አካል ጉዳተኛነት ልክ እንደ አንድ ሁለንተናዊ ጉድለት ተደርጎ ሲታይ ስለ መኖሩ የጋራ ስምምነት አለ ማለት ይቻላል። አዎ፣ አንድ ሰው “አካል ጉዳተኛ ነው” ከተባለ ሁሉም ነገር የሌለው ያህል ሲቆጠር ነበር። “ነበር” እንበል እንጂ አስተሳሰቡ በአንዳንድ ክፍሎች ዘንድ አሁንም አለና “አሁን የለም” እያልን እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል።
አካል ጉዳተኛነት ደዌ አይደለም። አካል ጉዳተኛነት በግል ከላይ የተሰጠ “እድል” አይደለም። አካል ጉዳተኛነት ፈልገው የሚያገኙት ጉዳይ አይደለም። አካል ጉዳተኛነት ፆታን፣ ሀይማኖትን . . . መሰረት ያደረገ አድሏዊ አይደለም። አካል ጉዳተኛነት ድንገተኛ ክስተት፤ ያልታሰበ አደጋ፤ ያልተጠበቀ እንቅስቃሴ ሁሉ . . . ሊያመጣው የሚችል፤ ማንኛችንም አካል ጉዳተኛ ላለመሆናቸን ዋስትና የማንወስድበት የጤና እክል ነው። በመሆኑም፣ የምናስበውን ያህል፣ ከምንም የማያግድ ምንም ማለት ሲሆን፤ ለዚህም የዛሬዎቹ ተሸላሚ አካል ጉዳተኞች የማሪዎች ማረጋገጫዎቻችን ናቸው።
ከዚሁ ጋር አያይዘንም፣ ባለፈው ጥር ወር የብሔራዊ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ቡድን አባላትን ለመሸኘትና (ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምታስተናግደው 11ኛው የአፍሪካ ዊልቼር ቅርጫት ኳስ ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድኗ ሁለቱም ፆታ የሚገኝበት) የመልካም እድል ምኞታቸውን ለመግለጽ የተገኙት ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ “አካል ጉዳተኛነት ከምንም ነገር አያገልም።” ማለታቸውንም ልናስታውስ እንችላለን።
ሰሞኑን የአምራች አካል ጉዳተኞችን ምርት በተመለከተ የገበያ እድልና ትስስር መፍጠርን ታሳቢ ባደረገ መድረክ ላይ በመገኘት “ውጫዊ የአካል ጉዳት ውስጣዊ የጥንካሬ መንፈስን አይገታም።” በማለት የተናገሩትን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ገነት ቅጣውንም ከዚሁ ጋር አያይዞ መልእክታቸውን መረዳት ይቻላል።
ባለፈው ሀሙስ እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ 6 ኪሎ በሚገኘው ቢሮው (ፍቅር ፕላዛ ህንፃ) አዳራሽ አንድ በአይነቱ ለየት ያለ፤ ደማቅና ተአምር የሚያሰኝ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። ከዚህ ውስጥ “ተአምር” የሚለውን የምናብራራው ሆኖ፣ ፕሮግራሙ በከተማው በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ላመጡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የእውቅናና ማበረታቻ ሽልማት የተሰጠበት ነበር።
በፕሮግራሙ ላይ ይታደሙ ዘንድ የበርካታ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች ተጋብዘው የተገኙ ሲሆን (የሚጠበቁት ሳይቀሩ አለመገኘታቸው እንዳለ ሆኖ)፤ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የተሸላሚ ቤተሰቦች በስፍራው በመታደም ለፕሮግራሙ ልዩ ድምቀትን ቸረውታል።
በተለይም ፕሮግራሙን “ተአምር” እንለው ዘንድ ያስገደደን በእስከ ዛሬዎቹ የተለያዩ የሽልማት ስነስርአቶች ብዙም ልብ ባልተባለ ሁኔታ የከፍተኛ ውጤት ባለቤት የሆኑ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ማእከልና ተሸላሚ ባደረገ መልኩ መከናወኑ ብዙዎቻችንን ያስደመመ ሲሆን፣ አንዳንድ የተሸላሚና የተሸላሚ ቤተሰቦች ንግግሮች የታዳሚን እምባ እስከ ማጫር (ለምሳሌ የተሸላሚ የአብስራ ሺፈራው እና የእናቷ የወይዘሮ ዘነበች አሊ) ድረስ ወደ ውስጥ የዘለቁ ነበሩና አጠቃላይ ሂደቱን “ተአምር” ስንል ያለ ምክንያት አልነበረም ለማለት ነው። ወደ ቢሮው አጠቃላይ መረጃ እንሂድ። (በቅርቡ የአብስራ ሺፈራውንና የእናቷ የወይዘሮ ዘነበች አሊን የተመለከተ ዝግጅት ይኖረናል።)
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ። እንደ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ “አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል መገመት እምብዛም አዳጋች አይሆንም።”
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ከላይ በጠቀስነው መድረክ ላይ ካሰራጨው መረጃ መረዳት እንደ ተቻለው፤ በከተማው የእግር ጉዳት ያለባቸው 5ሺህ 287 (39.7%)፣ ተደራራቢ የአካል ጉዳት ያለባቸው 2ሺህ 868 (21.5%)፣ ዐይነስውርነት 2ሺህ 389 (17.9%)፣ የአእምሮ እድገት ውስንነት 1ሺህ 040 (7.8%)፣ የመስማት ችግር ያለባቸው 777 (5.8%)፣ የእጅ ጉዳት 726 (5.4%)፣ እና የኦቲዝም ችግር ያለባቸው 220 (1.6%) ናቸው።
ከላይ ያየነው በ”የጉዳት አይነት” ሲሆን፣ በጉዳት መንስኤ ስንመለከተው ደግሞ 4ሺህ 173 (35.5%) በበሽታ፣ 3ሺህ 866 (32.5%) በተፈጥሮ፣ 2ሺህ 660 (22.5%) በአደጋ፣ 986 (8.3%) በጦርነት ሆኖ እናገኘዋለን።
የቢሮው መረጃ የአካል ጉዳተኛነትን ከትምህርት ደረጃ አኳያም ያሰፈረ ሲሆን፤ ያልተማሩ 6632 (44%)፣ ከ1ኛ – 4ኛ ክፍል የተማሩ 4817 (32.2%)፣ ከ9ኛ – 12ኛ ክፍል የተማሩ 2089 (14%)፣ ዲፕሎማ እና ሰርተፊኬት ያላቸው 448 (2.9%)፤ እንዲሁም የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው 355 (2.3%) ሆነው እገኛቸዋለን።
ከዚህ አምድና ገፅ አኳያ፣ ከመረጃው ልብ ልንል የሚገባን መሰረታዊ ጉዳይ ቢኖር 44% ጭራሽ ያልተማሩ መሆናቸውን ሲሆን፤ ይህም ለአካል ጉዳተኞች የትምህርት ተደራሽነትንና በመንግስት ሰነዶች ላይ የ”አካቶ ትግበራ” የሚባለውን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው መሆኑን ነው።
ይኸው መረጃ እንዳስቀመጠው አካል ጉዳተኞቹ መስራት የሚችሉበት እድሜ ላይ ከሚገኙት 13ሺህ 149 መካከል 1ሺህ 406 የሆኑት ስራ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአንፃሩ 11ሺህ 568 የሆኑት ምንም አይነት ስራም ሆነ ገቢ የሌላቸው ናቸው።
ከላይ ያየነው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአካል ጉዳተኞች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት አኳያ ገና ብዙ የሚቀር መሆኑን ነው። በትምህርቱም ዘርፍ እንደዛው።
ይህንን የአካል ጉዳተኞችን የተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ክፍተት ይሞላል ተብሎ የተቋቋመው የከተማው የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ይህንን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን ፕሮግራም በማዘጋጀት ሞዴል ተማሪዎቹን ለዚህ አይነቱ ሽልማት ማብቃቱ የሚያስመሰግነው ሲሆን፤ ሌሎችም ይህንን አርአያ ይከተላሉ የሚል ከግምት የዘለለ እምነት አለና እንደሚያደርጉት ይጠበቃል። ወደ እለቱ ፕሮግራም በመመለስ “አካል ጉዳተኛነት ማለት ምንም ማለት ሲሆን” በማለት የቀነበብነውን ርእስችንን እናብራራ።
እንደምናውቀውም ሆነ በፕሮግራሙ ላይ እንደተነሳው አካል ጉዳተኛነትን ካለ መቻል ጋር አብሮ የማየት፤ ወይም፣ አንድ አካል ጉዳተኛ አካል ጉዳተኛ ካልሆነው ጋር በንፅፅር ሲታይ ጤነኛው ከአካል ጉዳተኛው እንደ’ሚበልጥ፤ ወይም አካል ጉዳተኛው ከጤነኛው እንደ’ሚያንስ አድርጎ የመመልከት ስር የሰደደ አተያይ ነበር። በእውቅናና ሽልማት ፕሮግራሙ ላይ የታየው ግን እውነታው ከዚህ፣ ስር ከሰደደው አስተሳሰብም ሆነ አተያይ የተለየ ብቻ ሳይሆን ተቃራኒው ነው። የ”አይችሉም” ተቃራኒ “ይችላሉ” (ችለው ብቻ ሳይሆን ተሽለው ሁሉ መገኘታቸው) እስከ ሆነ ድረስ ማለታችን ነው።
ቢሮው በአጠቃላይ ከ170ሺህ ብር በላይ የገንዘብና በአይነት የሚያወጣ ሽልማት (የኪስ ገንዘብና የቁሳቁስ – ብርድልብስ፣ አንሶላ፣ ፎጣ፣ ቦርሳ ….) የሰጠ ሲሆን፤ ትልቁ 20ሺህ ብር፤ ትንሹ 18ሺህ ብር፤ አላማው አድናቆትና ማበረታታት መሆኑ አያሻማም። በእለቱ የነበረው እውነታም ያሳይ የነበረው ይህንኑ ሲሆን፤ እንዳበረታታቸውም ወደ መድረክ እየመጡ በአስተርጓሚዎቻቸው አማካኝነት ከገለፁት ሀሳብና ስሜታቸው መገንዘብ ይቻላል።
በእለቱ ፕሮግራሙን እንዲታደሙ በእንግድነት ከተጠሩት መካከል በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የነበሩ ሲሆን፤ እነሱም በተለያዩ ተቋማት በተለያዩ የሀላፊነት ደረጃዎች ላይ ያሉና ከፍተኛ ሀላፊነትን እየተወጡ የሚገኙ፤ አካል ጉዳተኛነት ምን ማለት እንደ ሆነ፣ የህብረተሰቡ አመለካከት ያለበትን ሁኔታና ደረጃ ወዘተ እያነሱ ሀሳባቸውን ያስተላለፉ፤ ወጥተው የወረዱበትን ዳገትና ቁልቁለት የተናገሩ፣ ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን፤ የእለቱ ተሸላሚ አካል ጉዳተኞችም አሁን ካሳዩት ጥንካሬያቸው የበለጠ ጠንካራ እየሆኑ መሄድ እንዳለባቸውና አበክረው ያሳሰቡበት፤ ከሁሉም በላይ ትምህርትና ትምህርትን አጥብቆ የመከታተል አስፈላጊነት ላይ ጠንከር ያለ መልእክት ያስተላለፉበት ሁኔታም ነበር።
ዓለም ዓቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በኢትዮጵያ ለ29ኛ ጊዜ ሲከበር፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ “የአካል ጉዳትና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከግለሰብና ህብረተሰብ ባለፈ የአንድ አገርና የዓለም ህዝብ ባጠቃላይም የመላው የሰው ልጆች ሁሉ የጋራ ጉዳይ ሊሆን ይገባል” እንዳሉት ሁሉ አሁንም የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን በተመለከ ጉዳዩ የጋራ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ቀደም ሲል የጠቀስነው “አከቶ ትግበራ” የሚለውም ከነቢብ ባለፈ ተግባር ላይ ሊውል፤ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ሊያደርግ የግድ ይለዋል እንላለን። ጉዳዩ ከመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋርም የሚያያዝ መሆኑን ማሰብ ይገባል ስንልም በአክብሮት ነው።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ብዙ ጊዜ ሲባል እንደሚሰማውና እንደምናምንበትም “ማንም ሰው አካል ጉዳተኛ ላለመሆን ምንም ዓይነት ዋስትና የለውም፤ አካል ጉዳተኛነት በማንኛውም ሁኔታ፣ ጊዜና ስፍራ እንዲሁም በማንኛውም ሰው ላይ ከጽንሰት እስከ ህልፈት ሊደርስ የሚችል አንዱ የህይወት አጋጣሚ ነው።” በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን ሁኔታ ስናስብ እራሳችንንም እያሰብን መሆን አለበት። ጉዳዩ “የጋራ ነው” ስንልም፤ “አካቶ ትግበራ” ሲባልም ይሄንን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆኑን በማሰብ ነው። (ሌላውን እንኳን ብንተወው፣ ሳንወድ በግድ የገባንበት የእርስ በርስ ጦርነት ስንትና ስንት ወገኖቻችንን ለአካል ጉዳተኛነት እንደሚዳርግ አስበነዋል?)
እንዲሁም፣ “ውጤታማ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ማበረታታት አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብ ለመለወጥ ያስችላል።” በሚል መነሻ ሀሳብ የሽልማት ስነስርአት ያካሄደው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ይህንን ለየት ያለና ብዙም ያልተለመደ (በትምህርቱ ዘርፍ ማለት ነው) ተግባር በማከናወኑ ሊመሰገን፤ አካል ጉዳተኛነት ማለት ምንም ማለት እንዳልሆነ አሳይቶናልና “አበጀህ” ሊባል ይገባዋል።
ባመጨረሻም፣ ተሸላሚ ተማሪዎቹ (በ2013 አ.ም ማትሪክ የተፈተኑ) ከጥቂት ጊዜያት በኋሏ ወደ እየተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎቻቸው ይሄዳሉ። በትምህርት ገበታቸውም ላይ ይቀመጣሉ። እኛም ከወዲሁ መልካም የትምህርት ዘመን እያልን፣ ከፈጣሪ ጋር ልክ እንዳሁኑ ሁሉ ከየዩኒቨርሲቲዎቻቸውም በከፍተኛ ማእረግ ተመርቀው እንደገና እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን። መልካም እድል!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም