በየዓመቱ የሚካሄደው ጉማ የፊልም ሽልማት ከተጀመረ እነሆ ዘንድሮ 8ኛ ዙር ላይ ደርሷል። በዛሬው ዕለትም የ8ኛ ዙር የጉማ ፊልም አሸናፊዎች ይታወቃሉ።
ጉማ የፊልም ሽልማት የፊልም መነቃቃት ይፈጥራል፤ ፈጥሯልም። ምንም እንኳን የሽልማቱ ትኩረት በተሰሩ ፊልሞች ላይ ቢሆንም፤ ወደፊት በሚሰሩ ፊልሞች ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፤ መነቃቃትን ይፈጥራል።
የፊልም መነቃቃት ይፈጥራል ሲባል፤ ዕጩዎች ከቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ ስለፊልም ይወራል። ስለተዋናዮች ብቃት ይወራል፤ ስለፊልሞች ይዘት ይወራል። የትኛው ፊልም ይሸለም ይሆን በሚል ፊልሞችን የመዳሰስ ሥራ ይሰራል። በተለይም በዕጩነት የቀረቡ ፊልሞች ስም ሲዘረዘር፤ ፊልሞችን ያላዩ ሰዎች አፈላልገው እንዲያዩት ሊገፋፋ ይችላል።
የተዋናዮች ማንነት ይታወቃል። በተለይም ወጣት ተዋናዮች ሥራዎቻቸውና ብቃታቸው እንዲታይላቸው እድል ይሰጣል። ጉማ የፊልም ሽልማት እንቅስቃሴ ከሚጀመርበት ሰሞን ጀምሮ በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በመድረኮች ስለፊልም ይወራል፣ ስለዕጩ ተዋናዮችና ሥራዎቻቸው ይቃኛል። በዚህ ሁሉ ውስጥ የፊልም መነቃቃት እየተፈጠረ ነው ማለት ነው። በአዘቦት ስለፊልም የማይሰሩ መገናኛ ብዙኃን ሁሉ በዚህ ሰሞን ትኩረታቸውን ወደ ፊልሙ ያዞራሉ። እግረ መንገድም አንዳንድ ፊልሞች ላይ ዳሰሳዎች ይሰራሉ ማለት ነው።
በሌላ በኩል ጉማ የፊልም ሽልማት የተለያዩ ዘርፎች ስላሉት፤ የተለያዩ የፊልም ሙያዊ መመዘኛዎችን ወደ ፊልሙ ዘርፍ የሚገቡ ሰዎች ይማሩበታል ማለት ነው። ፊልም ሲባል ብዙዎቻችን የምናውቀው ያለቀለትን ሥራ ነው። ዘርፎቹ ተዘርዝረው ስናየው ግን ከጀርባው ብዙ ቴክኒካል ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል። ይዘቱን ብቻ ሳይሆን ከፊልሞች ጀርባ ተደብቀው ያሉ ከማጀቢያ ሙዚቃው ጀምሮ የሜካፕ፣ የመብራት ወዘተ ባለሙያዎችን ሁሉ ብቃትና ልፋት እንዲገለጥ ያደርጋል። እነዚህን የፊልም ጥበቦች ብዙዎቻችን ልብ ስለማንላቸው በጉማ የፊልም ሽልማት ምክንያት ትኩረት ያገኛሉ።
ዛሬ የሚደረገውን 8ኛው ጉማ የፊልም ሽልማት ምክንያት በማድረግ ስለፊልም ማውራት ተገቢ ነው። በዛሬው ፕሮግራም እነማን ተሸላሚ እንደሚሆኑ ስለማናውቅ ባለፉት ዓመታት የነበሩትን ፊልሞችና ተሸላሚዎች እናስታውስ። ሁነቶች የፈጠሩትን የፊልም አብዮትም በነካ እጃችን እንቃኝ።
ፊልም በተለያዩ ዘርፎች ቢከፈልም፤ የሰውን ልጅ የአሁኑን የትላንቱንና የነገውን ሁኔታውን የሚያስተላልፍበት መገናኛ መንገድ ነው። የፊልም ሥራዎቻቸው ባደጉት በትላልቆቹ ዓለማት ደግሞ ያሉበትን ሉዓላዊነት ማንፀባረቂያ፣ ያላደጉትን አገራት ማስፈራርያ እና መማረኪያ ንብረታቸው ነው። ራሱን የቻለ ግዙፍ የኢንዱስትሪ ዘርፍም ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን፤ ኢትዮጵያና ፊልም ያላቸው ትውውቅ ከአንድ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ቢሆንም የዘመናዊ ፊልም ታሪኳ ግን ከሃያ ዓመታት ያልዘለለ ሆኖ እናገኘዋለን።
የኢትዮጵያ ፊልም እንደ ኢንዱስትሪ መታየት ጀምሮ በብዙ ውጣውረዶች አልፎ በሲኒማ ቤቶች ደረጃ መታየት የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው። እንደ ጉዲፈቻ፣ የበረፈዶ ዘመን፣ ስላንቺ፣ የወንዶች ጉዳይና የመሳሰሉት ፊልሞች የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፊልም ታሪኳ ውስጥ በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ጥቂቶቹ ናቸው።
እነዚህን ፊልሞቻችንን ይዘን ጉማ የፊልም ሽልማት ተጀመረ። ከሃምሳ ምናምን ዓመታት በፊት በሚሼል ፓፓታኪስ የተሠራው እና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ባለቀለም ፊልም በሆነው ‹‹ጉማ›› ፊልም መጠሪያውን ያደረገው ጉማ የተሰኘው ሽልማት ነው ዛሬ ላይ ስለፊልሞች በሰፊው እንድናወራ ያደረገን።
የአዘጋጆቹ ትጋትና ለፊልም ኢንደስትሪው እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅዖ ማንም ወደ ፊልሙ ተጠግቶ የማያውቅ እንግዳ ሰውም ሊመሰክረው የሚችለው ጉዳይ ነው። የተለያዩ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ፊልሞችን እየያዘ የሚመጣው ጉማ የፊልም ሽልማት በየዓመቱ ደመቅ ባለመልኩ ነው የሚከናወነው።
በነገራችን ላይ ጉማ የፊልም ሽልማት በ2012 ዓ.ም የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በማድረግ አልተካሄደም ነበር። ባለፈው ዓመት ነው እንደገና በደማቁ የተጀመረው። የባለፈው ዓመት 7ኛው የጉማ ፊልም ሽልማት ብዙ አነጋጋሪ ክስተቶች የታዩበት ነበር።
በኢትዮ ፊልም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የሚዘጋጀው ጉማ ፊልም ሽልማት ጥሩ ብቃት ላሳዩ ፊልሞች እና አርቲስቶችን ክብርና እውቅና መስጠት ዓላማው እንዳደረገ አዘጋጆች በተለያየ ጊዜ ተናግረዋል።
በባለፈው ዓመት ሰባተኛው የሽልማት መርሃ ግብር ላይ 45 ፊልሞች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚያ ውስጥ 15 ፊልሞች በተለያዩ 16 ዘርፎች ታጭተው ነበር። ‹‹እንሳሮ›› የተሰኘው የምስጋና አጥናፉ ፊልም በ13 ዘርፎች ታጭቶም ነበር።
የፍቅር ጥግ በ11፣ ማንያዘዋል በ11፣ ስንብት በ10፣ ከርቤ በ8፣ ምን አለሽ በ8፣ ሱማሌው ቫንዳም በ6 ዘርፎች ታጭተው ነበር። በዳይሬክቲንግ፣ በሲኒማቶግራፊ፣ በትወና እና በሌሎችም በአጠቃላይ 18 ዘርፎች ውድድር ተካሄዷል።
በምርጥ አጭር ፊልም ቀብድ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ እንዲሁም በምርጥ ፊልም ቁራኛዬ አሸናፊ ሲሆን በምርጥ ሲኒማቶግራፊ እንዲሁም ኤዲቲንግ ደግሞ እንሳሮ ፊልም ተሸላሚ ሆኗል።
በምርጥ ሴት ተዋናይ ዘሪቱ ከበደ በወጣት በ97 ፊልም፣ ምርጥ ዋና ወንድ ተዋናይ ደግሞ ሄኖክ አሸናፊ ሱማሌው ቫንዳም ላይ ባሳዩት የትወና ብቃት ተሸላሚ መሆናቸው የ7ኛው ጉማ የፊልም ሽልማት ክስተቶች ነበሩ።
ከዚህም በተጨማሪም የባለፈው ዓመት የጉማ የሽልማት ዘርፍ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሆኑት አንጋፋው ፀሐፌ ተውኔት ገጣሚና የዜማ ደራሲ እንዲሁም የፊልም ተዋናይ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ነበሩ።
ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚሰነዘርበት የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ እንዲህ አይነት የማነቃቂያ ሽልማቶች ያስፈልጉታል። የፊልም ኢንዱስትሪውም ወቀሳው ብዙ ስለተደጋገመ እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ ተወዳጅ ፊልሞችም ተፈጥረዋል።
በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት የጎሉ እንቅስቃሴዎች ታይተውበታል። ለምሳሌ፤ በጀርመን ታዋቂ በሆነው ዓለም አቀፍ የፊልም ውድድር በርሊና መድረክ እና በዩናይትድ ስቴትሱ የሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ሽልማትን ያገኘው የኢትዮጵያው «ድፍረት» የተባለው ፊልም ተጠቃሽ ነው።
በፊልም ስራ የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአሜሪካ ያጠናቀቀውና በርካታ ፊልሞችን እንደሰራ የሚነገርለት የጉማ ፊልም ሽልማት ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ብርሃነ መዋ፤ የጉማ ፊልም ሽልማት የተጀመረ ዓመት ለዶቼቬለ እንደተናገረው፤ ዝግጅቱ የፊልም ጥበብንና ጥበበኞችን ለመደገፍ የታሰበ ስነ ስርዓት ነበር። እነሆ አሁን እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ ብዙ መነቃቃትን ፈጠረ፣ ፊልሞችም በጥራት መሰራት ጀመሩ።
በጉማ የፊልም ሽልማት ሥነ ስርአት ላይ በተለያዩ ዘርፎች ከሚሰጠው ሽልማት በተጨማሪ ደግሞ፤ ለውድድር የማይቀርብ ዘርፍ አለ፤ ይህ ዘርፍ ‹‹የሕይወት ዘመን ተሸላሚ›› ነው። የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የሚሆነውን ሰው መርጦ ማውጣት ነው ።
የመጀመሪያው የጉማ ፊልም ሽልማት ላይ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ የነበሩት፤ ከአርባ ዓመት በላይ በፊልም ጥበብ ስራ ላይ የቆዩትና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፊልም ዳሬክተር ሚሼል ፓፓታኪስ ናቸው።
ሚሼል ፓፓታኪስ፤ አባታቸው አዲስ አበባ ውስጥ የፊልም ቤት የከፈቱ የግሪክ ዜጋ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ኢትዮጵያዊትና ትውልዳቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።
የፊልም ሽልማት ስነ ስርዓቱን ‹‹ጉማ›› ሲል መጠሪያ የሰጠው የስነ ስርዓቱ ዋና አዘጋጅ እና የፊልም ስራ ባለሙያው ዮናስ ብርሃነ መዋ በወቅቱ ለዶቼቬለ እንደገለጸው፤ በሚሼል ፓፓታኪስ የተሰራው ጉማ ፊልም፤ ስያሜውን ከኦሮምኛ ቋንቋ እንደወሰደና፤ ካሳ ማለት እንደሆነ ተናግሯል።
ፊልሙ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥ ስላለው የግጭት አፈታት ባህል ላይ የሚያውጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ነው። በአሁኑ ወቅት ፊልሙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ወመዘክር ውስጥ ይገኛል።
ጉማ የፊልም ሽልማት ስነ ስርዓት አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት እየታየ ላለው የቪዲዮ ፊልሞች ምርት መሰረት የጣሉትን ሰዎች ያስታወሰ፤ በዳኝነትም ሆነ አንጋፋ የፊልም ተዋናዮችን ታሳቢ ያደረገ መድረክ ነው።
የፊልም ኢንዱስትሪው እንዲያድግና፤ በኢኮኖሚው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የተቻለውን ጥረት እንዲያደርግ ያነሳሳል። ሆኖም ግን የመንግሥትም ድጋፍ መደረግ አለበት። ምክንያቱም ፊልሞች የኢትዮጵያን ባህል በማስተዋወቁም ረገድ ሆነ ዓመታዊ ገቢን ከፍ እንዲል በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል።
በኢትዮጵያ የፊልም ስራ ዕድገት፣ ጥራትና ኢትዮጵያዊ ደረጃን የጠበቀ እንዲሆን የፊልም ሰራተኛ ማህበሩ ጥረት እያደረገ መሆኑንም የዘርፉ ሰዎች ሲናገሩ ቆይተዋል። ስለዚህ እንዲህ አይነት ሽልማቶች፤ መንግሥትንም፣ የፊልም ባለሙያውንም፣ የፊልም ተመልካቹንም መነቃቃት ይፈጥሩለታል ማለት ነው።
የፊልም ተመልካቹ ላይ ግን አንድ ትዝብት እናጋራ። ሁልጊዜ የፊልም ኢንዱስትሪውን መውቀስ ብቻውን ለውጥ አያመጣም። የኪነ ጥበብ ዘርፍ እና ስፖርት አንፃራዊ ነፃነት ስላለው ይመስላል ሰዳቢው ብዙ ነው። ከማድነቅ ይልቅ መተቸቱ የሚቀል ይመስላል። እርግጥ ነው ወቀሳ ስለበዛበት ነው ያላደገው ማለት አይቻልም፤ ቢሆንም ግን ጥሩ የተሰሩ ፊልሞችን ማድነቅና እውቅና መስጠት ደግሞ የበለጠ ያበረታታል። ስለዚህ እንደ ጉማ አይነት የፊልም ሽልማቶች ሲደረጉ ከፊልም ባለሙያው በተጨማሪ ተመልካቹም ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።
ለምሳሌ፤ ያለፈውን ዓመት የጉማ ፊልም ሽልማት አስተያየቶች እናስታውስ። በመድረኩ በተለያየ ዘርፍ ከተሸለሙ ፊልሞች ይልቅ አጀንዳ ሆኖ የነበረው የሴት አርቲስቶች አለባበስ ነበር። የተሸለሙትን ፊልሞች የይዘትም ሆነ የቴክኒክ ጥራት ከመገምገም ይልቅ የአንድ ሴት አርቲስት አለባበስ የሳምንት አጀንዳ ሆኖ ነበር። እንዲያውም አሸናፊ የሆኑ ፊልሞች እስከሚረሱ ድረስ ዋናው መከራከሪያ አለባበስ ሆኖ ነበር። የዕለቱ የመድረክ አለባበስ ለዚያ ቅጽበት እንጂ በተሸለሙበት ፊልም ላይ የሚጨምረውም ሆነ የሚቀንሰው ነገር አልነበረም።
ይህ ሲባል ግን ከአዘጋጆችና ከተሸላሚዎችም ችግር የለም ማለት አይደለም። ከኢትዮጵያ ወግና ባህል ያፈነገጠ ነገር ማሳየትም ነውር ነው። ልክ በፊልሞቻቸው የኢትዮጵያን ወግና ባህል አሳይተው፣ ተደንቀው እንደተሸለሙት ሁሉ በመድረክ ላይም በእውናዊው ሕይወታቸውን ማሳየት አለባቸው።
የአገር ባህል ቀሚስ ለብሳ በተወነችው ፊልም ስትሸለም ራቁቷን ከመጣች፤ የፊልሙን ይዘት አታምንበትም ማለት ነው። ምንም እንኳን የገጸ ባህሪዋን ሕይወት ትኑር ባይባልም የአገርን ባህልና ወግ የሚጥስ ነገር ማሳየት ግን ነውር ነው፡ አዘጋጆችም ይህን ከግምት ማስገባት አለባቸው።
በአጠቃላይ የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ የሚያድገው በኪነ ጥበብ ባለሙያውም፣ በታዳሚውም በመንግሥትም የጋራ ፍላጎት ነውና ከሁላችንም የሚጠበቀውን እናድርግ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2014