የሚመለከታቸው “በአቋራጭ የመክበር ልክፍት”ን “ዴ ቱር” (de tour) ይሉታል። እኛም ይህንን ብያኔ መሰረት አድርገን፤ ከወቅቱ የገበያ አይሉት የግብይትና አገበየያት እብደት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ሀሳቦችን እናንሳ።
ስለ “ዴ ቱር” ለማወቅ ፈልጌ “ሰርች” ሳደርግ (ስፈልግ) ከሶስት ሚሊዮን በላይ (3,810,000,000) ውጤቶች ተዥጎደጎዱብኝ። የጤና አልመሰለኝምና “ተደናግሬ” እንዳለችው በመደናገር ስህተት ውስጥ ላለመግባት በማሰብ ተውኩትና ወደ ራሴ በመመለስ በተለመደው መንገዴ መጻፍን መረጥኩ።
ምንጩ ፈረንሳይኛ የሆነው “ዴ ቱር” ለብዙ ዘርፎች በብዙ መልኩ የሚያገለግል ሲሆን፤ እኛ ግን ከኢኮኖሚክስ ዘርፍ አኳያ መቃኘቱን መርጠናልና አንባቢያን ከዚሁ አንፃር እንዲረዱን አስቀድመን አደራ እንላለን።
“ዴ ቱር” ከተለመደው “ሕጋዊ አሰራር በማፈንገጥ የሚከናወን ሕገ ወጥ ተግባር ሲሆን፤ በተለይም በንግዱ አለም እልም ያለ የገበያ አሻጥርና ሙስኛነት የሚፈፀምበት የወንጀል ተግባር ነው።
ከትራፊክ፣ መንገድ አገልግሎትና ተለዋጭ መንገድን በተመለከተ “ዴቱር” (diversion routes) በሚል የሚታወቅ ሲሆን፤ ይህም አንድ መንገድ ሲገነባ ለጊዜው ያንን ተክቶ የሚሰራ፣ ግን ደግሞ በሕግ ያልፀደቀና ዘላቂ መንገድ ሆኖ ያልተመደበ ማለት ሲሆን፤ ይህም ከባለሙያዎች አኳያ ተገቢነት ያለውና በ”ተለዋጭ/ጊዜያዊ መንገድ”ነት እውቅናን ያገኘ መስመር ነው።
ባለ ሙያዎች ብዙ ጊዜ የብስክሌት ውድድር (ባለ ሞተሩን ጨምሮ)ን ከዚህ ከ”ዴ ቱር” (በተለይም ከTour de France) ጋር ያመሳስሉታል፤ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለመቅደም በሚያደርጉት ሽቅድምድም የሚደርስባቸውን የከፋ አደጋ መነሻ በማድረግ። ያንን ሁሉ መገለባበጥና መላላጥ፤ ከውድድር ውጪ መሆን፤ ከከፋም አካልና ህይወት ማጣት ድረስ የሚኬደው ከዚሁ ከ”ዴ ቱር” የተነሳ መሆኑንም ከስሩ በማስመር ማለት ነው።
ለመሆኑ “ዴ ቱር” መገለጫዎች አሉት? ካሉትስ ምን ምን ናቸው? የሚሉትን እንይና መገለጫዎቹ በአገራችን ስለ መኖር አለመኖራቸው ማረጋገጫ እንስጥ።
ከ”ዴ ቱር” መገለጫዎች አንዱና ቀዳሚው የታክስ ማጭበርበር ሲሆን፣ ኮንትርባን፣ ገንዘብ ማሸሽ፣ ሕገወጥ ንግድ፣ … በደላሎች፣ አበዳሪዎች …. አመካኝነት ከመደበኛው አካሄድ ውጪ የሚደረግ የገንዘብ እንቅስቃሴ፣ የሀሰት ዶኪዩመንቶችን ማዘጋጀት፣ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሰነዶችን ማቅረብ ወዘተ ካሉ፤ ያ አገር አደጋ ላይ ነው ማለት ነው። በመሆኑም ችግሩ “በብርሀን ፍጥነት” ካልተወገደ መጪው ጊዜ ብሩህ አይሆንም ማለት ነውና የሚመለከታቸው ሁሉ በቶሎ እጅ ለእጅ ሊያያዙና በጉዳዩ ላይ ሊዘምቱ ይገባል። (ከእስከዛሬው የመረጃ ቋታችን መረዳት እንደምንችለው፣ በአገራችን እነዚህ ሁሉ ያሉ ሲሆን፣ እንደውም “ሙስና ስርአታዊ ሆኗል” የሚሉ መኖራቸውን ነው።)
መቀበል፣ መስጠት፣ ማዘዋወር ወዘተን ጨምሮ “ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ካለ “ዴ ቱር” አለ፤ በአቋራጭ የመክበር ፍላጎትና ልክፍት አለ ማለት ነውና ያቺ አገርና ኢኮኖሚዋ ችግር ላይ ናቸው ማለት ነው። በተለይ ገበያ በገበያ አሻጥር ከተተበተበና ደላላ ከመራው አገርም፣ መንግስትም፣ ህዝብም፣ ገበያና ኢኮኖሚውም አደጋ ላይ ስለ መሆናቸው ማስረጃም ሆነ መረጃ ማፈላለጉ ከጊዜ መግደል ስለማያልፍ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። ዝቅ ብለን በምንጠቅሰው ቆይታችን ወቅት አቶ ሳምሶን ይስሀቅ በሶስት ቀን ውስጥ ግማሽ ሊትር ወተት 10 ብር መጨመሩን ሲነግሩን እያሉን ያሉት ይህንኑ ነውና ሳይደርቅ በእርጥቡ፤ ሰዋይርቅ በቅርቡ እንላለን።
ታማኝነት ከጠፋና አጭበርባሪነት ከተንሰራፋ፤ በሻጭና ሸማች መካከል መተማመን ከሌለ፤ ሸጭ ታማኝ ደንበኛውን ከከዳና ለጥቅም ብቻ ካደረ፤ ሸማች በሻጭ የአጭበርባሪነት ተግባርና አመል የተነሳ የሚበዘበዝ ከሆነ፤ የሚዘረፍ ከሆነ እዛ አገር “ዴ ቱር” ስለ መግባቱ መጠራጠር ዋጋ ያስከፍላልና መንቃት ተገቢ ነው። (“ሰዎች የሙስና ወንጀል የሚፈጽሙበት ዋናኛ ምክንያት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ሀብትና ንብረት ለማፍራት ነዉ፡፡” የሚለውን በፌዴራል የፍትህ አካላት ባለሙያዎች ስልጠና ማዕከል ማንዋልንም እዚሁ ጋ ማስታወስ ተገቢ ነው።)
አንድ አገር ውስጥ ባለ የገበያም እንበለው የ”ነፃ ገበያ” ሂደት ውስጥ የሰነድ ማጭበርበር፤ መደለዝና መሰረዝ ካለ፣ እዛ አገር “ዴ ቱር” የለም ማለት አይቻልምና መረባረብ የሚያስፈልገው ችግሩን ማምከኑ ላይ ሊሆን ይገባል።
በገንዘብ ኃይል ተጠቅሞ ለህዝብ ጥቅም ሲባል ስራ ላይ የተሰማራን ባለስልጣን ወይም መሰል ግለሰብ በጥቅም በመደለል፤ አሰራርን በማዛባ ለግል ጥቅም መሯሯጥ፤ ስልጣንን ለግል ፈጥኖ መክበሪያ መሳሪያነት የማዋል አዝማሚያው እንኳ ካለ (“Bribery” የሚሉት ማለት ነው) እዛ አገር አደጋ አለና ያሳስባል፤ ያ አገር ታሟልና ህክምናው ሊፈጥን ይገባል። ሙስና ቤቱን እየሰራ ነውና መዳኒቱን መርጨት የግድ ነው። (ምናልባት፣ በእለት ተእለት በመገናኛ ብዙሀን እየሰማን ያለነው፣ ፖሊስና የደንብ ባለስልጣናት ሳይቀሩ የተሰማሩበት ተግባር በመሆኑ ለምደነው ካልተውነው በስተቀር “Bribery” ችላ ሊባል የሚገባው አይደለም።)
