‹‹ኢትዮጵያውያን አብሮ የመብላት እንጂ አብሮ የመሥራት ባህል የላቸውም›› የሚሉ አሉ ።በሌላ በኩል ደግሞ ይሄንኑ ሀሳብ የሚቃወሙ በደቦ(በጅጌ) መሥራት የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው ሲሉ ይከራከራሉ። ይሄም ሆነ ሌሎች በጋራ የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸው ባይካድም በቂ ነው አብሮ የመሥራትና የመለወጥ ባህል አለን ብሎ ደፍሮ ለመናገር ግን ይከብዳል። በእርግጥ ነው በጋራ ሠርቶ ለመለወጥ ከሚደረግ ሩጫ በላይ አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የሚያደርገው ፍልሚያና ፍትጊያ እጅጉን ገዝፎ ይታያል። የሠራን የማድነቅና የማበረታታት ባህላችንም እንዲሁ ወደፊት ሊያራምደን ያልቻለና ኋላ ያስቀረን ደንቃራችን ነው።
ታድያ ‹‹መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ›› እንዲሉ ሆነና ነገሩ ኢትዮጵያውያን በሥራ ባህላችን በብዙ ብንታማም ዓለም የሌለው ጥብቅ የሆነ ማኅበራዊ ግንኙነት፤ አብሮ መብላትና መጠጣት እንዲሁም መረዳዳት ሀብት ንብረታችን ከመሆን አልፎ ልዩ ምልክታችን ሆኗል። ግለኝነት በነገሰበት በዚህ ዓለም ማዕድ አብሮ ከመቋደስ ባለፈ በኃዘንም ይሁን በደስታ ዘመድ አዝማድ ጎረቤት የሚረዳዳበትና ገመና የሚሸፋፈንበት ባህላችንም ከእሴቶቻችን አንዱና የምንኮራበት ባህላችን ነው።
ይሁንና በጋራ መሥራት ሳንችል በጋራ መብላታችን ብቻውን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያመጣልን አልቻለምና ዛሬም ደሃ ከተባሉ አገራት ተርታ ተሰልፈናል። ምንም እንኳን የድህነት ደረጃው የተለያየና ዘርፈ ብዙ መገለጫዎች ቢኖሩትም የኢትዮጵያውያን ድህነት ግን የድህነት ጥግ ላይ የደረሰ ለመሆኑ በየጥጋጥጉ በረሃብ የወደቀው ሕዝባችን፣ ለምጽዋት የተዘረጉ የበዙ መዳፎችና ደሳሳ ዛኒጋባዎቻችን ሁነኛ ምስክሮቻችን ናቸው።
ታድያ ከገባንበት የድህነት አረንቋ ለመውጣት ጠንክሮ መሥራት አማራጭ የሌለው ዘላቂ ምርጫ ቢሆንም የመረዳዳት አኩሪ ባህላችን ደግሞ ጊዜያዊ የረሃብ ማስታገሻችን ነው። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ምንም እንኳን ድሆች ብንሆንም ባለን አመስግነን፤ ካለን ላይ ቆርሰን በማካፈል ቀን የምንገፋ ብልሆችም ነን ። ለዚህም አንድ ሁለት ተብለው የሚቆጠሩ የመልካም ባህሎችና ታሪኮች ባለቤት በመሆን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለተራበ አጉራሽ፤ ለታረዘ አልባሽና የወደቀን በማንሳትም ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተናጠል ከሚደረጉ በጎ ሥራዎች ባለፈ ሚዲያውን በመጠቀም በቡድን በመሆን በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ።
በተለይም በሃገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተነሳሽነት በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ተሠርተዋል። ሥራዎቹም ፍሬ አፍርተው የብዙዎችን ቀዳዳ ደፍነዋል። ይህንን መነሻ ያደረጉ ሥራዎችን የተከተሉ መልካም ልቦች እዚህም እዚያም ተፈጥረው አይተናል። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ምንም እንኳን በሰዎች መልካም ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ ግለሰቡ በአሻው ጊዜና ቦታ ለሌሎች የሚያደርገው በጎ ነገር ቢሆንም በጎ ሥራን ባህል በማድረግ በጊዜ ገደብ ማከናወን የሚቻል እንደሆነም ማየት ችለናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምረው ለቁጥር የበዙ መልካም ሥራዎችን ሲሠሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ሰዋዊ በሆነው ባህሪያቸው ከደሃ እናቶች ጎጆ ዘልቀው የኑሮ ጎዶሏቸውን ሞልተዋል። በተለይም ዓመታዊ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ በሚለው መርሐ ግብር ከአቅራቢያቸው በመጀመር ጥቂት የማይባሉ እናቶችን የዘመመ ጎጆ በማቅናት ብርሃን ማየት እንዲችሉ አድርገዋል። ይሄው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተወስኖ እነሆ ዘንድሮም ቀጥሏል።
በቅርቡም የአረጋውያን፣ የአቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና በኢኮኖሚ የተቸገሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤት ማደስ ዓላማ ያደረገው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓመታዊ የበጎ ፈቃድ ሥራ መርሐ ግብር እንደተለመደው የአቅመ ደካሞችን ቤት በማፍረስ የግንባታ ሥራው ተጀምሯል። በየዓመቱ ክረምቱ ከመግባቱ አስቀድሞ የሚጀመረው ይህ የቤት እድሳት መርሐ ግብር በዘንድሮ ዓመትም በአዋሬ አካባቢ 23 ለሚደርሱ ግለሰቦች የመኖሪያ ቤት የግንባታ ሥራ ለመሥራት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በይፋ አስጀምረዋል።
በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን የሚያስመሰግነውና ሊበረታታ የሚገባው ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ታድያ አሁን አሁን በብዙዎች ዘንድ ተጋብቶ ይስተዋላል። በመሆኑም በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይህው መልካም ሥራ በተለይም የአቅመ ደካማ እናቶችን ቤት በማደስ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተው በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክተን ይበል ብለናል። ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያውያን የምንታወቅበትን አብሮ የመብላትና የመረዳዳት ባህል በዘላቂነት ለማስቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት መልካም ተግባር አንዱ ቢሆንም ቅሉ በየአካባቢያችን የተዘጉ ደጆችን መክፈት፤ ያዘመሙ ጎጆዎችን ማቅናት፣ የተራቡና የታረዙ ወገኖችን መጎብኘትና የኑሮ ሽንቁሮች መጠገን ከእያንዳንዱ የመልካም ልብ ባለቤቶች የሚጠበቅ ነው።
እርግጥ ነው በጎ የሚያደርጉ ሰዎች በራሳቸው መልካም ፍቃድና ተነሳሽነት የልፋታቸውን ዋጋ ሳይጠይቁ ወይም ከድርጊታቸው በስተጀርባ ሌላ ዓላማ ሳያነግቡ በአብዛኛው በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉበት ሰብዓዊ ተግባር ነው። በዓለማችን በተለያዩ ሃገራት የበጎ ፍቃድ ተግባር የሚያከናውኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች በርካቶች ናቸው። በኢትዮጵያም በመልካም ተግባር በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ዜጎች ብዙዎች ቢሆኑም መሪዎችን ብቻ ጠብቆ የሚሠራው ከሆነ ግን ዘላቂነት አይኖረውምና ለዘላቂነቱ ሁሌም ቢሆን ልባችንን በማዳመጥ ዙሪያችንን እንመልከት።
ኢትዮጵያውያን አለን የምንለውን አብሮ የመብላትና የመረዳዳት ባህላችንን ሀብት አድርገን መቆየት እንድንችል ሁሌም ቢሆን ካለን ላይ እናካፍል፤ ጊዜና ሰው ሳንጠብቅ መልካምን በማድረግ አኩሪ ባህላችንን አጠናክረን እናስቀጥል። መልካም ሥራ ረፍዶ ባያውቅም የየዕለት ተግባራችን ከማድረግ አንጻር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን አርመን ባለን አቅም ሁሉ በዙሪያችን የተራበ በማብላት፣ የታረዘን በማልበስ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ።
ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መረዳዳትና መተጋገዝን የሚያስገድድ ነውና ጠቅላይ ሚኒስትሩም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ግለሰቦች፣ የንግድ ተቋማት እና የመንግሥት ተቋማት ክረምት ከመግባቱ በፊት በአካባቢያቸው ላሉ አቅመ ደካሞች ምቹ እና ሰብዓዊ ክብርን መሠረት ያደረገ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ዓመታዊ ክንውን የበኩላቸውን እንዲወጡ ባቀረቡት ጥሪ በተለይም የንግድ ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ኑሮ ማሻሻል እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ታድያ ይህን የበጎ ተግባር በጎ ጥሪ ተከትለው ካለን ላይ ለብዙዎች ብዙ ማድረግ ይኖርብናል። በጎ ተግባር የሕግ አስገዳጅነት ባይኖርበትም የሕሊና አስገዳጅነት ግን አያጣም ። የተራበውን ፣ የታረዘውን ቤቱ በላዩ ዝናብ የሚያዘንበውን እያየን እና ከንፈር እየመጠጥን ከማለፍ አለፍ ብለን የመተጋገዝ ባህላችን ከፍ አድርገን እንተግበር። መልካምነት ዘግይቶም ቢሆን መልካም ዋጋን ይከፍላል። አሁንም በበጎ ተግባር ላይ የተሰማሩ ቅን ልቦች ያለንን አድናቆት እየገለጽን በቀጣይም በአገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች በስፋት የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ አብሮነታችን ደምቆ የሚታይበት መነጽር በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በአቅሙ የበጎ አድራጎት ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥል በማለት አበቃን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 4 ቀን 2014 ዓ.ም