ኢትዮጵያ ባህር ተሻግረውና ድንበር ጥሰው ሊያስገብሯት ሊወሯትና ቅኝ ሊገዟት አልመው ለመጡ ጠላቶቿ በየትኛውም ወቅት ሸብረክ ብላ፣ እጇን ሰጥታ አታውቅም። ጠላቶቿን በሙሉ እያሳፈረች ዘመናትን በድል ተሻግራለች።
ኢትዮጵያውያንም ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በአንድነት በመመከት አንፀባራቂ ታሪክ አላቸው። ለኢትዮጵያውያን አገራቸው መኩሪያቸውና መከበሪያቸው ናት። ስለ ፍቅር እጅ፣ ስለ ጠብ ከሆነም ነፍጥ በማንሳት የሚታወቁት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ክብር አይደራደሩም።
የኢትዮጵያ ልጆቿ በታሪኩ የሚታወቁትም አገራቸው ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች ሲጠብቁና ደማቸው አፍስሰው የሕይወት መስዋዕትነት ሲከፍልላት ነው። ሕዝቡ፣ የእናት አገር ፍቅር ስሜት ምን ማለት እንደሆነ በተለያዩ ትውልዶች አማካይነት አሳይቷል።
በተለይም አሸባሪ የሕወሓት ቡድን በሕዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ኢትዮጵያን መምራት የምችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ብቻ ነኝ›› በሚል ትእቢት ተወጥሮ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ማወጁ የሚታወስ ነው።
ይሁንና በታሪካቸው ለጠላት እጅ ሰጥተው የማያውቁት የኢትዮጵያ ልጆች፣ አገራቸውን ሊታደጉ ከያሉበት በመጠራራት ሕይወታቸውን፣ አጥንታቸውን፣ ጉልበታቸንውንና ሃብታቸውን ጭምር በመስጠት አገር አኩርተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና አጠቃላይ የፀጥታ ዘርፉ ኢትዮጵያን ወደ ሲዖል አወርዳታለሁ ብሎ የዛተውንና የሚዳክረውን ሕወሓትን አገር የማጥፋት ዓላማ በጋራ ክንድ አክሽፈዋል።
የተደቀነውን ወረራ ለመቀልበስ በተደረገው ርብርብ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ለአገር የሚዋደቁ ጽኑ ሕዝቦች መሆናቸውን አስመስክረዋል። የጥፋት ኃይሉ እንቅስቃሴ ተቀልብሶ ሰላም የተገኘውም ‹‹የክፉ ቀን ደራሽ፣ የአገር ባለውለታ እና ቆራጥ ጀግኖች ሕይወትና አካል ተገብሮበት መሆኑ እሙን ነው።
ለእናት አገር ፍቅር የሚከፈለው መስዋዕትነት በዋዛ የሚታይ አይደለም። ከሕይወት መስዋዕትነትና በአካል ላይ ከሚደርስ ጉዳት በተጨማሪ፣ የአገር ፍቅር ስሜት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር የነፃነት ተጋድሎ መገለጫ ጭምር ነው። ኢትዮጵያም አገርን ከወራሪ በመጠበቅ ረገድም ታሪክ ለሠሩ ባለውለታዎች ተገቢውን ክብር እውቅና ከመስጠት ረገድ የምትታማ አይደለም።
ባሳለፍነው ሳምንትም በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የዕውቅናና የምስጋና መርህ ግብር በባህር ዳር ከተማ ተዘጋጅቷል። ‹‹በህግ ማስከብርና በህልውና ዘመቻ የተከፈለ መስዋዕትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት” በሚል መሪ ቃል የተከወነም ነበር።
በዚሁ መድረክ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የክልል ርእሳነ መስተዳድሮችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ፤ ‹‹ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት ወረራውን ለመቀልበስ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት፣ ክልሎች፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ዲያስፖራው፤ በአጠቃላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተው ድጋፍና የፈጸመው ተጋድሎ እጅግ አስደናቂ ነው፣ ተግባሩም የኢትዮጵያ አንድነት ተጨባጭ ማረጋገጫ ነው›› ብለዋል።
በእውቅናና የሽልማት ፕሮግራሙ ጀብዱ የፈጸሙ የጸጥታ ሃይሎች፣ መስዋዕት የከፈሉ ቤተሰቦች፣ ብቁ አመራር የሰጡ የሰራዊት አመራሮች፣ ባለሃብቶች፣ ሚዲያዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በትግሉ ወቅት ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር ያለ ስስት አሳልፈው የሰጡ ጀግኖችንና ተቋማት እውቅና መስጠት ላበረከቱት አስተዋፅኦ፣ ማበረታታት፣ መደገፍ፣ ማድነቅ ትርጉሙ እንዴት ይገለፃል፣ ትሩፋቱስ ምን ይሆን በሚል ጥያቄ አቅርቧል።
አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከልም የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ አንዱ ናቸው። ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣በማንኛውም ስራ መስክ ተሰማርተው ውጤት ለሚያመጡ እውቅና ምስጋና እና ውዳሴ ማቅረብ ተገቢ ስለመሆኑ ያነሳሉ።
በዘመናት መካከል አገርን ከወራሪ በመጠበቅ ረገድም ታሪክ ለሠሩ የአገር ባለውለታዎች ተገቢውን ክብር መስጠት፣ ታሪካቸውን መዘከርና በቋሚነት እንዲታወሱ ማድረግም የተለመደ መሆኑን የሚያስታውሱት ሃምሳ አለቃው፣‹‹እኔም የሰራዊቱ አባል እያለሁ በአንድ ግንባር ወይም ስፍራ ላይ የሚሰጠንን ግዳጅ በተገቢና በውጤታማ መንገድ ስንወጣ እንሾም እንወደስ ነበር›› ይላሉ።
በህግ ማስከበር ዘመቻው የተሳተፉ ሕይወታቸውን፣ የሰጡ አካላቸውን ያጎደሉ፣ ላብን ደማቸውን ያፈሰሱ በርካታ ኢትዮጵያን መሆናቸውን የሚያወሱት ሃምሳ አለቃው፣ እነዚህን ወገኖች ጀግኖች ናችሁ ክብር ይገባቸዋል ልናመሰግን፣ ልናወድሳቸው ይገባል። ማለት ትልቅ ተግባር ነው፣ በተከፈለው ዋጋ ልክ እውቅና እና ምስጋና መቸር የግድ ነው። ይላሉ።
‹‹ስትሾም፣ ስትሸልም፣ ስታወድስ፣ ስታመሰግን፣ የሚደሰት እንዳለ ሁሉ ቅር የሚለው፣ ጥሩ ስሜት የማይሰማው ይኖራል ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፣ ምክንያቱም ሁሉንም ማስደሰት አይቻልም›› የሚሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚራገበው መልኩ ሳይሆን ለእውነት ስለእውነት ለአገር ለተዋደቁት እውቅና ሰጥቶ እናመሰግናለን ማለት ለሰሩት ስራ ሹመትና ሽልማት መስጠት ሊለመድ የሚገባውና ትክክል ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል።
እንደ ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ገለጻ፣ አንድ ለአገሩ ደጀን ለመሆን የወሰነን ሰው ተሰውቶ አሊያም ደሙን አፍስሶ አሊያም ደክሞ ዝም ስትለው የሚያስተላልፈው መልእክት እጅግ አደገኛ ነው። ዋጋ የከፈልከው ለአገር ነው እውቅና ሊሰጥህና ልትከበር፣ ልንሾምህ ይገባል ልንደግፍ ይገባል በሚል መስራት ከተቻለ ተስፋ ያለው ትውልድ መፍጠር ቀላል ነው።
መሰል የእውቅና ሽልማቶች ያበረታታል። የተሻለ እንዲመጣ ይግዛል። ያበረታታል። ጉልበት ይሆናል። አንድ የአንድነት ውጤቶች በመሆናቸው አንድ ለመሆን ከፍተኛ አቅም ይፈጥራሉ። ትውልድም ይህ ከሆነማ ነገ እኔም እሸለማለሁ፣ እታወሳለሁ ብሎ እንዲያስብ ያደርጋል።
በዛሬ ተግዳሎ ሁሉ አልፎ ታሪክ ሆኖ ሲወሳም ለነገው ትውልድ የሚያስተላላፈው መልእክት ግዙፍ ነው። በትውልድ ቅብብሎሽ ኢትዮጵያዊነት ታላቅነት አልሸነፍ ባይነት መሆኑን የማስረገጥ፣ ትውልዱም አገሩን እንዲጠብቅ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለበት የሚያስተምር ነው።፡
ከሁሉ በላይ ‹‹ትውልድ ለአገሩ ደጀን በመሆን በሚሰራው ታሪክ መሰል የክብር እጣ ይደርሰኛል ብሎ እንዲያስብ ያደርጋል የሚሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ አገርና ትውልድ እስከቀጠሉና ኢትዮጵያም እየገጠማት ካሉና ሊጠብቃት ከሚችሉ ፈተናዎች እስካሉ፣ ሰላሟ የፀና የተረጋጋ ቢሆን እንኳን በየጊዜው ጀግኖችን ማወደስና መሸለም ሊቋረጥ የሚገባው መሆን እንደሌለበት ያሰምሩበታል።
በህልውና ዘመቻው ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት በግንባርም ሆነ በማስልጠኛ ተቋማት በመገኘት ሙያዊ ልምድና እውቀታቸውን ማካፈላቸውን የሚጠቁሙት ሃምሳ አለቃው፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና የልማት ማህበር እንደ ተቋም ሚያዝያ 8 ቀን 2014 ዓ.ም ለሰራዊቱ የእውቅና መርሃ ግብር ማካሄዱን ይገልፃሉ።
‹‹የሆንከውን ሁሉ በሚገባ እንገነዘባለን እናከብራለን፤ ለእኔ ለእኛ እና ለኢትዮጵያ ነው ማለት ትርጉሙ ግዙፍ ነው›› የሚሉት ሃምሳ አለቃው፣ በመንግስትን እና በተቋማት ደረጃ ብቻም ሳይሆን መላ ኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ተግባር መከወን እንዳለበት ያስረዳሉ።
‹‹እኛ በሰላም ተረጋግተን ሕይወታችንን እንድንመራ ብሎም ስራችንን እንድንሰራ ሰራዊቱ ዋጋ ከፍሏል፣ መስዋእት ሆኗል። ለእኛ ነው የከፍልከው በሚል እሳቤ ማበረታታን ታሳቢ ያደረገ መድረከ ተፈጥሮ መርሃ ግብር ሊዘጋጅ ይገባል›› ይላሉ።
በህልውና ዘመቻ ወቅት በጀግናነት ግዳጃቸውን ከተወጡት ባሻገር መስዋእት የሆኑና አካል ጉዳት የደረሰባቸው የሰራዊት አባላትን ታሳቢ ማድረግ ቤተሰቦቻቸውን አይዛችሁ ማለትና መደገፍ እንደሚገባ አፅእኖት ሰጡት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ኢትዮጵያውያንም ቢሆን ሁሉም የሆነው ለእኛ ነውና እኛም ከጎናችሁ ነን ሊላቸው ይገባል፣ መሰል የመከባበርና የመደጋገፍ ባህልን ማጠንከር ከተቻለ ኢትዮጵያን ወደ ፈለገችው ከፍታ ማሸጋገር ቀላል ይሆናልም›› ነው ያሉት።
በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻው በሁሉም ደረጃ ያለው ሰራዊቱ ለሰራውን አኩሪ ገድልና በደማቅ ቀለም ለፃፈው ታሪክ የመላ ከህፃን እስከ አዛውንት የመላ የኢትዮጵያውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። ከአገር ውስጥ ባለፈ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበር ይታወሳል።
ዲያስፖራው ማህበረሰብም በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ኢትዮጵያ ከውጭም ከውስጥም ፈተና ሲበዛባት ሴራውን በመቀልበስ ረገድ ታሪክ የማይረሳው ጀብዱ ፈፅሟል። ኢትዮጵያ በውጭ ጣልቃ ገብነት የምትደክም፣ እጅ የማትሰጥ አገርና ሕዝቦቿም የማይንበረከኩ መሆናቸውን አሳይተዋል።
በተለይ ‹‹no more ወይም ‹‹በቃን›› በሚል የምዕራቡን ዓለም ጣልቃ ገብነት የሚያወግዝ ሰልፍ በመላ ዓለም በማዘጋጀት ኢዮጵያዊያን ተንበርክኮ ከመኖር ሞትን ተቀብለው ቀና እንዳሉ በክብር መሞትን የሚመርጡ ስለ ነጻነታቸው ቀናኢ የሆኑ ሕዝቦች መሆናቸውን አስመስክረዋል።
የጣልቃ ገብነት የሴራው ተዋናይ በሆኑ አገራት ሜዳ ተገኝተው በግልፅ ቋንቋ፤ ‹‹አንድ ነን! ሉዓላዊ ነን! ማደግ መብታችን ነው! ከመንገዳችን ውጡልን!፤ አገሬን አትንኩ!፣ ከአገሬ ላይ የክፋት ዓይኖቻችሁን ንቀሉ!፣ መሰሪ እጆቻችሁን አንሱ እምብኝ ለቅኝ ግዛት!፣ እምብኝ ለሴራ፣ እምብኝ ለሃሰት፣ እምብኝ ለጣልቃ ገብነት፣ እምቢ ለአገሬ!” የሚሉ መልእክቶቻችን አስተጋብተዋል።
በተቀናጀ መንገድ የተከፈተውን ወረራ ለመቀልበስ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውን ያደረጉት ዓለምን ያስደነቀ ርብርብ ለወዳጅም ለጠላትም ትምህርት ሰጥቷል። አንዳንድ አገራትም ሆነ የፀጥታው ምክር ቤቱ የፈለጉት ኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዳያሳካም ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር፣ አቶ ወንድወሰን ግርማም፣ ዲያስፖራው ማህበረሰብ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች በመወከል የአገሩን መብትና ጥቅም ከመከላከልና ባለፈ ለመከላከያ ሰራዊት፣ ለተፈናቀሉ ወገኖች ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው የአይነትና የገንዘብ ድጋፋ አድርጓል›› ይላሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄደው መርሀ ግብር ላይም የዲያስፖራው ማህበረሰብ በህግ ማስከበርና ህልውና ዘመቻ ላበረከት አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጥቶታል። አቶ ወንድወሰንም እውቅናው፣ በልዩ ልዩ አገራዊው ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይም ሆነ በአገራዊ ጥሪዎች ላይ እየተሳተፈ ለሚገኘው ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ትርጉም ግዙፍ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹ዲያስፖራው ለአገሩ ጥላ ከለላ እየሆነ ያለው ሽልማት ወይንም እውቅን ለማግኘት አይደለም፣ ለኢትዮጵያ ካለ ፍቅር እና ለሰላም እና ለእድገት ካለው ፅኑ ፍላጎት ነው›› የሚሉት አቶ ወንድወሰን፣በዚህ አግባብ ለአገሩ እየከፈለ ላለው ሁለንታናዊ መስዋትነት ክብርና እውቅና ማግኘቱም ይበልጥ የሚያበረታታና ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
‹‹እኛም ስለተሰጠን እውቅና ምስጋናቸውን ከፍተኛ ነው›› ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ በቀጣይ የዲያስፖራውን ድጋፍ የሚፈልጉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችና ወቅታዊ ጥሪዎች እንዲሁም ሜጋ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ዲያስፖራውም በተለመደው መልኩ ተገቢን ምላሽ በመስጠት ከሕዝብና ከአገር ጎን መቆሙን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣‹‹ጀግናን ማክበርና ማወደስ መልካም ባህል ነው። በችግር ቀን ደማቸውን፣ አጥንታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን ሰውተው ነፃነታችንን የሚሰጡንን ጀግኖች ማስታወስ፣ ማወደሰና ማመስገን ለሌሎች አርአያ እንዲሆኑ ማድረግም መታደል ነው››ብለዋል።
‹‹ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደህንነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች እውቅና መስጠት በርካታ ጀግኖችን ይፈጥራል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የሚታወቁና የማይታወቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረጋቸው እውቅና እና ምስጋና መስጠቱ አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል።
በሕግ ማስከበር እና በህልውና ዘመቻ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት የተሰጣቸው ሽልማት አገራቸውን ለሚወዱ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በደም እና በሕይወት ዋጋ ለከፈሉ ሁሉ ማስታወሻ የሚሆን ነው›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም በባህል፤ በሃይማኖት በቋንቋ፤ በፖለቲካ እሳቤ የሚለያዩ ሰዎች የነበሯት፣ ነገር ግን ልዩነቶቻቸው ሳያግዳቸው በኢትዮጵያዊነት ስለሚግባቡ ለኢትዮጵያ ህልውና በጋራ ተሰልፈው ነፃ አገር እንዳስረከቡን ሁሉ ዛሬም ከእያንዳንዱ ክልል፤ ከእያንዳንዱ ሃይማኖት፤ የተለያየ የፖለቲካ እሳቤ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ቢሆኑም ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን ለመድፈር ሲፈልጉ በጋራ የምንቆምና ህልውናችንን የምናስከብር መሆናችንን ከትናንትናው ድላችን ትምህርት ወስደው ደጋግመው እንዲያስቡ አሳስበዋል።
በመድረኩ፣ በህግ ማስከበሩና በህልውና ዘመቻው በርካታ ቁጥር ያላቸው የጸጥታ አካላት መስዋዕትነት ከፍለዋል፣ እውቅናና ሽልማቱም በመድረኩ ለተጠሩት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጀግኖች መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተመላክቷል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014