ታሪኩን መቼ እንዳነበብኩት ወይንም እንደሰማሁት አላስታውስም፡፡ብቻ ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች አስታውሰዋለሁ፡፡ መልዕክቱ በእጅጉ
ይገርመኛል፡፡ ታሪኩ እንዲሁ ነው፡፡ ሶስት ባልንጀራሞች ሲሄዱ ውለው ደክሟቸው ከዛፍ ስር ጋደም እንዳሉ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል። ሌሊት ላይ አንደኛው «ቆርጠም፣ ቆርጠም»የሚል ድምጽ ሲሰማ ፣ከጎኑ የተኛውን «ወንድሜ ሆይ፣ የምሰማው ድምጽ ምንድን ይሆን»? ሲል ይጠይቀዋል። ሰውየውም ወደ ጆሮው ተጠግቶ «እረ ዝም በል! ጅቡ የኔን እግር እየበላ ነው» ብሎ መለሰለት ይባላል። በዚህ ታሪክ መንገደኛው ከዚያ በላይ ምን እንደሚጠብቅ ሁሌም ሲገርመኝ ይኖራል፡፡
ዛሬ ላይ ደግሞ ልክ እንደ መንገደኛው ሁሉ የትግራይ ሕዝብ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ምን እስኪያደርገው ድረስ እንደሚጠብቅ እየገረመኝ ፣እየደነቀኝም እገኛለሁ፡፡ የሰቆቃና የዋይታውን ምንጭ በቅጡ አለመረዳቱ በእጅጉ ያሳዝነኛል።
የትግራይ ሕዝብ በቀደመ ታሪኩ በኢትዮጵያዊነት የሚያምን፣ ከጥንት ጀምሮ ለአገሪቱ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር የላቀ ዋጋ እየከፈለ የኖረና ምን ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያዊነቱን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶ የማያውቅ ሕዝብ ነው።
ስለ ተሓህት/ወያነ ማንነትና ምንነት ደግሞ ገና ድርጅቱ ጫካ ሳለ የተነገረና የታወቀ ጉዳይ ነው።ድርጅቱ ስልጣን ከያዘ በኋላም በወታደር ኃይል እየደፈጠጠ፣ በግፍ የንፁሓንን ሕይወት እየቀጠፈና ለመብታቸው የሚታገሉ ዜጐችን ዘብጢያ እያወረደ እውነተኛ ባህሪውን በገቢር አሳውቆናል።
በወረራ የተረከበውን በትረ-መንግሥት አስጠብቆ በቆየባቸው ዓመታትም ሲለው በዴሞክራሲ ስም እያላገጠ፤ ሲያሰኘው ደግሞ በፌዴራል ፖሊስና በጦር ኃይል እየደፈጠጠ ሲገዛ ኖሯል። ከሱ የተለየ አመለካከትና ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ የተለያዩ ቀለማ ቀለሞችን በመቀባት፣ የፈጠራ ስም በመለጠፍና ሰበብ አስባብ በመፈለግ በቀጥታም ሆነ በረቀቀ መንገድ የመመንጠር፣ የማፅዳት፣ የመሰወር፣ የማሰር፣ የመግደልና እርስ በርስ የማናቆር ሥራ ዋነኛ የሥርዓቱ ባህርይ መገለጫ ሆኖ መቆየቱ እሙን ነው።
ራሱን ከሌሎቹ የበለጠ አድርጎ የሚስለው ቡድን በጆርጅ ኦሩዌል መጽሐፍ የተጠቀሰውን፣ ‹‹ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው፤ ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ እኩል ናቸው:›› በሚል አንሻፎ በመተርጎም የራሱንና የራሱን ሰዎች ከሌሎች አብልጦ በእጅጉ ጠቅሟል፡፡
ቡድኑ ድርጐ እየሰፈረና ፍርፋሪ እየወረወረ ያሰማራቸው ባንዳዎችም በትግራይ ሕዝብ ሥም እያጭበረበሩ የትግራይ ሕዝብ የአገዛዙ ጭፍን ደጋፊና የሥርዓቱ ተጠቃሚ እንደሆነ አድርገው ሲነግሩን ቆይተዋል፡፡ ይሕን በማድረግም የአስተሳሰብ ባርነት ፈጥረዋል፡፡
በቅኝ-አገዛዝ ዘመን ፍፁም ተገዢና ጥገኛ የሆነ ኅብረተሰብ የተፈጠረበት ሂደት የአስተሳሰብ ባርነት (Conceptual Colonization) ይባላል።‹‹አባ በበሉ፣ እማሆይ አገሱ›› እንደሚለው ባለፉት ዓመታት ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ ይህን የባርነት አስተሳሰብ መፍጠር በመቻሉ፣ በተለይ ወጣቶች የሕወሓት እውነተኛ ጥቅም ስለተሰወረባቸው ቡድኑን ከጫካ አውጥተው ቤተ መንግሥት እስከ ማስገባት ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት አድርገዋል፡፡እናቶችና አባቶች ልጆቻቸውን ገብረዋል፡፡
ሕዝቡም የዚህ ፀረ ሕዝብ ኃይል የፕሮፖጋንዳ ሰለባ በመሆኑ፤ ከፊሉም በፍርሃት በመሸበቡ ሌላው ደግሞ ልጆች ወንድምና እህቶቹ በመሆናቸው እና ከቀሪውም ጋር በስጋና ጋብቻ ዝምድና እና በዘር የተጋመደ በመሆኑ፤ የፈለገ ዓይነት በደል ቢፈጽም ዝምታን በመምረጥ ዓመታትን በስቃይ አሳልፏል፡፡
የሕወሓት ቡድኑ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከስልጣን ሲባረር ትግራይን መሸሸጊያ አደረገ፡፡ ቡድኑ መቀሌ ከመሸገ ወዲህም አዲሱን ለውጥ ሲያጥላላና ሲቃወም የለውጡ ትሩፋትም ለትግራይን እንዳይደርስ እንደ ጎሊያድ መንገድ ሲዘጋ ነበር፡፡
በለመደው በተለየ የከፋፍለህ ግዛ መርሕ በጎሳዎች፣ በብሔሮችና በአጠቃላይ በሕዝቡ መካከል (encouraging blood feuds) የእርስ በርስ ጥላቻና መርዝ ሲያሰራጭ ሲያራግብ ከፍ ሲልም ስለ ጦርነት ሲዘምሩም አስተውለናል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያን መምራት የምችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ነኝ›› በሚል መረጃ እያምታታና በሚዲያ የበላይነት ራሱን ኢትዮጵያ ከምታክል አገር ይልቅ ለምዕራባውያን ፍላጎት የተሻለ አድርጎ ሲያቀርብ
ቆይቷል፡፡ ቡድኑ ከዚህ የባንዳ ተግባሩ ባሻገር ኢትዮጵያን የሚፈልጋት እርሱ እስከገዛትና የበላይነትን ይዞ እስከቀጠለ ብቻ በመሆኑ የኢፌዴሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ጦርነት ከፍቷል፡፡
ኢትዮጵያም በቡድኑ እብሪትና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት የተገደደች ሲሆን፣ ቡድኑ በተሳሳተ ስሌት በለኮሰው እሳት የትግራይ ሕዝብን የማይፈልገው ጦርነት ውስጥ በማስገባት ስቃይና መከራ ውስጥ አስገብቶታል፡፡
መንግሥት ለሕዝቡ በማሰብ መቀሌን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ መቃብር ፈንቅሎ ከወጣና መቀሌን በዊልቸርና ክራንች ታግዞ ከያዘ በኋላ ነፍስ ያለው ሁሉ እንዲታጠቅና እንዲሞትለት የክተት አዋጅ ለፍፎ ጦርነቱን ወደ አጎራባች ክልሎች ማስፋፋትም ችሏል፡፡ ብቻዬን አልሞትም በሚል የትግራይን ሕዝብ ይዞ ለመጥፋት ከውሳኔ ላይ ደርሶ በከፈተው እጅግ አደገኛ ጦርነት በርካቶችን ጨርሷል፣ አስጨርሷል፡፡
የትግራይ መንደሮችን ታዳጊ አልባ እንዲሆኑ በማድረግ፡ ከእርሻ መሬቶች ላይ ገበሬውን በማንሳት ለጦርነት ማግዷል። የቀረው እናት ማህጸን ውስጥ የሚገኝ ጽንስ ካልሆነ በቀር ለስክሪፕቶና እርሳስ ያልጠነከረን እጅ ክላሽ እንዲጨብጥ በማድረግ በዓለም ታሪክ የጭካኔ ጥግ የታየበትን ዘግናኝ ትራጄዲ ፈጽሟል፡፡
ትርጉም ለሌለው ጦርነት አዛውንቶችና ሕጻናት በመላክ እንደቅጠል አራግፏል፡፡ በሀሽሽ የናወዙ፡ የትግራይ ሕጻናትና አዛውንቶች ጥይት ወደሚጮኽበት የመትረየስ ላንቃዎች ወደሚያስካኩበት ስፍራ በደመነፍስ በማግተልተል የእሳት እራት አድርጓል፡፡
ይሁንና የቋመጠለትን ስልጣን መቆጣጠር ተስኖት፣ በመጨረሻ ‹‹በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት›› በሚል እሴት የተገነባው፣በየትኛውም ሁኔታ በማንኛውም የአየር ፀባይ ማንኛውም ግዳጅ በውጤት የማጠናቀቅ አንፀባራቂ ድል የማስመዝገብ አቅም እና ብቃት ባለው የኢትዮጵያ ሠራዊትና የቁርጥ ቀን ልጆች ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት ተመልሷል፡፡
የቡድኑ አባላትና ጋሻጃግሬዎቻቸው የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትዕቢት ተወጥረው ፣ጤንነታቸውን በሚያጠያይቅ መልኩ ስልታዊ ማፈግፈግ ከሚለው ጀምሮ የበሬ ወለደ አይን ያወጣ የውሸት ፕሮፖጋንዳቸውን ሲነዙም ከርመዋል፡፡ አስከፊ የሽንፈት ፅዋው እንዳከሰራቸው በሚያስታውቅ መልኩ ወደ ለየለት እብደት በመጠጋት ሕዝቡን ዳግም ከመጨቆንም አልተቆጠቡም፡፡
የትግራይ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት አስከፊ የሆነ ጭቆናና የውስጥ ቅኝ አገዛዝ (internal colonialism) ስር ይገኛል፡፡ ሕወሓት እንደ ባዕድ እንጂ፣ እንደ ሃገር ተወላጅ ትግራይን እያስተዳደረ አይደለም፡፡ ሕዝቡ የውጭ ወራሪ ሳይመጣ፣በክልሉ ተወላጆች ቅኝ ስር ወድቋል፡፡
በተደጋጋሚ ስለ ትግራይ ሕዝብ ረሃብ፣ ስለ ሰብዓዊ ዕርዳታ አስፈላጊነት የሚደሰኩሩት፣ጌታቸውና አጋሮቹ በጣም በሚያስገርምና በሚያስደነግጥ መልኩ ለክልሉ ሕዝብ የመጣን የእርዳታ እህል ዛሬም እንደ ትላንቱ የግል ጥቅም እያዋሉት መሆኑ ነው፡፡
ከትላንት እስከ ዛሬ የእርዳታ እህል እየበላ ሕዝብን ከዳር እስከዳር ለጦርነት የማገደውና በተስፋ መቁረጥ ጥልቅ ስሜት ውስጥ የሚሰቃየው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከማንም በላይ ለትግራይ ሕዝብ ምጽዓት ይዞ የመጣ ታላቅ መርገምት መሆኑን ማስመስከሩንም ቀጥሏል፡፡
ትላንት የ6 ዓመት ሕፃናትን እና 70 አመት አዛውንቶችን ከለላ አድርጎ በ(human shield) ዕድሜውን ያረዘመው አምባገነኑ የሕወሓት ቡድን፣ዛሬም ከሕዝብና ከሃገር ይልቅ የራስን ምቾት በማስቀደም ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሱ አያሌ ወጣቶችን አስከፊ ለሆነው ጦርነት መጠቀሚያ ለማድረግ እየተሰናዳ ይገኛል፡፡
ከማን እና ከምን እንደሆነ ባይታወቅም ነጻ አወጣሃለሁ የሚለውን ሕዝብ እያፈነ ይገኛል፡፡ ቡድኑ አሁን ላይ በየከተማውና በገጠር ትንሽ ትልቅ ሳይል ወያኔ ተቃዋሚዎቹን በማሰር በመግረፍ በማሳደድና እንዲሁም በመግደል ላይ ይገኛል ፡፡ትግራይን ተረካቢ ትውልድ እንዳይኖራት በሚያደርግ ጦርነት ውስጥ ይንደፋደፋል።
ቡድኑ ሕዝቡን ገንዘብ አምጣ፣ እህል አዋጣና የሚዋጋ ልጅ ስጥ እያለ እያሰቃየው ይገኛል፡፡ የቡድኑን ፍላጎት ማሟላት ያልቻለ ለእስርና ለእንግልት ብሎም ለሞት እየተዳረገ ይገኛል፡፡ቡድን ለሕዝቡ የሚመጣውን የእርዳታ እህል ምግብና መድኃኒት ለትግራይ ልዩ ኃይልና ለአመራሩ ቤተሰብ እየሰጠ፣ሃገር የማፍረስ ሴራውን ለማስፈፀም ሕዝብ ገንዝብና ቁሳቁስ አምጡ እያለ መቆሚያና መቀመጫ እያሳጣ ይገኛል፡፡
ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ችግር ውስጥ እንደሆነ እያወቀ እንኳን የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ዕዳ ካልከፈላችሁ እርምጃ እንወስዳለን በማለት በሕዝቡ ላይ ያለውን ጭካኔ እያስመሰከረ ይገኛል፡፡ ይህንንም የትግራይ ብልጽግና ቅርንጫፍ የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ አበባ በርሀ በመጋቢት ወር አጋማሽ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከሚታተመው ወጋሕታ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል፡፡
ሕዝቡ ባለበት ችግር ተደራቢ እዳ መክፈል አለብህ እያሉ እያስጨነቁት ስለሆነ ሕዝቡ ለመሰደድ ተገዷል ያሉት ወይዘሮ አበባ ፣ ሕወሓት የራሱን ስልጣን ለማራዘም እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ርህራሄ እንደሌለው እየሠራ ባለው ሥራ ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል::
ትግል መሄድ አለመሄድ የግል ምርጫ ነው፡፡ወደ ትግል አልወጣህም ተብሎ ወላጅን ማሰር ግን በዓለም ታይቶ የሚታወቅ አይደለም፡፡ ሕወሓት ግን በግልፅ በአደባባይ እያስመለከተው ይገኛል፡፡ አሁን ላይ ለመዝመት ፍቃደኛ ያልሆኑ ልጆች ወላጆችን እያሰረ ይገኛል፡፡
ቢቢሲ ያነጋገረው ለራሱና ለቤተሰቡ ደኅንነት ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው አንድ የትግራይ ተወላጅ፣ ልጆች ለመዝመት ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው ወላጅ አባቱ እና አጎቱ እንደታሰሩ ገልጿል። ወጣቱ ››ቢያንስ ከቤተሰብ አንድ ሰው ውትድርና መላክ አለበት፤ ማዋጣት አለበት የሚል ሕግ አለ” ብሏል፡፡
ከዚህ ወጣት በተጨማሪ በጦርነቱ ለመዋጋት ፍላጎት ስለሌላቸው ወላጆቻቸው እንደታሰሩባቸው ከሚናገሩት መካከል በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ክብሮም በርሀ ይገኙበታል። አቶ ክብሮም ልጅ አልዘምትም ካለ የታመሙ ወላጆች ሳይቀሩ ለእስር እንደሚዳረጉ የገለጹ ሲሆን ፍርድ ቤት የሚቀርቡበት ሁኔታ ሳይኖር በርካታ ሰዎችም ትምህርት ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
የቡድኑ አፈና እና ጭቆና አንገሽግሿቸው ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በአማራ ክልል በሃይቅ ጃሬ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙ ነዋሪዎችም አሸባሪው ሕወሓት የሚፈፅምባቸውን ግፍና መከራ መስክረዋል፡፡ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የአማራን ሕዝብ ጠላት አድርጎ ጥላቻ ቢሰብክም ሕዝቡ በፍቅር ተቀብሎ እያስተናገዳቸው እንደሆነ የገለፁት ተፈናቃዮቹ፣ጠላታቸው የአማራ ሕዝብ ሳይሆን ለስልጣን ጥሙ ግፍና መከራ የሚፈጽምባቸው ሕወሓት እንደሆነም አረጋግጠዋል፡፡
እዚህ ጋር የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ቅኝ እየተገዛ መሆኑን አስረግጦ በመረዳት ፤ ከዳር እስከዳር ተነቃንቆ ቡድኑ ላይ ያልዘመትንበትና ያላስዘመትንበት ምክንያት ምንድን ነው ብሎ መጠየቁ የማይቀር ነው፡፡ ይሁንና ቡድኑ እጅግ ሲበዛ ጨቋኝና ትንፍሽ የሚልን ከመግደል የማይተናነስ በመሆኑ የፍርሃቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡
ይሕ ማለት ግን የሕወሓት አፓርታይድ አገዛዝ ምቾት የሚሰጣቸው የአፓርታይዱ ተባባሪዎች፣ ደጋፊዎችና የዋሆች የሉም ማለት አይደለም፡፡በተቃራኒው ደግሞ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ በሚል ዘግይቶም ቢሆን ከነባራዊው እውነታ ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ የአፓርታይዱን ቡድን የሚሸሹና የሚቃወሙ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡
ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ ከሕወሓት ቀንበር ለመፈታት የአስተሳሰብ ባርነቱን ማስወገድ የግድ ይለዋል፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ ችግሩን ለመፍታትም ሆነ ከችግሩ ለማምለጥ አይቻልም፡፡ ሳይንቲስትና ፈላስፋ አልበርት አይንስታይን ‹‹ we cannot solve our problems with the same thinking we used when we created them››እንደሚለው፣ ማለት ነው፡፡
እናም ነፍሰ በላው ቡድን፤ እንደ ጅቡ እግራችሁን ቆርጥሞ እየጨረሰ፤ በሹክሹክታ መነጋገሩ ፈጽሞ አዋጭ እንደማይሆን መገንዘብ፣በተባበረው ትግል ይህን ቅኝ ገዢ የሽብር ቡድን አንኮታኩቶ የመጣያ ጊዜው ነገ ሳይሆን ዛሬ መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ግድ ይላል፡፡ ሁሉም የአቅሙን ያህል፣ የችሎታውን ያህል ከቅኝ ገዢዎቹ መላቀቅ ይኖርበታል፡፡
ወዳጅና ጠላቱን ለይቶ፣ ጥንካሬና ድክመቱን መዝኖ ከትላንት ስህተቱ መማር ይኖርበታል፡፡ ትግሉ የሚጠይቀውን ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅቶ መነሳት አለበት፡፡ ቡድኑ ከሚነዛው ጠባብ መንደርተኛ አስተሳሰብና ጨለምተኛነት ራሱን አፅድቶ፣ የቀደምት ትውልድን ሃገራዊ ተጋድሎና ጀግንነትን ወርሶና አድሶ መገኘትም ይጠበቅበታል፡፡
የአፋኙ ነጻ አውጪ ዳግም የጦር ጉሰማ ሕዝብ ከማስጨረስ በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው እሙን ነው፡፡ ወያኔ በቀለብ ሰፋሪዎቹ ምርኩዝነት የተወሰኑ ጊዜያትን ቢያስጨንቅም፣የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ በቅርቡ መውለቁ አይቀርም፡፡
ሰከን ብለን፡ ለአሉባልታና ለፕሮፖጋንዳ እጅ ሳንሰጥ፡ ግንባር ላይ ታሪክ እየሠሩ ላሉት ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ደጀንነታችንን በሁሉ መስክ ካረጋገጥን ሕወሓት ከትግራይ ምድርም ሆነ ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወርዶ ግብዓተ መሬቱ ተፈጽሞ ከእነቆሻሻ ስብዕናው ታሪክ ሆኖ ይቀበራል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም