ሴቶችን ከዓላማቸውና ከመንገዳቸው የሚያስቱ በርካታ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ያለእድሜ ጋብቻ የመጀመሪያዎቹን ተርታ ይይዛል። ሴቶች ያለ እድሜያቸው ወደ ትዳር ሲገቡ ከትምህርታቸው ነገ መሆን ከሚፈልጉት ሁሉ ከመሰናከላቸውም በላይ ትዳሩን ተከትሎ ለሚመጣ የኑሮ ጫና እንዲሁም ዝግጁ ባልሆነ አካላቸው አርግዘው ልጅ ለመውለድና ለማሳደግ ይገደዳሉ።
ለምሳሌ አህጉራችን አፍሪካ ውስጥ የምትገኘው ሴራሊዮን ታዳጊ ሴቶች ቶሎ ቶሎ የሚዳሩባት አገር ነች። እኤአ በ 2013 የተሰራ ዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑት ሴት ዜጎቿ መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት የልጅ እናቶች ናቸው። በአገሪቱ እኤአ በ2014 የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ስለነበር ያለ እድሜ ጋብቻ በመስፋፋቱ የመወለድ መጠኑ ወደ 65 በመቶ አድጎ እንደነበረም ተጠቅሷል።
እነዚህ መሰናክሎች ደግሞ በአካል ጉዳተኛ ሴቶች ላይ ሲሆን የሚያደርሱት ጫና ከፍ ያለ ነው። ፈተናው በእጅጉ ይከፋል። ዛሬ ተሞክሮዋን ለሴቶች ዓምድ ያካፈለችን የ21 ዓመቷ ዓይነ ስውር ወይዘሮ የትነበርሽ መለሰ ዕጣ ፋንታዋ ይሄው ሆኗል።
ዓይኗን ያጣችው ገና በጠዋቱ ነው። ይሄንንም ብዙም ማታስታውሳቸውና እሷን ለማስተማር ከገጠር አዝለዋት የመጡት እናቷ ናቸው የነገሯት። እናቷ በስድስት ዓመት ዕድሜዋ እንዳወጓት ጠራራ ፀሐይ ላይ ተኝታ በምች አማካኝነት ብርሃኗን ማጣቷን አጫውተዋታል። እናቷን ከባለቤታቸው አስኮብልሎ ከገጠር ያወጣቸው ደላላ ሥራ አስቀጥርሻለሁ ብሎ ነበር ፤ ነገር ግን ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ሥራ አላስቀጠራቸውም። ይልቁንም ሚስት አድርጎ ሲያስለምናቸው መቆየቱን ታስታውሳለች። እሷንም ከእናቷ ጋር ሲያስለምናት ቆይቷል። በዚሁ በልመና ላይ እያሉም ካመጣቸው ሰው አርግዘው በወሊድ ምክንያት ነው ሕይወታቸውን ያጡት።
እናቷ በዚህ ሁኔታ በሞት ከተለዯት በኋላ በቅርብ ርቀት ሆነው ስለሚሆነው ሁሉ ይታዘቡ የነበሩ አንድ መልካም ሰው በእናቷ እግር ከምትተካበት ልመና ድና ወደ ኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን እንድታቀና ሆነ። እዚህ በሚገኘው ባኮ ዓይነስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትም ለመጀመሪያ ጊዜ ከትምህርት ጋር የመገናኘት ዕድል አገኘች።
በልጅነቷ እናቷ በሞት ለተለየቻት ለወጣቷ ዓይነስውር ብቸኛ ዘመዷም ሆነ ተስፋዋ ይሄው ትምህርት ነውና ጥሩ አድርጋም ያዘችው። አዳሪ ትምህርት ቤቱ ወዲያ ወዲህ የማያባክንም ሆነ ለተለያዩ ችግሮች የሚጋልጥ አልነበረም። ይሄው ሁኔታ ታዲያ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን በጥሩ ሁኔታ ለመከታታል አስችሏት እንደነበረ የትነበርሽ ትናገራለች። በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናም 73 አማካይ ውጤት አምጥታ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ለማለፍ በቅታለች።
ወጣቷ ዓይነስውር የሁለት ልጆቿን አባት ያገኘችው በዚሁ በባኮ ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ነበር። ልጁ ወጣት ቢሆንም በዕድሜ በዓመታት ይበልጣታል። ዘንድሮ ሁለቱም የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ቢሆኑም ያኔ እሷ በክፍል ደረጃ ትበልጠው ነበር።
የባለቤቷ ዓይኖች ትንሽ ትንሽ ቢያዩም የዓይን ብርሃን ችግር አለበት። ታዲያ ይሄው ወጣት የትነበርሽን ከባኮ ወደ ሰሜን ሸዋ ቤተሰቦቹ ጋር ወሰዳት። የወሰዳት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን ትምህርቷን እኔ አስተምርሻለሁ በማለት ነበር። የትነበርሽ እሱ ያላትን በማመን ብቻ ሳይሆን የምትሄድበት ቤተሰብ ስለሌላትም ተከትላው ወደ ሰሜን ሸዋ ሄደች። በእርግጥ ሁለቱም ደብረ ኤባ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።
ነገር ግን በዚህ መካከል በእሱ ቤተሰብ ግፊትና ውትወታ ተጋቡ። ከገባሁ ልጅ ስለምወልድ በዓይነ ስውርነቴና እራሴን ባለመቻሌ ላይ ተደራርቦ ብዙ ችግር ሊፈጠርብኝ ይችላል በሚል ስጋት እንቢ ብትልም ቤተሰቦቹ ብዙ አግባብተዋትና ለምነዋት ወደ ትዳር ገባች ። ስጋቷ የበረታው ልጁም እንደ እሷ ተማሪ በመሆኑና ሥራ ስለሌለው እንደነበርም ወጣቷ ዓይነስውር አጫውታናለች።
የፈራችው አልቀረም በ15 ዓመት ለጋ ዕድሜዋ በመዳሯ አሁን ላይ ሦስት ዓመት የሆናትን የመጀመሪያ ልጇንም ወለደች። በዚህ ምክንያት ትምህርቷን አቋረጠች። ይሄ ወቅት ለእርሷ በጣም ከባድ ነበር። ከዚህ ከወሊድ በፊትም የነበሩት ዘጠኝ ወራቶች እንኳን ለዓይነስውር ለጤናማና የመውለድና የጋብቻ ዕድሜው ለደረሰ ሰውም ከባድ ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች። ይሄ ለዓይነስውሯ ወጣት የት ነበርሽ ከጽንስ ወቅት ጀምሮ ለዘጠኝ ተከታታይ ወራት አስቸጋሪ ሆኖባት ነው ያለፈው። ከጉዳቱ ጋር ጎንበስ ቀና ለማለት ሁሉ በእጅጉ ይከብዳት ነበር። ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ፤ ከትምህርት ቤት ወደ ቤት መመላለሱ በራሱ ሲያስጨንቃት ነው የከረመው። ልጇን ከወለደቻት በኋላም መቸገሯ ተባብሶ እንደቀጠለ ትናገራለች። ማጠብ፣ ማቀፍ፣ ማዘል፣ መንከባከብና መመገብ በራሱ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። አሳሳቢው ደግሞ ከምንም በላይ ለህፃናት ወተት ለሚወጣው ወጪ ቋሚ የገቢ ምንጭ አለመኖር ነው። እንዲህም ሆኖ እንደወለደች ትምህርት ቤት ስለማትሄድ በመውለዷ ምክንያት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ለወራት አቋርጣለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ የአንድ ሴሚስተር ፈተና እንደሚያመልጣት ቀድሞውኑም አስባው ነበር። ትምህርት ቤት ሄዳ እስክትመጣ ልጇን ቤተሰቦቹ እየያዙላት ብትቀጥልም እንደ ቀድሞው በትምህርቷ መበርታት አልቻለችም። የልጅ እናት ሆና ጊዜዋን ልጇ ስለምትሻማት ጥሩ ውጤት ማምጣት አልቻለችም። የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷን ያጠናቀቀችው እንደቀደመው በጥሩ ውጤት አልነበረም። ሆኖም ወደ 10ኛ ክፍል መዛወር ችላለች። የ10ኛ ክፍል ትምህርትም እንደ ዘጠነኛ ክፍል ትምህርቷ ሁሉ ከተወለደች ልጅ እንክብካቤ ጋር እንደነገሩ በዛው በደብረ ኤባ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ተጠናቀቀ።
ለወይዘሮ የትነበርሽ ከአይነስውርነት ጉዳቷ ጋር ተደማምሮ ልጅ ማሳደጉ ቀላል አልሆነላትም። ያም ቢሆን ግን ትምህርቷን ማቋረጥ አልፈለገችም። በትልቅ ችግር ውስጥ ሆናም የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወሰደች፤ ከዚህም በኋላ በአንዲት ጓደኛዋ አማካኝነት በ2011 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣች። ቱጌዘር የሚባል ዓይነ ስውራንን የሚደግፍ ድርጅትም ለልጇና ለእሷ ባደረገላቸው ድጋፍ በ2012 ዓ.ም በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን የመቀጠል ዕድል አግኝታ ነበር። ልጇን ድርጅቱ እየያዘላት መማሯ ተመችቷት የቆየ ቢሆንም የልጇ አባት እሷ በጓደኛዋ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ እግር በእግር ተከትሏት መጥቶ ነበርና ሁለተኛ ልጇን ፀነሰች። በዚህ ምክንያትም በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የጀመረችውን የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገደደች። ለመጀመሪያ ልጇ ሲያደርግ የነበረውን የገንዘብ ድጎማ ለሁለተኛ ልጇም ያደርጋል ። ገንዘቡ ለእሷና ለልጆቿ ቀለብ በቂ ቢሆንም የቤት ኪራዩ ጉዳይ ግን ጤና ነስቷታል።
ያም ሆነ ይህ ይሄን ከባድ የኑሮ ጫና ተቋቁማ ዘንድሮ ከ11ኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርቷን በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተከታተለች ትገኛለች። ወይዘሮ የትነበርሽ ትምህርቷን መቀጠል የቻለችው የባለቤቷ ቤተሰቦች ልጆቿን ተቀብለው እያሳደጉላት በመሆኑ ነው። ከዚህ ተነስታም ወጣት ሴቶች በተለይም እንደ እሷ ያሉና ብርሃናቸውን ያጡ በእንዲህ ዓይነቱ ግፊት ወደ ትዳር እንዳይገቡ ትመክራለች። ድርጅቱ ለየትነበርሽ የሚያደርግላት የገንዘብ ድጋፍ ለልጆቿ ሲል ነበርና ልጆቹን ለባለቤቷ ቤተሰቦች ስትሰጥ ድጋፉ ቆሟል። አሁን ራሷን የምታስተዳድረው ባኮ የዓይነስውራን ትምህርት ቤት በሚቆርጥላት 800 ብር ብቻ ነው። የተከራየችው ቤት ክፍያ ደግሞ 1ሺህ 500 ብር ነው። በዘንድሮ ዓመት ያለውን የቤት ኪራይ ንረትና የኑሮ ውድነት ያስተዋለው ትምህርት ቤት የተወሰነ ወራት የቤት ኪራይ ባይከፍልላት ኖሮ እስከ አሁን ያለውን ትምህርታዋን መቀጠል ትቸገር እንደነበርም ትናገራለች።
ወይዘሮ የትነበርሽ እንደምትለው አሁንም ቢሆን በቤት ኪራይም ሆነ በሁለት ህፃናት ልጆቿ ምክንያት ትምህርት ልታቋርጥበት የምትችልበት ሁኔታ ፈፅሞ አይኖርም ማለት አይቻልም። ምንም እንኳን የትነበርሽ ትዳር ውስጥ በመግባቷና ልጆች በመውለዷ ብዙ መከራና ስቃይ ደርሶባታል። ትምህርቷን ባሰበችው ጊዜ አጠናቃ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያደረገችውን ጥረት አደናቅፎባታል። በመሆኑም ሌሎች ዓይናማዎችም ሆኑ ዓይነስውር ወጣቶች ጥንቃቄ መውሰድ ይገባችኋልና ከየትነበርሽ የሕይወት ውጣ ውረድ ትምህርት ውሰዱ በማለት ጽሑፋችንን ደመደምን!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 9/2014