የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የፕሬዚዳንት ምርጫ በየአራት አመቱ በተካሄደ ቁጥር ውዝግቦች መነሳታቸው የተለመደ ነው። የእነዚህ ውዝግቦች መንስኤም በአብዛኛው ግልጽ ያልሆኑ ወይም ለተለያዩ ትርጉሞች የተጋለጡ የምርጫ ህጎች እንዲሁም ከፊፋና ከካፋ የምርጫ ህግና ደንቦች ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ የተለያዩ ውዝግቦች የሚነሱበትና በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ተደርጎ በብዙ አጋጣሚዎች ለትችት ሲጋለጥ ይታያል።
የስራ ዘመኑን በማገባደድ ላይ የሚገኘው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፌዴሬሽኑን መተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል ከፊፋ አንድ ባለሙያ ተመድቦለት ከአንድ አመት በላይ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፣ በትናንትናው እለትም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የተለያዩ ረቂቅ ደንቦች ላይ ውሳኔ እንዲተላለፍ አድርጓል።
ባለፈው መጋቢት እንደሚደረግ ፕሮግራም ተይዞለት የነበረው ይህ ጉባኤ ከታቀደለት ጊዜ ለሁለት ወራት ያህል ዘግይቶ ሲካሄድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሯል። አቶ ኢሳያስም አስቸኳይ ጉባኤውን በመጥራት የመተዳደሪያና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ ህጎች ላይ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ የተወሰነው ዘወትር የሚነሱ ውዝግቦችን ከወዲሁ እንዳይነሱ ፈር ለማስያዝ ታስቦ እንጂ ከጀርባው ሌላ አላማ እንደሌለው በንግግራቸው አብራርተዋል። ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በክብር እንግድነት የኢፌዴሪ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጀልሳ መርዳሳ ተገኝተው በፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ቢስተካከሉ ወይም ቢሻሻሉ ያሉዋቸው ነጥቦች ላይ ሀሳብ የሰጡ ሲሆን፤ በመቀጠልም የፌዴሬሽኑ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ አመራር እና ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
በዚህም ረፋድ ላይ የጉባኤው የመጀመሪያ አጀንዳ የነበረው የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ አመራር ረቂቅ ደንብ በሙሉ ድምፅ ጸድቋል። በቀጣይ ረጅም ጊዜ በፈጀ ሂደት የተሻሻለው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ከብዙ ሂደት በኋላ በከፊል እንዲፀድቅ ተደርጓል።
በተለይ ብዙ ሲያከራክር የዋለው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምፅ እና ውክልና ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ በ92 አባላት ተቃውሞ ከረቂቁ ለጊዜው እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን፤ የተቀሩት የረቂቅ ደንቡ ክፍሎች ግን በ103 አባላት ድጋፍ በአብላጫ ድምፅ ፀድቀዋል።
ከስራ አስፈጻሚና የፕሬዚዳንት ምርጫ ጋር በተያያዘ የተሻሻለው ረቂቅ ደንብ በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅ የነበረ ነው። በተለይም ከሶስት አመት በፊት በአፋር ሰመራ ተካሂዶ በነበረው የስራ አስፈጻሚና ፕሬዚዳንት ምርጫ ወቅት ከእጩዎች ጋር በተያያዘ የነበሩ የህግ ክፍተቶችና ጠንካራ ውዝግቦች ኋላ ላይ ባይረግቡ ኢትዮጵያን በፊፋ እስከማሳገድ ሊደርሱ እንደሚችሉ ይታወሳል። በወቅቱ አንድ ግለሰብ ከአንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ለቆ ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መወዳደር አይችልም ይችላል የሚል ውዝግብ አገራዊ አጀንዳ ሆኖ ብዙዎችን እስከማሟገት እንደደረሰ አይዘነጋም።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ትናንት ተሻሽሎ የቀረበው
የፌዴሬሽኑ ረቂቅ የምርጫ ህግና ደንብ ላይ አንድ ግለሰብ ከዚህ በፊት ሌላ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ውስጥ በስራ አስፈጻሚነትም ይሁን በፕሬዚዳንትነት አገልግሎ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ እጩ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዳይቀርብ ይከለክላል። ይህ ጉዳይ ያለፈው ምርጫ አይነት ውዝግቦች በቀጣይ እንዳይደገሙ ያደርጋል ተብሎ ቢታመንበትም ትናንት ከአንዳንድ የጉባኤው አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል። ይህም በሌላ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ውስጥ ስራ አስፈጻሚ የነበረ ወይም እያገለገለ ያለ ግለሰብ አቅምና የስፖርቱ ፍቅር ኖሮት ወደ እግር ኳስ መጥቶ ለማገልገል ቢፈልግ ስፖርቱን እንዳይጠቅም ያግደዋል የሚል ነው። ያም ሆኖ በአብላጫ ድምጽ ከጸደቁ ረቂቅ ደንቦች አንዱ ይሄንኑ ጉዳይ የሚዳስሰው ሆኗል።
በመጨረሻም ጉባኤው ከጥቂት ወራት በኋላ ለሚካሄደው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚና የፕሬዚዳንት ምርጫ አስፈጻሚ እንዲሁም ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችን መርጦ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት አቶ ሞላ ሀይሉ፣ወይዘሮ ረሂማ አወል፣ አቶ መንግስቱ መሐሩ፣አቶ በለጠ ዘውዴና አቶ ኢሳያስ ድንድር የምርጫ አስፈጻሚ ሆነው ተመርጠዋል። አቶ ተስፋዬ ዘውዴ፣አቶ አንበሳው እንየውና አቶ ብርሃኑ ከበደ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በመሆን በቀጣዩ ምርጫ እንዲያገለግሉ ጠቅላላ ጉባኤው ይሁንታ ሰጥቷቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም