አሜሪካ ካሏት አንሰላሳዮች ቀዳሚ የሆነው፤ የዝነኞቹ ሀርቫርድና የል ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅ፤ ትውልደ ሕንድ አሜሪካዊ፤ የአለማቀፍ ጉዳዮች ሊቅ፣ ጉምቱ ጋዜጠኛ፣ ደራሲና አንደበተ ርዕቱ ተናጋሪ ፋሪድ ዘካሪያ፤ የተወዳጁ የሲኤንኤን ቴሌቪዥን Global Public Square/GPS/ አዘጋጅ፤ የዋሽንግተን ፖስት (Washington Post) አምደኛ፤ የTIME መጽሔትን ከውጭ ሆኖ የሚደግፍ አርታኢ /editor_at large/ነው። በአለማችን ካሉ ጋዜጠኞች እንደሱ ልቅምና ጥንቅቅ ያለ ጋዜጠኛ ገጥሞኝ አያውቅም። ከአገር ውስጥ ደግሞ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና እንደ “አዲስ ዘመኑ” ወይም የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያው/ኤጀንሲው፤ ኋላ ላይ ደግሞ የ”ጦቢያው” ሙሉጌታ ሉሌ አይነት ጥልቅና ምጡቅ ጋዜጠኛ አላየሁም።
ወደተነሳሁበት ሀሳብ ስመለስ ዛሬ ለመጣጥፌ በርዕስነት ስለተዋስሁት ርዕሰ ጉዳይ ማለትም ስለ “ስሁት/የተሳሳተ መታጠፊያ፤” ወይም ውሳኔ ጦስና መዘዝ ፋሪድ በአንድ ዝግጅቱ ያነሳውን አስታውሳለሁ። “አንዳንድ ጊዜ አለምን የሚቀይሩ ሁነቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አበክረን ልንገምት እንችላለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ አጋጣሚዎች ወይም ያልተጠበቁ ሁኔታዎችና የግለሰብ ወይም የአገር መሪ የተሳሳቱ ውሳኔዎች የትውልዶችን፣ የአገራትንና የአለምን መጻኢ እድል ፈንታ እስከ ወዲያኛው ሲበይኑ እናስተውላለን፤” ይላል ፋሪድ።
ለ1ኛው የአለም ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት የሆነውም ይሄው ስህተት ነው። የአውስትሮ _ሀንጋሪ አልጋ ወራሽ ልዑል ፍራንዝ ፈርዲናንድ የግል ሹፌር በስህተት የሰርቢያ አክራሪዎች መናኸሪያ ወደ ሆነውና አሮጌው የፍራንስ ጆሴፍ አውራ መንገድ ሲታጠፍ ከሳርያቮ ቦስንያ አክራሪ የሰርቢያ ብሔርተኛ ጋቭሪሎ ፕሪንሲፕ ጋር ፊት ለፊት ይገጣጠማል። ሹፌሩ መሳሳቱን ቢረዳም ለማረም ጊዜ አላገኘም። ጽንፈኛ ብሔርተኛው ወዲያው በታጠቀው ሽጉጥ ልዑሉንና ሚስቱን ልዕልት ሶፊን ሰኔ 28 ቀን 1914 ዓም ይገድላል። በዚህም ወደ 1ኛው የአለም ጦርነት ተገባ።
በተደጋጋሚ እንደምለው ታሪክ ራሱን ይደግማል አይደግምም የሚለው ሙግት ጉንጭ እንዳለፋ መልስ ሳያገኝ ዛሬ ድረስ የቀጠለ ቢሆንም፤ ለካርል ማርክስ ግን ታሪክ ራሱን የመድገም ጉዳይ አጠያያቂ አይደለም። ለዚህ ይመስላል፣ “ታሪክ ራሱን ሲደግም መጀመሪያ በአሳዛኝ ሁኔታ በማስከተል በአስቂኝ ሁኔታ “ ያለው።
የ2ኛው የአለም ጦርነትም በናዚው አዶልፍ ሒትለር በ1939 ዓ.ም ፖላንድን የመውረር የተሳሳተ ውሳኔ መቀስቀሱን ስንረዳ ታሪክ ለምን ራሱን አይደግም አሳምሮ ይደግማል እንጅ እንላለን። በሁለቱ ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነቶች በአስር ሚሊዮኖቹ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ቁጥራቸው ከዚህ የማይተናነስ ቆስለዋል። በቢሊየን አልያም ትሪሊየን የሚገመት ሀብትና ንብረት ወድሟል። የሰውን ልጅ ስልጣኔ ወደ ኋላ መልሰዋል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ የሚታዩ ሁነቶችም የተሳሳተ መታጠፊያ መሆኑ ባያጠያይቅም ለመደምደም ግን ጊዜው ገና ይመስለኛል። ሆኖም 3ኛውን የአለም ጦርነት ለዛውም በኒውክሌርና በሳይበር የታገዘ ጦርነት እንዳያስነሳ ብርቱ ስጋት ደቅኗል። ጦርነቱ ላይ ላዩን ሲያዩት የራሽያና የዩክሬን ቢመስልም፤ ኔቶ፣ የተቀሩት ምዕራባውያን፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ በአንድ ጎን ራሽያ በሌላ ወገን የሚያካሂዱት የውክልና ጦርነት መሆኑ ስጋቱን ከስጋት በላይ ያደርገዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ባለፈው አመት ለንባብ ያበቁት፤ “A Promised Land “ መጽሐፋቸው ላይ፤ “ታሪካችን የየአንዳንዳችን ውሳኔና ተግባር ድምር ውጤት ነው። ታሪክ ሁልጊዜም የእኛ ጉዳይ ነው።” ይላሉ። ይሄን ብሂል ወደ አገራችን አውድ ስናመጣው ዛሬ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገርና መንግስት የምንወስነው ትክክለኛም ሆነ የተሳሳተ ውሳኔ ወይም የተሳሳተ መታጠፊያ የነገ ታሪካችን አካል ነው። የተሳሳቱም ሆነ ትክክለኛ ውሳኔዎቻችን ወይም መታጠፊያዎቻችን ነገ በታሪክ ሚዛን ያስቀምጡናል። በግሌ በስሁት መታጠፊያነት ወይም ውሳኔነት የለየኋቸውን ለመማሪያነት እና በድጋሚ ላለመሳሳት በአብነት የተወሰኑትን አነሳለሁ።
ለውጡ ከባተ ካለፉት አራት አመታት ወዲህ እጅን በአፍ የሚያስጭኑ 1001 ትክክለኛ መታጠፊያዎች ተሒዶባቸዋል። ወይም ትክክለኛ ውሳኔዎች ተወስነዋል። በዚህ መጣጥፍ የማነሳው ግን በተለይ ዛሬ ከምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ይገናኛሉ ብዬ የማምንባቸውን በተለይ የለውጥ ኃይሉንና የብልጽግናን ስሁት መታጠፊያዎች ወይም የተሳሳቱ ውሳኔዎችን ቢሆንም፤ ወደኋላ መለስ ብለን ብንፈትሽ የሕወሓት/ኢህአዴግ፣ የደርግና የቀደሙ አገዛዞችን ስሁት መታጠፊያዎችን እናገኛለን። እነዚህ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ዛሬ ለምንገኝበት አጣብቂኝ በመዳረግ ረገድ አስተዋጾ ቢኖራቸውም የዛሬው መጣጥፌ ትኩረት ባለፉት አራት አመታት ስለተስተዋሉ ስሁት መታጠፊያዎች መሆኑን እገልጻለሁ።
ሕወሓት ለ27 አመታት በበላይነት ይዞት ከነበረው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ከውስጡ በወጡ የለውጥ ኃይሎችና ለተከታታይ ሶስትና አራት አመታት በተካሔዱ ሕዝባዊ አመጾች በልክህ ሁን ሲባል ኮሽታ ሳያሰማ ጅራቱን ቆልፎ ሾከክ ብሎ ወደ መማጸኛ ከተማው መቀሌ ሲመሽግ ለጤና እንዳልሆነ መጠርጠር ይገባ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ልዩ ኃይሉን በስፋት ሲያሰለጥን፤ ሚሊሻውን እስከ አፍንጫው ሲያስታጥቅ፤ የጦርነት ድቤውን ሲደልቅ፤ ምድርን አርባ እየገረፈ ጦር አውርድ ሲል፤ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሰሜን ዕዝን ሲተናኮል ምን ሊመጣና ሊከተል እንደሚችል ገምቶና ተንትኖ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባ ነበር። የሕወሓትን ማንነትና ባህሪ አውቆ ቅድመ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ባለመቻሉ በምንም የማይተመን ዋጋ አስከፍሎናል።
