‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንዲሉ የሁኔታዎች ጥንካሬና አያያዝም ገና ከጅማሬው ይናገራል። እንደተባለው ሆኖ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ሳይወጣ፣ ከሰፌድ፣ ሞሰቡ ሳይዘረጋ፣ ከአፍ ከጉሮሮ ሳይገባ በእይታ ብቻ ያጠግባል። እንጀራው ከምጣዱ ቢበስልም፣ ባይበስልም ታስቦ ተጋግሯልና በረከት ቱርፋቱን መገመቱ አይቸግርም።እንዲህ ዓይነቱ እንጀራ ከምጣዱ ሳለ፣ ዓይኑ ያምራል፣ ወዘናው ይለያል፣ ሽታ መዓዛው ልብ ይገባል፡፡
ይህ ዓይነቱ እንጀራ በወጉ ቀርቦ ‹‹እነሆኝ›› የተባለ እንደሁ በዓይን ብቻ ለሰጪ፣ ተቀባዩ ያጠግባል።ለሚሹት ሁሉ ድንቅ ሆኖም በርካቶችን ከማዕድ ያጋራል።እንጀራው አስቀድሞ እንዲያጠግብ ሆኗልና ስስት ይሉት አያልፍበትም። ሲሳይ በረከቱ፣ ተጋባዡን እያባዛ፣ በበረከት እየበዛ ማጥገቡን ይቀጥላል።ከሞሰቡ የቀረበው፣ ከማጀቱ የሚቆረሰው ለምለም እንጀራ ለዕልፎች ፍላጎት ምላሽ ሆኖ ተርፎ በጥጋብ ይነሳል።
አንዳንዴ አንዳንድ ጉዳዮች እንዲህ ናቸው።ገና ከጅማሬያቸው ውጤታቸው ይገመታል። እንዲህ ዓይነቶቹ በጎ ልማዶች በበረከቱ ቁጥር ለብዙኃን መልካም ምሳሌ ይሆናሉ።ዛሬን በጥንካሬ ተሻግሮ ነገን በተሻለ ለመራመድም ያግዛሉ፡፡
የሚያጠግብ እንጀራው ዓይነት ምሳሌዎች መልካም እንደሆኑ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው። ሁሌም እየሰጡ፣ ከበረከታቸው እያካፈሉ፣ በጎደለው እየሞሉ ይጓዛሉ። አስቀድመው ፍሬያቸውን በመልካም መሬት አብቅለዋልና ለችግሮች መፍትሄ መሆናቸው ዕሙን ነው፡፡
አንዳንድ እውነታዎችን ስናስተውል ግን ከእንዲህ ዓይነቶቹ ምሳሌዎች የራቁ ሆነው ይገኛሉ።እንዲህ የምንላቸው ጉዳዮች ምንአልባትም እንደምጣዱ እንጀራ አስቀድመን የተረክንላቸው፣ ጅማሬያቸውን አይተን በአድናቆት የተገረምንባቸው ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ በአድናቆት የምንደመምባቸው ጉዳዮች በጠዋቱ ውጥናቸው ሲጀመርና መሠረታቸው ሲጣልም ለዝንት ዓለም የሚቆዩ እስኪመስለን ነው። ከስር መሠረታቸው አንስቶ የሚሰጣቸው ትኩረት፣ ድንቅ በመሆኑም ተሳታፊያቸው ይበረክታል።ተከታያቸው ዕልፍ ይሆናል። በከተማችን የሚስተዋልን አንድ እውነታ በዋቢነት እናንሳ፣ የአካባቢን ጽዳትና የንጽህናን ጉዳይ፡፡
‹‹የአፍሪካዋ መዲናችን›› እያልን በኩራት የምንጠራት አዲስ አበባችን ሁሌም ከቆሻሻ ፈተናዋ ጋር ዓመታትን ዘልቃለች።ይህች ዕድሜ ጠገብ መዲና ከስሟ ቀጥላ የምትታወቅበት የንጽህና ጉዳይም መለያ ሆኗት ፈተናዎችን ስትጋፈጥ ኖራለች።እስከ ዛሬ የአፍሪካ መቀመጫ ሆና በጽናት ትዝለቅ እንጂ ተቀናቃኞቿ ጥቂቶች አልነበሩም፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ ትሆን ዘንድ የማይሹ አካላት ከፍላጎታቸው በስተጀርባ እንደምክንያት ይጠቅሱት የነበረው አንዱ ነጥብ የቆሻሻውን እውነታ ነበር።እነሱ በእጃችን የገባውን መልካም ዕድል ለመንጠቅ ችግሩን እንደ ሰበብ ሲጠቀሙበት ኖረዋል።በእነሱ አገር ጎዳና አንዳች ጉድፍ እንደማይታይ ሁሉ አንዳንድ ወንድም አገራት የእኛይቱን ታሪካዊ አገር አጠልሽተው ቀዳሚውን ስፍራ ለመቆናጠጥ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ሞክረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረትን በቀዳሚነት እንደመመስረቷ የኅብረቱ መቀመጫ አክሊል ቢደፋላት አያንሳትም።ይህን ታላቅ ክብር ለመጎናጸፍ አንዳች የማይሳናት ድንቅ ከተማ በሆድዕቃዋ አጠራቅማ ያኖረችውን ጠንቅ አስወግዳ የዓመታት ስሟን መቀየር ያለመቻሏ ደግሞ አስገራሚ ያደርጋታል፡፡
አዲስ አበባ እንደስሟ ትቀጥል ዘንድ ስር ነቀል የጽዳት ለውጥ ያሻታል። ዘለቄታዊ መሠረት ያለውን ሂደት በተግባር ለማሳየትም ወረት የለሽ እንቅስቃሴ ሊኖር ግድ ይላል። አንዳንዴ ይህን መሰሉ ድርጊት ያሳይ ይመስል ፈጣን እርምጃ ቢጤ ሲተገበር ይስተዋላል። በድንገት በከተማዋ ጎዳናዎች መጥረጊያ የያዙ፣ ጋሪና የጽዳት መሣሪያዎችን ያሟሉ ‹‹ያገባናል›› ባዮች ተበራክተው ይታያሉ፡፡
ይህን ሰሞን ታዲያ በከተማዋ ጥግ አንዳች ቖሻሻ ተብዬ የሚታይ አይመስልም። አጉል ሽታና የፍሳሽ ቱቦዎች ሳይቀሩ በነበር የሚቀሩ ይመስላል። በቋሚነት ሥራውን ከያዙት ባለሙያዎች ባላነሰ በየዕለቱ የቆሻሻን ዘር ድራሹን ለማጥፋት የሚተጉ ብርቱዎች ይበራከታሉ። እንዲህ በሆነ ጊዜ የሚዲያ አካላትን ዓይንና ጆሮ ይስባሉ፣ ተግባራቸውን የሚያደንቁ፣ ከዓላማቸው የሚዘነቁ መሰሎችም ይከተሏቸዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሁሉም አካባቢውን ለማጽዳት ከመጥረጊያና ከጽዳት ዕቃዎች ጋር መታየት ልምዱ ይሆናል።የዜና ሽፋኑና ቅስቀሳው ሁሉ ጽዳትና ንጽህና ሆኖ ይከርማል። አነቃቂ መልዕክቶች በየስፍራው ይለፈፋሉ። በርካታ እጆች ቆሻሻን ሊያነሱ፣ የጤና ጠንቆችን ሊያስወግዱ በአንድነት ያብራሉ።‹‹ወዮልህ!›› የተባለው ቆሻሻም ዳግም እንዳይታይ ባለበት፣ እየተጠረገና እየተቃጠለ ይወገዳል፡፡
አንድ ሰሞን የከተማዋ ሽታና ጠረን ተቀይሮ ዓይኖች ጽዱ ስፍራዎችን ያስተውላሉ። ንጹህ አየር ስፍራውን ተቆጣጥሮም እፎይታ በእጅጉ ይነግሳል።ይህኔ ትጋታቸው የተመሰከረ ብርቱዎች ተግባር ይወደሳል። ጅማሬውን ያስተዋሉ ታዛቢዎችም የሚያጠግብ እንጀራን ደጋግመው ይተርካሉ።ችግሩ እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም። ጅምርና በጎ ተግባራት እንደመነሻው፣ ጠንክረው ያለመቀጠላቸው እንጂ።
ብዙ ጊዜ በአንድ ወቅት የሚጀመሩ እንቅስቃሴዎች እንደመነሻቸው ሲቀጥሉ አይስተዋልም። አካባቢውን በጽዳት ተቆጣጥረው የሚቆዩ እጆች ወደነበሩበት ሲመለሱ አፍታ አይፈጁም። ጉዳዩን ነገሬ ብለው የወጠኑ በርካቶች መጥረጊያቸውን ለመወርወር፣ ጋሪያቸውን ጥግ ለማስያዝ ይጣደፋሉ።ይህኔ ቆሻሻው እንዳሻው ሊናኝ ዕድል ያገኛል።ልማደኞችም በቀድሞ መንገዳቸው ይቀጥላሉ፡፡
በእርግጥ ለጽዳት የተጉ ልቦናዎች እንዳሉ ሁሉ ለጥፋት የሚዘረጉ በርካታ እጆች አይጠፉም።የተሠራውን በጎ ምግባር አፈር አልብሰው ጭቃ የሚቀቡ ዕልፍ ናቸው።በቆሻሻ አጠቃቀም ላይ ያለው ልማድና አጉል ተሞክሮ ለዚህ እውነታ ማሳያ ይሆናል።ቀን አጠራቅመው ያዋሉትን ቆሻሻ ጨለማን ተገን አድርገው የሚበትኑ፣ ምሽቱን ጠብቀው የመጸዳጃን ቱቦን በእግረኞች መንገድ የሚለቁ አይታጡም፡፡
እናስብበት ከተባለ ግን የእነሱን ልቦና በመልካም መቀየር ይቻላል። መፍትሄው ጀምሩን ተግባር ድንገት ማቋረጥ አይደለም። መስመሩን ሳይቆርጡ በብርታት መቀጠል ያስፈልጋል። ሁሌም የአንድ ሰሞን ዘመቻ የመሆኑ እውነት ለዘለቄታዊ መፍትሄ የሚበጅ አይሆንም።ጅምሩን ቀጥሎ ዳር በማድረስ በጥንካሬ መጓዝ ግድ ይላል፡፡
‹‹ነገርን ነገር ያነሳዋል›› እንዲሉ እንደ ጽዳት ዘመቻው ዓይነት ተሞክሮዎችን እንምዘዝ ካልን በርካታ ልማዶችን ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ የአካባቢ ጥበቃዎችንና የስፖርት እንቅስቃሴዎችን። ለጉዳዩ መንደርደሪያ እነዚህን ርዕሶች ነካን እንጂ ስለሌሎች አስታውሰን እንወቃቀሰ ካልን ጊዜና ቦታው አይበቃንም፡፡
አንድ ሰሞን በመዲናችን አዲስ አበባ የአካባቢ ደህንነት እንቅስቃሴው በስፋት ተጠናክሮ እንደነበር አንዘነጋም።ይህ ወቅት ጨለማን ተገን አድርገው ማጅራት ለሚመቱ፣ በየአጋጣሚው ኪስ ለሚዳብሱ፣ አስፈራርተው ንብረት ለሚነጥቁ ዓይነተኛ መፍትሄ ሆኖ ሰንብቷል።ሁሉም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር ዘብ በቆመበት የወንጀለኞች እግር ተሰብሰቦ አንድ የመሆን ዋጋ ሲረጋገጥ ቆይቷል፡፡
ይህ አጋጣሚ ነዋሪው እርስበርስ እንዲተዋወቅና ችግሮችን በጋራ እንዲመክር አስችሎታል። መንገደኞች ያለሀሳብ እንዲራመዱ፣ ክፉ አሳቢዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ፣ አካባቢ ሰላም ውሎ እንዲያድር መልካም ተሞክሮን አጋርቷል፡፡ይህ ዓይነቱ ልማድ በየስፍራው ዕውን በሆነ ሰሞን ተሞክሮው እንዲቀጥል ያሰቡ፣ የደህንነት ጥበቃው ቋሚ እንዲሆን የተመኙ በርካቶች ነበሩ፡፡
የአጉል ልማድ ተሞክሮ ሆነና ይህ በጎ ጅምር አሁንም በድንገት መቋረጡን አይተን አረጋግጠናል። ነዋሪው እርስበርስ ፖሊስ በሆነበት አጋጣሚ የተገኘው ውጤት መልካም ለመሆኑ እሳትና ውሃን በእጅ ነክቶ የመለየት ያህል፣ ትርፍ ኪሳራችንን አውቀነዋል፡፡
የአንድ ሰሞን የዘመቻ አባዜ ተጸናውቶን እሱንም በጅምር እስክንቀጨው፣ የሰላምን እፎይታ ስናጣጥም ቆይተናል።‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ይሉትን ተረት ጀምረን ሳንጨርሰው የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ ተረትን አስከተልን እንጂ አያያዛችን በጎ ጅማሬ ነበር። ይህ እየወጠኑ መተዉ አጉል ልማድ በአንድ ሰሞኑ የስፖርት እንቅስቃሴ ላይም በስፋት ተስተውሏል፡፡
የዛሬን አያድርገውና የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም መንደሮቻችን የስፖርት ማዘውተሪያዎች ነበሩ።አስከፊውን የኮቪድ በሽታ ለመከላከል በርካታው በቤቱ በዋለበት አጋጣሚ ስፖርተኛው በዝቶ ጤንነቱን የሚጠብቀው ተበራክቶ ነበር።ዛሬ ግን ይህ ልማድ እጁን እንደመቱት ሕፃን ሽምቅቅ ብሎ ባለበት ቀርቷል፡፡
በጎ ሀሰቦችን ለመቀጠል እኮ የግድ ክፉ አጋጣሚዎች ሊኖሩ አይገባም። ከተማችንን በቋሚነት ለማጽዳት የበሽታዎችን ወረርሽኝ፣ መጠበቅ የለብንም።የአካባቢያችንን ሰላምና ደህንነት ለማስከበርም ንብረታችን እስኪዘረፍና ፣ በተደራጀ ቡድን ወንጀል እስኪፈጸምብን መጠበቅ አይኖርብንም፡፡
በቋሚነት የስፖርት እንቅስቃሴዎችን የግላችን ለማድረግም ኮቪድን የመሰሉ በሽታዎች ሰበብ ሊሆኑን አይገባም።ጅምራችንን ቀጥለን በመስመራችን ለመጓዝ የሚበጀንን ማወቅና መለየቱ ብቻ በቂ ነው። ለሁኔታዎች ሰበብ፣ በመፍጠር ማደግ የጀመረ ተስፋችንን አናቀጭጭ።ብቅ አልን ስንል በአጭር እየቀረን ወደኋላ አንመለስ። እንደጉብሊቷም ጋሜ አይተረክብን።
የእንትናዬ ፀጉር ሁልጊዜ ውበት፣ አምና ካንገት ነበር፣ ዘንድሮ ካናት።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2014 ዓ.ም