ከውስጥ በሚነሱም ሆነ ከውጪ ለወረራ በሚመጡ ጠላቶች ምክንያት አገር ሕልውናዋ አደጋ ላይ ሲወድቅ፤ በዚህም የሕዝብ ክብርና አብሮነት ለፈተና ሲጋለጥ፤ የአገር ሕልውና እንዲጠበቅ፣ የሕዝቦችም ክብርና አብሮነት እንዲዘልቅ በዘመናት ሂደት ውስጥ አያሌ መስዋዕትነቶች ተከፍለዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከሦስት ሺህ በዘለለው የአገረ መንግስትነት ጉዞዋ መሰል ችግሮች ተደጋግመው ገጥመዋት፤ በልጆቿ መስዋዕትነት የውጭ ወራሪን አሳፍራ፣ የውስጥ ባንዳና አገር ሻጭን አደብ አስይዛ አንድነቷን ጠብቃ፣ ታፍራና ተከብራ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡
በዚህ መልኩ ሕልውናዋን ለማስጠበቅ፤ የዜጎቿን ክብር ለማስቀጠል በተደረገ ትግል ደግሞ አያሌ ጀግኖች ተፈጥረዋል። ለአገርና ሕዝብ ቅድሚያ የሰጡ የቁርጥ ቀን ልጆቿም ከፍ ያለ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡ ፡ ኢትዮጵያም ከሃዲዎችን የምትቀጣ ብቻ ሳትሆን፤ ለክብሯ የወደቀላትን የማትረሳና ጀግኖቿን የምታከብር ናትና፤ ወራሪን አሳፍረው፣ ባንዳን አደብ አስይዘው ከፍ ያደረጓትን ጀግኖቿን ከፍ ስታደርግ፤ ስታመሰግን፣ እውቅና ስትሰጥና ስትሸልም ኖራለች፡፡
ይህች ታላቅ እና የጀግና ምድር ኢትዮጵያ ታዲያ፤ ገናን ስሟ እንዲጠለሽ፣ ስልጣኔዋ እንዲሟሽሽ፣ የከፍታ ጉዟዋ እንዲገታ የሚፈልጉ በርካቶች እንደመሆናቸው በየዘመናቱ የሚተናኮሳት የውስጥም የውጭም ጠላት አታጣም፡፡ በቅርቡም አገር ሻጭ ተላላኪ አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ የፈጸሙት ክህደትም የዚሁ እውነት ማሳያ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ታሪክ ራሱን ሲደግም ደግሞ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ይሄን ክህደት የወለደው የአሸባሪ ሃይሎች አገር የማፍረስና የሕዝቦችን ክብር አዋርዶ አንድነታቸውን የመንጠቅ ክፉ ሕልም በአንድ ቆመው ማምከን ቻሉ፡፡
ኢትዮጵያም አፍራሾቿን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፤ ጠባቂዎቿን ማበርታት፣ ጀግኖቿን መሸለም ታውቅበታለችና ለሕልውናዋ የተዋደቁላትን፣ ለክብሯ የሞቱላትን አስባለች፤ ሸልማለች፣ ከፍ አድርጋም አሳድጋለች፡፡
በዚህ ረገድ ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አባላትና አመራሮች በየደረጃው የተሰጠው እውቅናና የማዕረግ እድገት ቀዳሚው ሲሆን፤ እንደየአበርክቷቸውለሚዲያ ተቋማት፣ ለሲቪል ማህበራት፣ ለጤና ባለሙያዎች፣… የተሰጠው ክብርና እውቅና አገር ባለውለታዎቿን ትናንትም ዛሬም የማትዘነጋ ስለመሆኗ ሕያው ምስክር የሚሆን ተግባር ነው፡፡
ሰሞኑንም በባህር ዳር ከተማ “በሕግ ማስከበር እና በሕልውና ዘመቻ የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት” በሚል በተካሄደ የእውቅናና ምስጋና መርሃ ግብር ይሄው ጀግኖችን የማስታወስ፤ ባለውለታዎችን የማሰብ፣ በክብር ስለ አገርና ሕዝባቸው ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉትን የመዘከር አገራዊ ባህል ውጤት ነው፡፡ በመሪ ሀሳቡ እንደተመላከተውም፤ አሸባሪው ሕወሓት አገርን የማፍረስ ተልዕኮውን እውን ለማድረግ የአገር ጋሻ ሆነው በኖሩት በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ፤ ስለ ኢትዮጵያ ክብርና ስለ ሕዝቦቿ አንድነት ሲሉ በሕግ ማስከበር ዘመቻው አያሌ ልጆቿ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
የሕግ ማስከበር ርምጃው በቀናት ውስጥ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት መከላከያ ሰራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በተደረገ ማግስት፤ የሽብር ቡድኑ ዳግም የባንዳነት ተልዕኮውን ለመወጣት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ለወረራ በመሰማራት እስከ ሰሜን ሸዋ ዘልቆ የጥፋት በትሩን አሳረፈ፡፡ ይሄ ደግሞ የአገርንም ሕዝብንም የሕልውና አደጋ ውስጥ የከተተ እንደመሆኑ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ዳግም ለመስዋእትነት ተሰልፈው ተላላኪዎችን ድል በመንሳት እንደ ቀድሞው ሁሉ በመስዋእትነታቸው ሕልውናዋን አስጠበቁ፡፡ ዛሬም ድረስ ይሄው ቡድን የሚያደርገውን ትንኮሳ የማክሸፍ፤ በቀጣይ ሊፈጽም የሚፈልገው ነገር ካለም በማያዳግም መልኩ ለመቅጣት በሙሉ ዝግጁነት ላይ መሆናቸው እየታየ ነው፡፡
በዚህ መልኩ አገርንም ሆነ ሕዝብን ከሕልውና ስጋት ነጻ ያወጡ እነዚህ የአገር የቁርጥ ቀን ልጆች ያለ ልዩነት በአንድ ተሰልፈው ዋጋ እንደከፈሉ ሁሉ፤ ድላቸውንም በአንድነት አጣጥመዋል፡፡ ዛሬም የጋራ መስዋዕትነታቸው ውጤት የሆነውን የምስጋናና እውቅና መርሃ ግብር በጋራ ታድመው፤ በጋራ ተመስግነዋል፤ ተሸልመዋልም፡፡ ይህ ምስጋጋና እውቅና ለአገር ሕልውና ሲባል የተከፈለን ከፍ ያለ ዋጋ ለማሰብ ብቻም አይደለም፤ ይልቁንም ቀጣይ ለሚፈጠሩ አገራዊ ስጋቶችና ፈተናዎችም የኖረ አንድነትን ጠብቆ በጋራ መሰለፍና መሻገር የሚያስችል ሙሉ ዝግጁነትን ስለመያዝ ማሳሰቢያና ይሄንኑ የማድረግ ኃላፊነትን የመስጠትም ጭምር እንጂ፡፡
በዚህ መልኩ የሚሰጥ እውቅናና ምስጋናን ተከትሎ የሚጠበቅ ታላቅ ኃላፊነትን የመቀበል ባህል ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም፤ ዛሬ ላይ ግን ከእውቅናው ባሻገር ያለው አደራ ቃል የመቀበል ኃላፊነት በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡ ፡ ምክንያቱም የዛሬዋ ኢትዮጵያ በውስጥም በውጪም ከፍ ያሉ ፈተናዎች ያሉባት፤ አያሌ ጠላቶች ትኩረት ያደረጉባት፤ ዜጎቿን የመከፋፈልና የማባላት ተልዕኮን አንግበው የሚንቀሳቀሱ አሸባሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ያቆጠቆጡባት ናት፡፡ ከዚህ ምስጋጋና እውቅና ማግስት የምንወጣው ኃላፊነትም እነዚህን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተገንዝቦና ይሄንን ለመሻገር የሚያስችለንን ሕብረት ፈጥሮ በመጓዝ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነ ብልጽግና እናደርሳታለን ሲባል፤ ወደ ብልጽግናው ለመሻገር የሚያስችሉ አቅሞችን አሰባስቦ መስራትና በሂደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአሸናፊነት መወጣትን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ሁለንተናዊ ብልጽግናው እውን የሚሆነው ደግሞ የአገር ሰላምና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፤ የዜጎችን ገብቶ የመውጣት ሕልውና ማስጠበቅ፤ የኑሮ ጫናን ከዜጎች አቅም በላይ እንዳይሆን ማድረግ፤ ተነጋግሮ የመግባባት ባህልን አጎልብቶ በሕብረት የመቆም መሰረትን ማጠንከር፤ ከምንም በፊት ለአገር እና ሕዝብ ከፍታ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ሲቻል ነው፡፡
ይሄን ማድረግ እንደሚቻል፤ ችግሮቻችንንና ፈተናዎቻችንን አሸንፈን የመሻገር አቅም እንዳለን ደግሞ የሩቅም የቅርብም ጉዟችን ሕያው ምስክር ነው፡፡ መመስገናችንም ይሄንኑ በማድረጋችን ነው፡፡
በቀጣይም ይሄንኑ አድርገን የአገራችንን ሕልውና አስጠብቀን፤ ሁሉን አቀፍ ብልጽግናችንን ከማረጋገጥ የሚያግደን ነገር ይኖራል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህ እንዲሆን ግን ከምንም በፊት የቀደመውን ሂደታችንን እያየን፣ የቀጣይ መዳረሻችንን እያሰብን ከልዩነቶቻችን ይልቅ ለድሎቻችን ትኩረት መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ ይሄን ስናደርግና ለዚሁ ተግተን በጋራ መሰለፍ ስንችል፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ በጋራ ታግለን እንደተመሰገንን ሁሉ፤ ነገም በጋራ ሰርተን መበልጸግ እንደምንችል በተግባር እናረጋግጣለን፡፡
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014