እግር ኳስ ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ስለስፖርቱ ፍቅር የማይታገሰውና የማያልፈው ፈተና የለም። ዶፍ ቢወርድበት የጸሃይ ሃሩር ቢያነደው፣ ጨዋታው ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ ድንበር ቢሻገርም፣ የሽንፈት አዘቅት ቢውጠውም ተስፋ አይቆርጥም። ይልቁንም ከሰዓት በኋላ ለሚደረግ ጨዋታ ማልዶ ይሰለፋል፤ አታካቹን ሰልፍም በትዕግስት ያሳልፋል። ሽንፈቱን እየተመለከተም ተስፋ ቆርጦ ብሄራዊ ቡድኑን ከመደገፍ ወደኋላ አይልም። ብዙ የሚገባው ይህ ህዝብ እንደ ልፋቱ ሳይከፈለው፤ ከሚወደው እግር ኳስም ጣፋጭ ድልን ሳይሆን መራራ እውነቶችን እየተጎነጨ አንድ ምዕተ ዓመት ሊሆነው ነው።
ሌላው ዓለም በስታዲየም ዲዛይንና ግዝፈት ብቻም ሳይሆን ቴክኖሎጂን በተግባር በማዋል በዘመነበት፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በተራቀቀበት እና አነስተኛ ከተማ የሚያስመስላቸውን መሰረተ ልማቶች ሁሉ እስከማሟላት በደረሱበት በዚህ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ግን ለስሟ መጠሪያ የሚሆን አንድ ስታዲየም ልታገኝ አልቻለችም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር ‹‹ዋሊያ›› የሚል የክብር መጠሪያ ያዘለው ቡድኗ ድንበር አቋርጦ በሰው ሀገር አቻውን ሊያስተናግድ ተገዷል። ውድድር አንድም በራስ ሜዳ፤ አንድም በተቃራኒ ቡድን ሜዳ የሚደረግ እንደመሆኑ ከተጓዙበት ሀገር ሲመለሱ በራሳቸው አየርና ደጋፊ ፊት መጫወት የእግር ኳስ ወጉ ነበር። ኢትዮጵያ ግን ይህንን ካጣች እነሆ ወራት ተቆጥረዋል፤ በዚህ ሁኔታ ትቀጥል ዘንድም በካፍ የበላይ አካል ተወስኖባታል።
ይህ ጉዳይ የስፖርት ቤተሰቡ ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያዊ የሆነን ሁሉ የሚያስቆጭ ነው። ለምን ቢሉ በየክልሉ በነፍስወከፍ የተገነባ አንድ አንድ ስታዲየም ያላት ሀገር ሆና ሳለ ለስታዲየም እጦት በመጋለጧ ነው። ባለፉት ዓመታት ከህብረተሰቡ መሰረታዊ ፍላጎትና አነስተኛ በጀት እየተቀነሰ እንዲሁም ከህብረተሰቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ ስታዲየም ሲገነባ ቆይቷል። ስታዲየሞቹ በተገቢ መንገድ ቢጠናቀቁ ኖሮ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ባለ በርካታ ስታዲየም ሀገሮች መካከል ለመሰለፍ ትችል ነበር። በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ ስታዲየሞች ለሪፖርት ማሟያ እና በዓል ማክበሪያ ከዋሉ በኋላ ይዘነጋሉ። በመሆኑም ስንዝር መራመድ አቅቷቸው መሻሻልና ለውጥ ሳይታይባቸው ዓመታት ተቆጥረዋል።
የተሻሉ ናቸው የሚባሉት ጥቂት ስታዲየሞችም ቢሆኑ መዋቅራዊ ስራቸው ተጠናቆ ነገር ግን ጣራ፣ ወንበርና መብራት ባለማሟላታቸው እንግልትን ቢፈጥሩም የስፖርት ቤተሰቡ ግን ቅሬታውን ሳያሳይ ቆይቷል። አህጉር እና ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ወደማስተናገድ እንዲሁም የስታዲየሞችን ደረጃ ወደ መመዘን ሲመጣ ግን ግዙፎቹ ስታዲየሞች ቀለው ይገኛሉ። ሊያሟሏቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነገሮች ሳይካተቱ ቀላል የሚባሉ መስፈርቶች ከባድ ችግርን አስከትለው በመታየታቸው ምክንያትም ኢትዮጵያ ያቀናችው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፊቱን ሊያዞርባት ችሏል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ‹‹ስታዲየሞቹ መስፈርቴን አላሟሉም›› በሚል እገዳ የሚጥለው መስፈርቶቹን በስታዲየሞቹ ዲዛይን፣ በሚያስተናግደው የደጋፊ ቁጥር አሊያም በጣራ ስለተከበበ አይደለም። ይልቁኑ ትኩረቱን መሰረታዊና ጥቃቅን የሚባሉ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ነው። ለአብነት ያህል የመጫወቻ ሜዳው ሳር ዓይነት እና በላያቸው ላይ የሚሰመሩት ምልክቶች ልኬት፣ ጨዋታዎች በማታ ቢካሄዱ ማስተናገድ የሚችሉበት መብራት፣ ተመልካቾችን ወደ ስታዲየሙ በነጻነት እንዲገቡና እንዲወጡ የሚያስችል መተላለፊያ፣ ደጋፊዎችን ጨምሮ ተጫዋቾች አደጋ ቢገጥማቸው የህክምና እርዳታ የሚያገኙባቸው ቁሳቁስ፣ ተጫዋቾች ወደ ጨዋታ ከመግባታቸው አስቀድሞ የሚያርፉበት ልምምድ የሚያደርጉበትና ንጽህናቸውን የሚጠብቁበት፣ የመገናኛ ብዙሃን ስራቸውን የሚያከናውኑበት ስፍራ እና የመሳሰሉት ናቸው።
ከመስፈርት ጋር ያለው ጉዳይ ሲጠቀለል ጉድለቶችን ለማሟላት ከሚወጣው ገንዘብ በላይ ስታዲየምን ያህል ትልቅ መሰረተ ልማት የሚገነባ አካል እንዴት ሊዘነጋቸው ቻለ የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ነገር ሲሰራ የራሱ የሆነ ደረጃና ልኬት አለው፤ ወደ 20 ቢሊዬን ብር የሚገመት ሀብት ፈሰስ የተደረገባቸው እነዚህ ስታዲየሞች ሲገነቡ እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች እንዴት ሊታለፉ ቻሉ። ሀገራዊ የስታዲየም ግንባታ መስፈርት ባይኖርም እንኳ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በግልጽ የተቀመጡ ሆነው ሳለ ህግን ባለማክበርና ደረጃዎችን ባለማሟላት መሰረት እና ጥቅም አልባ ማድረግ ተቀባይነት የሌለው ጉዳይ ነው። የስታዲየሞችን ግንባታ በበላይነት የሚከታተለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እነዚህን ጉዳዮች ማዕከል አድርጎ ክትትል አለማድረጉስ ሊያስጠይቀው አይገባም?