ይሄን ስል የደህንነትና የመከላከያ መዋቅሩ በሕወሓት እጅ ከወርች መቀየዱን አጥቼው አይደለም። ወይም አበው ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው የሚሉትን ወርቅ ይትበሀልም ዘንግቸው አይደለም። ሆኖም ውስን በሆነው የወታደራዊና የሲቪል ደህንነቱ አቅምም ቢሆንም ለሰሜን ዕዝ የተደገሰለትን ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይለውን ክህደትና ጭፍጨፋ ቀድሞ አውቆ የማንቂያ ደወሉን መንካት ቢቻል ኖሮ ጉዳቶን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንኳ ባይቻል መቀነስ ይቻል ነበር የሚል ቁጭት ይሰማኛል።
በሰሜን ዕዝ በተፈጸመው ጭፍጨፋና ክህደት የተነሳ መንግስት ተገዶ የገባበትን ጦርነት እጅን በአፍ ባስጫነ ድል ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ መቀሌ በመግባት የሕወሓትትን ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራር መደምሰስና መማረክ ቢቻልም፤ ድሉን ማስጠበቅ፣ ማጽናትና ማዝለቅ አልተቻለም። ችግሩ በጥናትና በግምገማ ተለይቶና ተረጋግጦ ይፋ ባይሆንም በውስንነትና በስሁት መታጠፊያነት ወይም በተሳሳተ ውሳኔነት የተረዳኋቸውን አንድ አንድ ነጥቦች ላንሳ። ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርሁት የመንግስት አብዛኛዎቹ ውሳኔዎች በመርህ ደረጃ ትክክል ቢሆኑም የሕወሓትን ማንነትና ባህሪ ግን ከግምት ያስገቡ አልነበሩም። ክልሉ ነጻ ከወጣ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በኮማንድ ፖስት መተዳደር ሲገባው እንደ ንግድ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲመራ መደረጉ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በቀላሉ በሕወሓት ደባ እንዲጠለፍ አስችሏል። በዚህ ላይ ሕግን ከማስከበር ዘመቻው ጎን ለጎን የትግራዋይን ልብ ለመማረክና የመረጃ ጦርነቱን ለማሸነፍ የተቀናጀ ርብርብ ባለመደረጉ ድክመቱን አባብሶታል። በአለማቀፍ ሚዲያውና ዲፕሎማሲው ሕወሓት ብልጫ ማግኘቱ በስንት መስዋዕትነት የተገኘውን ወታደራዊ ድል ለመጣል ተገደናል። የሚያሳዝነው ዛሬም ሕወሓትንና ጭፍሮቹን በልካቸው ትኩረት አለመስጠታችን ነው።
መንግስት ለሰብዓዊነትና ገበሬው እንዲያርስ፤ የትግራይ ሕዝብም የጥሞና ጊዜ እንዲኖረው ከትግራይ ክልል ለቆ ሲወጣ ተገቢውን ጥንቃቄና ዝግጅት ባለማድረጉና እንደ ኤርትራ ካሉ የክፉ ቀን አጋሮቹ ጋር መምከርና የመውጫ ስትራቴጂ መተለም ሲገባው ለምዕራባውያን ከክልሉ ለቆ እንደሚወጣ ከወር በፊት ማሳወቁ፤ ሕወሓት መረጃ ስለደረሰው ህቡዕ የገባውንና የተበተነውን ኃይሉን አሰባስቦ፤ ጥርሱን የነቀለበትን ደባ አክሎ ከክልሉ በመውጣት ላይ የነበረውን ሰራዊት ከማጥቃት ባሻገር የተወሰኑትን በመቁረጥና በሰላማዊ ሰዎች መንገድ በማዘጋት ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅሞበታል።
በዚህ የልብ ልብ የተሰማው ሕወሓት በምዕራባውያን በሚደረግለት የሳተላይት፣ የሚዲያና የዲፕሎማሲ ድጋፍ በመታገዝ በሕዝባዊ ማዕበል አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች የፈጸመው ሰቆቃ፣ ዘረፋና ውድመት መቼም ቢሆን ታሪክና ትውልድ አይረሳውም። ከሁሉም የአገራችንን የግዛት አንድነትና ህልውና ክፉኛ ፈትኗል። ሕወሓት የአዲስ አበባን አየር ጣርማ በር ላይ ሆኖ መማግ ቢችልም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በሁሉም ግንባሮች በመገኘት ከወታደራዊ አመራሮች ጋር በሰጡት በሳል አመራር በሶስት ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊና ሞራላዊ ኪሳራ ተከናንቦ ትርፍራፊ ኃይሉን እያንጠባጠበ ሽምጥ ጋልቦ መማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጓል።
ሆኖም ሰራዊቱ አሁንም እስከ መጨረሻው ከመደምሰስ ይልቅ በትግራይ አጎራባች አካባቢዎች ግስጋሴው እንዲገታ መደረጉ ሕወሓትን ለ3ኛ ዙር ጦርነት ድቤውን እንዲደልቅ የልብ ልብ ሰጥቶታል። ሌላው ስሁት መታጠፊያ እነ ስብሀት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተለቀቁበት በትክክለኛው ሰዓት አለመሆኑ በአገራዊ አንድነቱ ላይ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል። በዲያስፖራውም ሆነ በአገር ቤት ተፈጥሮ የነበረውን አንድነትም ክፉኛ ጎድቶታል። እንግዲህ አሁንም ተገደን ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ ከአንድም ሁለት ጊዜ ከፈጸምናቸው ስህተቶች በደንብ መማርና ለ3ኛ ጊዜ ላለመድገም አበክረን መዘጋጀት አለብን። ሌላው ለውጡንም ሆነ ብልጽግናን አመድ አፋሽና እጀ ሰባራ ያደረገው የኦነግ/ሸኔ ነገር ነው።
በለውጡ ማግስት ከተወሰዱ ደፋር እርምጃዎች ወይም ውሳኔዎች አንዱ በአሸባሪነት ተፈርጀው በጎረቤት አገራት ነፍጥ አንስተው በትጥቅ ላይ የነበሩ ተቃዋሚዎች በለውጥ ኃይሉ ከቅንነት በመነጨ ችኮላ ባልሰከነ ድርድርና ቅድመ ሁኔታ ወደ አገር ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ መፈቀዱ ሌላው ስሁት መታጠፊያ ነው። ይህን ውሳኔ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በተለይ ኦነግ/ሸኔ በአውሮፕላንና በአውቶብስ ወደ መሐል አገር ገብቶ ትጥቅ አልፈታም እስከ ማለት በመድረስ ገና በሁለት እግሩ ያልቆመን መንግስት መገዳደር ጀመረ። በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከሚቀሰቀሱ ሁከቶችና ግጭቶች ጀርባ እጁ እንዳለበት ተደጋግሞ ይነሳ ጀመር። በምዕራብ ወለጋ፣ በጉጂና በቦረና ዞኖች የንጹሐን ግድያ፣ ጠለፋና ዘረፋ ተባብሶ ቀጠለ። አባ ቶርቤ በመባል የሚታወቀው ገዳይ ክንፉም የኦሮሚያ አመራሮችን መግደል ጀመረ። የሞት ማስፈራሪያና ዛቻ በመላክ ታዋቂ ግለሰቦችንና አመራሮችን ማሸማቀቅን አጠናክሮ ቀጠለ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በለውጥ ኃይሉና በኦነግ መካከል የተፈጠረው ልዩነት እየተባባሰና እየተካረረ መጣ። ሆኖም የለውጥ ኃይሉ በልበ ሰፊነት እየተካረረ የመጣው ልዩነት በውይይት በሰላም ለመፍታት ጥረት አድርጓል። ይሄ ትዕግስቱም ፍሬ ያፈራ መስሎ ነበር። በአባ ገዳዎችና በታዋቂ ሰዎች አሸማጋይነት አምቦ ላይ እርቅ ወረደ። ሆኖም ይሄ እርቅ በሕግ የታገዘና አስገዳጅ ስላልነበር ብዙም ሳይቆይ ፈረሰና መካሰስ ተጀመረ። የለውጥ ኃይሉ ከኦነግ ጋር ያለውን ልዩነት በሰላም ለመፍታት የሄደበት እርቀት ለሴራ ትንተናና ለጥርጣሬ እየዳረገው መጣ። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የለውጡ ደጋፊም በመንግስት የአባባይነትና የልምምጥ አቋም ላይ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ። የኦነግ/ሸኔ ታጣቂዎች ማንነትን እየለዩ ንጹሐን መጨፍጨፍ፣ ማፈናቀልና መዝረፍን አባብሰው ሲቀጥሉ በለውጥ ኃይሉ ላይ እምነት የማጣት ነገር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጣ።
አዲስ አበባ የተቀመጠው ኦነግም በስሙ እየተፈጸመ ያለው ጭፍጨፋ እሱን እንደማይወክልና ከደሙ ንጹሕ መሆኑን ቢለፍፍም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም ነበር። ራሱን ሸኔ ብሎ የሚጠራው ወታደራዊ ክንፍም ጥቃቱን በማስፋት በኦሮሞ ሕዝብ ላይም ሕልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ መፈጸሙን አባብሶ በመቀጠል የሚቃወሙትን አባ ገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች ማሳደድና መግደል ጀመረ። በርካታ የኦሮሚያ ብልጽግና አመራሮችን ገደለ። በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎችም ተጠናክሮ ነጻ መሬት እስከመቆጣጠርና መዋቅርን እስከመያዝ በመድረስ ዕንቅስቃሴን እስከመግታት ደረሰ።
ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ ክህደትና ጭፍጨፋ በመፈጸሙ መንግስት ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባ ሸኔ አጋጣሚውን በመጠቀም እየተጠናከረ በመምጣት በስፋት መንቀሳቀስ ጀመረ። እንደሱ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋርና ከሌሎች ታጣቂዎች ጋር በመቀናጀት እዚህም እዚያም በንጹሐን ላይ የሚፈጽመውን ጭፍጨፋ አጠናክሮ ቀጠለ። ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ፊት ለፊት መግጠም ጀመረ። በኋላ ደግሞ ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር ግንባር በመፍጠር መንግስትን በኃይል ለመለወጥ ተንቀሳቀሰ። ዛሬም በተበታተነ ሁኔታ ቢሆንም የደህንነትና የጸጥታ ስጋት መሆኑ እንደቀጠለ ነው።
የትጥቅ ትግል ላይ በቆየባቸው በርካታ አስር አመታት አንዲት ጎጥ ተቆጣጥሮ የማያውቀው ይህ ቡድን እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው የለውጥ ኃይሉ ያለ አስገዳጅ ድርድርና ስምምነት ወደ አገር እንዲገባ ስላደረገ ነው። የለውጥ ኃይሉ ልዩነቶችና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በሰለጠነ ሰላማዊ ትግል ሊፈቱና ሊመለሱ ይችላሉ በሚል ቅንነት በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶች ወደ አገር እንዲገቡ ያሳለፈው ውሳኔ በመርህ ደረጃ ትክክል ቢሆንም በስርዓትና በድርድር የተቋጨ ስላልነበር ውድ ዋጋ አስከፍሎናል። እያስከፈለንም ይገኛል። ስሁት መታጠፊያዎች ወይም ውሳኔዎች ከአሰብነው መዳረሻ ወይም ግብ እንዳንደርስ አርጎናል የምለው ለዚህ ነው።
ስህተት እንደ ቡና አቦል፣ 2ኛና በረካ የለውምና ብንችል ከታሪክና ከሌሎች ስህተት እንማር፤ ካልቻልን ደግሞ ከስህተታችን በጊዜ እንማር። እርግጠኛ ነኝ መንግስት ሕወሓት ለ3ኛ ጊዜ ጦርነት ቢከፍት በሚል ከቀደሙ ስህተቶቹና ስሁት መታጠፊያዎቹ ተምሮ፤ ከሕወሓትም ሆነ ከቡችላዎቹ ቀድሞ ለማሰብና ለመንቀሳቀስ ዝግጁ ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም