አገር በትናንት ተግባራችን ዛሬ የደረሰች፤ በዛሬ ኑረታችን ፍሬ ለነገ የምትሻገር፤ በሕልምና ትልማችን ልክ ለነገው ትውልድ የምንሰራት ናት። የትናንት መሪዎችና ሕዝቦች የዛሬዋን አገር በሕልማቸው ሰርተው እንዳስረከቡን፤ የነገዋን ታላቅ አገር ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ አጽንቶና ሰርቶ ማሻገር ደግሞ ከዛሬው የእኛው ትውልድ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው። ይህ የሚሆነው ግን የትናንቷ ኢትዮጵያ እና ቀደምቶቹ ኢትዮጵያውያን በትናንት መስታወትነት ሲፈተሹ፤ የአሁኑ ባላደራዎችም በዛሬ ምግባርና ሕልማቸው ሲመዘኑ፤ የሁለቱ ድምር ውጤትም ስለ ነገዋ ታላቅ አገርና ስለመጪው ትውልድ የሚፈጥረውን የጠራ የብልጽግና መስመርና ከፍታ በሚኖረው ሕልም ልክ ሲፈተሽ ነው።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በጅግጅጋ ከተማ አንድ ታላቅ መርሃ ግብር እያከናወነ ይገኛል። ይህ መርሃ ግብር “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሲሆን፤ በመርሃ ግብሩ የፎቶ አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍ ምርቃት እንዲሁም በኢትዮጵያ አሁናዊ ፈተናዎችና መልካም እድሎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት የተካሄደበት ነበር። የእነዚህ ሶስት ሁነቶች ግብም ኢትዮጵያን በትናንት ኑረቷ፣ በዛሬ እውነቷ እና በነገ ተስፋዎቿ ላይ ሰፊ ውይይትና ምልከታ በማድረግ ግንዛቤን ማስጨበጥ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸው ጥያቄዎች፣ እንዲሁም የመሪዎቻቸው እሳቤና ምላሽ ትናንት ምን ነበር? ዛሬ ላይስ እንዴት ይገለጻል? ነገ እንዲሆን ከሚጠበቀው አኳያ ምን ሊከወን ይገባል? የሚሉ ሁነቶች ላይ ያተኮረም ነው።
ይሄን በተመለከተ ከውይይቱ መድረክ ባለፈ በተለይ የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩንና የፎቶ መጽሐፉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ እንዳመለከቱት፤ የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕዩ በየዘመኑ የነበሩ መሪዎች ምን ርዕይ ነበራቸው? በየዘመናቱ የተነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ምን ነበሩ? እንዴትስ ተመለሱ? አገዛዞቹስ የሕዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ ረገድ ምን ተሳካላቸው? ምንስ አልተሳካላቸውም? የሚለውን የሚያሳይ ነው። በድርጅቱ ተዘጋጅቶ የተመረቀው ስለኢትዮጵያ የፎቶ መጽሐፍም በዋናነት ያካተተው በንጉሱ፣ በደርግና በአህአዴግ ዘመን የነበረውን ሀገራዊ ህልም፣ የሕዝብ ጥያቄና የስርዓት ለውጥ ሲሆን፤ ከሀገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘም ስለ ኢትዮጵያ ፈተና፣ ድልና ተስፋ የሚያመላክት ነው።
በኢፕድ የተዘጋጀው ይሄን አይነት መርሃ ግብር ዛሬ አገር ይዞ ያለው ሕዝብም ሆነ አገር እየመራ ያለው መሪ (ስርዓቱ እንደ አጠቃላይ)፤ ስለ ትናንት የሕዝብ አስተዳደርና ጥያቄዎች እንዲሁም ለጥያቄዎቹ ይሰጡ የነበሩ ምላሾች እንዲገነዘብ እድል የሚሰጥ ነው። ይህ ሲባል በወቅቱ የነበረው ሥርዓት የነበረውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምልከታ፤ የሕዝቡ እና የሥርዓቶቹን ቁርኝት፤ ሕዝቡ በየሥርዓቶቹ ሲያነሳቸው የነበሩ ሁሉን አቀፍ ጥያቄዎች ይዘትና ትኩረት፤ ብሎም የየዘመናቱ ሥርዓት መሪዎች የህዝብን ጥያቄ ተቀብለው የሚያስተናግዱበትን (በመልካምም በመትፎም የሚነሱ ሊሆኑ ይችላሉ) አግባብ እንዲያውቅ የሚያስችሉ ናቸው። ይህ ሲሆን ደግሞ የትናንቶቹ ሥርዓቶችና አመራሮች ከሕዝባቸው ጋር ያላቸውን አዎንታዊም አሉታዊም ቁርኝት ከመገንዘብ ባለፈ፤ ዛሬውን እንዲፈትሽና ነገውን በወጉ እንዲተልም መንገድ አመላካቾችም ሆነው ያገለግላሉ። ምክንያቱም የትናንት መልካም ግንኙነቶች ለዛሬው መሰረት የሚጥሉ እንደሆኑት ሁሉ፤ ያልተገቡ ሂደቶችን በመለየት ዛሬ ላይ ታርመው የተሻለ ስልትና መንገድ ለመያዝ ትምህርት ስለሚሰጡ ነው። ይህ ግን ሁሉም እንዳለ ይወሰዳል ወይም ይጣላል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ትናንት የነበረው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነት ከዛሬው ጋር የሚወራረሰውም፣ የሚያለያየውም አያሌ እውነቶች አሉ። በመሆኑም የትናንቱን መልካምም ሆነ መልካም ያልሆነ ሂደት ለዛሬ ትምህርት የማድረጉ ጉዳይ እንደየዘመኑ እውነትና ተጨባጭ ሁኔታ እየተመዘነ የሚወሰድ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባው ነው።
ይህ ሲባል የትናንቱ አገራዊና ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ከዛሬው ጋር ሊገናዘብ ያስፈልጋል። የትናንቱ የሕዝብ ፍላጎትና ትያቄ ከዛሬው የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ጋር ሲነጻጸር አገራዊ ገጹም የቴክኖሎጂ እድገቱም ጋር ተገናዝቦ መሆን ይጠበቅበታል። ለምሳሌ፣ የትናንቱ የመደብ፣ የመሬት ላራሹና የብሔር ጥያቄ እና የነበረው ምላሽ ዛሬ ላይ በትናንቱ ቅርጽና ይዘት አይቀርብም። ምናልባት ዛሬ ላይ ከፍ ብሎ የሚነሱት እኩል የመልማትና ተጠቃሚነትና፣ ሰላምና ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና መሰል ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ የዛሬ ጥያቄዎች ደግሞ ሚዛናቸው ይለያይ እንጂ ትናንትም ሲጠየቁ የነበሩ ናቸው።
ለምሳሌ፣ ዛሬ ላይ ከፍ ብሎ የሚነሳው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ጉዳይ፤ ትናንት በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም የሚነሳ፤ በደርግ ስርዓትም ሆነ በኢህአዴግ ወቅት የሚስተጋባ ነበር። ጥያቄውም እንደየሥርዓቶቹ መልክና አተያይ ሲመለሱ መቆየታቸውም እሙን ነው። ታዲያ በየሥርዓቱ ጥያቄዎቹ እንዴት ተነሱ፤ እንዴትስ ሥርዓቶቹ አራማጆች ምላሽ ተሰጣቸው፤ የሕዝቡስ እርካታ ምን ነበር፤ አሁንስ ከእነዚህ ሂደቶች ምን መልካም ነገር ሊወሰድና ሊጎለብት፤ ምን ክፍተቶችስ ታርመው ሊስተካከሉ ይገባል? የሚለውን ወስዶ ዛሬ ላይ የሚነሳውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ጥያቄ በልኩ ለመመለስ እድል ይገኝበታል።
በተመሳሳይ ሌሎች የሰላምና ፀጥታ፣ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የልማት፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣… ጥያቄዎች የዚህ ዘመን ጥያቄዎች ብቻ ያለመሆናቸውን ለመረዳት እድል ከመስጠቱ ባሻገር፤ እነዚህን ጥያቄዎች በየዘመናቱ ለመመለስ የተሄደባቸውን ርቀቶች ለመመልከት፣ ከእነዚህ ልምድ ቀምሮና ከዘመኑ ጋር አስማምቶ ለመስራት እድል የሚሰጥ ነው። ይህ ደግሞ በተለይ ከለውጥ ማግስት ያለውን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና የማረጋገጥ ጉዞ በማሳካት ረገድ ልምድን በመቀመር ትልቅ አቅም ፈጥሮ ለመስራት የሚቻልበትን አውድ የሚፈጥር ይሆናል።
በመሆኑም እንዲህ አይነት ሁነት በተለይ ዛሬ ላይ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችንም ሆነ ችግሮች ምላሽና እልባት ለመስጠት መንገድ ከማመላከቱ ጎን ለጎን፤ ዛሬን አልፈን የምናልመውን ነገ ለመስራት ያሉብንን ፈተናዎች፣ ያስመዘገብናቸውን ድሎችም ሆነ ያሉንን እድሎች በወጉ እንድንለይ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም የትናንቱ ጉዞ ለዛሬው መሰረትም ትምህርትም እንደሚሆን ሁሉ፤ ከትናንት ተምረን ዛሬ ላይ የምናኖረው መልካም መሰረት ለነገ መዳረሻችን ጽኑ አምድ ሆኖ ያሻግረናል። ለዚህ ደግሞ ነገ ምን ለመሆን አስበናል? ሕልማችን ጋ ለመድረስ ምን እንዴትስ መስራት አለብን? በሂደቱስ ማን ምን መስራት አለበት? የሚሉና መሰል መሰረታዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ጉዟችን በተባበረ አቅም እንዲፋጠንና እንዲሳካ ያደርግልናል። ስለሆነም “ስለ ኢትዮጵያ” መርሃ ግብር የኢትዮጵያችንን ትናንት ተረድተን፣ ዛሬን ተባብረን ነጋችንን እንድንሰራ መንገድም አቅምም የሚያቀብል እንደመሆኑ፤ ሊዘልቅም ሊሰፋም ይገባል።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 /2014