ከሠላሣ ዓመታት በላይ “ሥራዬ ቋሚ ምስክር ይሁነኝ። እኔ በአደባባይ ወጥቼ ይህን ሠራሁ ብዬ አልናገርም።” በማለት ሥራ ሥራቸውን ብቻ ሲሠሩ የቆዩ፤ በርካታ ሕፃናትን አሳድገው ለወግ ማዕረግ ያበቁ፤ አንድም ቀን “እኔ ይሄን ሠራሁ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለፈቀደ እኔን መጠቀሚያ አደረገኝ።” በማለት ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑትን አንድ ታላቅ ሰው እንተዋወቅ።
ወይዘሮ ፀሐይ ሮሽሊ ይባላሉ። አጠር ያለ ቁመታቸው ላይ የለበሱት የሃገር ልብስ ፍክት አድርጋቸዋል። ፈገግታቸውና አሰተያየታቸው ፍፁም እናታዊ ነው። ንግግራቸው የተቆጠበ ሲሆን፤ በተረጋጋ አንደበት እንዲህ ተጨዋውተውናል መልካም ንባብ።
ለመቶ አለቃ ድልነሳው አላምረው እና ለወይዘሮ አበባ ፍቅረማሪያም የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ፀሐይ በ1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ አከባቢ ይችን ዓለም ተቀላቀለች። ታናናሾቿ ከሆኑት እህት ወንድሞቿ ጋር እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ቤተሰቦቿን እያገለገለች አደገች። ቤታቸው ላሞች ዶሮዎች በርካታ የቤት እንስሳት የሚገኙበት እንደነበር ታስታውሳለች።
ትንሿ ፀሐይ አንድ ቀን በቤታቸው አቅራቢያ በሚገኘ አንድ ወንዝ አካባቢ እየተጫወተች የውጭ ሃገር ዜጎች ተመለከተች። ቀደም ሲል ከእነሱ የተለየ የቆዳ ቀለም ያላቸውን ሰዎች ተመልክታ ስለማታውቅ ተገርማለች። ምን እንደሚመስሉ በቅርበት ለመመልከት ጠጋ ትላለች። የነጮቹ ልጆቹ ይጫወታሉ፤ እናታቸው ቁጭ ብላ ልጆቿን ትመለከታለች። ፀሐይ ፈረንጆች እንቁላል ይወዳሉ የሚል ነገር ትሰማ ሰለነበር በሩጫ ወደ ቤቷ ተመልሳ እንቁላል አምጥታ ሰጠቻቸው። ቋንቋ በሌለበት ዝም ብለው ሲተያዩ ከቆዩ በኋላ በእጅ ምልክት ወደ ቤቷ ጋበዘቻቸው። እነሱም ተከትለዋት ወደ’ነፀሐይ ቤት ሲገቡ የፀሐይ እናት ላም እያለበች ያገኟታል። የፀሐይ እናትም ከምታልበው ወተት ቀድታ ሳትሰስት ለእነዚህ ነጮች ትሰጥና በምስጋና ይሰነባበታሉ።
በቀጣዩ ቀን በፌስታል የተሞሉ ምግቦች፤ አልባሳት፤ መጫወቻ ብቻ ምኑ ቅጡ ለልጆች ያስደስታል የተባለውን ሁሉ ይዘው መጥተው ያለ አንዳች ንግግር ሲተያዩ ቆይተው ፀሐይን ይዘዋት ሜክሲኮ፣ ትንባሆ ሞኖፖል አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሄዱ። ፀሐይ በሕይወቷ አይታ የማታወቀውን አይነት ቤት ስታይ በጣም ተገረመች። ከነጮቹ አራት ልጆች ጋር በመሆን ስትጫወት ከቆየች በኋላ ወደ ቤቷ ትመለሳለች።
እንዲህ እንዲህ እያለ ያለ ምንም ንግግር የተግባቡት እነዚህ የሁለት ዓለም ሰዎች ዝምድናቸው እንደመጥበቅ ኣለ። በመሐል የፋሲካ በዓል ስለነበር እነፀሐይ ቤት እንዲመጡ ነጮቹ ግብዣ ተደረገላቸው። በወቅቱ ጠረጴዛውንም ከነጮቹ ቤት በመበደር ቤት ያፈራውን ዶሮም፤ ጥብስም፤ ዱለትም፤ ከየዓይነቱ ለበዓል የተዘጋጀው ምግብ ለእነዚህ ሰዎች ቀረበ። በፍፁም ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ሲደሰቱ ውለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
ከዛ በኋላ በዚህ ቤተሰብ ፍቅር የወደቀችው ነጯ ሴት አስተርጓሚ የሚሆን ሰው እቤታቸው ይዛ መጥታ ፀሐይ ከእነሱ ጋር እንድትኖር ተጠየቀ፤ ከዛም የፀሐይ ወላጆች ተማክረው ልጃቸው ወደ ነጮቹ ቤት ሄዳ እንድታድግ ተወሰነ። የሶሰተኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ፀሐይ ከነጮቹ ልጆች ጋር በመሆን ጀርመን ትምህርት ቤት አንደኛ ክፍል ተመልሳ እንድትገባ ተደረገ።
በዚህ መካከል ፀሐይ ወላጆቿንም እየጠየቀች ስትኖር የፀሐይ አባት በጠና ታመው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ብዙም ሳይቆይ የፀሐይ እናት ባላቸውን ተከትለው ልጆቻቸውን ያለ አሳዳጊ በትነው አረፉ። ያኔ በአቅራቢያቸው የነበሩ የእነፀሐይ አጎትና አክስት ልጆቹን ተከፋፍለው ለማሳደግ ተስማሙ። የእነ ፀሐይን ኃዘን ኃዘናቸው አድርገው የሰነበቱት ነጮች ግን እነዚህ ሕፃናት ተለያይተው ማደግ የለባቸውም፤ መፍትሔ እንፈልጋለን ብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
ቤታቸው እንደደረሱ ልጆቻቸውን ሰብስበው የፀሐይን ወንድም እህቶች ይዘን ልንመጣ ነው ብለው ሲያማክሯቸው በደስታ ተስማምተው ልጆቹ ወደ ነጮቹ ቤት ሄደው እዛ እየኖሩ መማር ጀመሩ። የራሳቸውን አራት ልጆች ለማሳደግ የመጡት፤ ስድስት ልጆች ተጨምረው አንድ ላይ አ ስር ልጆችን ያሳድጉ ጀመር።
አሳዳጊ አባቷ ዴቪድ ሮሽሊ፤ አሳዳጊ እናቷ ሜሪ ሊውስ ሮሽሊ የራሳቸው አራት ልጆች ያሏቸውና ከተጨማሪዎቹ የፀሐይ እህት ወንድሞች ጋር አስር ልጆችን ለማሳደግ ኑሮው ከበድ ይል ስለነበር በሰበታ አካባቢ ዶሮ የማርባት ሥራ ጀመሩ። የፀሐይ አሳዳጊዎች ዶሮውን አርደው ለሱፐር ማርኬቶች የማከፋፈል ሥራንም ይሠሩ ነበር።
በዚህ መካከል የንጉሡ ዘመን አብቅቶ የደርግን ወደ ስልጣን መምጣት ተከተሎ የእነ ፀሐይ አሳዳጊዎች ከሃገር መውጣት ግድ ይሆንባቸዋል። ያኔ እናሳድጋቸው ብለው የወሰዷቸውን ልጆች ጥለው የመሄዱ ነገር ጭንቅ ሆኖባቸው ወደ ኤምባሲ በመሄድ ልጆቹን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያማክራሉ። ኤምባሲው በማደጎ መውሰድ እንዲችሉ ደብዳቤ ለመፃፍ ተስማምተው አስሩንም ልጆች ይዘው በጅቡቲ በኩል ከሃገር ወጡ።
የወለዷቸውን ልጆች አባታቸው ይዘው ወደ ሲዊዘርላንድ ቢሄዱም አሳዳጊ እናታቸው ግን ወረቀታቸው ተስተካክሎ ልጆቹን ይዛ ወደ ሃገሯ እስክትሄድ ድረስ ለአራት ወራት የምታሳድጋቸውን ልጆች ይዛ ጅቡቲ ከቆየች በኋላ ልጆቿን ይዛ ወደ ትውልድ ሃገሯ ስዊዘርላንድ ገባች።
ገና ልጆች ይዛ የመምጣቷን ዜና የሰሙት ዘመድ ጎረቤቶቿ ለተጨማሪዎቹ ልጆች የሚሆኑ አልባሳትና የምግብ ቁሳቁሶች ከማዘጋጀታቸውም ባሻገር የአሳዳጊ እናቷ ወንድም ቤት በመስጠት እንዲመቻቸው ለማድረግ ተረባረቡ።
ፀሐይ ገና ፈረንጅ ሃገር እንደሄደች በወቅቱ የምታውቀው ትልቅ ሕንፃ የንግድ ባንክ የነበረ ሲሆን እዛ ሃገር ሁሉም በሰፊ ቤት፣ በትልልቅ ሕንፃ ውስጥ የሚኖሩ ይመስላት እንደነበር ትናገራለች። ነገር ግን ጠበብ ባለ ቦታ እየኖሩ ባላቸው ትንሽ መሬት አስፈላጊ አትክልቶችን በመትከል በደስታ የሚኖሩት የስዊዞቹ ቤተሰቦቿን ኑሮ ስታይ በጣም እንደተገረመች ትናገራለች።
ስዊዘርላንድ ስትደርስ የአስራ ዘጠኝ አመት ወጣት የነበረችው ፀሐይ እህት ወንድሞቿ ወደ ትምህርት ቤት ቢሄዱም እሷ አሳዳጊ እናቷ ላይ የወደቀው ልጅ የማሳደግ ኃላፊነትን ለመርዳት ቤት ትቆያለች። ኢትዮጵያ እያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት አሳዳጊ አባቷ ወደ ሃገራቸው ሲመለሱ በተማሩበት ዘርፍ ሥራ ማግኘት ባለመቻላቸው የተገኘውን ሥራ በመሥራት ሰፊውን ቤተሰብ ለማስተዳደር ደፋ ቀና ይሉ ጀመር። በዚህም ሰዎች ባላቸው ይረዷቸው ጀመር። ፀሐይም አሳዳጊዎቿን ለመርዳት የሚያስችላትን የፋብሪካ ሥራ መሥራት በመጀመር በመረዳዳትና በፍቅር ኑሮን መግፋት ጀመሩ።
ከብዙ ጊዜ በኋላ ፀሐይ ቤት ተከራይታ በመውጣት የሯሷን ኑሮ መኖር ጀመረች። በወጣትነት ጊዜዋ መሥራትን፤ ገንዘብ ማግኘትን፤ ዓለምን መዞርን፤ ሕልሟ ያደረገችው ይች ወጣት ቀን በፋብሪካ ስትሠራ ውላ ማታ ደግሞ ቢሮ በማፅዳት ሥራ ላይ ተሠማርታ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረች። የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሊያልፍ የቀረቡ ምግቦች በርካሽ ስለሚሸጡ እነሱን በመግዛት እየተመገበች ገንዘብ ላለማባከን እየተጠነቀቀች የምትኖረው ፀሐይ አንድ ቀን ሕይወቷን የቀየረውን ዜና በቴሌቪዥን ትመለከታለች።
ከሠላሳ አምስት ዓመታት በፊት ፀሐይ ወደ ስዊዘርላንድ ከሄደች ከአስራ ሦሥት ዓመታት በኋላ ሃገሯን አስታወሰች፤ ሀብታም መሆን፣ መኪና መግዛት፣ ቤት መግዛት ሕልሟ የነበረው ይች ልጅ ሃገሯ በረሃብ እየተጎዳች ወገኖቿ እንደቅጠል እየረገፉ እንደሆነ የሚያሳይ ዜና ነበር የተመለከተችው። ሃገሯን ረስታ
የቆየችው ወጣት ቀኑን ሙሉ የሰማችው ነገር ሲከነክናት ዋለ። ሲከነከናት የዋለውን ዜና ዳግም በማታው ስርጭት ተመለከተች። ያ ሀብታም የመሆን ሕልሟ፤ ያ ዓለምን የመዞር ታላቅ ሰው የመሆን ሀሳቧ ሁሉ ተቀይሮ “እንዴት ነው ለወገኔ የምደርሰው?” በሚል ሀሳብ ተተካ። ከገንዘብ በላይ የሰው ልጆችን ነፍስ ለማትረፍ የሚያስችል በጎ ተግባር ለመሥራት ቆርጣ ተነሳች።
በስዊዘርላንድ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንዴት እርዳታ መላክ እንደሚቻል ያውቁ ስለነበር ፀሐይ ማግኘት የሚገባትን አካል አገናኝተው ልብሶችና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደ ሃገር ቤት እንድትልክ ያደርጓታል። በወቅቱ ሕፃናት ኮሚሽን የሚባል ተቋም ውስጥ የእርዳታ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ልብሱን ተቀብለው በፍጥነት እንዲያደርሱላት ብታስብም ያለው ቢሮክራሲ ግን ባሰበችው ፍጥነት ሊያደርሱላት ባለመቻላቸው ወደ ሃገር ቤት መሄድ እንዳለባት ወስና ሥራ አስፈቅዳ ወደ ኢትዮጵያ መጣች።
ገንዘብና አስፈላጊ ቁሳቁስ ይዛ ወደ ትውልድ ሃገሯ የተመለሰችው ፀሐይ “አንድ 20 ልጆችን ለመርዳት ብፈልግ ከመንግሥት የሚገኘው ድጋፍ ምንድን ነው?” ብላ ስትጠይቅ መሬት እንደሚሰጣትና ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ለማስገባት የሚቻል መሆኑ ይነገራታል። በዚህም መሥራት ያለባትን ሥራዎች በማሰብ የእርዳታ ማስተባበሪያዎቹ ሰዎች ወደ ወሎ እንደሚሄዱ ስትሰማ ለመሄድ ተነሳች። ተጓዦቹን ተከትላ ቦታው ስትደርስ ያየችው ነገር በጣም አሰቃቂ የነበረ እጅግ የከፋ፤ ለማየት የሚከብድ ሁኔታ ላይ የነበረች መሆኗን ትናገራለች።
መንግሥት የሚያደርግላትን ድጋፍ ማረጋገጫ ደብዳቤ ከያዘች በኋላ ወደ ስዊዘርላንድ ተመልሳ በመሄድ ለወዳጅ ዘመዶቿ በማባዛት አሰራጭታ ስትጨርስ በርካታ ገንዘብ ወደ አካውንቷ መግባት ሲጀምር ለሥራው የሚያስፈልገውን ማቴሪያል በሙሉ በኮንቴነር አስጭና ጅቡቲ ደረሰች። በዛው ጊዜ ደግሞ መንግሥት ቃል የገባላትን መሬት በመረከብ ልጆቹ የሚያርፉበት ቤት ግንባታ ተከናወነ።
የመጀመሪያ በሰላም ሕፃናት መንደር የሚያድጉ ልጆችን ለማምጣት ወደ ወሎ ስትሄድ በርካታ ሕፃናት ተሰልፈው ከዛ ሰቆቃ የሚያስመልጣቸውን ሰው እየተጠባበቁ አገኘቻቸው። ከተሰለፉት ልጆች መካከል የቻለችውን ያህል መርጣ 28 ሕፃናትን በማምጣት ሥራው “ሀ” ብሎ ተጀመረ። ከዛ በኋላ ግን ያየችው ነገር አስከፊ ስለነበር ቤቶችን በማስፋፋት በሦስት ወር ውስጥ ዘጠና ሕፃናትን ወደ ሰላም የሕፃናት መንደር አስገብታ የማሳደጉ ሥራ ተጀመረ።
በወቅቱ ትምህርት ቤት በማሳደጊያው ውስጥ ስላልነበረ በደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን እየላኩ ማስተማር ጀመሩ። ሥራው በአግባቡ እንዲደገፍ በእርዳታ ተሰብስበው ከስዊዘርላንድ የመጡ ልብሶችን ልጆቻቸውን አልብሰው የተረፈውን በመሸጥ በማሳደጊያ ቅጥር ግቢ ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመሥራት ተቻለ። ሕፃናቱን ከማሳደግ ጎን ለጎን በጊቢው ውስጥ አትክልት የመትከል፤ ከብት ማርባት፤ ዶሮ ማርባት ላይ ትኩረት አድርጎ በተቻለው መጠን የልጆቹን የምግብ ፍላጎት በውስጥ ምርት ለማሟላት ተግተው ይሠሩ ጀመር።
የፀሐይ አሳዳጊ አባት ዴቪድ ሮሽሊ የልጁን በሥራው ላይ ትኩረት ማድረግ የበርካታ ሕፃናትን ነፍስ ለማዳን የምታደርገው ሩጫ ስለማረከው ከትውልድ ሃገሩ ስዊዘርላንድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሕፃናቱ አድገው የቀለም ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የሚማሩበት “ሰላም ዴቪድ ሮሽሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ”ን ከፈቱ።
ይህ ማሰልጠኛ ተቋም ለትርፍ ያልተቋቋመና በተለያዩ ሙያዎች ወጣቶችን በጣም በአነስተኛ ክፍያ እስካሁን ድረስ እያሰለጠነ የሚገኝ መሆኑን ተመልክተናል።
ኮሌጁ በአዲስ አበባ ሞዴል ኮሌጅና በስልጠና ጥራቱ በአዲስ አበባ በአይ ኤስ ኦ 9001፡2008 ብቸኛ ሰርቲፋይድ የሆነ ኮሌጅ፣ በኮሌጁ የከባድና ቀላል እንዲሁም የእርሻ መኪናዎች ጥገና ስልጠና ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት፣ በሥራ ፈጠራ እና በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ሞዴል ኢንተርፕረነሮች የሆኑ እና በሃገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ ዋኖቹ በዚሁ ኮሌጅ ውስጥ ሰልጥነው የወጡ ወጣቶች መሆናቸውን ተከትሎ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች። ኮሌጁ በተለያዩ ዘርፎች የሙያ ብቃት ምዘና ማዕከልም በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ወይዘሮ ፀሐይ ሮሽሊ ነግረውናል።
በሕፃናት መንደሩ ያደጉ ልጆች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው መመልከት እጅግ በጣም እንደሚያስደስታቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ፀሐይ ሁሉም ልጆቻቸው ተሳካላቸው የሚባል ባይሆንም፤ የራሳቸውን ድርጅት የከፈቱ ልጆች ብዙም ያልተሳካላቸውን ወንድሞቻቸውን በመሰብሰብ ሕይወታቸው እንዲቃና ለማድረግ ሲታትሩ መመልከት፤ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ ሲደጋገፉ ማየት እጅግ በጣም የሚያስደስታቸው መሆኑን ወይዘሮ ፀሐይ ትናገራለች።
ወይዘሮ ፀሐይ ስላልተሳካላቸው ልጆቻቸው ስታወራ በርህራሄና በእናትነት አንጀት፤ በ”እንዴት ይሁን?” በሚል መንፈስ ውስጥ ሆነው ሲሆን አድገው ተምረው ማቋቋሚያ ተሰጥቷቸው ከግቢው የተሸኙት ልጆች፤ የተለያዩ ሱሶች ውስጥ ገብተው፤ ገንዘብ አልበቃ ሲላቸው ደግም ተመልሰው ያደጉበት ቤት ደጅ ላይ ስትመለከታቸው፣ ለእናት ምን ትልቅ ቢሆን ልጅ ልጅ ነውና ዳግም ተቀብለው አጥበው፣ አልብሰው፣ አብልተው ሌሎቹ የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ልጆች እንዲያግዟቸው እንደምታደርግ ታስረዳለች።
ከተሳካላቸው ልጆቻቸው መካከል ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ትልቅ ፋሲል ኢንጂነሪንግ የሚባል የግል ኢንቨስተር ልጃቸው ልጆቹ ከሱስ የሚወጡበትን መንገድ በማስተካከል ዳግም የተቃና ሕይወት ውስጥ እንዲገቡ በሚያደርገው ጥረት እንደሚያመሰግኑት ይናገራሉ።
ሌሎቹ ልጆች ተምረው ሲያጠናቅቁ ቤታቸውን ማገልገል ከፈለጉ ተወዳድረው መግባት የሚችሉበት ሥርዓት ያለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግቢው የራሱን ገቢ በራሱ ለመሸፈን በሚያደርገው ጥረት ሬስቶራንት ከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን፤ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፤ ክሊኒክ፤ ትምህርት ቤት፤ የግቢው የአስተዳደር ሥራና ሌሎች ዘርፎች ላይ ተሠማርተው ይገኛሉ።
እያንዳንዱ የበጎ አድራጎት ሥራ የተሳካ እንዲሆን በስዊዘርላንድ ያሉ ዘመዶቿና ጓደኞቿ አስተዋፅኦ ከፍ ያለ እንደነበረ የምትናገረው ወይዘሮ ፀሐይ በወቅቱ በሃገሪቱ ውስጥ የነበሩት ባለስልጣናት ትልቅ ትብብር በማድረግ ለሥራዋ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማድረጋቸውን ትናገራለች።
በፈቃደኝነት ለማስተማር፤ በሙያቸው ለመርዳት የሚመጡት የስዊዘርላንድ ዜጎች በማሳደጊያው ውስጥ በተዘጋጀላቸው ክፍል በመቀመጥ፤ እንደ ኢትዮጵያዊ በመኖር ሲያገለግሉ የሚቆዩ ሲሆን ይዘው የመጡትን እቃ ለማሳደጊያው ሰጥተው የተለያዩ ባህላዊ ሻርፖችን፤ ባህላዊ ምግቦችን ወደ ስዊዘርላንድ በመውሰድ ተሽጠው ለማሳደጊያው ድጎማ እንዲሆን የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን በስዊዘርላንድ የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት ያለ ሲሆን የወይዘሮ ፀሐይ ታናሽ እህት ኃላፊነቱን ወስደው ይሠራሉ፤ የወይዘሮ ፀሐይ የመጀመሪያ ልጅ ሄኖክም የቦርድ አባል ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ፀሐይ ስዊዘርላንድ ከመሄዷ በፊት ቤተሰቦቿ የሚያረቡትን ዶሮ ለየሱፐርማርኬቱ የማከፋፈል ሥራ ላይ እያለች የተዋወቀችው አንድ የሂሳብ ሠራተኛ ዳግም እርዳታ ለማድረግ ወደ ሃገሯ ስትመለስ በአጋጣሚ ተገናኝተው ለትዳር እንደበቁ ትናገራለች። ይህ ሰው የኤርትራ ዜግነት የነበረው ሲሆን ሶስት ልጆችን ካፈሩ በኋላ መለያየታቸውን ታስረዳለች።
የአብራኳ ክፋይ የሆኑት ሄኖክ፤ ዳንኤልና ሚካኤልም አሁን በስዊዘርላንድ የሚገኙ ሲሆን ሁሉም ለወግ ማዕረግ የበቁ የእናታቸውን በጎ ተግባር ለማስቀጠል የሚታትሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።
ወይዘሮ ፀሐይ እርዳታ በጀመረች ጊዜ አካባቢ ሙዳይ ይዘው ቤተክርስቲያን አካባቢ እየለመኑ ለራሳቸው ሳይኖራቸው የብዙዎች እናት የሆኑትን አበበች ጎበናንም ካላት ላይ በማካፈል አግዛቸው እንደነበረ ይነገራል።
ሰጥቶ የማይነጥፍ እጅ ራርቶ የማይደክም ልብ ባለቤቷ ወይዘሮ ፀሐይ በትምህርት ራሴን ላሳደግ እንኳን ሳትል፤ ለዘመናት ለሌሎች ብርሃን ስትሆን ኖራለች። ፀሐይ ገና በልጅነቷ ጀርመን ትምህርት ቤት እስከ ሰባተኛ ክፍል ብቻ የተማረች ሲሆን፤ በተለያዩ ኮርሶች ራሷን ከማጠናከር በስተቀር፣ ምንም ዓይነት የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራም አለመከታተሏን ታስረዳለች። ጊዜዋን በሙሉ ልጆቿን በማሳደግ ሥራ ተጠምዳ የኖረች ሰው ነች።
“እማማ ፀሐይ አንቺ ካለፍሽ በኋላ የዚህ መንደር መጨረሻ ምን የሚሆን ይመስልሻል?” ስንል ላነሳንላት ጥያቄ ስትመልስ “ይህ ቤት በርካታ ጠንካራ ልጆችን ያፈራ፣ በጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት የሚመራ ሲሆን እኔም ሞቼ ስሜን እያስጠራ ወላጅ ለሌላቸው ወላጅ፤ ደጋፊ ለሌላቸው ደጋፊ በመሆን ይቀጥላል” ብላለች።
አሁን ልጆችን ተቀብሎ ከማሳደግ ባሻገር ልጆቻቸውን የሚይዝላቸው አጥተው በችግር የሚቆራመዱ እናቶችን፤ ልጆቻቸውን ተቀብሎ በማቆየት የዕለት ሥራቸውን ሠርተው እስኪመለሱ ድጋፍ የሚሰጡ መሆኑን ተናግረዋል። በድርጅቱ በርካታ ሴቶች በነፃ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ በሙያቸው ሥራ የሚያገኙበት ሁኔታም መመቻቸቱን ትናገራለች።
በመንደሩ የሚሠሩ ሠራተኞችም ሆኑ በእማማ ፀሐይ እጅ ያደጉ ልጆቻቸው ስለ እማማ ፀሐይ ሲጠየቁ ከቃሎቻቸው ቀድሞ እንባቸው እየፈሰሰ “የእሷን ደግነት በቃላት መግለፅ አይቻልም፤ የተፈጠረችው ለመስጠት ነው። ለመስጠት የተሰጠች ስለሆነ ፈጣሪ እድሜና ጤና እንዲለግሳት ከመመኘት ያለፈ ቃል የለም” ሲሉ ነው የሚደመጡት።
በአንድ ሙሉ መጽሐፍ ተተርኮ የማያልቀውን የእማማ ፀሐይን ታሪክ በዚህ አጭር ጽሑፍ ተርኬ ባልጨርሰው ስማቸው ከሥራቸው ቀድሞ የሚጠራ ከባለ ወርቅ ልቦች መካከል አንዷ፤ ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ቴሬዛ የሚል ስያሜ ያንሳቸዋል ለማለት ደፍሬያለሁ።
እማማ ፀሐይ ስለልጆቻቸው ስትናገር “ልጆቼ በታላላቅ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሃገርንና ሕዝብን በማገልገል ላይ መገኘታቸውን ሳስብ ደስታ ይሰማኛል። ከነዚህም በተጨማሪ የራሳቸውን ትልልቅ የቢዝነስ ተቋሟት ከፍተው ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች የሥራ እድል የፈጠሩ መኖራቸው ደግሞ ይበልጥ ያኮራኛል።”
“በመንደሩ አድገው የራሳቸውን ኑሮ ከመሠረቱት የቀድሞ ልጆቻችን ጋር አሁንም ግንኙነት አለኝ፤ የተለያዩ የእናትነት ፍቅር መግለጫ ስጦታ ያበረክቱልኛል። በአንድ ወቅት የነበረብኝን ቀሪ የመኖሪያ ቤት እዳ እኔ በማላውቀው መንገድ አሰባስበው ከፍለውለኝ ደረሰኙን የሰጡኝ እለት ልቤ እጅግ በጣም ነው የተነካው። ያሳደኳቸውን ልጆች ከአብራኬ ከወጡት በላይ እወዳቸዋለሁ” ብላለች።
የሰው ልጅ አንዱ ለመስጠት አንዱ ለመቀበል ይፈጠራል፤ የፈጣሪ ሥራ አይመረመር ነውና ይህንን ድንቅ ጥበቡን በእማማ ፀሐይ እናትነት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆች ልጅነት ያስተሳሰረ ፈጣሪ አሁንም በሃገራችን በተፈጠረው ሰላም ማጣት ያለ ወላጅ የቀሩትን ልጆች ሰብሳቢ ይዘዝላቸው። ያለ ጧሪ፣ ቀባሪ የቀሩትንም ጧሪ ቀባሪ ይለግስልን። ሃገራችንን ሰላም አድርጎ ወደ አንድነቷ ይመልስልን፤ በሚለው የእማማ ፀሐይ መልዕክት ቆይታችንን አብቅተናል።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 7 ቀን 2014 ዓ.ም