ታሪክ ማለት…
ሃገር እንደ ሃገር የቆመው በትናንቱ መደላድል ላይ ስለመሆኑ ገላጭ አያስፈልገውም። የዛሬ መሠረቱ ትናንት ስለመሆኑም ደጋግመን ጽፈናል። ትናንትን ትናንት ያሰኘውም ጠቅልሎ የያዘው ታሪኩ ነው። ዛሬንም ዛሬ ያሰኘው ኑሯችን ሲሆን፤ ነገን ነገ የሚያሰኘው ደግሞ በተስፋ መታጨቁ ነው። ስለዚህም ትናንት ስብዕናችንን ቀርጾ ለዛሬ አቀብሎናል። ዛሬ ከኑሮ ጋር እያታገለ ያፋልመናል። ነገ በተስፋ እንቁልልጮሽ እያማለለ እንድንናፍቀው ያባብለናል፤ ሲለውም እያስበረገገ ያባንነናል። እነዚህ ሦስቱ የጊዜ ገጾችና ምዕራፎች ሊገለጡና ሊመረመሩ የሚገባቸው እንደየባህርያቸው ነው የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
“በእኔና በስብሑ የማይበረታ የለም” አለ ይባላል፤ በወገኖቹ መገፋት የተማረረ “እከሌ” የማይባል የሃይማኖት አገልጋይ። “ስብሑ”፡- ስብሐት ለአምላክ፣ ምሥጋና ለፈጣሪ እንደማለት ነው። ይህንን ቃል አብዛኛው የክርስትና እምነት ተከታይ በሰርክ ጸሎቱና ማዕዱን ከመቁረሱ አስቀድሞ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት የአፍ ማሟሻው ነው። የተማረም ይሁን ማይም ምዕመን ይሄንን ቃል ሳይጠራ ውሎ አያድርም። ከቤተ እምነት ደጀሰላም እስከ እያንዳንዱ ግለሰብ ደጃፍ ፈጣሪ የሚመሰገንበትን ይህንን የሁሉም የሆነ አባባል ለማስታወስ የተፈለገው አንድ “ብጤ ጉዳይ” ለማስታወስ ተፈልጎ ነው።
ነገረ ታሪክም እንዲሁ ልክ እንደ “ስብሑ” የፈለገ ሁሉ ሲያነሳውና ሲጥለው የሚውል የጋራ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። ማንም ተነስቶ ታሪክ ልተርክ ቢል “የት ታውቅና”፣ ወይንም “መቼ ደረስክበትና” አለበለዚያም “ማስረጃህን አቅርብ” ተብሎ አይገሰጽም፣ አይወቀስምም። ማንም እየተነሳ የታሪክን እውነታ ቢሰብር፣ ቢያጣምምና እንዳሻው ጭራና ቀንድ እየጨመረ ከራሱና የራሱ የክፋት ዓላማ ማስፈጸሚያ ሰሌዳ ላይ ቢጽፍና ቢስል ወይንም ቢያሾፍና ቢያላግጥ የአርምሞ ትዝብት ይተርፈው ካልሆነ በስተቀር ተቆጭም ሆነ ተሟጋች እስከማይኖር ድረስ “የታሪክ ጉዳይ እንደረከሰ የገበያ ሸቀጥ” የሚያፍሰውና የሚበረታበት ሁሉም ዜጋ ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ።
“ታሪክ አይጣመም! ታሪክ አይወላገድ! ወዘተ.” እያለ በመጮኽ የሚገስጽ አልጠፋም ቢሰኝ እንኳን ለወቀሳውና ለአራሚነት ፈጥነው ምላሽ የሚሰጡት “እኛ የተሻለ እናውቃለን” የሚሉ ሰዎች እንጂ “እስቲ እነ እከሌ ይጠየቁ” ተብሎ ሁነኛ ምስክር ለመቁጠር እንኳን እያዳገተ ስለመሆኑ ዋቢያችን የውሎ አምሽቷችን ገጠመኝ ነው። ስለዚህም የስብሑን ምሳሌ በመዋስ በትናንቱ ታሪክ ላይ መሟገቱ ዋና ጉዳይ ሆኖ ዛሬ መዘንጋቱ ሆድ አብሶ ግድ ያለን ዜጎች “በእኛና በታሪክ የማይበረታ የለም” ብለን አባባሉን ከዐውዳችን ጋር ብናስማማ “ይደልዎ!” ቢያሰኝ እንጂ የሚያስወቅስ አይመስለንም። በተለይም በዚህ ግራ ቀኙ በጠፋን ወቅት፣ ከዕለት ኑሮ ጋር መፋለሙና በኃዘን መርዶና ጨርቅ መቆራመዱ ያነሰን ይመስል በነበር ታሪክ ላይ ዱላ እያሳረፉ የሚያጯጯኹትን ሃይ የሚልልን ኃይል አጥተን እንዲሁ እንደተብሰለሰልን “ኑሮ ካሉት…” እያልን፤ ኑሮን እንገፋለን።
በአጥናፈ ዓለማችን ዙሪያ-ገብ ላይ የተመራመሩ፣ የተራቀቁና ለሰዎች ልጆች በጎ በመዋላቸው ከሚጠቀሱት ብርቅዬ የምድራችን የዕውቀትና የጥበብ ፈርጦች መካከል “ታሪክ ማለት…” እያሉ ድንጋጌና ፍቺ ያልሰጡት ይመረጡ ቢባል ልንቆጥር የምንችለው ጥቂቶችን ብቻ ነው። ለምን ቢሉ የታሪክ ባለሙያዎች ብቻም ሳይሆኑ የበርካታ የሙያ ዘርፍ ባለቤቶች ሳይቀሩ ስለ ታሪክ ብያኔ ቁጥር ስፍር የሌለው ድንጋጌ ለመስጠት ሞክረዋልና። ዛሬም ድረስ እየሰጡ እንደሚገኙ ቴክኖሎጂ ደጉን በማማከር ብቻ ምላሹን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
ስለ ታሪክ ምንነት ከሚያወሱት ተደጋጋሚ፣ ተጠቃሽና ተወዳጅ ጥቅሶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ቆንጥረን በማስታወስ ወደ መነሻ ጉዳያችን እናቀናለን። “ታሪክ በአንቱታና በግድፈቶች የተሞላ የኩነቶች ድምር ውጤት ነው።” የሚለውን አስቀድመን ሌሎቹን እናስከትላለን። “ታሪክ ያለፈ ክስተት ብቻ ሳይሆን ከአንድ አቅጣጫ የተቃኘ የኃላፊ ጊዜያት ጠቋሚ ካርታ ጭምር ነው። አንተ ዘመንኛው ተጓዥ ሆይ! በካርታው ካልተመራሁበት ብለህ ግብ ግብ አትፍጠር።
ታሪክ እንደ ኮምፓስ የቀደመውን መንገድ በትዝታና በነበርነቱ እንድታስታውስ፣ እንድታከብርና መሰል ስህተት በዛሬዋ ጀንበር እንዳትፈጽም የሚረዳህ ነው። ከበጎነቱም እንድትማር ያግዝሃል እንጂ እንደ አሠርቱ ትእዛዛት ከዘፍጥረት እስከ ዘመነ ፍጻሜ እንድትመራበት “በሙሴ በጽላት” መልክ ተቀርጾ የተሰጠህ መመሪያ አይደለም።” ሦስተኛ ሠልሰን እናብቃ። “ታሪክ ተገቢውን ምላሽ ሊሰጥ የሚችለው ምንና እንዴት መጠየቅ ለሚችሉት ብቻ ነው።”
ታሪካችን እፎይ ይበል ስንል…
ቀደምት ታሪኮቻችንን እረፍት በመንሳት በነጋ በጠባ እየጠቀስን የምንኮራባቸውንና የምንራኮትባቸውን አንዳንድ ጉዳዮች እየጠቃቀስን እንደተለመደው ጥቂት ደቂቆች መድበን ለማሰላሰል እንሞክር። “ብዙ ዜጎች በኃላፊ ታሪክ ላይ ዱላ እየመዘዙ ለመቀጥቀጥ እጅግ ብርቱ ናቸው።” ጥቂት ማከያ ሃሳብ እንፈነጣጥቃለን።
እንኳን እስትንፋሳቸው ቀርቶ አጽማቸውንም ቢሆን በአግባቡ ማግኘት ከሚያዳግት “ተወቃሽ ናቸው ከሚላቸው” ባለ ታሪኮች ጋር ፍልሚያ ካልገጠምን እያሉ የሚያቅራሩ አንዳንድ ሳይሞቅ ፈላ የነገር “ጎታዎች” ወላንሶ መግጠማቸው የጀግንነት ወኔ ግድ ስለሚላቸው ሳይሆን ፈሪ ስለሆኑ ነው። ራሱን ለመከላከል አቅም የሌለውን ታሪክና ከመቃብር በታች የዋሉ ባለታሪኮችን በሚመዙት የእብሪት ዱላ አናት አናታቸውን የሚሏቸው “የጅል ፈሊጥ” ተጠናውቷቸውና የቂም በቀል ጥማታቸውን ያረኩ እየመሰላቸው ስለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን በመጠቃቀስ መወያየት ይቻላል።
እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ባለፈ ታሪክ ለመጣላትና ሰይፍ ካልተማዘዝን ብለው የሚያቅራሩት ፍልሚያው አሸናፊም ይሁን ተሸናፊ እንደማይኖረው ጠፍቷቸው አይደለም። እንደ “መስቀል ጦርነትም” ከዘመን ዘመን የሚሸጋገር “ጠብ ያለሽ በዳቦ” ይሉት ዓይነት ኩነኔ መሆኑም ስላልገባቸው አይደለም። ይልቁንስ ይህንን በማድረጋቸው ስብዕናቸውን ለማግዘፍና ባዶነታቸውን የጋረዱ እየመሰላቸው ነው። ባይሆን ኖሮማ “ስህተት ነበር” የሚሰኘው የታሪክ ክስተት እንኳን ሊታረም የሚችለው በሰላማዊ ውይይትና ምክክር እንጂ “በቆፈሩት ምሽግ ውስጥ” ተገን ይዘው በመታኮስ መሆን አልነበረበትም። “የተሳሳተ” የሚሰኝ ታሪክን ለማረም ከሰይፍና ከጎመድ ይልቅ የሚያዋጣው ውይይት! ወይይት! ወይይት! ብቻ ነው።
የሆነው ሆኖስ እስቲ አከራካሪ ታሪኮችን ብቻም ሳይሆን ደፈርና ጠንከር ብለን “ታሪካችን” እያልን የምንኩራራባቸውንና የምንዘናጋባቸውን አንዳንድ ክስተቶች እየጠቃቀስን እንወያይ። ቀደም ባሉት ጽሑፎቼ በተደጋጋሚ ለማስታወስ እንደሞከርኩት አገራችን የታሪክ ባለጸጋ ብቻ ሳትሆን የተግባር ድሃ መሆኗንም ጭምር በአግባቡ ልንነግራት ይገባል።
ኢትዮጵያ ሦስቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች (የአይሁድ እምነትን፣ ክርስትናንና እስልምናን) የተቀበለችው በሰላም እጆቿን ዘርግታ በፍቅር እያቀፈች እንደነበር በቀዳሚው ጽሑፎቼ ዝርዝሩን አስነብቤያለሁ። ሃይማኖቶቹ ቤትኛ ከሆኑ በኋላ ግን በረጂሙ የታሪካችን ጉዞ ውስጥ የኖሩትና የተስፋፉት ያለ እንከን ነበር ማለት ግን አይደለም። በሰላምና በፍቅር የተስተናገዱት እነዚህ የሺህ ዓመታት ባለታሪክ ሃይማኖቶች ዛሬ ዛሬ ምን ያህሉ “ከማራኪ መዓዛቸው” ጋር አሉ? ምእመናኖቻቸውስ ምን ያህል በተሰበከላቸው የፍቅርና የሰላም መልዕክት ታንጸው እምነታቸውን ለመተግበር እየጣሩ ነው? የየእምነቱ ቀኖናዎችና ትምህርቶች አማኒያኑን ወደ ፈጣሪ ለማቅረብ ምን ያህል ብርታትና አቅም አላቸው? የየእምነቶቹ “አበ ነፍሳትስ” ምን ያህሉ የሰላም ሐዋርያትና የበጎነት ተምሳሌቶች ናቸው?
በየደጀሰላሙ ምስባኮች ላይ የሚጎርፈው የየእምነቱ ትምህርትና እግዚኦታስ ምን ያህሉ ወደ ፈጣሪ መንበር ደርሶ ምህረትና ፈውስ ይዞ የመምጣት መንፈሳዊ ብርታት አለው? በሃይማኖት ስም ከሚጠፋፉት ነፍሳት መካከል “የሚጸድቀው” የትኛው ነው? ንጹሑና ደሙ የፈሰሰው “አቤል” ወይንስ በሃይማኖት ቀናኢነት ደም የሚያፈሰው “ቃየል?” የበጎነቱ ሥራ በፈጣሪ መዝገብ ላይ የሚመዘገብለትስ የሌላውን ሃይማኖት ማምለኪያ ሕንጻ እያቃጠለ የፈጣሪን ስም የሚያሞግሰው ነው? ወይንስ ቤተ እምነቱ ስለተቃጠለበት እምባውን እያፈሰሰ ፍርድን የሚማጸነው?
ለእነዚህን መሰል ሺህ ምንተ ሺህ ጥያቄዎች ጥርት ያለ ምላሽ እስካላገኘን ድረስ “ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ዘጠና ዘጠኝ ከመቶው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሃይማኖት ተከታይ ነው” እያልን የምንፎክርበትን እስታትስቲክ ለጊዜው ከፊታችን ዞር አድርገን ብናስቀምጠውና ባንጠቅሰው የተሻለ ይሆናል። ለምን ቢሉ የቁጥሩ ትምክህት አዋረደን እንጂ አላከበረንም፤ አሳቀቀን እንጂ አላሳቀንም።
ስለዚህ የሃይማኖቶቻችንን ጥንታዊ አገባብና የምዕመኑን የዛሬ ቁጥር ችላ ብለን፣ ከታሪክ ሙግቱና አታካራም ፋታ በመውሰድ ራሳችንን ገለል በማድረግ ከፈጣሪያችን ጋር ብቻ በጓዳችን ውስጥ ጣጣችንን መጨረሱ ብልህነት ነው። የየሃይማኖቱ ቤተእምነቶችም ቢሆኑ “የምዕመናኖቻችን ቁጥር በሚሊዮን የሚሰላ ነው” እያሉ መፎከሩንና ማስፎከሩን ለጊዜው ተወት አድርገው እንደ ሃይማኖታዊ ባህላቸው በንስሐና በሱባዔ ከፈጣሪ ጋር ቢስማሙና ቢታረቁ ይበጃል።
ሌላውና ደማቁ አገራዊ ቀረርቷችን ከእንግዳ ተቀባይነታችን ጋር የሚያያዘው ትምክህት ነው። እርግጥ ነው በቀደምት ታሪኮቻችን ውስጥ የሚጠቀሱ አንዳንድ በጎ ተግባራት መኖራቸው ላይካድ ይችል ይሆናል። ለምሳሌ፡- የሃይማኖቶችን ወደ አገራችን መግባትና አቀባበላቸውን በተመለከተ ከላይ የጠቀስነውን ታሪክ ደግሞ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። በአንዳንድ የሃገራችን የገጠር አካባቢዎች የእንግዳ ክብርና በፍቅር የታጀበ አቀባበል ሙሉ ለሙሉ ተሟጦ ጠፍቷል ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገርም ያዳግታል። ምክንያቱም ቅሪቱ ዛሬም ድረስ ስላልደበዘዘ።
ነገር ግን እውነቱን አፍርጠን እንተማመን ከተባለ በዛሬው የአገራችን ዐውድ አንኳንስ እንግዳና የአካባቢው ነዋሪ ዜጎችስ በአንቱታ ይከበራሉ። “መጤ ስለሆንክ ከአካባቢዬ ውጣ!” እየተባሉ ስንቶቹ ለዓመታት ከኖሩበት መኖሪያቸው እየተፈናቀሉ አይደለም? ንብረታቸውስ አልወደመም? በግፍና በጥላቻስ የሺህዎች ደም ደመ ከልብ ሆኖ ቀባሪ እንኳን አጥተው የአውሬ ሲሳይ አልሆኑም? ለአንድ አካባቢ ባዕድ የሆነ ዜጋስ እንደልቡ ለሥራም ይሁን ለግል ጉዳይ ከአገሩ ጫፍ እስከ ጫፍ በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላል? ሠርቶ ንብረት ማፍራትስ መብቱ ነው?
የዓለም ሃገራትና ሕዝቦች ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያውቋት በእንግዳ ተቀባይነቷ ነው ወይንስ ዜጎቿን ለስደት በማበረታታትና ባዕዳን ሕዝቦች ልጆቿን “እንዲያዝሉላት” ሸክም አድርጋ በመወርወር? ቢመርም፣ ቢኮመጥጥም አፍረታችንን ሳንሸሽግና ያደግንበት የማለባበስ ባህል ሳይጫነን በታሪክና በባህል የተጀቦንባቸውን ገመናዎቻችንን ልንገላልጥና ልንወያይባቸው ይገባል። የተኮፈስንባቸውንና በሰንኮፎቻቸው የተለከፍንባቸውን ማኅበራዊ ደዌዎችንም እያፈረጥን ለመፈዋወስ መጨከን ይኖርብናል። የሚበጀው ከታሪክ ኩራታችንንና ሙግታችን ለጊዜው ፋታ በመውሰድ ወደ ኅሊናችን ተመልሰን ለፈውስ መሥራቱ ላይ ነው። ለጥሞና ጊዜ በመውሰዳችንም ስናንቆለጳጵሳቸው የኖርነው ታሪኮቻችን የትም አይሄዱብንም። የምንፎክርባቸው ባህሎቻችንም አይሸሹንም። ይኼው ነው። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014