ተወልዳ ያደገችው በሀዋሳ ከተማ ነው።መምህር ከሆኑት ወላጅ አባቷ ሰርቶ ማደርን ራስን ማሸነፍና በራስ መተማመንን ተምራለች። ለቤተሰቧ ሶስተኛ ሴት ልጅ ስትሆን ወላጅ አባቷ ቤተሰቡን ለማኖር ከመምህርነት በተጨማሪ የሥዕል ሥራዎችን ጨምሮ የገቢ ምንጭ የሚሆናቸውን በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ እየተመለከተች ብቻ ሳይሆን ሥራውን እያገዘች አድጋለች። አባቷ ለእጽዋት ልዩ ፍቅር የነበራቸው በመሆኑም በግቢያቸው የተለያዩ አይነት ዛፎችና የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ቀዳሚ አልነበራቸውም።ከእነርሱ ግቢ ችግኝ መትከልና እጽዋትን መንከባከብ መደበኛ ሥራ ከመሆን ባለፈ ያሸልማል።
እጽዋትን መትከልና መንከባከብን ባህሉ ካደረገ ቤተሰብ የተገኘችው የዛሬዋ የስኬት እንግዳችን ከእህት ከወንድሞቿ በተለየ ወደ ችግኝ ተከላና እጽዋትን ወደ መንከባከብ አዘንብላለች – ወይዘሮ በረከት ወርቁ።ወይዘሮ በረከት፤ ዳያስፖራ ከመሆን ባለፈ አየርላንዳዊ ከሆነው የትዳር አጋሯ ሁለት ልጆችን ወልዳለች።በአገሯ ሰርታ መለወጥና ለሌሎችም መትረፍ ያለባት መሆኑን በማመን ኑሮዋን በአገሯ አድርጋ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችላለች። በተለይም በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት የስኬት ማማ ላይ ለመድረሷ በልጅነቷ ከወላጅ አባቷ ጋር በመሆን ያሳለፈችው የተግባር ሥራ የጎላ ድርሻ አለው።
በችግኝ ተከላና የጓሮ አትክልትን በማልማት ያደገችው ወይዘሮ በረከት፤ እራሷን ለመቻል ባደረገችው ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ሱዳን ሥራ የመሥራት አጋጣሚ አግኝታለች።በደቡብ ሱዳን መከላከያ ውስጥ በምትሠራበት ወቅት ለአትክልት ካላት ውስጣዊ ፍቅር የተነሳ አብዛኛውን ጊዜዋን በግቢ ውስጥ ችግኝ እያፈላች ዛፍ በመትከልና በመንከባከብ ታሳልፍ ነበር።ከደቡብ ሱዳን ወደ ኡጋንዳ በተላከችበት ወቅትም ኢትዮጵያ እያለች አቋርጣ የነበረውን የህግ ትምህርቷን ቀጥላለች።አየርላንዳዊ ዜግነት ያለው የትዳር አጋሯንም በዚሁ አጋጣሚ ማግኘቷን ትናገራለች። ሰርጋቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹ቱላማ›› በተባለው በኦሮሞ ባህል እንደነበር ታስታውሳለች፡፡
በደቡብ ሱዳን መከላከያ ተቋም ውስጥ ዋና ሥራዋ የነበረው የጦሩን ትጥቅ ማቅረብ ቢሆንም ቆስጣና ሰላጣን ጨምሮ ለምግብ የሚሆኑ አትክልቶችንና የተለያዩ ዛፎችን በፓርላማ ግቢ ውስጥ ሳይቀር ትተክል የነበረችው በረከት ጋብቻዋን ከመሰረተች በኋላ ኑሮዋን በአየርላንድ አድርጋለች።
‹‹ከኢትዮጵያ ውጪ አንድ ሳምንት ስቀመጥ አገሬን የማጣት ይመስለኛል›› የምትለው ወይዘሮ በረከት፤ ታድያ ለአገሯ ያላትን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ወደ አገር ቤት ተመልሳ ኢንቨስት ለማድረግ ብዙ ማሰብ ሳያስፈልጋት ከልጅነት እስከ ዕውቀት የምታውቀውን የግብርና ዘርፍ ተቀላቅላለች።ፊቷን ወደ ግብርና ለማዞር በአገር ቤት ከነበራት ተሞክሮ በተጨማሪ በአየርላንድ የተመለከተችው የግብርና ሥራ እጅጉን ያስደመማትና ያስቆጫት እንደነበር ትናገራለች።በአገሪቱ ያለውን የአየር ንብረት በተለይም በረዶውን ተቋቁመው አነስተኛ በሆነው ቦታ ላይ የሚያመርቱት ምርት ከራሳቸው አልፈው አፍሪካን መርዳትና ወደ ውጭ መላክ መቻላቸው ይበልጥ እንድትቆጭና ወደ መስኩ እንድትገባ አድርጓታል፡፡
በተመሳሳይ ደግሞ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ውሃ፣ ለም አፈርና ምቹ የአየር ንብረት ያላት ሆና ለምን ተራብን የሚለው ደግሞ ይበልጥ አስቆጭቷታል። ከዚህም በመነሳት ወደ ሀገሯ ተመልሳ የእርሻ ሥራን ለማስፋፋት ወሰነች።በወቅቱም በኦሮሚያ ክልል ወንዝ ያለበት ቦታ እንዲሰጣት በጠየቀችው መሰረት አርሲ ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ላይ 40 ሄክታር መሬት ተቀብላ በረከት ወርቁ አትክልትና ፍራፍሬ በሚል ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ስታለማ ቆይታለች።
በ40 ሄክታር ላይ 46 ሠራተኞችን ቀጥራ በምታለማበት ጊዜ አንድ ዓመት እንዳስቆጠረች ታድያ ከተራራ ላይ የመጣ ከባድ ጎርፍ ፓፓዬን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ወድሞባታል።ይሁን እንጂ በደረሰው አደጋ ተደናግጣ ወደ ኋላ ሳትል ችግሩን በመጋፈጥ መፍትሔውን አፈላልጋ ለውሃው መውረጃ መንገድ በመክፈት ወደ ሥራዋ ብትመለስም ሌላኛው ፈተና ከደጃፏ ደርሷልና በ2009 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ረብሻ ሰላም የሚሻው ኢንቨስትመንት ልማቱ ተናጋ።የእርሻ ቦታዋ በድጋሚ ሰው ሰራሽ በሆነው አደጋ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ደረጃ ወደመ።ያም ሆኖ ወይዘሮዋ በአገሯ ተስፋ አልቆረጠችም ፤ሌሎች አማራጮችን ማማተር ቀጠለች፡፡
በወቅቱ 30 ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር የሚገመት የንብረት ውድመት የደረሰባት ቢሆንም ከህመሟ በላይ መቀየር በምትችለው ነገር ላይ ታማና ተጨንቃ ዳግም ወደ ሥራዋ ተመልሳለች።በወራት ጊዜ ውስጥ የደረሰባትን ጉዳት ተቋቁማ ወኔዋን በማሰባሰብ የማይቀረውን ሥራ ለመቀጠል መቂ ላይ 140 ካሬ ሜትር መሬት ከገበሬው ገዝታ የእርሻ ሥራዋን ስትቀጥል ታድያ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ሠራተኞቿን እዛው በመተው ሌሎቹን ይዛ ነበር፡፡
በዚሁ ይብቃኝ ያላለችው ትጉዋ ባለሀብት፤ የእርሻ ሥራዋን ለማስፋፋት ወደ ደቡብ ክልል ፊቷን አዙራለች።በወቅቱ የነበረው የወላይታ ዞን ኢንቨስትመንት ኃላፊ ባደረገላት ቀና ትብብር ወላይታ ኦቢቻ ወረዳ ላይ 600 ሄክታር መሬት ተረክባ ወደ ሥራ ገብታለች።ይሁንና አካባቢው ድቅድቅ ያለ ጫካ ከመሆኑ የተነሳ በወቅቱ ብዙዎች ሊለማ የሚችል ቦታ አይደለምና ይቅርብሽ ብለዋታል።ውስጧን በማዳመጥ ከራሷ ጋር በመምከር ድቅድቁን ጨለማ ብርሃን በማድረግ ጫካ መንጥራ ወንዝ ጠልፋ የእርሻ ሥራዋን በመሥራት ዛሬ ተዝቆ የማያልቅ አትክልትና ፍራፍሬዎቿን ለገበያ ማቅረብ ችላለች።
በዚሁ የእርሻ ቦታ ታድያ ለሠራተኞች መኖሪያ ቤት ከመገንባት ባለፈ በአባቷ ግቢ ስትተክል የኖረችውን ዛፍም ለአካባቢ ጥበቃ በሚል የተለያዩ አገር በቀልና የውጭ ዛፎችን በመትከል አካባቢውን ገነት ማድረግ ችላለች። ዛፎቹን የሚንከባከቡ ሠራተኞችን ለብቻ በመቅጠር ከ700 ሜትር ርቀት ላይ ውሃ በመጥለፍ ዛፍ መትከልን ከእርሻ ሥራዋ እኩል አስቀጥላለች።
ለአካባቢው ሰባተኛ አልሚ የሆነችው ወይዘሮ በረከት፤ ከእርሷ አስቀድመው ስድስት አልሚዎች ገብተው አቅቷቸው እንደወጡ ታስታውሳለች። የአካባቢው ሰዎች ግን እርሷም አቅቷት እንደምትወጣ ግምት የነበራቸው ቢሆንም ግን ጫካውን መንጥራ ውሃ ጠልፋ አካባቢውን የምድር ገነት በማድረግ ማሳየት ችላለች።ከእርሻ ቦታውም የሚመረተውን አትክልትና ፍራፍሬ በዋናነት ለሲዳማ ክልል ኤልቶ ሸማቾች፣ ለሀዋሳ ከተማ ሸማቾች፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ጋርመንት ገበያ፣ ጣፎና ለሌሎችም የገበያ ቦታዎች እያቀረበች እንደሆነ አጫውታናለች፡፡
ለግብርናው ዘርፍ ቅርብ ከመሆን ባለፈ ጥልቅ ፍቅር ያላት ወይዘሮ በረከት፤ በሰላም እጦት ንብረቷ በወደመባት አርሲ አካባቢ ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ትታወቅ ነበር።በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ወደ አካባቢው ተመልሳ ማልማት እንድትችል የአገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ይቅርታ ጠይቀዋት ተመልሳ በ40 ካሬ ሜትር ቦታዋ ላይ ማልማት ጀምራለች።በድጋሚ ወደ ልማት በተመለሰችበት አርሲ ዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ከማልማት ባለፈ በዙሪያዋ ላሉት አርሶ አደሮች ትራክተርን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ምርታማ መሆን እንዲችሉ በማገዝ ማህበራዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች፡፡
በኦሮሚያና በደቡብ ክልል አትክልትና ፍራፍሬን በስፋት እያመረተች የምትገኘው ባለሀብት፤ በተለይም በደቡብ ክልል ብላቴ ላይ ሙዝ በከፍተኛ መጠን ታመርታለች። በዘንድሮ ዓመት ብቻ 42 ሺ የሙዝ እግር መትከል የቻለች ሲሆን፤ በዓመቱ መጨረሻም 100 ሺ የሙዝ እግር የመትከል ዕቅዷን ለማሳካት እየሠራች ነው። የገበያ መዳረሻዋም ሱማሌ ድረስ እንደሆነ አጫውታናለች፡፡
ከግብርና ሥራዋ በተጨማሪ ከብቶች በማርባት ወተትና የወተት ተዋጽኦዎችንም ለገበያ ታቀርባለች። በከብቶች እርባታ ዘርፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር የሆነውን የከብቶች መኖ እጥረት ለመከላከልም በእርሻ ቦታዋ የከብቶች መኖን ማምረት ቀጥላለች። በቀጣይም ምርቱን በስፋት ለማምረት ዕቅድ ያላት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከሁለት የእርሻ ቦታ ጥሩ ምርት አለ ከተባለ በአማካኝ ከ28 እስከ 30 ሺ ኪሎ ግራም ምርት ይሰበሰባል። ዝቅተኛ ከሆነ ደግሞ ከአምስት እስከ ስድስት ኪሎ ግራም ታገኛለች፡፡
መንግሥት የኢንቨስትመንት መሬት ለባለሃብቱ ሲያቀርብ የአካባቢው ማህበረሰብ ከኢንቨስትመንቱ የሚጠቀመው ነገር እንዲኖር ታሳቢ በማድረግ መሆኑን የተረዳችው ወይዘሮ በረከት፤ ለእርሻ ሥራዋ በተሰማራችበት አካባቢ በርካታ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን እየተወጣች ትገኛለች። ለአብነትም በደቡብ ክልል ብላቴ ላይ የጤና ኬላ ለአካባቢው ማህበረሰብ እየሠራች ሲሆን በኦሮሚያ ደግሞ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያስገነባች ትገኛለች፡፡
“ሀገሬ ላይ ሠርቼ እለወጣለሁ፤ ሀገሬንም እለውጣለሁ፤ ብዙዎችን በመጥቀም ለአገሬ ውለታዋን እከፍላለሁ” በማለት ከምትኖርበት አየርላንድ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርታለች። ምንም እንኳን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች የገጠሟት ቢሆንም ተስፋ ሳትቆርጥ ችግሩን ተቋቁማ ለአገሯ የድርሻዋን ለማበርከት በቁጭት ትሠራለች።ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ነውና ብሂሉ በአሁኑ ወቅት ለ130 ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከአራት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታልም ማስመዝገብ ችላለች፡፡
ከእርሻ ሥራዋ ጎን ለጎን በአካባቢ ጥበቃ ላይ በርካታ ችግኞችን በመትከል ለዛፍና አትክልቶች ያላትን ጥልቅ ፍቅር መወጣት የቻለችው ወይዘሮ በረከት፤ በደቡብ ክልል ኦቢቻ ወረዳ ላይ ብቻ 84 ሺ የሚበላ ፍሬ የሚሰጡና የማይሰጡ፤ አገር በቀልና የውጭ ዛፎችን መትከል የቻለች ሲሆን በኦሮሚያ ክልል አርሲ ላይም እንዲሁ ከ100 ሺ በላይ አገር በቀልና የውጭ ዛፎችን ተክላለች፤ በቀጣይም ዛፍ ተከላውን አጠናክራ የምትቀትል እንደሆነ ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት አምርታ ለገበያ እያቀረበች ያለውን ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬ በቀጣይ እሴት በመጨመር ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ዕቅድ አላት። ለአብነትም ቲማቲም ድልህና ጁስ ፣ ካቻፕና ሌሎችንም ፕሮሰስ በማድረግ በስፋት የማምረትና ወደ ውጭ ገበያ በመላክ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል ማድረግ ነው፡፡
ዘርፉን ማስፋት ሲቻል በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችንም ይዞ ማደግ ይቻላል የምትለው ወይዘሮ በረከት፤ ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ያመርቱ የነበሩ አርሶ አደሮች በአሁኑ ወቅት ግን እርሷ በምታደርገው እገዛ ሁለትና ሶስት ጊዜ ማምረት እንዲችሉ አድርጋለች። ለዚህም ከረጅም ርቀት ውሃ ጠልፋ በማምጣት እንዲሁም የእርሻ ቦታዋን አልፎ የሚሄድ ጎርፍን በማስቆም ወደ እርሻ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ትጠቀማለች። በተጨማሪም ምርጥ ዘር በማባዛት፣ ማዳበሪያ በማቅረብ ለምታግዛቸው አርሶ አደሮች መሬታቸውንም በትራክተር እንዲያርሱ ምክንያት ሆናለች፡፡
ከግብርና ሥራ ጋር ተወዳጅታ በርካታ ችግሮችና በማለፍ ስኬታማ መሆን የቻለችው በረከት፤ ሁሉም ሰው ከልቡ ለአገሬ ብሎ በቁጭት መሥራት ከቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቷን መለወጥ የሚቻል መሆኑን ስትናገር፤ በተለይም በውጭ አገር ያሉ ዲያስፖራዎች በሰው አገር ተቀምጠው እንዲህ ቢሆን እንዲያ ቢሆን ከሚሉ ወደ አገራቸው ገብተው ማልማት ቢችሉ ከራሳቸው ባለፈ አገርን መለወጥ እንደሚቻል ትመክራላች።ለዚህም እርሷ ምስክር ናት። የማይቻል የሚመስለውን ችላ ጫካ መንጥራ ከባድ የሚባለውን የግብርና ሥራ በስኬት ተወጥታዋለች። እኛም የእርሷን ምክር በመዋስ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ያለችን አንድ አገር ናትና ሰርተን አገራችንን እንለውጥ በማለት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014