አንዳንድ ሰዎች ሰሞኑን መነጋገሪያ ያደረጉት ነገር ቢኖር የሕወሓት አካሄድ አስገራሚ፣ እብደት የተሞላው፣ አለማወቅ የበዛበት…. ነው እያሉ ሃሳብ ሲለወዋወጡ ለመመልከት ሞክሬ ነበር። ይህ ሐሳብ ለምን መነጋገሪያ ሆነ ሲባል የትግራይን ወጣት ለስልጣኑ ሲል አገርና እና ወገን አልባ እያደረገ፤ በርሃብ አለንጋ እየገረፈ፣ የጥይት ማብረጃ እያደረገ መጓዙ ማነጋገሩ ብዙም አዲስ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በጣም አስገራሚ የሚያደርገው ከሰማይ በታች ሕወሓትን የሚዳፈር አካል የለም፤ ሲሉ የነበሩት ወደ ትቢያ አፈር መቀየራቸው ነው። የምስራቅ አፍሪካ የኃይል ሚዛን ጠባቂ እና አስጠባቂ አድርገው ራሳቸውን የሳሉት ራሳቸውን መከላከል ተስኗቸው፤ የትግላችን መነሻ በሚሏት በደደቢት በረሃ የሕይወታቸው መጨረሻ መሆኑን ስንመለከት ነው።
ታዲያ እንደ እድል ሆኖ ከተረፉት ጥቂት የሕወሓት አመራሮችም ውስጥ አሁንም የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ኤርትራንም ኢትዮጵያንም እንሰለቅጣለን ማለታቸው ነው። ይህ ቅዠት ሕወሓት እንደሚያስበው ሊሳካ ባይችልም፤ አለው አለው ለማለት ይህን መናገራቸው አያስገርምም። ሕወሓት አሁን ቁመናው ምን ላይ ነው የሚለውን ለማወቅ በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፓርላማ ላይ ሲናገሩ የነበረውን ማስታወስ በቂ ነው።
ይሄም ቡድኑ በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ይዞት የነበረው የአንድ ቡድን የበላይነት ነው። ለምሳሌ፣ ባለ አራት ኮከብ ወይንም ሙሉ ጀነራል 60 ከመቶ፣ ሌፍተናት ጀነራል 50 ከመቶ፣ ሜጀር ጀነራል 45 ከመቶ፣ ብርጋዴር ጀነራል 40 ከመቶ፣ ኮሎኔል 58 ከመቶ፣ እንዲሁም ሌተናል ኮሎኔል 66 ከመቶ፣ ሻለቃ 53 በመቶ በአንድ አካባቢ ተወላጆች የተያዘ ነበር። በጥቅሉ ከሙሉ ጄኔራል ጀምሮ እስከ ሻለቃ ድረስ በአማካይ ሲታይ 55 ከመቶ የሚሆነው ከአንድ አካባቢ ነው።
በመከላከያ ዋና መስሪያ ቤትም የሚመሩት በዋና መመሪያ እና መምሪያ ደረጃ ያሉት 80 ከመቶ ከትግራይ ክልል ነው። አመራር የሚሰጠው 80 ከመቶ ከአንድ አካባቢ ነው። ይህ ምን ማለት ደግሞ ቡድኑ የሚገዛውን ትጥቅ፣ ስልጠናው ግንኙነቱን ሁሉን በራሱ ሰንሰለት ብቻ የሚፈጽም የሚያውቀውም ራሱ ብቻ እንደነበር ነው። ቡድኑ ይሄን ሲያደርግም አቅም ያለው አመራር ከአንድ አካባቢ እንዲወጣ በማሰብ ነው። ይህ ደግሞ ለትግራይም ሆነ ለኢትዮጵያም አይጠቅምም። ምክንያቱም መከላከያ የአገር ጋሻ እንደመሆኑ በሚገባውና ባለው ህዝብ ልክ መሳተፍና አገር መጠበቅ አለበት።
ኢትዮጵያ የነበራት ዕዝ አዛዥ እና ምክትል አዛዥ መቶ በመቶ ከትግራይ ነው። ለምሳሌ፣ ሜካናይዝድ መቶ በመቶ፤ እንዲሁም በእግረኛ ክፍለጦር 80 ከመቶ ከትግራይ ነበሩ። በመከላከያ የስልጠና ተቋማትም ቢሆን 85 ከመቶ በትግራይ ልጆች የሚመሩ ነበሩ። ከለውጡ ማግስት ግን ሁሉም በሚገባው ልክ ድርሻውን መውሰድ እንዳለበት ታምኖ በሪፎርም የታገዘ ሁሉን የሚመስል የኢትዮጵያ መከላከያ ወደመገንባት ነው የተገባው።
ታዲያ በዚህ ውስጥ መረዳት የሚቻለው ነገር ቢኖር ሕወሓት አለን ብሎ ይመካበት የነበረው የአንድ ዘውግ የመከላከያ ሰራዊት አመራር ሚዛኑን በጠበቀ መንገድ መበወዙ ሳይወድ በግድ ፌጦ እንደመጋት ነበር። ቡድኑ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ያደረገው መፍጨርጨር ከሽንፈት ያልታደገውም ይሄው ከክልል የተሻገረ ኢትዮጵያን የሚመስል መከላከያ መገንባት መቻሉ ነበር።
ከእስካሁኑ ጉዞው የምንገዘነበውም ሕወሓት ስለ እኩልነት የሚሰብክ ግን እኩልነትን የማያውቅና የማይወድ፤ ስለነፃነት እየደሰኮረ ለራሱ ነፃ ያልወጣ ድርጅት ስለመሆኑ በግልፅ መረዳት ይቻላል። ከሞያሌ እስከ ቶጎ ጫሌ፤ ከሱዳን እስከ አዲስ አበባ በተዘረጋው የእከክልኝ ልከክልህ ስብስብ ብዙ ፀረ-አገር ተግባራትን ሲያከናወኑ ነበር። በአንድ ሕወሓታዊ አስተምሮ በተጠመቀና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ህልውናዬ ነው በሚል ጀነራል ቀጭን ትዕዛዝ አገር አምሰዋል። ታዲያ ሕወሓት ይህን ሁሉ ቅጥ ካጣ በኋላ እንዴት ሊኖር ይላል ብሎ ማሰብ ነው።
ሕወሓት አገርን መዝረፍ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን የዲፕሎማሲ ትስስር ከኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም አኳያ ሳይሆን ከግለሰቦች ስብስብ ጥቅም አኳያ የተቃኘ አድርገውት ነበር። ለዚህም ማሳያ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። ሕወሓት በጦርነት መሸነፉን የሰሙ አሜሪካ እና አውሮፓውያን የፈጠሩትን ጫና ማስታወስ በቂ ነው። ለአብነት በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ 17 ጊዜ ዜጎቹ አዲስ አበባ ለቀው እንዲወጡ መግለጫና ማስፈራሪያ መሰል መረጃዎችን ማውጣቱም የሚታወስ ነው። ኤምባሲው በተደጋጋሚ የፀጥታ ስጋት መልዕክት በማውጣት ዜጎቹ በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ሲወተውት ነበር። መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ግፊት ሲያደርግ እንደነበርም ይታወሳል።
በዚህም ብቻ አላበቃም፤ ቀጣዩ ጥያቄ በኢትዮጵያ መረጋጋት እስኪሰፍን የአፍሪካ ህብረት ዋና ጽህፈት ቤት በጊዜያዊነት ወደ ሌላ አገር ይዛወር የሚል እቅድም ነበር። አሜሪካ ይህንን ለማድረግ የፈለገችው ኢትዮጵያን ገሸሽ አድርጋ የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ፖሊሲዋን በኬንያ በኩል ለመፈጸም ስለወሰነች ሲሆን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ዘንድ ያላትን ተደማጭነትንም ለማፈራረስ ያለመ ነበር እንደ ሃሳባቸው ባይሳካም። ዳሩ ግን የዘንድሮ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄዱም ለሕወሓትም ለጠላቶቻችንም ራስ ምታት ነበር።
ዓለም ያልተረዳው እኛም ያላስረዳነው አንድ እውነት አለ። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በሕወሓት እሳቤ እና ፍልስፍና ልክ የተሰራ አለመሆኑንና በእጅጉ የገዘፈ ማንነት የተላበሰ ስለመሆኑ ማስገንዘብ አለብን። ሕወሓት ኢትዮጵያ የሚል ሰፊ እሳቤ አይገባውም። ከኩሬ የተጣባ ከሃይቅ ዝምድና የለውምና። በመሆኑም ሕወሓት ቀንደኛ ሰዎች እንጂ የሕወሓት እሳቤ አልሞተም። ኢትዮጵውያን ሕወሓት ዳግም ጦርነት ቢናፍቅ ሊገርማቸው አይገባም። የለመደው እኩል አለመሆንና ኢ- ፍትሃዊነት ነውና።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም