የዩኒቨርሲቲ የስቴም ማዕከል አስተዋጽኦ

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ምህንድስና ትምህርት መስኮች የማፍራት ግብ ሰንቆ ነው ወደ ሥራ የገባው። ዩኒቨርሲቲው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍ የሚያደርጉ ምርጥ ባለሙያዎችን ማፍራትንም ተቀዳሚ ተልዕኮው አድርጓል። ‹‹ዩኒቨርሲቲ ለኢንዱስትሪ›› የሚል መለያ መርህም አንግቧል።

ዩኒቨርሲቲው ይሄን መሠረት አድርጎ ወደ ሥራ ከገባበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሎም በአህጉረ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ምሩቃንን እያፈራ ይገኛል። አሁን ላይ ከትምህርታቸው በተጨማሪ ስብዕናቸው የተገነባ እና የልዩ ልዩ ክህሎት ባለቤት የሆኑ ዜጎች አብቅቶ ማውጣት ችሏል። በአሁኑ ወቅት እነዚህ ዜጎች ጎግል እና ብሉምበርግ ድርጅቶች ላይ ተቀጥረው እስከ መሥራት የደረሱ ስለመሆናቸውም ከዩኒቨርሲቲው የወጣው መረጃ ያመለክታል። መረጃው ዩኒቨርሲቲው የሮቦክስ ሮቦቲክስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል ባለቤት እስከ መሆን የደረሱ ተማሪዎች ስለማፍራቱም ያመለክታል።

ዩኒቨርሲቲው ከዚሁ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን የሳይንስና ቴክኖሎጂውን ደርዝ ሳይለቅ የትምህርትን እና ምርምር ሥራዎችን ከመሥራት ባሻገር ለአካባቢው ኅብረተሰብ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ንቁ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። አስተዋጽውን በማድረግ ማኅበረሰቡን በማገልገል ላይ የሚገኘው በስቴም የትምህርት መርሃ ግብር ነው። ስቴም በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አሳታፊነት ዳይሬክቶሬት ስር በተቋቋመው የሳይንስ ባሕል ልማት ማዕከል ውስጥ ነው የሚገኘው።

በዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ባሕል ልማት ማዕከል አስተባባሪ ናትናኤል ንጉሴ (ዶ/ር) በዚህም 55 በመቶ የሴት ተማሪዎች ተዋጽኦ ጨምሮ በአካባቢው ያሉ 50 የመንግሥትና 50 የግል ትምህርት ቤቶች የማኅበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ የሥልጠና ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ያነሳሉ። እስካሁን በአካባቢው የሚገኙ ከ25 በላይ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶችን የሥልጠናው ተደራሽ አድርጓል። በትምህርት ቤቶቹ የሚያስተምሩ መምህራንም የሥልጠና ዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል።

አስተባባሪው እንደሚናገሩት የስቴም ማዕከሉ (STEM Center) ወደ እዚህ ተግባር የገባው ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ነው። ከምሥረታው ጀምሮ በአካባቢው ለሚገኙ ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እና ድጋፎች እየሰጠ ይገኛል። ሥልጠናው የተማሪዎችን ችግር የመፍታት ክህሎት ለማሳደግ እንዲሁም የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱ በማስቻል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። የሳይንስ ሙዚየም ተማሪዎች እንዲጎበኙት በማድረግ ለሳይንስ ትምህርት ያላቸውን ግንዛቤም ያሳድጋል። የስቴም የትምህርት መርሃ ግብር ስንል በአጭሩ በትምህርቱ ሳይንስን፣ ቴክኖሎጂን፣ ኢንጂነሪንግን እና የሂሳብ ትምህርቶች አቀናጅቶ ማስተማር የሚያስችል ነው። ተማሪዎች ችግሮችን የመፍታት ክህሎታችውን፣ የፈጠራ ክህሎታቸውን እና ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተባብረው የመሥራት ክህሎታችውን በማሳደግ፤ ምክንያታዊ አስተሳሰብን እንዲያጎለብቱ ያግዛልም ይላሉ።

ሥልጠናውን ለማግኘት ወሳኙ የተማሪዎች ፍላጎት መሆኑንም ያነሳሉ። ተማሪዎቹ በማዕከሉ መማር ሲፈልጉ ሪፖርት ካርድ (ውጤት)፣ ከሚማሩበት ትምህርት ቤት የተሰጠ የድጋፍ ደብዳቤ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ እና የወላጅ (አሳዳጊ) ፈቃድ እንደሚጠየቁም ይጠቅሳሉ። ‹‹ዩኒቨርሲቲው ትምህርቱን ያለ ክፍያ ነው የሚያስተምረው›› የሚሉት አስተባባሪው ለተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያቀርብም ይናገራሉ። በስቴም ትምህርት መርሃ ግብሩ አላማና ጥቅም ገለፃ ያደርጋል። የተማሪዎቹ የመረዳት አቅምም መሠረት በማድረግም፦

በደረጃ አንድ- መሠረታዊ የሳይንስ ኮርሶች (ባዮሎጂ፣ ኬሚስትሪ፣ ሂሳብ እና ፊዚክስ) (Basic Science Cours­es (Biology, Chemistry, Mathematics and Phys­ics)፤ በደረጃ ሁለት- የቴክኖሎጂ እና የምህንድስና ኮርሶች (Technology and Engineering Courses) – በደረጃ ሦስት STEM ፈጠራ ፕሮጀክት (STEM Innovation Project) አስተምሮ ያሰለጥናል።

በእያንዳንዱ ደረጃም ተማሪዎችን ለሁለት ወር ቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም ደረጃ ሦስት ለደረሱ የስቴም ተማሪዎች መሥራት ለሚፈልጉት ፕሮጀክቶች ግብዓትና ቁሳቁሶችን ያሟላል። በ2017 ዩኒቨርሲቲው ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ለ34 ፕሮጀክቶች ድጋፍ አድርጓል። ማዕከሉ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ በየዓመቱ ተማሪዎችን የመቀበል አቅሙን በማሳደግ እያስተምር ይገኛል። በዚህም መሠረት በ2016 ዓ.ም ከእቅድ በላይ ለ1ሺ51 ተማሪዎች የትምህርት እድሉን ሰጥቶ አስተምሯል። በዚህም ዓመት እስከ ሚያዝያ ወር ደረስ ለ1 ሺ 96 ተማሪዎች እድሉን ሰጥቶ አያስተማረ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው የስቴም ማዕከል በአካባቢው ላሉ ትምህርት ቤቶች መምህራን የስቴም ትምህርት አስጣጥ ሥልጠና የሚሰጥ ስለመሆኑ ያነሳሉ። በ2016 ዓ.ም ለ150 በአካባቢው ላሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን እንዲሁም በ2017 ዓ.ም ለ75 በአካባቢው ላሉ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መምህራን ፤ ከስቴም ሲነርጅ (STEM Synergy) ጋር በመተባበር ሥልጠና ስለመስጠቱም ያስታውሳሉ። እንደሳቸው ገለፃ ስቴም ሲነርጂ (STEM Synergy) ዩኒቨርሲቲው የስቴም ትምህርትን ለማሳደግ አብሯቸው ከሚሠራቸው ባለ ድርሻ አካላት አንዱ ነው። ከዩኒቨርሲቲው ጋርም በጋራ በመሆን ለተለያየ አገልግሎት የሚዊሉ የሮቦትክስ ኪቶች እና ላብራቶሪዎችን ለተማሪዎች ያደራጃል። ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላትና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከአራት ጊዜ በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ “የሳይንስ እና የምህንድስና ትርኢት” በዩኒቨርሲቲው አዘጋጅቷል። በተጨማሪም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የ2024 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሮቦቲክስ ውድድር “የምድር አጋሮች” “Earth Allies,” በሚል መሪ ቃልም አዘጋጅቷል።

”የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የስቴም ማዕከል ዋናው አላማው የተማሪዎችን በአካባቢያቸው ያለውን ችግር የመፍታት ክህሎታቸውን ፣ የፈጠራ ክህሎታቸውን ማሳደግ ነው” ይላሉም አስተባባሪው ናትናኤል ንጉሴ (ዶ/ር)። በተጨማሪም ለሳይንስ ትምህርት ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ስለመሆኑም ያስረዳሉ። በዚህ የትምህርት መርሃ ግብር አልፈው በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የደረሱ ስለመኖራቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም። ለምሳሌም፦ የራሳቸውን ካምፓኒ የከፈቱ ተማሪዎች አሉ ብለውናል። ቴክፕላስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ተጥቃሽ ስለመሆኑም ነግረውናል። በተጨማሪም በ2016 ዓ.ም ትምህርት ሚኒስቴር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ሀገር አቀፍ “የሳይንስ እና የምህንድስና ትርኢት” (Science and En­gineering Fair) ላይ ማዕከሉን ወክለው ከተወዳደሩ ተማሪዎች በተወዳደሩበት ዘርፍ 1ኛ እና 3ኛ የወጡ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የስቴም ማዕከልም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁለተኛ ሆኗል ነው የሚሉት። በ2017 ዓ.ም Science and Engineering Fair (የሳይንስ እና ምህንድስና ትርኢት) ዩኒቨርሲቲውን በመወክል ከተወዳደሩት በ ‘Robotʾ ውድድር በሁለተኛነት ደረጃ ያሸነፈ ሲሆን የ2024 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሮቦቲክስ ውድድር “Earth Al­lies,” “የምድር አጋሮች” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ላይ የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በመወክል የተወዳደሩት የስቴም ማዕከሉ ተማሪዎች በሶስተኝነት ደረጃ አሸነፈዋል። meal mate robot (የምግብ ጓደኛ ሮቦት) እንዲሁም በዓሣ እርባታ ሮቦት ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ከተወዳደሩት ናኦል እጅጉ፤ ሰላም ደረጀ እና ካኖን ዓለማየሁ እንደሚጠቀሱም አስተባባሪው ናትናኤል ንጉሴ (ዶ/ር) አብራርተውልናል።

ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ተወዳድረው በሁለተኛ ደረጃ ያሸነፉ ተማሪዎች ከአካባቢው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተመልምለው እና ዩኒቨርሲቲው የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልተው በመግባት የሚስፈልጋቸውን የግብዓት አቅርቦት አሟልቶ ያሰለጠናቸው ናቸው። በቅርቡም የፈጠራ ሥራቸውንም ለሽያጭ እንዲያቀርቡና እንዲያስተዋውቁ ያስቻላቸው አውደ ርዕይ አዘጋጅቶላቸው እንደነበርና በዚሁ ላይ እንደተሳተፉም ነግረውናል ተማሪዎቹ።

‹‹ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂው የፈጠራ ሥራ መሳተፋቸው ሴቶች ለሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ያልተፈጠሩ በማድረግ የሚያገለውን አንዳንድ የተሳሳተ አስተሳሰብ ይሰብራል›› የምትለው በዩኒቨርሲቲው የምትማረው ተማሪ አፍራህ ሁሴን ናት። አፍራ ሥልጠናው ለመደበኛ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራ ችሎታቸውን እንዲያጎለብቱ በብርቱ እንደሚያግዝ ትናገራለች። እንደምትለው እሷ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን በወሰደችው ሥልጠና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ስትሬቸር ሮቦት ሠርታለች። ሮቦቱ የአካል ጉዳተኞችን ምቾት የሚጠብቅ ነው። የመቀመጫቸው ሚዛን በመጠበቅ በምቾት ደረጃ መውጣት መውረድ ያስችላቸዋል።

ሌላው ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው ሥልጠና ያለፉት በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኘው የገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር አሰፋ ኤባ ናቸው። መምህሩ ዩኒቨርሲቲው በሰጣቸው ሦስት ደረጃ ያለው ተከታታይ ሥልጠና በመታገዝ ቢንቢዎች የሚያጠፋ ማሽን መሥራታቸውንም ነግረውናል። ማሽኑ በሚያመነጨው ካርቦንዳይኦክሳይድ ቢንቢዎቹ እንዲሳቡ ያደርግል። ቢንቢዎቹ ተስበው በመግባት 330 ዲሲ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ሲያርፉም ከመቅጽበት ወደ ጭስነት በመቀየር ያጠፋቸዋል። ሕፃናትም ሆኑ አዋቂዎች እንዳይነኩት ቢንቢ መግደያው ከፍ ብሎ ነው የሚቀመጠው። በተጨማሪም አዋቂም ሰው ሆነ ሕፃን ቢነካው እንኳን በኤሌክትሪክ እንዳይያያዝ ከፊትም ከኋላም መከላከያ ሽቦ ተገጥሞለታል። ሽቦው ቢንቢዎችን ብቻ የሚያሳልፍ እና በቢንቢዎች መጠን ልክ የተሠራ ነው።

እንደነገሩን የሠሩት ከወዳደቁ ፓውዛ ቦርድ 230፤ ኤሲ ቦርዶች ወደ 110 በመቀየር በፊዚክስ ቲዮሪ ገጣጥመዋቸው ነው። በባህሪያቸው ትንኞች ይሄኛውን ዓይነት መምህሩ ከፍሎረሰንት የሠሩትን አልትራ ቫዮሌት የሚባለውን የብርሃን ዓይነት እንደሚወዱና እንደሚመርጡትም ያነሳሉ። ማታ መብራት ሲጠፋ ወደ ሰው ከመሄድ ይልቅ ተሯሩጠው ወደዚህ ብርሃን ይሄዳሉም ይላሉ። መምህሩ እንዲህ ዓይነት በመምህሩም ሆነ በተማሪዎች የሚሠሩ የፈጠራ ሥራዎች በትምህርት ጥራት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንደሚያመጡም ይናገራሉ። ስቴም ለፈጠራ ሥራ መጎልበት ለትምህርት ሥራ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን ያነሳሉ።

የዩኒቨርሲቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ያሬድ በቃሉ ‹‹በሰለጠነ ዓለም ሁሉም ዜጋ የፈጠራ ሥራ መሥራት አለበት በተለይ ትምህርት ቤቶች ከታች ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ በዚሁ ዙሪያ ተማሪዎቻቸውን ማብቃት ይገባቸዋል›› ሲሉ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። ትምህርት እንዲህ ባለው የተግባር ፈጠራ በሚደገፍበት ጊዜ ውጤታማ ይሆናል፤ ጥራቱም ይጠበቃል፤ መንግሥት ለፈጠራ ሥራ ትኩረት ሰጥቶ ከታች ጀምሮ በብርቱ እየሠራ የሚገኘውም ለዚሁ ፋይዳ ነውም ብለዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሀገራችን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸው በዚህ መልኩ እንዲሠሩ ከተቋቋሙ ሁለት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አንዱ ስለመሆኑም አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲው ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ምህንድስ ትምህርት መስኮች እያስተማረ ስለመገኘቱም ነግረውናል። ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቃንን ለማፍራት ይረዳው ዘንድም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናቸውን ወስደው የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎችን በመፈተን ሲቀበል መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኬሚስትሪ ትምህርት ባለሙያ አቶ ጌትነት ጌታቸው እንደሚሉት ተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ሥራ እየሠሩ ለራሳቸውም ለማኅበረሰቡ የሚያቀርቡበት የፈጠራ ሥራቸውንም በየዓመቱ እያሳደጉ እውቅና እና ሽልማት የሚያገኙበት ነው። እንደ ትምህርት ቢሮ በአዲስ አበባ ደረጃ ተማሪዎች በየዓመቱ በሠሩት የፈጠራ ሥራ ይወዳደራሉ። ቢሮው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ለወጡ አሸናፊ ተማሪዎች የእውቅና ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን፤ ዘንድሮም እንዲህ ዓይነቱ ውድድር በሚያዝያ ወር መጨረሻ ሳምንት አካባቢ የተደረገ ሲሆን ውድድሩ ከባለፈው ዓመት በተሻለ ሁኔታ ቀጥታ ተግባር ላይ በመዋል የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የፈጠራ ሥራ ውጤቶች የታዩበት ነበር።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You