ከፈጣሪዬ ቀጥሎ መቼም ስለሀገሬ ተስፋ እንዳልቆርጥ ወኔና ብርታት ከሚሆኑኝ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደሙ ተቀዳሚ ሙፍቲሕ ሀጂ ኡመር እንድሪስ ናቸው። በዚያ ሰሞን በጎንደር ተለኩሶ በመላ ሀገሪቱ ሊቀጣጠል ዳር ዳር ብሎ የከሸፈው ሕወሓትና ግብረ አበሮቹ ስፖንሰር ያደረጉትና ስምሪት የሰጡት ሀይማኖት ለበስ መቆራቆስ ከኢትዮጵያዊነት ከፍ ሲልም ከሰውነት ከፍታ ወርዶባቸው ቢቸገሩ ሼሀችን፤”…ሰው እንሁን!” አሉ ። ይህ ታላቅ ድምጽ የመቤዠት ድምጽ ነው ። ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ከፍ ብሎ መስተጋባት ያለበት የማንቂያ ድወል። በሁሉም ልሒቃንና ሚዲያዎች መተርጎም ፣ መተንተንና መብራራት ያለበት መዳኛና ከገባንበት ቅርቃር መውጫ ጽንሰ ሀሳብ ነው። እኔም ከተቀዳሚ ሙፍቲሕ ሀጂ ኡመር ጋር በንግር/foreshadow/ ከሁለት አመት በፊት በተወሳ ሀሳብ መውጫው ደጅ ላይ ፊት ለፊት የተገጣጠምሁበትን የ”ሰው እንሁን”ኛ ንዑድ ሀሳብ እነሆ።
“The Prodigal Daughter “፤ በተሰኘው የጄፍሪ አርከር ማለፊያ ልቦለድ፦ የተረኩ ባለቤት የሆኑት ዋና ገፀ ባህሪያት ፍሎሬንቲ እና ሪቻርድ ባልና ሚስት ቢሆኑም የተለያየ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ ናቸው:: ፍሎሪ የዴሞክራት ሪቻርድ የሪፐብሊካን ፤ ታሪኩ በተዋቀረበት ዘመን የዴሞክራት እጩ የነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ 35ኛ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት በመሆን በጠባብ ልዩነት ሪቻርድ ኒክሰንን ይረታሉ:: የፕሬዚዳንት ኬኔዲ በዓለ ሲመት ድንቅ አነቃቂ ንግግር የፊሎሪን የሀገሯ የመጀመሪያ ሴት ፕሬዚዳንት የመሆን የልጅነት ሕልሟን ከተኛበት ይቀሰቀስባትና በጨዋታ መሀል ወግ አጥባቂ የሪፐብሊካን ደጋፊ የሆነውን ባለቤቷን” …ውዴ ! የዴሞክራቶች እጩ ሆኘ ብቀርብ ትደግፈኛለህ ? “ ስትል ድንገት ትጠይቀዋለች፤ እሱም ያለአንዳንች ማመንታት፤ “ይዘሽው የምትቀርቢው የፓሊሲ ሀሳብ ይወስነዋል :: … “ ሲል ተደራሲውም እሷም ያልጠበቁትን መልስ ሰጠ:: ፍቅሬ ፣ የልጆቼ እናት ስለሆነሽ ብሎ “ እንዴታ…! አንቺ ለመወዳደር ያብቃሽ እንጅ ከቶ ማንን ልደግፍ… !? “ አላላትም ::
ይህ የሪቻርድ መልስ አብዛኛዎቹን የሀገራችንን የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሙህራን፣ ፓለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ፀሐፍት፣ ጦማርያን ፣ ደራሲያን፣ ልሒቃን ፣ ወዘተ. ዘውጋዊ ማንነትና ውግንና አስታወሰኝ:: ያለፉት 30 አመታትም ሆኑ ከዚህ ቀደም ያሉት አመታት ያለፉት በዘውግ፣ በብሔር ፣ በማንነት ፖለቲካ መሆኑ ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል:: ብኩርናችንን፣ ቀደምትነታችንን አስቀምቶናል:: አሰውቶናል:: አስማርኮናል :: እንደ ሪቻርድ በምክንያታዊነት ሳይሆን ሁሉን ነገር በዘውግ መነፅር እንድንመለከት አድርጎናል::