እንደ ባለሙያዎች ከሆነ ይህ ለገበያ ስርአትና በአቋራጭ መክበርን በተመለከተ ስራ ላይ ለማዋል ከተፈለገ ወይም ከተሞከረ ወንጀል ነውና ያስጠይቃል፤ ያስቀጣልም። ወደ አሁኑ፣ ተጨባጩ የአገራችን ሁኔታ እንምጣ።
አሁን በአገራችን ያለው የግብይት ሁኔታ ሁሉንም ነገር የሳተ ነው። ዜጎችን ለሁለት (ገዥና ሻጭ) ከፍሎ እያነታረከ ሲሆን፤ የዋጋ ጭማሪን በተመለከተ በየሰከንዱ ለማለት ጥቂት እስኪቀረን ድረስ እየናረ፤ ሸቀጦች ትናንት በገዛንባቸው ዋጋ ዛሬ የማይገኙበት ወዘተርፈ ሁኔታ ነው ያለው።
እውነቱን ለመናገር የአሁኑ የግብይት ስርአት ይሉኝታም የለው፤ ሃይ ባይም የለውም፤ እንኳን ገሳጭ ገልማጭ እንኳን የለውም። ባጭሩ፣ ምንም የሌለውና እራሱን በራሱ የሚያስተዳድር “ዴ ቱር” ነው።
አዲስ ዘመን በጠረጴዛ ዙሪያ ያነጋገራቸው የፈረንሳይ አካባቢው አቶ አስፋወሰን ሺመላሽ “አንድ የፈረንጅ እንቁላል 10 ብር፣ አንድ የአበሻ ዶሮ እንቁላል 11 ብር ከሀምሳ፤ አምስት ቤተሰብ ያለው ሰው እያንዳንዳቸው አንድ አንድ እንቁላል እንኳን ቢበሉ በአጠቃላይ የእንቁላሉ ወጪ ብቻ ወደ 60 ብር ሄደ ማለት ነው። ይሄ ነው መሬት ያለው እውነታ።” እንዳሉት ይሆንና ገበያው በእነ እንቶኔ ይጠለፋል። ያኔ ደግሞ እዳው ገብስ አይደለምና ያሳስባል።
የምስካዬ ኅዙናን አካባቢ ነዋሪውና ሌላው የጠረጴዛ ዙሪያው ታዳሚ አቶ ሳምሶም ይስሀቅም የምርት እንጂ የተለየ ሀሳብ አላመጡ። “ግማሽ ሊትር ወተት ባንድ ጊዜ 30 ብር?” የሚለውን በማጉላት ነው ውይይቱን ሲሳተፉ የነበረው።
በቅርቡ ከአዲስ ዘመን ጋር ቆይታ ያደረጉት አባ ወራ (ጎዳና ተዳዳሪ) “በ12 ብር 10 ዳቦ እየገዛሁ ቤተሰቦቼን አቃምስ ነበረ። ዛሬ እሱም ጠፋ። በጣም ችግር ነው።” ያሉትም ዝም ብሎ ከንፈር ብቻ የሚመጠጥለት ጉዳይ ሳይሆን መፍትሄን የሚሻ ጉዳይ ነውና ችላ ሊባል አይገባም።
ባጠቃላይ ከላይ ያነጋገርናቸውና ሀሳባቸውን የሰነዘሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ለማሳያ ያህል እንጂ እነሱ የነገሩን ብቻ አይደለም እውነቱ። እውነቱና አይነቱ ብዙ ነው። በመሆኑም፣ በህግም ይሁን በፀሎት ወንጀለኞችንና ወንጀሉን ለማቆም አስፈላጊው ሁሉ መደረግ አለበት።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም