ዛሬ ለአገር ስለሚጠቅሙ አስፈላጊ ወጣቶች እናወራለን። አገር የምትፈልጋቸው ወጣቶች ምን ዓይነት እንደሆኑ እናወጋለን። እስኪ ልጠይቃችሁ አገራችን ናት ያልተመቸችን ወይስ እኛ ነን ያልተመቸናት? ይሄን ጥያቄ በመመለስ ቀጣዩን ጽሑፍ እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ። ቀደም ብዬ ያነሳሁትን ጥያቄ በራሴ አተያይ ለመመለስ ያህል፤ ለአገራችን ያልተመቸናት እኛ ነን ባይ ነኝ።
እኛ ለአገራችን ብንመች አገራችን ለእኛ የማትመችበት ምንም ምክንያት አይኖርም። እሷ የአባቶቻችን ሀቅ ናት። እሷ የደጋግ ልቦች ስፍራ ናት። እሷ የነምኒልክ፣ የነአብዲሳ አጋ፣ የነዘርዐይደረስ ርስት ናት። እኛ እንጂ እሷ ውሸት ሆና አታውቅም።
አገር እኮ የእኔና የእናንተ አስተሳሰብ ናት። በተዛባ አስተሳሰብ የፈጠርናትን አገራችንን አትመችም ብሎ ማሰብ ፍርደ ገምደል ያስብላል እንጂ ጀብድ አይሰጥም። ከዓለም ሀቆች አንዱ የትኛውም ሕዝብ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሀሳብ ከቆመ አገሩን እንደሚፈልገው አድርጎ መሥራት ይችላል የሚለው ነው። ብዙዎቻችን ወደ አገራችን ጣታችንን የምንቀስር ነን። እንደምታውቁት አገራችን ኢትዮጵያ ከአገሬው ሕዝብ ከፍ ያለ ቁጥር የያዘ ወጣት ካለባቸው የዓለም አገራት ውስጥ አንዷ ናት። ግን በሚፈለገው መልኩ ወጣቱ በአገር ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርግ አይታይም።
የአገሬ ሰው ወጣትነትን ከኃይል ጋር ሲያቆራኘው ‹ወጣት የነብር ጣት› ይላል። ወጣትነት የኃይል፣ ለውጥ፣ የብርታት አብራክ ነው። ያለምንም ጥርጥር ወጣትነት በአንድ አገር ላይ ሕዝብ የሚፈልገው፣ መንግሥት የሚፈልገው፣ ትውልድ የሚፈልገው የኃይል ሞገድ ነው። ወይም ደግሞ ለአንድ አገር ዋልታና ማገር ነው ብለን በአጭሩ ልንገልጸው እንችላለን። አሁን ላይ በኢኮኖሚ አቅማቸው የዓለምን ስልጣኔ በበላይነት የሚመሩ አገራት አንድ ወቅት ላይ ወጣቶቻቸውን የተጠቀሙ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በኢኮኖሚ ኋላ የቀሩ አገራት የወጣት ኃይላቸውን ሳይጠቀሙ ያለፉ እንደሆነ መገመት አይከብድም።
አገራችን ኢትዮጵያ በጉያዋ ብዙ ወጣቶችን ታቅፋ በመካንነት የምትኖር አገር ናት። የወጣቱን ኃይል፣ እውቀትና ጊዜ የሚፈልጉ በርካታ ማህበራዊ አገልግሎቶች ቢኖሩም በተፈለገው መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል የሚታይ የወጣት ኃይል የለም። አብዛኛው ወጣት ሥራ ፈጥሮ ከመሥራት ይልቅ የመንግሥትን እጅ የሚጠብቅ ነው። አብዛኛው ወጣት በሱስና በማይጠቅመው ነገር ጊዜውን የሚያጠፋ ነው። አብዛኛው ወጣት ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ በአቋራጭ መበልጸግን የሚናፍቅ ነው። አብዛኛው ወጣት በእውቀትና በምክንያታዊ ሀሳብ ከመኖር ይልቅ በስሜት የሚነዳ ነው። እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች ለአገርና ወገን ሸክም ከመሆን ባለፈ ለአገር የሚፈይዱት አንዳች ነገር የለም።
አገር ራዕይ ያለው ወጣት ትፈልጋለች። የሚሠሩ እጆች፣ በቅንነት የተሞሉ ልቦች ትሻለች። አገራችን ኢትዮጵያ ይሄን ሁሉ ወጣት ይዛ ለምን ድህ የሆነች ይመስላችኋል? በአንድ አገር ላይ የሕዝብ ቁጥር ወይም የወጣት መብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም። እጅ መሥራት ካልለመደ፣ አእምሮ ማሰብ ካልጀመረ፣ ልብ ትህትናን ካልተማረ የወጣት መኖር ብቻውን ጥቅም የለውም። ወጣት ኃይልና ብልጽግና የሚሆነው ከስንፍና ወጥቶ መሥራት ሲጀምር ነው። ተምሮ ሥራ ከመጠበቅ ሥራ ፈጥሮ ለሌሎች ዕድል መፍጠር ሲቻል ነው።
አሁን ላይ በሕዝብ ቁጥራቸው አነስተኛ ሆነው በኢኮኖሚ አቅማቸው የበለጸጉ ብዙ አገራት ሞልተዋል። እኚህ አገራት ምንም ተዐምር አልሠሩም የወጣት ኃይላቸውን በአግባቡ ነው የተጠቀሙት። ዋናው የሕዝብ ቁጥር መብዛት ሳይሆን የሕዝብ የሥራ ባህል ነው። የሥራ ባህል ባልዳበረባት አገር ላይ የወጣት መብዛት ብቻውን ችግር እንጂ መፍትሄ አይሆንም። የአገራችን ወቅታዊ ችግርም ከዚህ የዘለለ አይደለም። የተማሩ ብዙ ወጣቶች አሉን፤ ግን የመንግሥትን እጅ የሚጠብቁ ናቸው። ብዙ ወጣቶች አሉን፤ ግን ሥራ ፈጥሮ ለመሥራት የሰነፉ ናቸው። ብዙ ወጣቶች አሉን ግን ብዙ ጊዜአቸውን በሱስና በማይጠቅም ነገር ላይ የሚያሳልፉ ናቸው።
አገር የምትፈልጋቸው ወጣቶች ብርሃናማ ናቸው። በራዕይ የተሞሉ፤ ከትንሽ ነገር ተነስተው ትልቅ ቦታ ለመድረስ የሚታትሩ እንዲህ ናቸው። ይሄን ጽሑፍ የምታነቡ ወጣቶች አገራችሁ የእናንተን ኃይል የእናንተን እውቀት ትፈልጋለችና ለአገራችሁና ለሕዝባችሁ መልካም ነገር ለመሥራት ትጉ። የነገዋ የኢትዮጵያ ተስፋ በእናንተ እጅ ውስጥ ነው። ብዙ ያደረገላችሁን አገርና ሕዝብ ለማገዝ ትክክለኛ ጊዜ ላይ ናችሁና ከስንፍና ወጥታችሁ ወደ ልማት ግቡ። ዘረኝነት ለእናንተ አይመጥንም። ሱስና አልባሌ ነገር ጊዜአችሁን ከማባከን ባለፈ የሚሰጣችሁ ትርፍ የለም። ከትንሽ ነገር ተነስታችሁ ትልቅ ነገር መስራት ይቻላችኋል። ሁሉም ትልቅ ነገር ከትንሽ የተጀመረ ነው። ሁሉም ስኬታማ ሰው ከምንምነት የተነሳ ነው።
በእርግጥ ውስጣቸው አንድ ኃይል ነበር። እርሱም ስኬታማ የመሆን ጽኑ ፍላጎት ነው። እርሱም አገር የመለወጥ ጽኑ ምኞት ነው። ጽኑ ፍላጎት ካላችሁ እመኑኝ የፈለጋችሁትን መሆን ትችላላችሁ። ብዙዎቻችን ራዕይ አልባ ነን። በወጣትነታችን ውስጥ ለአገር የሚሆን ምንም የለም። ይሄ ደግሞ ወደ ፊት እንዳንሄድ የሚከለክለን አደገኛ ነገር ነው። መጀመሪያ የሁሉም ነገር መሠረት የሆነውን ራዕይ ልበሱ። ከዚያም ወደ ፈለጋችሁበት መሄድ ትችላላችሁ። ህልማችሁ ሀብታም መሆን ከሆነ፣ ህልማችሁ ገንዘብ ማግኘት ከሆነ፣ ህልማችሁ ቤትና መኪና ከሆነ በህልማችሁ በኩል የምታገኙት ነውና ይቻላችኋል። ሆኖም ራዕይ ገንዘብን መፍጠር ሲችል፤ ገንዘብ ግን ሁልጊዜ ራዕይን መፍጠር ይቸግረዋል።
ሁሉ ነገር እንዲኖራችሁ ከሁሉ አስቀድማችሁ መልካም ራዕይን የእናንተ አድርጉ። ከሁሉ በፊት የአገር ፍቅር ስሜትን ውረሱ። ራዕይና የአገር ፍቅር ስሜት አንድ ላይ ሲገናኙ ተዐምር የመፍጠር ኃይል አላቸው። በውስጣችን ከሁለት አንዱ ከጎደለ ግን የምንፈልገውን እኛን መሆን አይቻለንም። የዓለምን ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ታሪክ ብትበረብሩ ባለራዕይና በአገር ፍቅር ያበዱ ሆነው ታገኟችኋላችሁ። መጀመሪያ በአገር ፍቅር ስሜት እበዱ፤ በአገር ፍቅር ስሜት ስናብድ ርምጃችን ሁሉ አገር ወደሚጠቅም፣ ትውልድ ወደ ሚቀርጽ ነው የሚሆነው። በአገር ፍቅር ስሜት ስናብድ ሌሎችን ከማፍቀርና ከመውደድ ሌላ ለአልባሌ ነገር የሚሆን ጊዜ አይኖረንም። እንደ ወጣት ወጣቱን የምመክረው እንዲህ ነው፤ በአገር ፍቅር ስሜት እንዲያብድ።
ሰው አገሩን ሲያፈቅር ትህትናን ነው የሚማረው። ድሀ ወገኑን ከችግር ለማውጣት ራዕይ ነው የሚሰንቀው። የዚህ ዘመን ወጣት ትልቁ ችግራችን እንደ አባቶቻችን ያለ አስተማሪና በጸጋ የተሞላ ነፍስና ልብ በዙሪያችን ማጣታችን ነው። በዙሪያችን ያለው ነገር ሁሉ ለመለያየት፣ ተስፋ ለመቁረጥ መንገድ የሚከፍት ነው። ገንዘብ እያላቸው ራዕይ የሌላቸው ሰዎች አታውቁም? እኔ ግን አውቃለሁ። የምትፈልጉትን የሚሰጣችሁ ራዕያችሁ ነው። ራዕይ ያለው ዜጋ በመሆን የአገራችሁን ትንሳኤ እንድታበስሩ እለምናችኋለሁ። በወጣቱ ዘንድ በብዛት የተለመደውና ጥንካሬአቸውን የሚያጡበት አንዱና ዋነኛው ነገር ምንም የለኝም የሚል አፍራሽ አመለካከት ነው። ትልቅ የሚሆኑት ትንንሽ ነገሮች እንደሆኑ ገና አልገባንም። በአንድ ጊዜ ትልቅ ነገር የምንመኝ ነን። ትላልቅ ነገሮች የተቀመጡት ደግሞ ለሚሠሩና ለሚሞክሩ ነው።
አጠገባችን ያለን ትንሽ ነገር ወደ ትልቅ የሚለውጥ ህልምና ራዕይ ያስፈልጋል። ውስጣችን ለመለወጥ የሚሆን በቂ ራዕይ ስለሌለ ሁልጊዜ ሰበበኞች ነን። ልባም ሰው ሰበብ አይፈልግም። ተነስቶ ይሠራል እንጂ። የቁጥሮች መጀመሪያ ዜሮ አይደል? ዜሮ የሌለበት ትልቅ ቁጥር ታውቃላችሁ? ትልቅ ነገር ከፈለጋችሁ ከዜሮ ጀምሩ፤ ከምንምነት ተነሱ። ታላቅ ነገር ያለው ምንምነት ውስጥ ነው። ለምሳሌ ብናይ ሊንደን ጆንሰን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከመሆናቸው በፊት ያልሠሩት ሥራ አልነበረም። በልጅነታቸው ጫማ ጠርገዋል፣ የጽዳት ሥራ ሠርተዋል፣ ሳህን አጥበዋል፣ አትክልተኛ ሆነው ሠርተው ነበር። በእኛም አገር ከትንሽ ነገር ተነስተው ትልቅ ቦታ የደረሱ በርካታ ሰዎችን አውቃለሁ።
እናንተም ህልማችሁ ማደግና መለወጥ ከሆነ አሁን ካላችሁበት ቦታ ላይ ተነስታችሁ የምትፈልጉትን መሆን ትችላላችሁ። ለምንም ነገር ህልማችሁ ይቅደም። ለምንም ነገር የአገር ፍቅር ስሜታችሁ ይቅደም። የምንፈልገው ድንቅ ነገር ሁሉ ህልማችንን ተከትሎ የሚመጣ ነው። መጀመሪያ ከሱስ እንውጣ። መጀመሪያ ከዘረኝነት ነፃ እንሁን። መጀመሪያ ለአባቶቻችን ሥርዓት እንገዛ። መጀመሪያ የተማረ ሳይሆን የተባረከ ትውልድ ለመሆን እንጣር። ውስጣችን ሳይጠራ፣ አስተሳሰባችን ሳይስተካከል የምናሳካው ጥሩ ነገር የለም። በራዕይና በአገር ፍቅር የታጀበ ለድሀ ሕዝብ የሚሆን ጥሩ ሀሳብና ጥሩ ምኞት ይኑረን። በራዕይ መኖር ስልጣኔ ነው።
በዚህ ስልጡን ዘመን ላይ እየኖርን ጊዜን በማይጠቅም ነገር ላይ እንደማሳለፍ የሚቆጭ ምንም ነገር የለም። ጊዜው ለራሳችንም ለሌሎችም መልካም ሥራ የምንሠራበት ወቅት ነው። ዝም ብሎ ከመኖር መውጣት አለብን። እስካሁን ለራሳችንም ለአገራችንም ሳንበጅ በከንቱ የኖርንበት ጊዜ ነበር። ከእንግዲህ ግን በዋጋ መኖር አለብን። ለአገር ስጋት ከመሆን ወጥተን ክብርና ኩራት ወደመሆን መሸጋገር አለብን።
የምንደክመውም የማንበረታውም በውስጣችን ተስፋ ሲጠፋ ነው። በውስጣችን ተስፋቢስ ስንሆን በሕይወታችንም ተስፋ ቢስ እንሆናለን። በውስጣችን ስንበረታ በዓለምም እንበረታለን። ይሄ ማለት ነጋችን የሚፈጠረው በእኛው አስተሳሰብ ልክ ነው ማለት ነው። ብሩህ ነገ እንዲኖረን ብሩህ አስተሳሰብ ሊኖረን ግድ ይላል። ከአይሳካልኝም አስተሳሰብ ወጥተን ወደ ይቻላል፤ ወደ ይሳካልኛል ሀሳብ መምጣት አለብን።
ለዚህም ወጣቶች ኃይላችሁን መግደል የለባችሁም። አገራችንን ሳንጦራት፣ ለቁም ነገር ያበቃንን ድሀ ወገናችንን ሳንደግፍ ወጣትነታችን እንዳያልፍ እንፍራ። ድህነት የማይንደው፣ ችግር የማይበግረው ከተስፋ መቁረጥ ከፍ ያለ የይቻላል መንፈስን በውስጣችን እንገንባ። ለመለወጥ ከተሰናዳን መለወጥ ይቻለናል። ምንም ነገር ለማድረግ ኃይሉ አለን። የወጣትነት ዕድላችንን ከተጠቀምን የማንፈነቅለው የድህነት ቋጥኝ አይኖርም።
የሕይወት ትልቁ ጸጸት በተሰጠን ዕድሜ ተጠቅመን ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች የሚጠቅም በጎ ሥራ ሳንሰራ ማለፍ ነው። በዚህ የወጣትነት ዘመናችን፣ በዚህ የጉብዝና ጊዜአችን በድህነት ላይ የበላይ ሆነን አገራችንን ከኋላ ቀርነት ማላቀቅ ከሁላችን የሚጠበቅ የቤት ሥራ ነው። ምክንያቱም ዛሬ አገር ካለ እኛ ማንም የላትም፤ የአገራችን ተስፋ እኛ ወጣቶች ነን። የምንሰጣት ካልሆነ የምትሰጠን ምንም የላትም።
የምናደርግላት ካልሆነ የምታደርግልን አንዳች የላትም። ኃይላችንን ተጠቅመን ለራሳችሁም ሆነ ለአገራችን በጎ ነገር ለመሥራት መትጋት ይኖርብናል። እንደ ዜጋ በአካልም ሆነ በአእምሮም ተሠርቶ ያለቀ ማንነት ያስፈልገናል። ስኬት ራሳቸውን ላዘጋጁ ሰዎች የተቀመጠ እንደመሆኑም ለምንም ነገር የተዘጋጀን ልንሆን ይገባል።
ስኬት እየወደቁ መነሳት ነው፤ ወድቆ መቅረት ግን አይደለም። እየደከሙ መበርታት ነው፤ ደክሞ መቅረት ግን አይደለም። የተሸነፉ መስሎ ማሸነፍ ነው፤ ተሸንፎ መቅረት ግን አይደለም። ስኬት መንገድ ነው፤ መድረሻ የሌለው ጥግ አልባ የሕይወት ህልቆ መሳፍርት። እንደ ወጣት ራዕይ ከሌለን መነሻም መድረሻም አይኖረንም።
የመኖርን ትርጉም የምንረዳው በራዕይ በኩል አልፈን ስንኖር ብቻ ነው። ለዚች ዓለም ምን ያክል አስፈላጊዎች እንደሆንን የምንረዳው ዋጋ ያለን እንደሆንን ሲገባን ነው። መልካም ነገር ያለው በመራመድ ውስጥ፣ በመሞከር ውስጥ ነው። እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ለራሳችንም ሆነ ለድሀ አገራችን የምንጨምረው ነገር የለም። ካልሠራን፣ ካልሞከርን ድህነትን ምርጫ አድርገን እንደተቀበልን ማወቅ አለብን።
በትጋት ያልታጀበ ወጣትነት ነገ ላይ ጸጸት ይጠብቀዋል። ምንም ነገር ለማድረግ ትክክለኛው ጊዜአችን አሁን ነው። ሁሉን የሚሰጠን መኖራችን ሳይሆን በመኖራችን ውስጥ የምንገነባው ታላቅ የመለወጥ ፍላጎት ነው። በምክንያት በታጀበ እውቀት ፍላጎታችን እንዲመራን መፍቀድ እንጂ ለድህነት እጅ ሰጥተን መቀመጥ አርነት አያወጣንም። ከድንግዝግዝ ሕይወት ወጥተን ለአገራችን የሚሆን ብርሃንን እናመንጭ። በሌሎች ብርሃን ለመኖር አትሞክሩ ሌሎች በእናንተ ብርሃን እንዲመላለሱ ሆናችሁ ወጣትነታችሁን በዋጋ ኑሩት። ለስኬት ተብሎ የተፈጠረ የተለየ ቀን የለም ራዕይ ያላቸው ሁሉ ለስኬት የተፈጠሩ ናቸው። ስኬት በራዕይ የሚፈጠር የጽኑ ፍላጎት ፍጻሜ ነው። ምንም ነገር ለማድረግ የምትጠብቁት ጊዜ አይኑር።
ለመለወጥ ፍላጎት ካላችሁ አሁኑኑ መለወጥ ይቻላችኋል። እኛ ከተለወጥን የማይለወጥ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ነገር ልክ ሊሆን የእኛን መለወጥ እየጠበቀ ነው። ለውጥ በዕድሜ መጨመር ሳይሆን በአስተሳሰብ መላቅ፣ በአእምሮ መበልጸግ ነው። ለውጣችሁን የአእምሮ እንጂ የአካልና የዕድሜ ለውጥ አታድርጉት። በአእምሮ ካልጎለመሳችሁ፣ በአስተሳሰብ ካበረታችሁ የአካል ጉልምስናችሁ ምንም ነው። ለውጣችሁ ያለው በማሰባችሁ ውስጥ ነው። የነገ ብሩህ ቀናችሁ ያለው በአእምሯችሁ ውስጥ ነው። ከእስራታችሁ ወጥታችሁ አገራችሁ የምትፈልጋችሁ ጥሩ ዜጋ ሁኑ።
በአካል ጎልምሰው በአእምሮ የደከሙ በርካታ ወጣቶች በዙሪያችን አሉ። እነዚህ ወጣቶች በአካላቸው የሚያስቡ፣ በፈርጣማ ጡንቻቸው የሚመኩ እንሰሳዎች ናቸው። ጥሩ ከማሰብ ይልቅ ጥሩ የጸጉር ቁርጦችን በመቆረጥ ጭንቅላታቸውን የሚያሳምሩ እንዲህም ናቸው። ጭንቅላት የአሁኑን ዓለም ያስገኘ የለውጥ ማዕከል ሲሆን አካል ደግሞ የሚታየውን ዓለም የሚያጠፋ የድንቁርና ጥግ ነው።
ብዙዎቻችን ከአንገት በላይ ውበት ያለ አይመስለንም። አሳራችንን የምናየው ለገጻችን ነው። ውበት ከጭንቅላት እንደሚወጣ ገና አልገባንም። ውበት ጥሩ ማሰብ ነው። ውበት በራዕይ መኖር ነው። ህልምና ራዕይ የሌለው ሰውነት ውበት የለውም። ውበታችሁን ራዕያችሁ ውስጥ ፈልጉት። አገራችን የምትፈልገን ታማኝ ዜጋ በመሆን የበኩላችንን እንወጣ እያልኩ ላብቃ። ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014