ሰሞነኛው የታሪካችን፣ የኢትዮጵያዊነታችን ጠባሳ መግፍኤም ይኸው ነው:: ሚያዚያ 18፣ በጎንደር የተለኮሰውና በተከታይ ቀናት ወራቤንና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ለማቀጣጠል የተሞከረው የሀይማኖታዊ አክራሪነትና ጽንፈኝነት እሳት ሀገራችንን የማንደድ አደገኛ ደባ አካል ነው። ከጭፍን ጥላቻ ፣ ከጎሰኝነት ይልቅ በተጠየቅ፣ በአመክንዮ በተመሰረተ ንግግር ፣ ውይይት፣ ሙግት በጠረጴዛ ዙሪያ ልዩነቶችን የመፍታት ክፍተት እንዳለብን የሚያውቁት የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን በተደጋጋሚ ሀገራችንን ለመበተንና እርስ በርሳችን ለማባላት ሞክረውበታል። የሚያሳዝነው በአናቱ ደባና ሴራ ተጨምሮበት የተፈጠረውን ውዥንብር እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሁለቱም ወገን ደረቅ ወንጀለኞችን ለሀይማኖታቸው ቀናኢ አድርጎ ለማሳየት የተሄደበት ርቀት ያሳፍራል ። ያሳዝናል። ትላንት ዘውጌ’ዊነት ዛሬ አክራሪነትና ጽንፈኝነት ህሊናችንን እንዴት እንደጋረደው ያሳያል:: በሆነው ነገር አንጥፎ ሙሾ ከማውረድ ይልቅ መውጫችን ላይ መነጋገር ይበጃል ብዬ ስለማምን፤ ተቀዳሚ ሙፍቲሕ እንዳሉት እኔም ከዚህ አዙሪት የመውጫችን በር ሰውነት ነው እላለሁ::
አዎ! ዘውጋዊ ማንነትና ማንኛው አይነት ጽንፈኝነት ሀገርን፣ ወገንን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ ምክንያታዊነትን፣ ተጠየቃዊነትን፣ እውቀትን፣ ሰብ’ዊነትን፣ ታሪክን … ፤ አስገብሮን በምትኩ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞን፣ ዘረኝነትን ፣ ግዕብታዊነትን፣ ኢአመክኖያዊነትን፣ ኢተጠየቃዊነትን፣ ድንቁርናን፤ አስታቅፎናል:: የጥላቻን፣ የመጠራጠርን የጦር እቃ አስታጥቆናል ፣ የቂምን የሾህ አክሊል ፣ የበቀልን ጡሩር አስለብሶናል :: የሶስት ሺህም ሆነ ከዛ በላይ የሆነውን የታሪካችንን ቀለም አደብዝዞታል::
ከዚህ ከፍ ሲልም ምሽግ አስይዞናል:: ጉድብ አስጎድቦናል:: በዚህ ይዞታችን፣ አኳኋናችን ለሀገራችን የምንመኘውን የምንፈልገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም:: ሀቀኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ፍትሕንና እኩልነትን ለማስፈን፤ የሌብነትንና የዘረፋን ሰንኮፍ ከዚች ሀገር ለመንቀል፤ የሕግ የበላይነትን ዘላቂና አስተማማኝ ሰላምን አውን ለማድረግ በእውነት ላይ የተመሰረተ ይቅርባይነትን ለመሻት ወዘተ. ባለፉት 30/50 ዓመታት በብሔር፣ በዘውግ ፓለቲካ የተዘረፍናቸውን የተነጠቅናቸውን ከላይ የተዘረዘሩትን ምርኮዎቻችንን ማስመለስ አለብን:: ሰው እንሁን ማለት ሀገርንም ፣ ሕዝብንም፣ ሰውንም በቁም ከሚበላው ጥላቻ አርነት መውጣት ነው።
ምርኮዎቻችንን የምናስመልሰው በዘውግ፣ በብሔር ግርዶሽ ተሸብበን ውረድ እንውረድ እየተባባልን የጥላቻ ጦራችንን በመስበቅ፤ የቂም በቀል ቀስታችንንና ፍላፃዎቻችንን ለማንበልበል ደጋን በመወጠር አይደለም:: በእውቀት፣ በሳይንስ፣ በተጠየቅ፣ በምክንያት ላይ በተመሰረተ የሰከነ የሀሳብ ፍጭት ሙግት በማድረግ ገዥ ሆኖ ልዕልና ያገኘውን ሀሳብ ፍኖተ ካርታ በመከተል ሲገባ እየሆነ ያለው ግን በብሔር በዘውግ የተቆፈረ ምሽግ ይዞ መጠዛጠዝ ነው:: ይህ አልበቃ ብሎን አሁን አሁን ደግሞ ወደ ሀይማኖት ዞረናል። የውይይቱ ፣ የንግግሩ፣ የሙግቱ መሰረት የሚገነባው በሳይንሳዊ እውቀት፣ በምክንያታዊነት፣ በተጠየቃዊነት ፣ በእውነት፣ በሀቅ አለት፣ …ሳይሆን ፤ በዘር ፣ በጎሳ ፣ በማንነት ፣ በዘውግ፣ በሀይማኖት፣ …፤ ድቡሽት ላይ በተቀለሰ ሰቀላ ነው:: ወገንተኝነት ታማኝነት ለሀቅ፣ ለአመክኖአዊነት፣ ለህሊና ሳይሆን ለተገኘበት ጎሳ ወይም ሀይማኖት ነው:: በዚህ አሰላለፍ ሀገራችንን ከገባችበት ቀውስ ማውጣት አደለም እርስበርሳችን መቀባበል፣ መነጋገር፣ መደማመጥ አልቻልንም:: ለፅንፈኝነት፣ ለአክራሪነት ተዳርገናል:: እውቀት፣ ተጠየቅነት ፣ ምክንያት ፣ ሳይንስ በዘውጌአዊነት፣ በብሔርተኝነት ተደፍቀዋል ::
በተለይ በእነዚህ አራት አመታት ከምክንያታዊነት፣ ከተጠያቂነት፣ ከአብርሆት ይልቅ በማንነት፣ በዘውግ ተከፋፍለን ምሽግ ይዘን፣ የተከላከልናቸውን፣ የተጠዛጠ ዝንባቸውን፣ አቋም የወሰድንባቸውን፣ የተሟገትን ባቸውን፣ ጥያቄዎች፣ ስጋቶች ፣ ፍላጎቶች እንደ ክብደት ቅደም ተከተላቸው ጥቂቶችን እንመልከት፦
ሀ. የሕወሓት ተገፋን ፣ ተከበብን ዋይታ …፤
ባለፉት 30 አመታት ሀገራችንና ሕዝባችን ለቀውስ የዳረጋት ዋናው የህወሀትና ጀሌዎቹ የተገፋንና ተከበብን የፈጠራ ትርክትና ልፋፌ ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ጎልተው ከሚሰሙ አመክኖአዊ፣ ተጠየቃዊ ካልሆኑ ለቅሶዎች፣ ዋይታዎች፤ ቀዳሚው የሕወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ ከማዕከላዊ መንግስት ስልጣን ተገፋ፣ ተገለለ ፤ የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክና ለመዋጥ ጥረት እየተደረገ ነው፤ ሊወረርና ሊጠፋ ነው የሚሉ የፈጠራ ሀቲትና ትርክት ድሪቶዎች ናቸው ::
እውነታው ግን የሕወሓት ልሒቃን ላለፉት 27 አመታት በበላይነት፣ በብቸኝነት ይዘውት የነበረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት ፣ የመከላከያ የበላይነቱን በሕዝባዊ አመፅና በለውጥ ኃይሉ አጣ እንጂ፤ የትግራይ ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቱን አላጣም፤ አያጣምም:: የትግራይ ልሒቃን ከእውነታው ይልቅ በመደበኛም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያው እያስተጋቡት ያለው ሕወሓት ሊያነብር የፈለገውን የተገፋን ሀቲት ነው:: ልሒቃኑ ከማንነት ፈለፈላቸው ወጥተው በተጠይቅ፣ በአመክንዮ ማሰብ፣ ማንሰላሰል ቢፈቅዱ ኑሮ የሕወሓት ትርክት የተዛባ መሆኑን ገልፀው ከሀቁ ጎን ይቆሙ ነበር:: አብዛኛው የትግራይ ልሒቃን እንደ ጋዜጠኛ ሔርሜላና እናቷ ፕሮፌሰር ሀረገወይን ከእውነት ጎን ለመቆም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሕወሓት ትግራይን ትውልድ አልባ እያደረጋት ነው ። የሚቆጨው በዚህ የተሳሳተ ተረክ በመቶ ሺህዎች የሚገመቱ መሞታቸውና መቁሰላቸው ፤ የሀገርና የሕዝብ ሀብት መውደሙና መዘረፉ ነው። ህወሀትና ደጋፊዎቻቸው ዛሬም ከዚህ ስህተት አለመማራቸው ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል።
ለ. የመካድ አባዜ፤
ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን፤ መንግስት ከትግራይ ለቆ ሲወጣ የአማራና የአፋር ክልሎችን በመውረር የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ወንጀል መፈጸሙን ፣ ህጻናትንና መነኮሳትን መድፈሩን ፣ የሀገርና የሕዝብ ሀብትና ንብረት ማውደሙን፣ ከለውጥ በፊት ባሉት 27 አመታት ደግሞ በሀገሪቱ የተፈፀሙ ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ስቃዮች እንዲያ በዘጋቢ ፊልም ሰለባዎች እየተገለፁ ሀገር ጉድ እያለ፤ ከእነ ዶ/ር አረጋዊ በርሔ እና ከጥቂቶች በስተቀር ብዙዎቹ ትግራዋይ ሙህራን ድርጊቱን ካለማውገዝ አልፈው ትህነግን ከሕዝብ ለመነጠል እንደተሰራ ደረቅ ፕሮፓጋንዳ መቁጠራቸው ተጠየቅ፣ አመክንዮ በማንነት እንደተጋረደ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ::
ሐ. የውለታ፣ የውርስ ሽሚያ፤ …፤
ከአራት አመታት ወዲህ የለውጡን መባት ተከትሎ በመደበኛም በማህበራዊ ሚዲያዎች፤ ከተስተዋሉ ተጠይቅ፣ አመክንዮ ከጎደላቸው እሰጥ አገባ፣ ሽሚያና ውርክቦች ፤ ቀዳሚው ፤ ለውጡን ያመጣሁት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ የሚለው ንጥቂያ ነው :: በሁለቱ ጦርነቶች የተስተዋለው የድል ሽሚያም የዚህ እኩይ ተግባር አካል ነው ። በሀገሪቱ ፖለቲካ ታሪክ አይደለም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአፄዎች አገዛዝም እንዲህ ያለ የግዳይ፣ የድል፣ የውለታ ሽሚያ ታይቶ አያውቅም:: ሀገሪቱ በምንም አይነት የማህበራዊ ቀውስ ተዘፍቃ እንኳ እረኛው፣ አዝማሪው ጀግንነትን በዜማው ለሚገባው ያደላድላል፤ እውቅና ይሰጣል እንጅ ጀግናው ራሱ ተነስቶ ጀግና ነኝ ይህን ድል ያመጣሁት እኔ ነኝ አይልም ::
መናገር ግድ ቢሆን እንኳ የእናት የአባቴ አምላክ ረድቶኝ ለዚህ በቃሁ ይላል እንጅ፤ እንዲህ እንደዛሬዎቹ ጉዶች ለውጡን እኛ ነን እኛ ነን ያመጣነው በሚል እብሪት አይታበይም:: ህወሀትን የገረፍነው እኛ ነን እኛ ነን አይባባሉም። አዎ! ክቡር ጠ/ሚ ደጋግመው እንደሚሉት፤ ለውጡን ያመጣውም በህወሀት ላይ ድል የተቀዳጀው ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጅ አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ አይደለም :: ለውጡ ግፍ ፣ በደልና ጭቆና አምጦ የወለደው ነው:: ድሉም የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጅ የማንም ቡድን አይደለም ። የሚገርመው ጊዜያዊ ሸብረክ ማለት ሲያጋጥም ደግሞ ሁሉም ራሱን ከተጠያቂነት በማሸሽ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ባይና ጣት ቀሳሪ መሆኑ ነው ።
መ. የብሔር ወይስ የመደብ ጭቆና..!?
በተማሪዎች የ1960ዎቹ ዕንቅስቃሴ ከእነ ግርማቸው ለማ፣ መለስ ተክሌ (የቀድሞው ጠ/ሚ ስሙን የወረሱት)፣ ሰለሞን ዋዳ፣ ጥላሁን ግዛው ይልቅ ዛሬ ድረስ በበጎም፣ በክፉም ስሙ ከፍ ብሎ የሚወሳው የደሴው ዋለልኝ መኮንን ነው:: ከእነ ሌኒን ማንፌስቶ እንዳለ ገልብጦ፣ ኮሩጆ ማታገያውን ከመደብ ጭቆና ወደ ጠባቡ የብሔር ጭቆና በማውረዱ፤ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ለምትገኝበት ምስቅልቅል መግፍኤ ከመሆኑ ባሻጋር፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ልሒቃኑን በሁለት ጎራ ከፍሎ ይገኛል:: በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው አይደለም የብሔር ጭቆና ነው በሚሉ ሁለት የማይታረቁ ቅራኔዎች የብሔር ጭቆና በተጠየቃዊነት በምክንያታዊነት የሚተነተን ሳይሆን በማንነት በስሜት የሚቀነቀን የሚራገብ መሆኑ ልዩነቱን የማጥበብ ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል:: እዚህ ላይ በህወሀት፣ በኦነግ እና የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን በሚያራምዱ ወገኖች መካከል ያለውን ልዩነት በአብነት ማንሳት ይቻላል ::
እንደ መውጫ
ልዩነቶቻችንን አቆይተን እስኪ መጀመሪያ ወደ ቀደመው ማንነት ማለትም ወደ ሰውነት፣ አዳምነት፣ ሔዋንነት አልያም ዳርዊናዊነት እንመለስ:: በማስከተል በይደር ያቆየናቸውን ልዩነቶች እንደ አንገብጋቢነታቸውና ቅደም ተከተላቸው በአብርኆት (enlightenment)፣ በተጠየቃዊነት፣ በአመክኖአዊነት፣ በገለልተኝነት፣ …፤ መነፅር እንመርምራቸው ፣ እንተንትናቸው:: ከዚያ መቋጫ መውጫ መፍትሔ እናብጅላቸው፤ የዛን ጊዜ ሁላችንንም ሊያግባቡ፣ ሊያቀባብሉ፣ ሊያቀራርቡ የሚችሉ መፍትሔዎች ላይ እንደርሳለን::
እዚህ ላይ ማንነቶቻችንን እንተዋቸው እንርሳቸው እያልሁ አይደለም :: እነሱን መካድ አይቻለንም:: ተቀዳሚ ሙፍቲሕ እንዳሉት ሰው እንሁን:: ለዚህ ደግሞ ከዘራችን፣ ከመደባችን፣ ከሀይማኖታችን፣ ከአመለካከታችን፣ ከፆታችን ከእነዚህ ማንነቶች ቀድሞ ወደነበረው ወደ መጀመሪያው የጋራ ማንነት ወደ ሰውነት እንመለስ:: ይሄን ያደረግን ጊዜ ከመጀመሪያው ጀመርን ማለት ነው:: ሰው የመሆን ልምምድን ከመጀመሪያው ስንጀምር ደግሞ ያለፍንበትን ስህተት እየነቀስን እያረምን ስለምንመጣ፤ ስህተትን የመድገም ፈተናን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ እንኳ ባንችል መቀነስ ግን እንችላለን። ለዚህ ነው ከመጀመሪያው እንደገና መጀመርም የመፍትሔ አካል የሚሆነው። አዎ! ሰው እንሁን!
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም