“መልክአ” – ሲበየን፤
“መልክአ” የሚለው ቃል በስፋት አገልግሎት ላይ ውሎ የምናገኘው ለሃይማኖታዊ ጉዳዮች ነው።በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለእምነታቸው መስዋዕትነት ከፍለው ያለፉትንና በቀኖናዋ መሠረት ተከብረው የተለዩትን የጻድቃን፣ የሰማዕታትና የቅዱሳን ገድሎች የምትተርከው “መልክአ…” የሚለውን ገላጭ ቃል በመጠቀም ነው።“መልክአ” ውጪአዊውንና አካላዊውን ላህይ (መልክ፣ ውበት፣ ወዝ፣ ደምግባት፣ ግርማ ሞገስ) ለመግለጽ የሚውል ብቻም ሳይሆን ውስጣዊ ብቃት፣ ንጽሕናንና ቅድስናን የሚያመለክት ጭምር ነው፡፡
“መልክአ” በሚል ርእስ ኢትዮጵያን ለመግለጽ የተፈለገበት ዋና ጉዳይ የገጸ ምድሯን አማላይ ውበት፣ የወንዝና የተራሮቿን ሞገስ፣ የታሪካዊ ቅርሶቿን ድምቀትና ክብር ለመተንተን ተፈልጎ አይደለም።እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ሃብቶቿ፣ ኩራቶቿና የፈጣሪ ስጦታ የሆኑ ፀጋዎቿ በሚገባ ሲተዋወቁና ሲገለጹ ስለኖሩና ዛሬም በስፋት እየዋወቁና እየተገለጹ ስለሆነ ዜጎቿ ብቻም ሳይሆኑ ባዕዳንም ጭምር ለእነዚህና ለመሰል ውጫዊ ገጸ ምድሯ በቂ እውቀት እንዳላቸው ይታመናል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የሚሞከረው የአገሬ ፊት በወቅት ወለድ ችግሮችና መከራዎች፤ በውጫዊ ተጽእኖዎችና በውስጣዊ የቤት ጉዳዮቿ ምክንያት ላይዋ ጠውልጎ እንደምን ማዲያት ለብሳ እንደተከፋች ለማመልከት ተፈልጎ ነው።ማዲያት (Melasma) በፊት ቆዳ ላይ የሚከሰት የጤንነት ችግር ነው።አብዛኛውን ጊዜ በሽታውን በተመለከተ በምክንያትነት የሚገለጸው የሰውነታችን ሆርሞን መዛባት ሲገጥመው እንደሆነ በዘርፉ ባለሙያዎች ተረጋግጧል።Progesterone እና Estrogen የሚባሉ ሆርሞኖች ሲዛቡ በቆዳ ስር የሚገኙ Melanin የተባሉ ለቆዳ ቀለም መለወጥ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሆርሞኖችን ያባዛሉ።እነዚህ የተባዙ ሆርሞኖች ደግሞ ቆዳ ላይ ተጽእኖ በመፍጠር ለህመምና ለስቅቅ ይዳርጋሉ።
ለማዲያት መፈጠር በዋነኛነት ምክንያቱ ከላይ የተጠቀሰው ሳይንሳዊ ትንታኔ ይሁን እንጂ ጭንቀትና ድብርትን የመሳሰሉ እረፍት የሚነሱ የውስጥ ስሜቶች ሲስተናገዱም ማዲያት ሊከሰት እንደሚችል ተረጋግጧል።አብዝቶ ለፀሐይ መጋለጥና በእርግዝና ወቅትም አልፎ አልፎ ይሄው መልክ አጥፊ ጸር እንደሚያጋጥም ሐኪሞች በማረጋጊያ ምክራቸው ውስጥ አጽንኦት ይሰጡበታል።ሕመሙን ለማስወገድና ለመከላከልም ብዙውን ጊዜ በፋብሪካ ውስጥ ከሚመረቱት መድኃኒቶች ይልቅ ጥንቃቄ ታክሎበትና ምጣኔው ተስተካክሎ ቤት ውስጥ በሚዘጋጁ ባህላዊና ተፈጥሯዊ “መቆነጃጃዎች” እና ፈዋሾች መጠቀም ቢቻል ተመራጭ እንደሚሆንና የጎንዮሽ ጉዳቱም እንደሚቀንስ የዘርፉ ሐኪሞች አበክረው ይመክራሉ፡፡
መልክአ ኢትዮጵያን ለማዲያት የዳረገው ዋነኛ ችግር ከውጭ አካላት የሚመጣው ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን ከውስጧ የሚመነጨው የእኩያን ልጆቿ ተደራራቢ ችግር እንደሆነ እምባችን ተሟጦ እስኪደርቅ አስለቅሶናል።ያረገዘቻቸው መከራዎቿም
ፊቷን ለማዲያት ዳርጎታል።ከአሁን ቀደም ደጋግሜ የጠቀስኩትና በዘመነ ተማሪነታችን አዘውትረን የምናነበንበው የመምህሬ የዶ/ር ኃይሉ አርአያ አንድ ግጥም ተቆንጥሮ ቢታወስ ከዛሬው ርእሰ ጉዳይ ጋር በሚገባ ስለሚገጥም ጥቂት ስንኞችን መዘን እንድንቆዝምባቸው መልካም መስሎ ታይቶኛል፡፡
“ይኸው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር፤ ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ፊቷን ያከሰላት ጥቁር ያስለበሳት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡”
የአገሬ ችግር ለምን እንደ መዥገር ተጣብቆና ተጣብቶን የፈውስ አቅም እንዳሳጣን አስበንም ሆነን ተመራምረን መንስኤው “ይኼ ነው” ለማለት እንደተቸገርንበት ዘመን ጠብቶ ነግቷል። የአገሬን ዘመን ለመግደል እያደቡ ያሉት የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች ሴራና ተንኮል ያነሰን ይመስል የራሳችን በምንላቸው የእንግዴ ልጅ ሽሎች እነሆ የአገር መልክ ወይቦ፤ የእኛም ኑሮ ተመሳቅሎ በልዩ ልዩ ወጀቦች እንደተላጋን “ኑሮ ካሉት…” እያልን፤ ኑሮን እየገፋን ሳይሆን ኑሮ ራሱ እያላጋን ዕድሜያችንን እየቆጠርን ወደ ፍጻሜያችን እንገሰግሳለን። ቀብራችንን በውዳሴና በአበባ እያስዋብንም በቁም ያላማረብንን የኑሮ ሳንካ በሞታችን ተበቅለን በእንባና በአደባባይ ስጦታ እንከበራለን፡፡
ለዚህ ጸሐፊ እንቆቅልሽ ከሆኑበት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱና “ለካስ በውስጣችን ሸሽገን የኖርነው ይህንን ሁሉ ጉድ ነው!” በማለት አጃኢብ የሚሰኝበት አንዱ ትዝብቱ መመሰጋገን ብርቅ፤ መደናነቅ ውድ የመሆኑ ጉዳይ ነው። ጥቂት ላፍታታው። በአገር ሰማይ ስር መልካም ተግባራት ሲስተዋሉ መተቸት፣ በጎ እቅዶች ጥንብ እርኩሳቸው እንዲወጣ መረባረብ፣ ደሃ ሲደገፍ መተቸት፣ መሪዎች ከሕዝብ ጋር አደባባይ ሲውሉ መቃረን፣ ስራ በዝቶባቸው ከሚዲያ ገለል ሲሉ ማሟረት፣ ለመሆኑ ምን ይሉት “የአገር ባህል አባዜ” ነው ጎበዝ? እውነት ነው የኢትዮጵያ ችግሯ ዘርፈ ብዙ መሆኑን እንኳን ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ቀርቶ ለሌሎች ባዕዳንም ሳይቀር እንደተገለጠ መጽሐፍ በጉልህ የሚነበብ ነው።አንዳንዱን እንጠቃቅስ፡፡