በሌላ አንጻር የፌዴራሉ መንግስት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት እጅግ ግዙፍ፣ ዘመናዊና ሀገርን ሊወክል የሚችል ብሄራዊ ስታዲየም በመገንባት ላይ ይገኛል። በተመሳሳይ ሁኔታ ግን ይጠናቀቃል በሚል በዕቅድ ከተያዘው ጊዜ ሁለት ዓመታትን ዘግይቶም ጨዋታ ማስታናገድ የሚችልበት አቅም ላይ አልደረሰም። በእርግጥ የዚህ ስታዲየም ችግር ከውጭ ሊገቡ የሚገባቸው መሳሪያዎች በውጪ ምንዛሪ እጥረት ባለመገዛታቸው ስለመሆኑ ተነግሯል። ሆኖም ከወጣበት ገንዘብ አኳያ ከሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ሊመደብ የሚችለው ግንባታ ለዓመታት በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉ አያጠያይቅም። ለስታዲየሙ ማጠናቀቂያ የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ ለስታዲየሞች ኪራይ መዋሉም የግድ ይሆናል። ሰሚ ካጣው የውጭ ምንዛሬ ጎን ለጎን በህገወጥ ሰፋሪዎች አለመነሳት ምክንያት ሌሎች ስራዎች በቆሙበት መቅረታቸውም የሚታለፍ አይደለም።
በእርግጥ በርካታ ችግሮችና መሰረታዊ መጓደሎች ባሉባት ሀገር ስለ ዘመናዊ ስታዲየም ማሰብ ቅንጦት ሊመስል ይችል ይሆናል። ነገር ግን ከፍተኛ የሀገር ሀብት ፈሶባቸውም ጥቂት ተጉዘው ተሰናክለው የቀሩትን ስታዲየሞች እንዲሁም ስለስፖርቱ ፍቅር የሚፍጨረጨሩና የስራ ዘርፋቸው ያደረጉት በርካታ ወጣት ዜጎች ላሉባት ሀገር ቁምነገር ስለመሆኑ አያጠያይቅም። ባንዲራውን አስቀድሞ ለሀገር የበላይነት በሰላማዊው አውድ የሚፋለመው ቡድን ‹‹ከሀገርህ ወጥተህ ተጫወት›› መባሉ በራሱ ትልቅ ስነልቦናዊ ጉዳት አለው። በየሰፈሩና መንደሩ ታዳጊዎቻችን ከሚያስተናግዱት አሸን ሜዳዎች አንስቶ በየክልሉ በርካታ ስታዲየሞች ያላት ሀገር፤ ምንም እንደሌላት ቡድኗን ማስተናገድ አቅቷት ከሌላ ሀገር ደጅ ስትጠና ማየት በእውነትም ልብ ይሰብራል።
እንደሚታወቀው ስፖርት አካላዊ ክንዋኔ ይሁን እንጂ ለአሸናፊነት የሚያበቃው ግን አእምሯዊ ብቃትና ስነልቦና ነው። ስነልቦና በተጫዋቾች ላይ ትልቅ ስፍራ ካለው በዚህ ምክንያት ተጫዋቾቻችን ለሚደርስባቸው የሞራል ስብራት ተጠያቂው ማን ሊሆን ይችላል?። በሜዳቸው ላይ በሀገራቸው ልጆች ድጋፍ እያገኙ በለመዱት የአየር ሁኔታ እና የቦታ አቀማመጥ ታግዘው የሚያገኙትን የአሸናፊነት ጥቅም ስለማጣታቸውስ ምን ዓይነት ካሳ ያገኛሉ። ቡድኑ በዚህ ሁኔታ ለሌላ ሀገር ሜዳ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥቶም ማለፍ ባይችልስ ጸጸቱ ተደራራቢ አይሆንም?
በእርግጥ የስታዲየሞች ግንባታ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው። ቢሆንም በስታዲየሞችም ሆነ በዙሪያቸው አስፈላጊ የሚሆኑ መሰረታዊ ጉዳዮችን አጢኖ አቅምን ያገናዘበ ግንባታ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ከአንድ ጉዳይ አስቀድሞ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ መስፈርት ማዘጋጀትም የግድ ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን መሰል አደጋ ከማስተናገድ ባለፈ በርካታ ጉዳቶችን ያስከትላል። ይህ በዚህ አልፎ ስታዲየሞችም መስፈርት አሟልተው ጨዋታዎችን የማድረግ ፈቃድ ቢያገኙም እንኳን ሌላኛው የአስተዳዳሪነት ጥያቄ ደግሞ በተራው መነሳቱ አይቀሬ ነው። በመሆኑም ይህም በዚሁ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው እላለሁ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም