ወተት በውስጡ በያዛቸው በርካታ ንጥረ ነገሮች አማካይነት ለሰው ልጆች ሁሉ በተለይም ለሕፃናት እጅጉን አስፈላጊ ነው። ይሁን እንጂ የወተት ልማት ዘርፉ በየጊዜው እየጨመረ ከመጣው የሕዝብ ቁጥር ጋር የተጣጣመ አይደለም። በመሆኑም በኢትዮጵያ የአንድ ሰው የወተት ፍጆታ በዓመት 19 ሊትር ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ ደግሞ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው የወተት መጠን እጅግ በጣም አነስተኛው እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከሰው ልጆች ዕድገት፣ ደህንነትና ጤንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘው ወተት በተለይም ለሕጻናት ዋነኛ ምግብ ሆኖ ያገለግላል። ከሕጻናት ባለፈም ወጣትም ሆነ አዛውንት ለሁሉም ሰው ገደብ በሌለው መጠን እንዲጠጡትና ከምግብ ይዘቱም ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ይመከራል። ወተት ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የካልሲየም እና የፖታስየም ማዕድናትን እንዲሁም ቫይታሚን ዲን የያዘ በመሆኑ ሁሉም ሰው ቢያንስ በቀን አንድ ብርጭቆ ወተት እንዲጠጣ ይመከራል።
ታዲያ ይህ ፍላጎቱና አቅርቦቱ አልጣጣም ያለው የወተት ምርት በአሁን ወቅት ከእጥረቱ ባለፈ የዋጋው መናር እስከ ሶስት ዓመት ወተት ብቻ መመገብ ያለባቸው ሕጻናት እንኳ ማግኘት እንዳይችሉ የወተት መሸጫ ዋጋው ትልቅ ችግር እንደሆነ ይነገራል። ታዲያ ከሰሞኑ በወተት ምርት ላይ እየታየ ስላለው የዋጋ መናር አንስተን ያነጋገርነው የቤት ለቤት ወተት አቅራቢ ለወተት ዋጋ መናር ምክንያቱ የመኖ መወደድ መሆኑን ይናገራል።
የቤት ለቤት ወተት አቅራቢው አቶ ጌታቸው አየለ፤ ከኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ አካባቢ የሚያመጣውን ወተት በመኖሪያ አቅራቢያው በሆነው ጀሞ ቁጥር አንድ፣ ቁጥር ሁለትና ቁጥር ሶስት ድረስ ሲያከፋፍል የቆየ ቢሆንም በአሁን ወቅት የከብቶቹ መኖ መወደድ በየጊዜው በወተት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲያደርግ አስገድዶታል። ይህም ለሥራው እንቅፋት ከመሆን ባለፈ ደንበኞቹን ሊያሳጣው እንደሆነ ይናገራል።
አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ሁለት ጊዜ ጭማሪ ለማድረግ መገደዱን የተናገረው አቶ ጌታቸው፤ በቅርቡ የአንድ ሊትር ወተት ዋጋ 30 ብር የነበረና በአሁን ወቅት ግን 60 ብር ለማድረግ መገደዱን ያስረዳል። በዚህ ምክንያትም አብዛኛውን ደንበኛ በወር ኮንትራት ገብቶ ሲወስድ የነበረ ውሉን እያቋረጠ ነው በማለት አጠቃላይ የኑሮ ውድነቱ እያደረሰ ያለው ጫና በተለይም የወተት ዋጋ መወደድና የምርት እጥረት መኖሩ ከባድ ፈተና መሆኑን ያስረዳል።
ቤት ለቤት ለሕጻናቱ ከሚከፋፈለው ወተት በተጨማሪ በየሱቁና ሱፐርማርኬቶች አካባቢ ለገበያ የሚቀርበው ወተትም እንዲሁ ከፍተኛ የሚባል ጭማሪ ያሳየ መሆኑን መመልከት ችለናል። ማማ፣ ሾላ፣ ሎሚ፣ ሐርሜና ወዘተ መጠሪያ ያላቸው ፓስቸራይዝድ የሆኑት የወተት አይነቶች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 20 ብር ይሸጡ የነበረ ቢሆንም የፋሲካ ጾም ከተፈታ ወዲህ ግን ማንኛውም የላስቲክ ወተት ዋጋ ከ28 እስከ 30 ብር እየተሸጠ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።
ቀድሞም የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ያለበት የወተት ልማት በአሁን ወቅት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ የታየበት ከመኖ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ስለመሆኑ ብዙዎች ያነሳሉ። እርግጥ ነው የወተት ዘርፉን ምርታማና ውጤታማ ለማድረግ የእንስሳት መኖን ማሻሻል ወሳኝ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ይታመናል። የመኖ ስትራቴጂ መኖር ያለበት ስለመሆኑም በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ይደመጣል። በቂና የተመጣጠነ የእንስሳት መኖ በአገሪቷ መልማትና መስፋፋት እንዳልቻለና ይህን ማስፋትና ማልማትም የግድ ነው ይላሉ።
ከመኖ በተጨማሪ የእንስሳቱን ዝርያ ማሻሻልም ወሳኝ እንደመሆኑ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በአገሪቱ በማምጣት እንዲሁም የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅ በወተት ምርት ላይ ውጤት ለማምጣት መሠራት ያለበት መሆኑ ይታመናል። ታዲያ በዘርፉ ምን እየተሠራ ነው? በአሁን ወቅት ያለው የወተት ዋጋ መናርስ ከምን የመጣ ነው? መፍትሔውስ? ስንል ላነሳነው ጥያቄ በግብርና ሚኒስቴር የወተት ሀብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አስመላሽ በርሄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።
በወተት ገበያ ላይ አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ውድነት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩትም በዋናነት የወተት አምራቾች ለወተት ልማት ግብዓት የሚጠቀሟቸው ምርቶች መካከል የመኖ ዋጋ መወደድ በዋናነት የሚጠቀስ ነው።
የመኖ መወደድ በአሁን ወቅት በወተት ዋጋ ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አድርጓል። ይሁንና የግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከዚህ ቀደም በወተት ልማትና ግብይት የሚታዩ መሰል ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ስትራቴጂ ቀርጾ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ጀምሯል። ከእነዚህም መካከል የመኖ አቅርቦት አንዱ ነው።
ለከብቶች አስፈላጊ የሆነውን መኖ በጥራትና በስፋት ማቅረብ እንዲቻል በተለይም ከተረፈ ምርት ጋር ተያይዞ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከፍተኛ መጠን ያለው ተረፈ ምርት የሚገኝባቸውን አካባቢዎች በመለየት የመኖ አቅርቦቱን ማሻሻል እንዲቻልና ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት እየተደረገ ሲሆን ለአብነትም በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና ሲዳማ ክልሎች ላይ ሥራው ተጀምሯል።
ሥራውም ከአራቱም ክልሎች የተውጣጡ ባለሙያዎች በማሰልጠንና ከግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች ጋር በማቀናጀት በየወረዳው ካሉ አርብቶ አደሮች ጋር መኖን የማሻሻል ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። መኖን በማሻሻል ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል እንዲሁም ሌሎች በዘርፉ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤
የመኖ እጥረትን ለማሻሻልና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከተጀመረው ሥራ በተጨማሪ በቅርቡ የወተት ዋጋ በገበያው ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ ምክንያት ከኅብረተሰቡ እየተሰሙ ያሉ ሮሮዎች ስለመኖራቸው አስታውሰው በዘርፉ ከተሰማሩ አካላትም የተለያዩ ጥያቄዎች እንደቀረቡላቸው ተናግረዋል። ጥያቄውንና የኅብረተሰቡን ሮሮ ተከትሎም ችግሩን ለመለየትና መፍትሔ ለማፈላለግ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
አጠቃላይ ለወተት ማምረት ከሚወጣው ወጪ 60 በመቶ የሚሆነው ለመኖ የሚወጣ ወጪ እንደሆነ በጥናት የተረጋገጠ መረጃ ያሳያል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በጥናት የተረጋገጠ ባይሆንም በአሁን ወቅት ደግሞ መኖ ከ60 በመቶ በላይ ወጪ የሚጠይቅ ስለመሆኑ እየተነገረ ነው። በመሆኑም በአሁን ወቅት የመኖ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመር ጥያቄ የሆነባቸው ወተት አምራች የሆኑ ማኅበራት ወደ ግብርና ሚኒስቴር የወተት ልማት ዳይሬክቶሬት ጋር እየመጡ ሲሆን ዳይሬክቶሬቱም አማራጭ ያላቸውን የመፍትሔ አቅጣጫዎች እያስቀመጠ መሆኑን አስረድተዋል።
በተለይም ባለሃብቱ ስንዴን በሰፊው እያለማ ከራሱ አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት እየተሠራ ነው። በከተማና ከተማ ዳርቻ የሚገኙ ወተት አምራቾች በዋናነት የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን ለወተት ላሞች መኖ የሚጠቀሙ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችም በተለያየ መንገድ እጥረት እያጋጠማቸው ይገኛል።
የተረፈ ምርቱ እጥረትም በአገር ውስጥ የሚገኙ የዘይትና የዱቄት ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ምርት እጥረት እያጋጠመው መሆኑ ነው። ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ምርት እጥረት ካጋጠመው የሚገኘውም ተረፈ ምርት እንዲሁ የሚቀንስ በመሆኑ መኖ መሆን በሚችለው ተረፈ ምርት ላይም እጥረት የተከሰተና እጥረቱም የዋጋ ንረት እንዲከሰት አድርጓል።
በአገር ውስጥ ከሚመረቱና ፕሮሰስ ከሚደረጉ ምርቶች መካከል ለእንስሳት መኖ የዘይትና የዱቄት ፋብሪካዎች ቀዳሚዎች ናቸው። ይሁንና በአሁን ወቅት ካለው ችግር በመነሳት የገጠመውን የመኖ እጥረት ለመቀነስ በተለይም ቢራ ፋብሪካዎች ከሚያመርቱት ምርት የሚገኘውን ተረፈ ምርት ከደላላ ውጭ በሆነ መንገድ መጠቀም እንዲቻል እየተሠራ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የመኖ ዋጋ መናር አጠቃላይ በአገሪቱ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የተያያዘ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ፋብሪካዎች በሚያመርቱት ምርት ላይ የሚጨምርባቸውን የተለያዩ ግብዓቶች ፣ የትራንስፖርት ጭማሪ እንዲሁም የሠራተኛ ወጪን በመደመር በተረፈ ምርት ላይ ጭማሪ ማድረጋቸው እንዳለ ሆኖ በመሐል ያለው ደላላ የዋጋ ንረቱን እያባባሰ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በመሆኑም በፋብሪካዎችና በወተት አምራች ማኅበራቱ መካከል ያለውን ደላላ ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ተረፈ ምርቱን ማኅበራቱ በቀጥታ ከፋብሪካዎቹ ማግኘት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሠራ ነው። ለዚህም ትልቁን ድርሻ መውሰድ ያለባቸው ወተት አምራች ማኅበራቶቹ ናቸው። ማኅበራቱ ገፍተው በመሄድ ከፋብሪካዎች ጋር ቀጥታ ግንኙነት መፍጠር አለባቸው። በዚህ ጊዜ ተረፈ ምርቱን ከደላላ ውጭ በሆነ መንገድ ማግኘት ይችላሉ። ይህን አማራጭ መጠቀም እንዲችሉም ዳይሬክቶሬቱ የማመቻቸት ሥራ እየሠራ ሲሆን መንግሥትም ገበያውን የማረጋጋት ሥራ መሥራት ያለበት እንደሆነ ተናግረዋል።
አጠቃላይ በሃገሪቱ የሚቀርበው የወተት ምርት ከአነስተኛ አርሶ አደሮች አካባቢ እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በእነዚህ አነስተኛ አርሶ አደሮች እጅ የሚገኙት የወተት ላሞች ደግሞ ከአምስት ያልበለጡ ናቸው። እነሱም ምርታማነታቸው ዝቅተኛ ነው ይላሉ። የወተት ላሞቹ ሃገረሰብ ዝርያዎችን የያዙ በመሆናቸው ቢበዛ በቀን እስከ አንድ ነጥብ አራት ሊትር ወተት የሚሰጡ ናቸው። ነገር ግን በአሁን ወቅት በማዳቀል ቴክኖሎጂ የሚይዟቸው ዝርያዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም በቀን እስከ ስድስት ሊትር ወተት መስጠት የሚችሉ ናቸው።
ይሁንና ከእነዚህ አርሶ አደሮች የሚገኘው የወተት ምርትም ሙሉ ለሙሉ ወደ መደበኛ ገበያው ወይም ወተት መሰብሰቢያ ጣቢያ እየገባ አይደለም። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ሲሆን የወተት ገበያው በመደበኛ የገበያ ሥርዓት እየተመራ አለመሆኑ አንዱ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተው፤ የወተት ግብይት ሥርዓቱ ጠንካራ አለመሆን አንዱ ችግር ነው ብለዋል።
የወተት ምርቱ ወደ ገበያ የሚወጣው በአብዛኛው መደበኛ ባልሆነ የገበያ ሥርዓት በመሆኑ ቁጥጥርና ክትትል የለውም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ቁጥጥርና ክትትል በሌለው ሁኔታ የሚመጣ ምርት ደግሞ የዋጋም ሆነ የጥራት ቁጥጥር አይኖረውም። ስለዚህ በአሁን ወቅትም የሚታየው የዋጋም ሆነ የጥራት ችግር ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው።
በሃገሪቱ በዋናነት ወተት የማምረት አቅም አላቸው ተብለው የተለዩ ክልሎች አሉ። በተለይም በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ደብረብርሃንና ሰሜን ሸዋ ሲሆኑ፤ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ፣ ሻሸመኔና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ ደግሞ አዳማና አሰላ አካባቢ የወተት ምርት ስለመኖሩ ተለይቷል። በሲዳማ ክልልም እንዲሁ ሀዋሳ ዙሪያና ዲላ የሚገኝ ሲሆን በደቡብ ክልል ደግሞ ከምባታ ጠንባሮ አካባቢ ከፍተኛ አቅም ያላቸው መሆናቸው ተለይቶ ከዝርያ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠራ ነው።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠራው ዝርያን የማሻሻል ሥራ በቀጣይ ውጤት ማምጣት የሚችል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም መንግሥት ተነሳሽነቱን ወስዶ በተለያዩ የምርምር ማዕከሎችና ራንቾች ላይ የቦረናና የፎገራ ከብቶችን በማስገባት የማዳቀል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍም በስፋት ገብቶ መሳተፍ ያለበት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከመንግሥት በተጨማሪ በተለይም ከዝርያ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ የማዳቀል ሥራ ላይ እንዲሁም ብዜት ላይ የግል ባለሃብቱ ትልቅ ድርሻ ያለው ነውና ሊሳተፍ ይገባል። የግል ባለሃብቱ በዘርፉ መሳተፍ እንዲችል በመንግሥት በኩል ከመሬት አቅርቦት ጀምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በማሟላት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንዳሉና የተጀመሩት ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመጨረሻም ከመኖ ጋር ተያይዞ የመኖ አቅርቦትን በስፋት ለማምረት ከፋብሪካዎች በተጨማሪ የወተት አምራች ማኅበራቱ በራሳቸው መሬት በመጠየቅ መኖ አምርተው ለራሳቸውም ሆነ ለሌሎች መትረፍ የሚችሉበትን መንገድ በመከተል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበት አጋጣሚ መኖሩን በመግለጽ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014