኑን፣ ደህንነቱን፣ የንግድ ስርዓቱን፣ ግብርናውን፣ ኢንቨስትመንቱን፣… ጠቅልሎ ተቆጣጥሮት ኖሯል:: በዚህም ከቤተ ክህነት እስከ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት፤ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እስከ መቀሌው አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት አገሪቱን ሲገዙ የነበሩት ሴራን ታቅፎ ወደ ትግል የወጣው እና ከነሴራው ስልጣን ላይ የተቆናጠጠው የእነ ስብሃት ነጋ ቤተሰብ አባላት እንደነበሩ ይነገራል::
የባንዳነት ተግባር
አሸባሪው ሕወሓት ከጅምሩ ጫካ ሲወጣ የሕዝብን ጥያቄ አንግቦ ሳይሆን፤ የውጪ ኃይሎችን ተልዕኮ ተቀብሎ ለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ:: ለዚህ ደግሞ የንጉሱን ሥርዓት በጋራ ታግለው ለውጥ ከመጣ በኋላ ሌሎች ድርጅቶች ወደ ሰላማዊ ትግል ሲመለሱ፤ ሕወሓት ግን ዳግም ራሱን ለጫካ ትግል ማጨቱ እንደ ምክንያት ይነሳል:: ይህ ብቻ አይደለም፣ ለቡድኑ በሰብዓዊ ድጋፍ መልክም ሆነ በሌሎች የመሳሪያና ሎጀስቲክስ ጉዳዮች ከውጪ አገራት ሰፊ ድጋፍ ሲደረግለት እንደነበር፤ በእነዚሁ ኃይሎች እገዛ ወደ ስልጣን እንደወጣ፤ ስልጣን ላይ ከወጣም በኋላ በእነዚሁ የውጪ ኃይሎች እሳቤ አገር ሲመራ እና የተዳከመች አገርን ለመፍጠር ሲሰራ መቆየቱን በማሳያነት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው::
ይህ ቡድን፣ ከትጥቅ ትግል እስከ ሥልጣን መንበሩ የዘለቀው የውጭ ኃይሎች ተላላኪነትና አገርን ለባዕዳን አሳልፎ የመስጠት የባንዳነት ተግባሩ፤ ከ2010ሩ አገራዊ ለውጥ በኋላ በተፈጠረበት ተስፋ መቁረጥ ምክንያት በግልጽ አደባባይ መውጣቱ ይነገራል:: ይህ ደግሞ ቡድኑ አገርን የማፍረስ ተልዕኮው የመጨረሻ አማራጭ የሆነውን የአገር መከላከያ ላይ ጥቃት በመፈጸም አገርን ጠባቂ አልባ የማድረግና ለጠላት አጋልጦ የመስጠት ሕልሙን እውን የማድረግ እኩይ ተግባሩን ማየት በቂ ነው:: ከዛም በላይ እነዚህ አገራትና የውጭ ኃይሎች ለቡድኑ ሲያሳዩ የነበረው ድጋፍና ተቆርቋሪነት፤ ቡድኑም ጩኸትና አቤቱታውን ለእነዚሁ ጋላቢዎቹ የሚያቀርብበት ተጨባጭ ሁነት ተደማሪ እማኝ የማይሻ ማረጋገጫ ነው::
የትናንቱ ዛሬም ሲገለጽ
በትጥቅ ትግል ስም ስልሳ ሺህ የትግራይ ልጆች ለዚህ ቡድን ለስልጣን መብቃት መስዋዕት ሆነዋል፤ ሌሎች ብዙ ሺዎችም አካላቸውን ገብረዋል:: ይሁን እንጂ የእነዚህ ብዙ ሺዎች መስዋዕትነት ለጥቂቶች መበልጸጊያ የሥልጣን ኮርቻን ከማደላደል የዘለለ ብዙሃኑን የትግራይ ሕዝብ ከድንነትም፣ ከጭቆናም አላላቀቀም:: ብዙ ሺዎች ለነጻነትና ልማት ሲሉ አካላቸውን ቢገብሩም የበዪ ተመልካች ከመሆን፣ በየጎዳናው ወድቆ ከመለመን የዘለለ ጠብ ያለላቸው የለም:: ብዙዎች ዋጋ ከፍለው ለውጥ ቢያመጡም ዛሬም ድረስ ጧሪ ልጆቻቸውን እያሰቡ ከመብሰልሰል፤ የትዳር አጋሮቻቸውን ተነጥቀው ከመቆዘም፤ ብዙ ነገሮቻቸውን ተነጥቀው የጉስቁልናን ሕይወት ያውም በአፈና ውስጥ ሆነው ከመግፋት ሌላ አማራጭ ሳይኖራቸው እድሜያቸው ባክኖ ቀርቷል::
ይህ የትግል ወቅት ፍዳ እና ከትግል ማግስት ያለ ችግርና ሰቆቃ ሳያንስ፤ ዛሬም ሌላ ሞት፣ ሌላ ጉስቁልናን፣ ሌላ ጥፋትና ስቃይን በአናት በአናቱ እንዲጋር እያደረገ ይገኛል:: ይህ ደግሞ ቡድኑ ከሰላም ሳይሆን ከጦርነት፤ ከልማት ሳይሆን ከልመና የሚያተርፍ በመሆኑ፤ ይሄን ካላደረገም (ሕዝቡን በጦርነት፣ ኑሮውንም በዳረጎት ላይ እንዲመሰረት ካላደረገ) ሕልውናውን ማቆየት ስለማይችል ነው:: እናም ዛሬ የትግራይ ሕዝብ በረሃብ ሲንገበገብ፣ የሕወሓት ሹማምንት በሕዝብ ስም በለመኑት ሃብት ውስኪ መራጨታቸውን ቀጥለዋል:: ሰላም የሰፈነ ሲመስላቸውም ልጆቻቸውን በውጭ አገራት እያንደላቀቁ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ የተራበውን የድሃውን ሕዝብ ልጅ ወደ እሳት እየማገዱ መሳለቁን በየምዕራፍ ከፋፍለው አስቀጥለውታል::
የባንዳነት ተልዕኳቸውን ከዳር ለማድረስ የትግራይ ሕዝብን እንደ ማስያዣ ይዞ በስሙ ሲነግድ፤ ሕዝቡን እንዳሻው ለማዘዝ ያስችለው ዘንድም በዙሪያው ጠላት የማበጀት፣ በውስጥ በልቶ የማደር ሕልውናው በመንፈግ፣ እረፍት እንዳያገኝ የጦር ነጋሪት በመጎሰም፤ ከልጆቹ ሐዘን እፎይ ብሎ እንዳይተኛ ሕልውናውን በጦርነት ማቆየት ግድ ስለሚለው ልጆቹን ወደ እሳት እየማገደ ዘወትር በድህነት፣ በጦርነት፣ በዋይታና ሰቀቀን ውስጥ እንዲማቅቅ እያደረገው ይገኛል:: የእለት ጉርሱን በልጆቹ መንዝሮ እንዲያገኝ፤ ሕልውናውን ከጦርነት ጋር አጣብቆ እንዲመለከት፤ ከወንድም ሕዝቦች ጋር ተደጋግፎ እንዳይኖር ዙሪያውን በጦር አጥሮ የቁም እስረኛና ግዞተኛ አድርጎ ይዞታል:: እነዚህ እና ሌሎችም አያሌ ሊነሱና ሊነገሩ የሚችሉ ማሳያዎች፤ የጥፋት ቡድኑ ከትናንት ያልተማረ፤ ዛሬም በትናንቱ የሴራ እና የሞት መንገድ እየተጓዘ የትግራይን ሕዝብና ወጣት ዋጋ እያስከፈለ፤ በግፍና ሰቆቃ ተግባራቱ እየተገለጠ ያለ፤ የክፋት ማሳያ፣ የሴራ መታወሻ ሆኖ ዘልቋል::
ማሙሻ ከአቡርሻ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም