ግጥም የስነ ውበት ምስጢር በመሆኑ ስሜታዊ ግንዛቤን የሚመረምር የፍልስፍና ዘርፍ ነው ይላሉ ሊቃውንቶቹ። ለኔ ግን የንስሀ ፀሎት ይመስለኛል። ምክንያቱም ጥበብ እንደ ተገለፀ ቅርፅና ፅንሰ-ሀሳብ መኖሩ ውስብስብ ታሪክ ቢኖረውም ከጥንት ጀምሮ እስከ ሰው ልጅ የፍፃሜ ታሪክ ድረስ ስነ መለኮታዊ ኃይል አለው ብለው ከሚያምኑት አንዱ በመሆኔ የሀጢአትን እድፍ ለማፅዳት ከነፍስ አባት ጋር የሚደረግ ሚስጥራዊ ኑዛዜ ሆኖ ይሰማኛል።
እንደ ዓለማዊ ስናስበው ደግሞ ያንድን ነገር ጥቅምና ጉዳቱን አመዛዝኖና መስጥሮ ቢሻው በዜማ ካልሆነም በእንጉርጉሮ የነገሮችን ስብጥርና ቅላፄ ከሽኖና ምጥን አርጎ በመጭመቅ ከአንድ አረፍተ ነገር ተነስቶ ብዙ ሺህ ሕልሞችን መፍታት የሚችል ኃይል እንዳለው የስነግጥም ሃያሲያን ቃላቸውን ሰተውለታል። ከዚህ አኳያ፣ የሥነ ውበት ፈላስፋዎች አጥብቀው የሚያጠያይቁትም ሰዎች ምን መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት፣ መንካት እና መቅመስ እንደሚወዱ ከገጣሚው አዕምሮ የሚፈልቁትን ሚስጥረ ሐሳቦችን ታዳሚውን በኀዘንና በትካዜ፣ በሳቅና በደስታ ማማለላቸውን ከመመርመርመርና ከመግለፃቸው ባሻገር፤ የጥበብ ፍልስፍና የውበት፣ የተፈጥሮ እና የፍጥረት ውስጣዊ እና ውጫዊ ግንኙነትን መለኪያ ሚዛን አድርገው ወስደውታል::
ስለዚህ ገጣሚዎች ስለ ሩቁ ታሪካዊ ዘመን፣ ስለ ሰዎች፣ ፍጹም የተለየ የአኗኗር ዘይቤ ሊናገሩ ይችላሉ:: ቁምነገሩ ገጣሚዎቹ ሁል ጊዜ የሚሰማቸው ስሜቶች አሁን ላለው አድማጭም ሆነ አንባቢ እንዴት እንደተረዱት በምናባቸው በፈጠሩት ውብ ዓለም አካል የሆነውን ሕይወታችንን ለማጣጣም መሞከራቸውን አድናቂ ነኝ::
ለዛሬው ስለ ስነግጥም ባለችኝ ዕሩብ የማትሞላ እውቀቴ ይህን ያክል ካሉኩኝ ይብቃኝና ወደ ርዕሴ ልመለስ። እአአ 14/ 5/2022 ቅዳሜ በለንደን ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ታላቅ የግጥም ምሽት ለመከታተል ኖርዝ ለንደን ቾክ ፋርም በአንድ ኮሌጅ አዳራሽ ውስጥ ተገኝቼ ነበር። ምስራቅ ተረፈና ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ እንዲሁም ትዕግስት ማሞ ለስሜት ተፈላጊ የሆኑ ውበት አላቸው የሚባሉ ምርጥ የስነ ግጥም ሥራዎቻቸውን አቅርበው ሳዳምጥ አንድ ነገር ትኩረቴን ሳበው::
ለካስ ውበት ከተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ከሰው ሥራም ይመነጫል። በሰው ልጅ ኅሊና ውስጥ የሚመላለሱ እንደዚህ አይነት ቁም ነገሮች ሲነበቡ ማድመጥ ምን ያህል ሊያስደስት እንደሚችል በዚህ ክፉ ዘመን ላለን ትውልዶች አንድ እውነት አስጨብጠውናል። ምክንያቱም ይህ እውነት የተከናወነውና ከግጥማቸው ስንኞች የተደመጡ ሃሳቦች ያስተጋቡት በኪነ ጥበብ ልሳን የፍቅርን አሸናፊነት ነው:: እኔም በሰማሁት ደስተኛ ከመሆኔም በላይ በሀሳባቸው እስማማለሁ።
በፕሮግራሙም ላይ የቀረቡት ሶስቱ ገጣሚዎች የራሳቸውን ፈጠራና ለእይታ ቅርብ ያደረጋቸውን የስነ ጥበብ ምአዛቸውን የሰው ልጅ ደስታን እንዲያጎናፅፍ አድርገው ከማቅረባቸውም ባሻገር፤ ይሄን የፍቅርን አሸናፊነት ከፍ ያደረገ ጥበባቸውን ያሳረፉበት ለትውልድ የሚተርፍ የግጥም መደብል ፅፈው አበርክተውልን ገዝተን አስፈርመናል::
ታዲያ አበጃችሁ ብዕራችሁ አይንጠፍ ማለት ተገቢ በመሆኑ ለሶስቱም አድናቆቴ ይድረስልኝ:: በኔ በኩል ስለ እያንዳንቸው ብቃት ብፅፍ ደስ ባለኝ ነበር:: ነገር ግን ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ገጥሞኝ ፕሮግራሙን ሳልጨርስ ወጣሁ:: እስከ ነበርኩበት ሰዓት ግን የተሰማኝን አንድ ነገር ብቻ ማለት እፈልጋለሁ። እንደምታውቁት በአንድ ጊዜ ሁሉንም የዓለም ሙዚየሞች መጎብኘት አይቻልም፤ ሁሉንም ሲምፎኒዎች፣ ሶናታስ፣ ኦፔራዎችን ማዳመጥ አይችልም። ሁሉንም የስነ-ህንፃ ዋና ሥራዎችን መገምገም አይችልም። ሁሉንም ግጥሞች እንደገና ማሰላሰል አይችሉም፤ እናም ከሁሉም ዓይነት ውስጥ አንድ ሰው ለነፍሱ በጣም ቅርብ የሆነውን ነገር ይመርጣል። ይህም ለአእምሮው እና ለስሜቱ ማረፊያ የሚመርጠው ነው:: ለኔም የነፍስ ማረፊያ ሆና ብዕሬን እንዳነሰ የገፋፋችኝ “የጦቢዋ “ ምስራቅ ተረፈ ያቀረበቻቸው ስነ ግጥሞች የፍቅር ሰቆቃና ሐያልነት የያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ስለነበሩ ትኩረቴን ስብው ከሷ ጋር አብሬ አቆያችሁ አለሁ።
ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ አዲሱን የህብረተሰብ አመለካከት ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው አድርጋ የቀየሰቻቸው የስነ ግጥም ምህንድስናዋን አለማድነቅ ንፉግነት ስለሚሆንብኝ ትንሽ ማለት ወደድኩኝ:: ምስራቅ ተረፈ ከአለባበሷ ጀምሮ አፃፃፏም አቀራረቧም ባሕላዊ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የጠበቁ የሞራል ጭብጦችን ተጠቅማ በመሆኑ ለኔ ቢጤ የስነ ግጥም አድናቂዎች የነፍስ ምግቦች ነበሩ:: በእርግጥ በተለምዶ የውበት ተፈጥሮን የሚያሳዩ ብዙ የዕለት ተዕለት ገጠመኞችና ምሳሌዎች ቢኖሩም የምስራቅ ተረፈ ግጥሞች ግን የውበትን ዳኝነት ለመስጠትና የጥበብን ሚስጥር ለመረዳት እንደ መነሻ ጣዕም፣ ምናብ እና የተፈጥሮ ውበት ርዕሶች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ::
ግጥሞቿ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሚና ስለሚኖራቸው የወደፊት ትውልዶች በሥነ ምግባር እንዲቀረፁ ይረዳሉ:: ገጣሚዋ ሕይወትን ከፍቅር ጋር አቆራኝታ በተለያየ እይታ፣ በተለየ መንገድ፣ ከተራ ነገር በላይ ለማየት፣ እንድንችል የሰላ ስሜቷን ገልፃበታለች::. ልክ እንደ አንድ ሰው ብዙ ትናንሽ ደም መላሽ ቧንቧዎች፣ የደም ስሮች፣ የአካል ክፍሎች እንዳሉት ሁሉ ምስራቅ ተረፈም ስነ ግጥሟን በዚህ ምሳሌ አሳይታበታለች።
በቀላል አገላለጽ ሥነ ግጥም አንድ ሰው የሚያምር ነገርን ወደ እውነት ለመተርጎምና ከእንደዚህ ዓይነቶቹ ነገሮች የውበት ደስታን ማግኘት እንደሚችል ማረጋገጥ ስለሆነ፣ ምስራቅ ተረፈ ይህንን ድርጊት በችሎታዋ ስትገልፀው በዓይናችን አይተናል:: ምስራቅ በደራሲ እና በአድማጭ መካከል የማይሰሙ የሚመስሉ የንግግር ክፍተቶችን ሞልታ በስነ ውብት ድር አስተሳስራ ሕይወት በመስጠት ሰሚ/አንባቢ/ተመልካች ዳግም አንድ አይነት ሊሆኑ እንዲችሉ፤ ሀ… ግእዝ፣ ሁ…ካዕብ …ላ…ራብእ… እያለች የስነ ግጥምን ሀሁ አስቆጥራን አምሽታለች:: የጥበብ ባህሪው ደግሞ እውነታውን መወከል በመሆኑ የማቱ ሰላምን ዕድሜ ተመኘሁላት:: ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ:: አብራችሁኝ፣ ስለ ቆያችሁ አመስግኜ መልካሙን ሁሉ ተመኘሁላችሁ። ሰላም!
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 10/2014