የእርስ በእርስ ጦርነታችንና መጠፋፋታችን፣ ከመደማመጥ ይልቅ “ውረድ እንውረድ” እየተባባልን መፎከራችን፣ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ተጻራሪ መንፈስን እየካደምን ሰይፍ መማዘዛችን፣ ፖለቲካ በሚሉት ቁስላም ደዌ ከተለከፍንበትና ከምንለከፍበት ሴራ ራሳችንን ነፃ በማውጣት ለአገር ክብር ከበሬታ ለመስጠት አገንጋኝ መሆናችን፣ ኢኮኖሚው እንዳይረጋጋ “የባህር ጃዊሳ” ሆነን የነውጥ ሰበብ መሆናችን፣ ፍትሕን በቂም፣ ርትዕን በበደል ማርከሳችን ወዘተ. በዚህ ሁሉ እንቅልፍ በሚነሳ አበሳ የኢትዮጵያ መልክ በማዲያት ቢወረር ያንስ ካልሆነ በስተቀር በዛ አያሰኝም፡፡
የአገር ማዲያት በአንድ ሁኔታና ወቅት ብቻ ተገልጦና አሳቅቆ የሚያልፍ የግል ደዌ አይደለም። ተስቦው ከትውልድ ትውልድ ተሸጋግሮ የሚበክል ነው።ለነገውም ትወልድ ይቀጥላል፣ ይገሰግሳል፣ ይጓዛል። ዛሬ ኢትዮጵያን ጥቁር የሀዘን ጨርቅ ለማልበስ ብቻም ሳይሆን ቢሆንላቸው በሩቅ ሆነው በከፈን ገንዘው ሊቀብሯት የሚፈልጉ ኃይላት ቁጥርም በዋዛ የሚታይ አይደለም።እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ጉዳይ ደግሞ ከገዳዮቿ ጋር የሚያብሩት “በላዔ አገር” ዜጎች የራሴ የምትላቸው “ፍልፈሎች” መሆናቸው ነው፡፡
የአገር ፊት ፈክቶ ላለማየት የተማማሉት ጠላቶቿ ፍላጎታቸው ሁሌም ኢትዮጵያ ሀዘንተኛ መስላ እንድትታይ መትጋታቸውና ዐይናቸውን ለመልካምነት አሳውረው የሚቃዡት ስቃዩዋ እንዲበረታ ለማድረግ ነው።የአገር ልማት ጉዳይ ሲነሳ የተለከፉበት የክፋት አብሾ እያስገዘፈ ያስለፈልፋቸዋል።መልካም ሲታቀድ መንፈሳቸው እየተረበሸ ጨርቃቸውን እስከ መጣል ያደርሳቸዋል።እነርሱ የሚረኩት በስቃይና በሞት ዜና ነው።የሰላምና የደስታ ዜና ሲሰሙ ውስጥ-ውጫቸውን ያሳክካቸዋው። ያስፎክታቸዋል። ያቅበዘብዛቸዋል። እምባ እንጂ የሕዝብ ዕልልታ መስማትም ያጥወለውላቸዋል። ቢሆንላቸው ኢትዮጵያ በዓለም ፊት ከምትከበር ይልቅ ተዋርዳ መሳለቂያ ብትሆን ፈቃዳቸውና “ሰይጣናዊ ጸሎታቸው” ጭምር ነው፡፡
አገር በማፍረስ ፈራሽ ሥጋቸውን ማደለቡ ዋናው አጀንዳቸውና መሪ ሃሳባቸው ነው። የመልክአ ኢትዮጵያ ገድል በዓለም አደባባይ ፊት ከሚነበብ ይልቅ ሽንፈቷ እየተተረከ ብትዋረድ ምርጫቸው ነው።ከጠላት ጋር አብረው ለማሴርም የቀን እረፍትም ሆነ የሌት እንቅልፍ አይናፍቃቸውም። ሁሌም የሀዘን ጨርቅ እንደመተሩላት፣ የመቀበሪያ ጉድጓድም እንደማሱላት ውለው ያድራሉ።ዛሬ እውነቱን እንነግራቸዋለን።እነርሱ ራሳቸው ተዋርደው እውነት እርቃናቸውን ታስቀራቸዋለች እንጂ ኢትዮጵያ እንደሆነች ቢያደነቅፋትም ተንገዳግዳ ፀንታ መቆም ታውቅበታለች። ይብላኝ ቀባሪ አጥቶ አደባባይ ለተሰጣው በድን ህሊናቸው። ይብላኝላቸው በውጭ ልብስ ቢጀቦኑም የውስጥ ስብዕናቸው ተራቁቶ እርቃናቸውን ለሚኖሩት የውስጥ ጠላቶች!
እርግጥ ነው የአገሬ ፊት በማዲያት አልተጠቃም ማለት አይቻልም።ከሃዲያኑ “የይሁዳ ልጆች” ለሞት አሳልፈው ሊሰጧት በጦርነት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የውስጥ አሻጥሮች “መስቀል በማሸከም” ወደ ጎልጎታ ሊገፈታትሯት ሞክረዋል፤ አስሞክረዋልም። በዓለም አደባባዮች ፊት በመቆምም “ትሰቀል!” እያሉ “ፈራጅ ነን ላሉት ጲላጦሳዊያን” አሳልፈው ለመስጠት ሞክረዋል። የአውሮፓዎቹና የአሜሪካኖቹ ጲላጦሳዊ ስብስቦችም ከአንዴም አሥር ጊዜ በወንጀል ሊከሷት ፋይል ከፍተው ፎክረዋል። “እንኳን ከተፎከረ ከተወረወረም ያድናል” እንዲል የሕዝባችን እምነት እውነቱና ንጋቱ እየጠራ ሲሄድ የመዘዙትን የክፋት ሰይፍ ወደ ሰገባው ለመመለስ እየተገደዱ ነው፡፡
እርዳታን ለማስፈራሪያ፣ ብድርን ለድርድር፣ ድጋፍን ለማእቀብ ቅደመ ሁኔታነት እያቀረቡ ማዲያት የአገሬንና የሕዝቧን ፊት እንዲወር ብዙ ጥረትና ሙከራ አድርገው አልተሳካላቸውም። ጥርሳቸው ውስጥ ከተው ለማላመጥ ሞክረውም “የብረት አሎሎ” ሆናባቸው ተደናግጠዋል። ለሰላም እንዳትዘምር ቅኝቷን ወደ ሀዘን እየለወጡ ሙሾ እንድታሞሽ ያልፈነቀሉት ድንጋይ፤ ያልመለመሉት አስለቃሽ አልነበረም። የሕዝቧ ጸሎትና የፈጣሪዋ ተራዳኢነት ታክሎበት ኢትዮጵያ እንደተከበረች ትኖራለች እንጂ “በጅብ ቆዳ የወጠሩትን ከበሮ ቢደልቁም” ደንብራ ወጥመዳቸው ውስጥ አትገባም።መልኳን ለማዲያት የዳረጋት የውጭ ተግዳሮት ከጦረኞቹ የራሷ የሞት ሱሰኛ ልጆቿ ጋር ተዳምሮ ሲገመገም ዓይነቱም ሆነ መልኩ ይህንን ይመስላል፡፡
ሌላው የማዲያቷ በሽታ ምክንያቱ ከውስጥ እየተፈለፈለ ጤናዋን የሚያውከውና እለት በእለት የሚስተዋለው ሥር የሰደደ አገራዊ ችግር ነው።“በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ ክብራቸው ነውራቸው በሆነ በአንዳንድ መንግሥታዊ ሹመኞችና ባለሙያዎች እየተፈጸሙ ያሉ ግልጽ በደሎች ሕዝቡን እየቆሰቆሱ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየመሩት እንደሆነ መወትወት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል። መንግሥት እየሰማ እንዳልሰማና እያየ እንዳላየ በመሆን እስከ መቼ እንደሚቆይ ግራ ያጋባል።ተስፋውና ተግባሩ አልጣጣም ሲለንም የእንቆቅልሹ ፍቺ ተወሳስቦ ግራ ያጋባናል።
በየትኛውም የመንግሥትም ሆነ የግል ሴክተር ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ለተገልጋዮች የእርካታ ምንጭ ከመሆን ይልቅ ማስለቀስን ለምን እንደ መርህ እንደሚቆጥሩት ለማሰብና ለማሰላሰል ያዳግታል።ሰው በወገኑ ደስታ ይደሰታል እንጂ እንዴት ባለጉዳይን በማጉላላት መደሰት ይቻላል? ይሄ ተቀዳሚውና የአገሬን ፊት በማዲያት አድምቆ ያጠቆረው መከራዋ ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገልግሎት የሚሰጠው በጉቦ ብቻ መሆኑ የታወጀ እስኪመስል ድረስ “ይህን ያህል ክፈል!” ማለት ትዕዛዝ እንጂ የድብቅ ሹክሹክታ መሆኑ አብቅቷል። በተለይም ከመሬት አቅርቦት፣ ከሕጋዊ ካርታና ከተያያዥ አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ያለ ጉቦ ተፈጸሙ የሚል አንድ ዜጋ ማግኘት እስከሚያቅት ድረስ የመንግሥት መዋቅር ክፉኛ ተተብትቦበታል፤ ተግማምቷል። ተጣሞ ያደገው የፍትሕ አሰጣጥ ሥርዓትማ በማንና በምን እንደሚቃና ለመተንበይ እስከሚያስቸግር ድረስ የሕዝብ እምባ ማከማቻ ጎታ ወደ መሆን ተቀይሯል ማለቱ ይቀላል፡፡
መንግሥታችን ሰሚ ጆሮና አንባቢ ዐይን ካለው አንዳንድ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን እንጠቁም።እንደ ስልጡን አገራት ልምምድ በመንግሥታዊም ሆነ በሕዝባዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ የየዕለቱን የአገልግሎት አሰጣጣቸውን የሚታዘቡ ዜጎች ተራ ተደልድሎላቸው በየተቋማቱና በየፍርድ ቤቶች ቢመደቡና የዕለት ተዕለት ተግባራቱን አክብረው አገልግሎት ሰጪዎቹን በዐይነ ቁራኛ መከታተል እንዲችሉ ቢደረግ መፍትሔ ሊገኝ ይችል ይሆናል፡፡
መቼም አንድ በጎ ሃሳብ ሲሰጥ ማፋረሻውን ማዘጋጀት ያደግንበትና ያሳደግነው “ባህላችን” ስለሆነ “ምን ሲደረግ ይታሰባል” የሚሉ ፎካሪዎች ዘራፍ እንደሚሉ አይጠፋንም። አቅራሩም አላቅራሩም ቢቸግረን ይህንን ሃሳብ የምናቀርበው የአገራችን ፊት ከማዲያቱ እንዲፈወስ ስለሆነ መንግሥት ሆይ “ሰምቻለሁ በለን!” ማረጋገጫውን ስጠን ወይንም እንደተለመደው ማፋረሻውን በቁጣ ግለጽና ብእራችንን አደብ አስገዝተን እንደጨስን ኖረን እንለፍ። አቤት! አቤት! አቤት! የመንግሥት ያለህ! ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 6/2014