ሃገራችን የምትገኝበትን እጅግ ውጥንቅጥ ፣ ውስብስብና ጥልፍልፍ ነባራዊ ሁኔታን መልሼ መላልሼ ባንሰላሰልሁ ፤ ታጥቦ ጭቃ ስለሆነው ሁለነገራችን በቆዘምሁ ፤ መውጫ መንገዳችን ከእርዮተ አለምና ከሥርዓት በላይ መሆኑን በታዘብሁ ፤ እንደ ዜጋ ከዚህ ቀለበት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰብሮ ለመውጣት የጋራ ጉልበት እየከዳን እንደሆነ ሲሰማኝ ፤ ለችግሮቻችን መፍትሔ ይሆናሉ ብለን ያሰብናቸው ነገሮች ሁሉ ባልተጠበቀና ባልተገመተ ሁኔታ አባባሽና አቀጣጣይ ቤንዚን ሆነው ሳገኛቸው ፤ ከርቀት የሚታየኝ ተስፋ ስደርስበት የሀሩር ሚራዥ እየሆነ ግራ ሲገባኝ ፤ የሔድንባቸውም ሆኑ የመጣንባቸው መንገዶች ከዋሻው አውጥተው ብርሀን ማሳየት ሲሳናቸው ፤ ያልሔድንባቸውንም ሆነ ያልመጣንባቸው መንገዶች አሳሽና ተቅበዝባዥ ሁኜ አረፍሁት።
ጥንታዊውን የሀገራችንን ታሪክ አቆይተነው ፤ ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ወዲህ ማለትም አፄ ቴዎድሮስ ከነገሱበት ዘመን ወዲህ እስከ ዛሬ ያለውን መለስ ብለን ገለጥ ገለጥ ብናደርግ እንኳ፤ ለነጻነታችን ፣ ለሉዓላዊነታችን ፣ ለአንድነታችን ፣ ለግዛት አንድነታችን፣ ለእኩልነታችን ፣ ለፍትሕ ፣ ለዴሞክራሲ ፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታችን ፣ ለሰላም ፣ ለፍቅር ፣ ለይቅር ባይነት ፣ ለመደማመጥ ፣ ለመነጋገር ፣ ለመቀባበል ፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት ፣ ከመሀይምነትና ከድንቁርና፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ከሴራና ከደባ ፣ ከአቅላይነት ለመላቀቅ ፤ ለእድገት ፣ ለብልጽግና ፣ ወዘተረፈ ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ደም ብናፈስ ፣ አጥንት ብንከሰክስ፣ አካል ብናጎድል ፣ ሺህዎችን ብናጉር ፣ ብናሰቃይና ብናሳድድ ፤ ነጭ ላብ በጀርባችን ብናቆረቁር ፣ ከዚህም ከዚያም የተቀራረመ እውቀት ብናፈስ ፣ ጉልበት ብናባክንም ከሁለንተናዊ ቀውስ አዙሪት በማያዳግም ሁኔታ ሰብረን መውጣት አልቻልንም ። ነገረ ሥራችን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ እንደሆነ ቀጥሏል ።
በአድዋ ፣ በማይጨው ፣ በካራማራ ፣ በከረን ፣ በባድመ ፣ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ከአሸባሪው ሕወሓትና ከቡችሎቹ ጋር ፣ ወዘተረፈ በመቶ ሺህዎች ደማችንን አፍስሰን አጥንታችንን ከስክሰን ፤ በርካታ ቢሊዮኖችን ገፍግፈን ዛሬም ሃገረ መንግሥቱን በሁለት እግሩ ማቆም ላይ እየተውተረተርንና እየተፍገመገምን እንገኛለን ። አንዳንድ ጊዜ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ እየሄድን፤ ሌላ ጊዜ ባለንበት እየረገጥን እንገኛለን ። የፓርቲ ፖለቲካ ታሪካችን ከግማሽ ክፍለ ዘመን ቢሻገርም ዛሬም አድሮ ቃሪያዎች ነን ። ለትግል የፖለቲካ ፓርቲ ያስመሠረቱን ጥያቄዎች ዛሬም በቅጡ አልተመለሱም ። ቀይ ሽብር ፣ ነጭ ሽብር ብለን አንድ ወርቃማ ትውልድ የጨረስንበት ሕዝባዊ መንግሥት ከእነ ውስንነቱ ገና የሁለት ዓመት ጨቅላ ስለሆነ ወፌ ቆመች ! ወፌ ቆመች ! እያልነው እንገኛለን ።
የመጣ የሄደው አገዛዝ ተቋማትን በአምሳያው ጠፍጥፎ ለመሥራት ሲያፈርስ ሲሠራቸው በሁለት እግራቸው መቆም ተስኗቸው እየተንገዳገዱ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በዚህ የተነሳ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ፤ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመለስ፤ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ፤ ብሉሽ አሠራርን ማስወገድ ፤ የገነገነ ሙስናን ከስሩ መንግሎ መጣል ፤ ጠንካራ ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ መገንባት አልቻልንም ። ያን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍለን ዛሬም የምንመኘውንና የምንፈልገውን ሥርዓት ማምጣት አልቻልንም ።
በነገራችን ላይ ትላንትም ሆነ ዛሬ እያለፍንባቸው ላሉ ውድቀቶችና ቀውሶች እንደ ሕዝብም እንደ መንግሥትም ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን ። የሚገባንና ይበላቸው የሚያሰኝ አገዛዝ እንዲፈራረቅብን የሆነው ከዚህ ለተሻለ ሥርዓት ዝግጁ ስላልሆን ነው። በስንትና ስንት መስዋዕትነት ያመጣነውን ለውጥ ለሃገርና ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል ስላላበጀነው ፣ ስላልጠበቅነውና ስላልተከላከልነው በምንም ሊተመን የማይችል ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል ። የ66ቱን እና የ83ቱን ይቅርና አሁን የምንገኝበትን ለውጥ እየተከላከልነውና እየጠበቅነው አይደለም ። ለዚህ ነው ከዚህ አዙሪት በማያዳግም ሁኔታ ሰብሮ መውጣትና አዲስ ምዕራፍ መክፈት ግድ የሚለን ።
እንደ ልዑል እግዚአብሔር አንድያ ልጆቻቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አጋፔያዊ ለሆነ ፍጹም የሃገርና የሕዝብ ፍቅር አባቶችና እናቶች አሳልፈው በሰጡን አንድያዎቻቸው መስዋዕትነትና ከፍ ብሎ እንደተመለከተው እደግመዋለሁ ፤ ከጦርነት፣ ከግጭት ፣ ከልዩነት፣ ከጥላቻ ፣ ከቂም ፣ ከበቀል፣ ከጎሰኝነት ፣ ከሌብነት ፣ ከስግብግብነት ፣ ከአልጠግብ ባይነት ፣ እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል ባይነት ፣ ከአቅላይነት ፣ ከሴረኛነት፣ ከድህነት ፣ ከኋላቀርነት ፣ ከረሀብ ፣ ከእርዛት፣ ከቁሞ ቀርነትን አባዜ ፣ ከሐሰተኛ ትርክት ለፋፊነት ፣ ከተጠቂነት አባዜና ከቸነፈር ሊቤዡን ካልቻሉ፤ ኃጢያታችንና በደላችን ከተከፈለልን ዋጋ በልጦ ይሆን ብዬ ብቸገር ሊመጣጠን ይችላል ያልሁትን ከዚህ ቀደም ያልተከፈለ ዋጋና መስዋዕትነት ለጣኦቶቻችን ይዤ መጥቻለሁ። ዋጋውንም ሆነ መስዋዕትነቱን ሁላችንም ለምናመልካቸው ጣኦቶቻችን አንድ በአንድ የምንከፍለው ነው ። እሱም መሞት ነው ። አዎ መሞት ! አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደግሞ ደጋግሞ መሞት ነው የጣኦታቱ ምስ። በቤተሰብ መሞት ፣ በትምህርት ቤት መሞት፣ በአብያተ ክርስቲያናት መሞት፣ በመስጅዶች መሞት ፣ በዋርካው ጥላ መሞት፣ በመሥሪያ ቤት መሞት ፣ በፖለቲካ ፓርቲ መሞት ፣ ወዘተረፈ በመሞት ለጣኦቶታቻችን ምስ መሆን።
አዎ! ጸረ ሕዝብና ሃገር ለሆኑ ጣኦታት ያለመተባበርና ያለመገዛት ሞት ነው ምሱና መፍትሔው። ከልዑል እግዚአብሔር ፣ ከነብዩ መሐመድ ፣ ከዋቄ ፈና እና ከሌሎች አማልክት በላይ ለምናመልካቸው ጣኦታት መሞት። ካስፈለገም መሰቀል። ሞቱ አካላዊ ሞት አይደለም። ለጣኦታቱ አልገብርም ፤ መስዋዕት አላቀርብምና አልተባበርም የማለት የአስተሳሰብና የአመለካከት ሞት እንጂ። ለመሆኑ እነዚህ ጣኦቶቻችን እነማን ናቸው ብላችሁ ግራ እንዳትጋቡ ፤ ለፍለጋም ሩቅ እንዳትሔዱ ፤ ደምና ሕይወት እየገበርን ያደለብናቸው ሰርክ በእብሪትና በትዕቢት በእያንዳንዳችን አዕምሮ ጓዳ የሚጎማለሉ ጣኦታት ናቸው ። ጎሰኝነት ፣ ጥላቻ ፣ ልዩነት ፣ ቂም በቀል ፣ ሌብነት ፣ የፈጠራ ትርክት ፣ ደባና ሴራ ፣ ወዘተረፈ እና ከፍ ብሎ ከአንድም ሁለት ጊዜ ለመዘርዘር የሞከርኋቸው ናቸው ጣኦታቱ ። አዎ ለእነዚህና መሰል ጣኦታት አምልኮ መሰዊያ ላይ ላለመገኘት መወሰንና መቁረጥ ነው ሞቱ ።
ጎሰኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ግጭትን ፣ ሴራን ፣ ወዘተረፈ በቤቴ፣ በእምነት ተቋሜ ፣ በፖለቲካ ፓርቲዬ ፣ በትምህርት ቤቴ ፣ በመደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያዬ ፣ ወዘተረፈ አልተባበርም ፣ አላስተናግድም ነው ሞቱ ። እነዚህን ጣኦታትን ከአዕምሮ ጓዳችን አውጥተን መጣል፣ ማንከባለልና መስበር ነው ሞቱ ። ይሄን ስናደርግ የዚህ ጊዜ ስህተቶቻችንን አርመን ፤ ጥፋቶቻችን አስተካከልን፤ እድፍና ጭቅቅታችንን አጸዳን ተቤዠን ማለት ነው። ዳግም እንዳንመለስባቸው ተቆራረጥን ማለት ነው ። እንደ ንስር ታደስን ፣ በከፍታ በረርን ማለት ነው ።
ጀግኖቻችን ለዘመናት ሞተውልን ካልተቤዥን፤ የቀረን ነገር በኃጢያታችን የተነጠቅነውን ፣ አሳልፈን የሰጠነውንና ያጣናውን ምርኮ ማስመለስ የምንችለው ሁላችንም ሞተን ሃገራችንና ሕዝባችን መቤዥና መታደግ ስንችል ብቻ ነው ። ለዚህ የሚበጀው ደግሞ የመቤዠት ፖለቲካ ነው ። በመተላለፋችን ፣ በኃጢያታችንና በበደላችን ለዘመናት የተነጠቅነውንና ያጣነውን ምርኳችንን የሚያስመልስልን ፤ ስህተቶቻችንን የሚያርምልን ፣ የሚያስተካክልልንና እድፋችን የሚያነጻልን ዋጋ ማለትም መሞት ብቻ ነው።
የሶሻሊስትና የልማታዊ/የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካ አሳራችንን አበዛው እንጂ መፍትሔ አላመጣም። መደመር/…ሪዝምን ለመገምገም ጊዜው ገና ቢሆንም የመቤዠት ፖለቲካ አይነት ሆኖ አግኝቸዋለሁ። “መደመሪዝም” በአንድም በሌላ በኩል ስህተትንና ጥፋትን የማረም ፤ እንደ ሃገር ፣ ሕዝብና ኢትዮጵያዊ ያጣነውን ወረት የማስመለስ ግብን ያነገበ ስለሆነ ለመቤዤት ፖለቲካ ይቀርብብኛል ። ምንም እንኳ ብልጽግና ራሱ ደፍሮና አፉን ሞልቶ ሃገር በቀል ርዕዮተ ዓለም ነው ባይለንም እኔ ግን በዚህ ማንጸሪያ ነው የምመለከተው ። “መደመሪዝም” እንደ አዲስ እይታ ብቻ ሳይሆን እንደ ርዕዮተ ዓለም ተወስዶ ሊጠናና ሊተነተን ይገባል የሚል እምነት አለኝ ።
ሃገራችንንና ሕዝባችን ለማዳን የቀረን ብቸኛ ነገር ቤዛ መሆን ነው ። በብዙ እዳ የተያዘችውንና የተወሰደችውን ሃገራችንና ሕዝባችን ሁላችንም ዋጋ ፣ ካሳና ለውጥ ከፍለን ማስመለስ የቀረን ብቸኛ አማራጭ ነው። ኢየሱስ ለሚያምኑበት ሁሉ በሞቱ ቤዛ ሆኖ ከዘላለማዊ ሞት እንዳዳናቸው ፤ በሞታችን ቤዛ ሆነን ሃገራችንን ከሞት ማዳን አለበን ። ቤዛ የምንሆነው በሮማውያን መስቀል በቀራኒዮ ተሰቅለን አይደለም። የምንሞተው ሃገራችንና ሕዝባችን ለዚህ ህልቆ መሳፍርት መከራና አሳር ለዳረጉ እኩይ ተግባራት ከዚህ በኋላ ላለመተባበር በመወሰንና በመማማል ነው ።
የተፈጸሙ ስህተቶችንና እንደ ጎን ውጋት አላላውስ ብለው ቀስፈው የያዙንን ችግሮች ለጊዜያዊ ፖለቲካ ጥቅም ከማዋል ይልቅ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለማረምና ለማስተካከል መረባረብና መጣር አለብን ። የሁሉም ዜጎችና ተቋማት ግብም በዚህ የተቃኘ ሊሆን ይገባል። የፖለቲካ ፕሮግራማችን ፣የልማት ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጂዎቻችን ፣ ሥርዓተ ትምህርታችን ፣ የታሪክ ትምህርታችን፣ የዐውደ ምሕረት ስብከታችን ፣ ወዘተረፈ የቀደሙ ስህቶቻችን ለማረም የሚተጉ እንጂ በጥፋት ላይ ጥፋት ፣ በችግር ላይ ችግር ፣ በቀውስ ላይ ሌላ ቀውስ የሚለፍፉና የሚጋብዙ መሆን የለባቸውም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም