“ዳዴ”፡- ጨቅላ ሕጻናት ቆመው ለመሄድ የሚውተረተሩበት ተፈጥሯዊ የዕድሜያቸው ባህርይ ነው። “ወፌ ቆመች!” እየተባሉ ሲውተረተሩ ማየት እንኳን ለወላጆች ቀርቶ ለተመልካችም ቢሆን ደስታው እጥፍ ድርብ ነው። ሕጻናቱ አጥንታቸው ጠንክሮ ያለ ድጋፍ መቆም እስከሚችሉበት ጊዜ ድረስ ያለችው ያቺ አጭር ዕድሜ የምታሳሳና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግባት ወቅትም ነች። ሕጻናቱም ቢሆኑ ሲደነቃቀፉ ማልቀስ፣ መነጫነጭና እምባቸውን በማፍሰስ ስሜታቸውን መግለጽ የተለመደ ባህርያቸው ነው።
በግድ ካልቆምን ብለው ከተፈጥሯቸው ጋር ሲታገሉና ሲውተረተሩ መውደቃቸውና መላላጣቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በወላጆቻቸው “የእንትፉቱፍ ሽንገላ” የወደቁበት መሬትና ያደነቃቀፏቸው ቁሳቁስ በጥፊ እየተመቱላቸው ማባበልም የተለመደና ከጨቅላ ሕጻናቱ አስተዳደግ ጋር የተያያዘ ሌላው አዝናኝ ትርዒት ነው።
ማቲዎቹ በተሰበሰቡበት አንድ ክፍል ውስጥ መጫወቻ ከፊት ለፊታቸው በመወርወር እየዳኹም ሆነ ዳዴ እያሉ ተሽቀዳድመው እንዲያመጡ የሚደረገው ትእይንትም ብዙ የሚባልለት ነው። በዳዴ “ሩጫቸው” እየተውተረተሩ መጫወቻውን ቀድሞ ለመንጠቅ የሚያሳዩት ግብግብ ብቻ ሳይሆን “ለእኔ ብቻ ካልሆነ” በማለት የሚገጥሙት ትግል፣ ትርምስና የ“ተበለጥን” መጯጯኽም ሌላው የዘመናቸው መታወቂያ ነው። ልጅነት እንደሚባለው ጅልነት ሳይሆን “ማርና ወተት” እየተባለ የሚንቆለጳጰሰውም እነዚህን መሰል የጨቅላነት የዕድሜ ውበቶች እንደተወደዱ በተፈጥሮ “ቸርነት” ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ ስለሚኖሩ ጭምር ነው።
ይህን መሰሉ መልካም የጨቅላነት ዕድሜ ትሩፋት የሚወደደውና የሚናፈቀው ሁሌም በጊዜው ሲስተዋል ነው። በዕድሜያቸው ድኸውና ዳዴ ብለው ከማደግ ይልቅ መንፏቀቁንና ዳዴ ማለቱን የሙጥኝ የሚሉ ሕጻናት አንድም የጤና ችግር ወይንም የአስተዳደግ ጉድለት ያለባቸው ብቻ ናቸው። በጊዜው ያልዳኸ፣ በወቅቱ ዳዴ እያለ ያላደገና የማያድግ ሕጻን ለቤተሰብ የሀዘን ምክንያት፤ ለሆስፒታልም ቤትኛ ሆኖ ከመኖር ውጭ ሌላው አማራጭ የጠበበ ይሆናል። “ለሁሉም ጊዜ አለው” በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን የተወልን ታላቅ ምክርም እዚህ ቦታ ቢጠቀስ መልካም ይሆናል።
ከዳዴ እሽቅድምድም ያልተላቀቀው ፖለቲካችን፤
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወልደው የሚሞቱት ገና በዳዴ ዕድሜ ላይ እያሉ ነው። ረጅም ዕድሜ ይቆያሉ ቢባል እንኳን አኗኗራቸው ገና በጠዋቱ በመከፋፈል ልምሻ ስለሚለከፍ ነፍስ አውቆ ዓላማን ማስፈጸም ብርቅ እየሆነባቸው በአጭሩ የሚቀጩት ከእንፉቅቅ መዳኽ ሳይላቀቁ ነው። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዜና መዋዕል ውስጥ ለሥልጣን የሚደረገው የቡድኖች ትርምስ የቃላት ምርጫ ሳያስፈልግ ከጨቅላ ሕጻናት የመጫወቻ ቅሚያ ፍልሚያ ጋር የሚመሳሰል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ለምሳሌ፡- ፊውዳላዊው ሥርዓተ ማኅበር በዴሞክራሲ ፈለግ እንዲመራ ለማድረግ የኢትዮጵያ ለውጥ አላሚ ወጣቶች የከፈሉት መስዋዕትነት ይህ ቀረሽ የሚባልለት አልነበረም። ብዙዎች ለዴሞክራሲ እውን መሆን ታግለዋል። የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል እንኳን ሳይሳሱ “ጭዳ ሆነው” በነፍሳቸው በመወራረድ የማይተካ ደማቸውን ለዓላማቸው ገብረው አልፈዋል።
“መሬት ላራሹን!” እየፈከሩ፣ “ያልተማረ ይማር!” የሚል ምኞት እየዘመሩ፣ “ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ምድር እንዲሰፍን እየታገሉ”፣ “ሕዝባቸው ከድህነት እንዲላቀቅ” አምርረው ሥርዓቱን እየተቃወሙ የወደቁና እንደ ሻማ ቀልጠው ያለፉ የሕዝብ ልጆች ቁጥራቸው ሺህ ምንተሺ ነው። ዳሩ ምን ያደርጋል! ይህንን ለለውጥ የጨከነ ትውልድ የመሩትና ያሰማሩት መሪዎቻቸው በሥልጣን ጥምና ርሃብ ናውዘው የሰከሩ ስለነበሩ “እኛ እያሉ ወጣቱን እያስፈከሩ፤ ለእኔነት የግል ጥቅማቸው” መቃዠትን ስለመረጡ ያ የለውጥ ኃይል እንዲበተንና ደሙ “ደመ ከልብ” ሆኖ እንዲቀር ፈርደውበታል።
ንጉሣዊ ሥርዓቱ ከመንበሩ እንዲወገድ ለጥቂት ዓመታትና ወራት ያህል ታግለው በማታገል የፊት አውራሪነቱን ሚና የተጫወቱትና በተለያየ ስም ይታወቁ የነበሩ ግራ ዘመም የህቡዕ ታጋዮችና የአደባባይ ተፋላሚ አመራሮች የሚመሩትን ኃይል በጥበብ፣ በማስተዋልና በውይይት አስተባብሮና መርቶ ወደ ጋራ ግባቸው ከማድረስ ይልቅ “የዳዴ እንፉቅቅን የሙጥኝ ብለው” እርስ በእርስ መቦጫጨቅና መገዳደልን ተቀዳሚ ምርጫ በማድረጋቸውም መንጋቸው ተበታትኖ፣ እነርሱም ነፋስ እንደገባው እብቅ የት ደረሱ ሳይባል በከንቱ ባክነው ቀርተዋል።
አንዳንድ ፀረ አገርና ሕዝብ ፓርቲ ተብዬዎችም ለሱማሊያው እብሪተኛ መሪ ለዚያድ ባሬ ወራሪ ሠራዊት “አለኝታ በመሆን” በታሪክ ይቅር የማይባል ክህደት መፈጸማቸው የሚዘነጋ አይደለም። ያ “የሻምላ ትውልድ” እርስ በእርስ መፋለሙ ብቻም ሳይሆን ትግሉን አኮላሽቶ ለወታደራዊው ደርግ አሳልፎ መስጠቱም ሌላው “የዳዴ እንፉቅቅ ዘመኑ” መገለጫ ነው።
በዘመነ ደርግ የመጀመሪያው ዓመታት ግድም በኢማሌድኅ (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት) ጃንጥላ ሥር ለመሰባሰብ የሞከሩት “የዳዴ ተንፏቃቂ ስብስቦችም”፤ “የማይዘልቅ ማሕበር በጠጅ ይጀመራል” እንዲሉ፤ የጨቅላ ስብስባቸው የተጠናቀቀው መጠፋፋትን ምርጫ በማድረግ ነበር። በቀይና በነጭ ቀለማት የተወከሉት አገራዊ ሽብሮችም የምን ያህሉን ወጣቶችና ጎልማሶች ሕይወት እንደቀሰፉ በጥቁር ቱቢት የተሸፈኑትን የታሪክ ድርሳኖቻችንን ብንፈትሽ እውነቱን በግልጽ ይመሰክሩልናል።
የዘመነ ኢህአዴግ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዳዴ እሽቅድምድምም ገና ከጅምሩ በልምሻ የተለከፈ ነበር። በረኸኞቹ “ጌቶች” በምድረ በዳ የቀመሩት “ጨቅላ የፖለቲካ ቡድኖችን አሽመድምዶ ማስገበር” ስትራቴጂ ተተግብሮ የተሳካላቸው መቶ በመቶ ነበር ማለት ይቻላል። ከጎጥና ከብሔር ጋር “ጡት በማጣባት” የፈለፈሏቸው ቡድኖች እንዴት እንደኖሩና እንደሞቱ፣ እንዴትም እየኖሩ እንዳሉ የምናውቀው ስለሆነ ሙት ወቃሽ ሆነን ዜና እረፍታቸውን “መቃብራቸው ላይ ቆመን” መተረኩ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል። በእንፉቅቅ መኖሩ የተጣባቸው አንዳንድ “የልምሻው ዘመን ቅሪቶችም” የዕድሜ አዛውንት ፀጋቸውን አዋርደው የአስተሳሰብ ድንክዬ በመሆን እስካሁንም በጨቅላ ድርጊቶቻቸው ጤና እየነሱን እረፍት እንዲርቀን ምክንያት ሆነዋል።
የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች የሚገልጽና ስሜትን ፈታ የሚያደርግ አንድ የግል ገጠመኝ ላስታውስ። ይህ ጸሐፊ በዘመነ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪነቱ የጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አንድ “ዝነኛ” የህንድ መምህር ስም ተደጋግሞ ሲነሳ ያደምጥ ነበር። የጸሐፊው መኖሪያ ከትምህርት ቤቱ ተጎራባች ስለነበር ከጓደኞቹ ሪፖርት ብቻ ሳይሆን በጉርብትናም ጭምር መምህሩን በሚገባ ያውቀዋል።
ይህንን መምህር “ዝነኛ” ያሰኘው የዕውቀት አቅሙና የማስተማር ችሎታው ሳይሆን ታሪኩ ሌላ ነው። መምህሩ ቢያንስ ከሠላሳ እስከ አርባ ዓመት ለሚገመት ጊዜ በማስተማር ላይ በቆየበት እዚያ ት/ቤት ውስጥ የሚያስተምረው ኢትዮጵያ ከመምጣቱ አስቀድሞ ባዘጋጀው የማስታወሻ ደብተር እንጂ በአዲስ አቀራረብና ዝግጅት ለተማሪዎቹ እንደ ወቅቱ ማሻሻያ እያደረገ አልነበረም። ያቺ ዕድሜ ጠገብ የማስታወሻ ደብተሩ ከማርጀቷና ከመተሻሸቷ የተነሳ መልኳ ራሱ ወይቦ ከእርሱ ውጭ ማስታወሻውን የሚያነብ ሌላ ሰው ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ነበር።
ከበርካታ ዐሠርት ዓመታት በኋላ ት/ቤቱ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትነት ወደ ኮንስትራክሽን ኮሌጅነት አድጎና ይህ ጸሐፊም ወግ ደርሶት በዚያ ት/ቤት በትርፍ ሰዓት መምህርነት ለማገልገል ዕድል ባገኘባቸው ዓመታትም ያ መምህር ይጠቀም የነበረው በዚያችው ማስታወሻ ደብተር ነበር። ብዙ ተማሪዎች የዚህን መምህር ባህርይና የማስተማሪያውን ደብተር ምሥጢር ስለሚያውቁ በእርሱ ክፍለ ጊዜ ከመግባት ይልቅ ከቀዳሚዎቹ ተማሪዎች ደብተር በመዋስ ማጥናትን ይመርጡ ነበር። ይህ “መምህር እከሌ” ለብዙዎች የመዘባበቻ ምክንያት በመሆንም “በቃ እንደ ህንዳዊ…መምህር ማስታወሻ ደብተር ችክ አትበል” እየተባለ የቀልደኞች መሳሳቂያና መሳለቂያም ሆኖ ነበር።
ይህንን መምህር በተመለከተ አንባቢያን ብዙ ጥያቄዎችን ሊያነሱ ይችላሉ። የት/ቤቱ አስተዳደር ይህንን አያውቅም ነበር? ለምን ችላ ተብሎ ኖረ? በትምህርት ጉዳይ ተቆጣጣሪ የሆኑት በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ ተቋማትስ ስንፍናውን ሳይሰሙ ቀርተው ነው? ወዘተ.” የሚሉት መሟገቻዎች መነሳታቸው አግባብ ነው። መልሱ እርግጥ ነው የተጠቀሱት አካላት በሙሉ ጉዳዩን ያውቁ ነበር። ችግሩ መምህሩ የት/ቤቱን ኃላፊዎችና የትምህርት አመራሮችን የሚይዝበት ዘዴና ብልሃት በጣም የረቀቀ ስለነበር “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ ማንም ሃይ ባይ ተቆጭ ሳይኖረው ከዳይሬክተሩ ባልተናነሰ ስልጣን እንደተፈራ መኖሩን ብዙዎች ያውቁ ነበር። ለብዙ አገራዊና ወቅታዊ ጉዳዮችም ቀድሞ የቤት ሥራው ይሰጥ የነበረው ለዚሁ መምህር እንደነበርም የማያውቅ አልነበረም። ምስክሮች በአካል ይፈለጉ የሚባል ከሆነም እማኞችን ወደ አካባቢው ሄዶ ማፈላለግ አይገድም።
አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በሃምሳ ዓመት የአዲዮሎጂ ፍልስፍና ካልመራን እያሉ በአረጀ አስተሳሰብ ሙጭጭ ማለታቸው ከዚህ መምህር ጋር ሊያመሳስላቸው ይችላል። አንድም የዳዴ ተሽቀዳዳሚዎች መሆናቸው፣ ሁለትም ህልማቸውና ቅዠታቸው ሥልጣንና እርሱን ተከትሎ የሚመጣው ጥቅማ ጥቅም ውል ስለሚላቸው ሁሌም ከእዬዬያቸው ተገትተው አያውቁም። የወጣትነት አፍሮ ፀጉራቸው ብቻ ሳይሆን ርእዮተ ዓለማቸውም ሸብቶና ጎብጦ ከመቃብር አፋፍ ላይ መቆሙን እንኳን ባንነው ሊያስተውሉ አልቻሉም።
ተጨባጭ መከራከሪያ ይቅረብ ከተባለም በርካታዎቹ “የዳዴ ተሽቀዳዳሚ ፖለቲከኞች” ባለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት ውስጥ ብቻ ጨቅላ አስተሳሰባቸው ግድ እያላቸው ለምን ያህል ጊዜያት አንዱን ቡድን በማክሰም ሌላ ቡድን እየፈጠሩ፣ እየተዋሃዱና እየተገነጣጠሉ ሲገለባበጡ እንደኖሩ ማስታወሱ ብቻ በቂ ይሆናል።
ፖለቲካቸውን እንደተጸየፈና በድኩምነታቸው እንደሚያዝንላቸው አንድ ዜጋ የጸሐፊው ምክር አንድና አንድ ብቻ ነው። ሃምሳ ዓመት በእንፉቅቅ ከመጓዝ ነፃ ወጥተው ለግላቸው ጥሞና ሱባዔ ይግቡ። ያረጀውን የፖለቲካ ርእዮተ ዓላማቸውንም ይጎንድሉና አዳዲስ ችግኞች እንዲበቅሉ ለወራሾቻቸው እድል ይስጧቸው።
እንኳን በፖለቲካ ዓላማቸው ተወዳድረው ሊያሸንፉ ቀርቶ ቋንቋቸው ራሱ ዘመን የሚመጥን ያለመሆኑንም ይረዱት። ቢቻላቸውና ቢሆንላቸው ከሚዲያ ፉከራና ቀረርቶ አደብ ገዝተው ራሳቸውን ይፈትሹ። በዳዴ እሽቅድምድም ተወዳድረው ለማሸነፍ የዘመኑ “ፈጣን ጎዳና” ስለማይመጥናቸው የሽንፈታቸውን የረጅም ጉዞ እየሰነዱ ቢያስነብቡን ለእነርሱም ለእኛም የሚበጅ ይመስለናል። “ልብ ያለው ልብ ያድርግ” አለ ይባላል የአገሬ አስተዋይ መካሪ። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014