ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ በተለየ ሁኔታ ከሚገልጹ በርካታ መገለጫዎች መካከል የእምነት ተቋማትና ተከታዮቻቸው ለዘመናት ተቻችሎ የመኖር ዕሴት በዋነኝነት ይጠቀሳል:: በአገሪቱ የሚገኙ እምነቶችም የሚታወቁትም አንዳቸው ከሌላው ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት ነው::
ይሁንና አንዳንዶች ይሕን የዘመናት የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የመተዛዘንና መረዳዳት ውድና መልካም ዕሴት ለማጥፋት በተደጋጋሚ ሞክረዋል:: አንድ ጊዜ በሃይማኖት ሌላ ጊዜ በብሔር ስም ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት ጥረት ሲያደርጉም ተስተውለዋል::
ሰሞኑንም በተለይም የእምነት ካርድ በመጠቀም በተለይ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለማጋጨትና ይህንንም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋት በኢትዮጵያ ውስጥ የማይጠፋ እሳት ለመለኮስ ሙከራ ማድረጋቸው ይታወሳል::
በዚህ ሂደት ውስጥም ሴራውን በውል ያልተገነዘቡ ጥቂት የተለያዩ እምነት ተከታዮች ጉዳዩን ለማራገብና አገራችንን ወደለየለት ብጥብጥ ለማስገባት ሞክረዋል:: ሁከትና ግርግር እንዲፈጠርና የዜጎች ሕይወት እንዲጠፋና ጉዳት እንዲደርስ፣ ሀብትና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል::
ይሑንና አብዛኛው ሕዝብ አላማውን በመገንዘቡ የታለመው ሴራ ሊከሽፍ ችሏል:: ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገውና በአክራሪነትና በጽንፈኝነት እሳቤ የተፈጸመውን ድርጊትም፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የእምነቶቹ ተከታዮች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በፅኑ ተቃውመውታል::
አዲስ ዘመንም ለዘመናት በሰላምና በፍቅር የኖረውን ሕዝብ እርስ በእርሱ ለማጋጨት የሚተጋው አካል ምንጩ ከየት ነው? የሃይማኖት ግጭት ጠማቂዎች እነማን ናቸው? ደባውን ለማክሸፍ የእምነት ተቋማትና አባቶች ሚና ምን መሆን አለበት? በቀጣይስ ከሃይማኖት ተቋማትና፣ አባቶች እንዲሁም ከምእመናን ምን ይጠበቃል? የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርቧል::
አስተያየት ሰጪዎቹም ለዘመናትን የተሻገረውን የእምነት ተቋማት አንድነትና መቻቻል ለመናድና በተቋማቱ መካከል አለመግባባትና ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ የሚተጉት የሃይማኖት ግጭት ጠንሳሾች የአገር ውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ስለመሆናቸው ይናገራሉ::
አስተያየታቸውን ካጋሩን መካከልም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት መምሪያ ዋና ሃላፊ መጋቤ ካህናት አባ ሃብተጊዮርጊስ አሥራት አንዱ ናቸው:: በኢትዮጵያ የክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች በማህበራዊ ህይወታችን ተለያይተው እንደማያውቁና ሀዘንና ደስታን እየተጋሩ ብዙ ዓመታትን አብረው ስለመኖራቸው የሚያስታውሱት አባ ሃብተጊዮርጊስ፣ ሌላው ቀርቶ ቤተክርስቲያኖች ሲሰሩ ሙስሊሙ በገንዘብም በጉልበትም፤ መስኪዶችም ሲሰሩ ክርስቲያኑም እንደዚያው እንደሚረዳ ያስገነዝባሉ::
‹‹ዛሬ እሚቃጠሉ ቤተ-እምነቶች የአንድ እምነት ተከታዮች ብቻ የሠሯቸው አይደሉም፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመስጊዶች መቃጠል ይቆጫሉ እንጂ አይደሰቱም፤ እውነተኛ ሙስሊሞችም በቤተክርስቲያኖች መቃጠል ያዝናሉ እንጂ አይደሰቱም››ይላሉ::
የሃይማኖት ሰዎች በዚህ ልክ ግጭት ይፈጥራሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚናገሩት አባ ሃብተጊዮርጊስ፤ ከግጭቱ ጀርባ የፖለቲከኞች እጅ አለበት ባይ ናቸው። ‹‹የሃይማኖት ተቋማትና ምእመናንን ኢላማ ያደረጉ የፖለቲካ ነጋዴዎች በሚፈጥሩት ሴራ፤ አንዳንዶቹ ተልእኮ ይዘው ሌሎችም ሁኔታው ሳይገባቸው ግጭት እየፈጠሩ ለዘመናት ተከባብሮ የኖረው ምእመን እንዳይተማመን የማድረግ ሥራ እየሠሩ ናቸው›› ይላሉ::
‹‹የፖለቲካው ጉዳይ የሚቀጣጠለው የሃይማኖት ጦርነት ስናስነሳ ነው በሚል አስልተው፣ አቅደውና ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች አሉ›› የሚሉት አባ ሃብተጊዮርጊስ፣ እነዚህ ጥቂት ሰዎች የብዙኋኑን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለስሜቱ ስስ የሆኑ ጉዳዮችን በመነካካት ትርምስ እንዲፈጠር እየጣሩ ስለመሆናቸውም ያስገነዝባሉ::
ይሕን እሳቤ የሚጋሩት የተለያዩ የሃይማኖት ሰዎችም፣ ‹‹ሰሞኑን የሃይማኖት መልክ ይዞ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ግጭት ‹‹ኢምፖርት›› የተደረገ ወይም የውጭ ኃይሎች ቀርጸው ወደ አገራችን ያስገቡትና በፋይናንስ የሚደግፉት የታሰበበት አጀንዳ ነው›› ይላሉ።
ዶክተር ወዳጄነህ መሐረነ፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሃይማኖቶች መቻቻል ከምንም በላይ አስፈላጊና ወሳኝ ነው›› ይላሉ:: ይሑንና በተለይም በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል ያለውን ወንድማማችነት፣ አብሮነት፣ ፍቅር፣ መዋደድና መተሳሰብ የማይፈልጉና የሚያስቆጣቸው ኃይሎች እንዳሉ ይጠቁማሉ::
ከሰሞኑ የተፈጠረውን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚፈጠሩ ሃይማኖት ነክ ችግሮች መነሻቸው ከውስጥ እንዳልሆነ አፅእኖት ሰጥተው የሚያስገነዝቡት ዶክተር ወዳጄነህ፣ ‹‹የእነዚህ ሃይሎች ፍላጎትም ሃይማኖት ሽፋን በማድረግ የማይበርድ የሃይማኖት ግጭት በማስነሳት ኢትዮጵያን ማንኮታኮት ነው፣ ይሕን እኩይ አላማ በማንገብ ተልእኮአቸውን ለማሳካትም በተለያዩ ጊዜያት በብርቱ ደክመዋል፣ ይሁንና ተቀባይ በማጣታቸው ሊሳካላቸው አልቻለም›› ይላሉ::
የኢትዮጵያ ጠላቶች የብሄር አልሰራ ሲል የሃይማኖት ግጭት እንደሚያዋጣቸው አውቀው ወደ ሥራ የገቡት ሕዝቡ በተለይም ወጣቱ በሃይማኖቱ ከመጡበት ወደኋላ አይልም የሚለውን ስስ ስሜቱን ሊጠቀሙበት አስበው መሆኑ ይታመናል:: ይሕ እስከሆነ ደግሞ ዜጎች በአክራሪና ጽንፈኛ ሀይሎች ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቁ ማድረግ የግድ ነው።
በተለይ አንዳንድ ምእመናን በጥቅማጥቅም ተደልለው እና በጽንፈኞች ከንቱ ስብከት ሰክረው በእዚህ የጥፋት ተግባር ሊሰለፉ ስለሚችልም፤ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ፤ ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነት እንዲከተሉ የእምነት ተቋማት ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው ይታመናል::
በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ ስለሚገኘውና አሁን ላይ ሃይማኖታዊ መልክ ይዞ ስለመጣው የጠላት ደባ የእምነቶቹ ተከታዮች ይበልጥ እንዲረዱ በማድረግ ረገድ የሃይማኖት ተቋማትና አባቶቸ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው የሚወተውቱ አሉ::
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሚሰጡም፣ ‹‹የእምነቱ ተከታዮች በአክራሪዎችና ጽንፈኞች ወጥመድ ውስጥ እንዳይገቡ ማድረግ የሚቻለው ምእመናን በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት እምነታቸውን እንዲያራምዱ ማድረግ ሲቻል ነው። እያንዳንዱ እምነት ተቋም፣ የእምነት አባትና ምእመን ትክክለኛውን የሃይማኖት አስተምህሮ መሰረት በማድረግ አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን መዋጋት አለበት›› ይላሉ::
አዲስ ዘመንም በቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮትና የስነልቦና መምህር መላከምህረት ቆሞስ አባ ጌዴዎን ብርሃነ፣ አሁን ላይ የሚስተዋለው ችግር መንስኤና መፍትሔያቸው ምንድን ነው ይላሉ? የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር::
እርሳቸው ሲመልሱም፣ ‹‹የመጀመሪያው ችግር የሃይማኖት ተቋማት እንደ ተቋም ያላቸውን ራዕይ ለማሳካት ቁርጠኝነት ያለመኖሩ፣ መንፈሳዊ ተልዕኮ እና ዓላማ ላይ ያለማተኮርና፣ በተጨማሪም ለእምነቱ ያለመሰጠት እና የመንፈሳዊነት እጦት ውጤት ነው››ይላሉ::
መምህር መላከምህረት ቆሞስ አባ ጌዴዎን ብርሃነ፣ የሃይማኖት መሪዎች እነሱ ሞተው ሕዝቡን ደህና የማድረግ፣ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ማለትም ብልሃትን፣ እውቀትን፣ ጥበብን፣ ክህሎትን እና መንፈሳዊነት ይዘው ህዝብን ማገልገል ግድ ይላቸዋል›› ይላሉ::
በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ሆነው በጎሳና በቋንቋ እርስ በእርስ የሚጣሉ በርካቶች ስለመሆናቸው የሚጠቁሙት መምህሩ፣ እነዚህ ሰዎች ከፈጣሪ ይልቅ ጎሳንና ቋንቋን የሚያስቀድሙ፣ በሃይማኖት ካባ ውስጥ ሆነው በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች መሆናቸውንም ያስገነዝባሉ::
በነሺዳ ስራው የሚታወቀው ሙሺድ አስማማው አህመድ በበኩሉ፣ በወጣቶች አስተማሮ ረገድ፣ የሃይማኖት አባቶች የቤት ሰራ ከፍተኛ መሆኑን ይስማማበታል:: የእምነት ተቋማቱ ያሉ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች የቆየውን ተቻችሎ የመኖር ዕሴት ለማስቀጠል ተቀራርበው መነጋገርና ለአገር ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አፅእኖት ይሠጠዋል::
የእምነት መሪዎቹ ከሁሉ በላይ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለማስከበር መትጋትና ህዝቡን ሊታደጉ እንደሚገባ የሚያስገነዝበው ሙሺድ፣ በተለይ የእምነት አባቶች ስጋዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈው ለሰላምና ለፍቅር መኖርን በህይወታቸው ተርጉመው ሊያሳዩ ይገባል›› ይላል::
አብዛኞቹ የሃይማኖት አባቶች አጠገባቸው ያለውን ሁሉ በንፅህና ስለሚያምኑ ወደ ስህተት የሚመራቸውን ሰው ሃሳብ የሚቀበሉበት ሁኔታ እንዳለና ፖለቲካውን ስለማያውቁት በፖለቲከኞቹ ሴራ ሳያስቡት እንደሚጠመዱ የሚጠቁመው ሙሺድ፣ ከችግሩ ግዝፈት አንፃር በቀጣይም የእነዚህን ሰዎች ምክር ባይሰሟቸውና የፈጣሪን ፈቃድ ብቻ ለመፈፀም ቢተጉ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝም›› ይላል:: ህዝብን ከስህተት መንገድ መመለስ የሚችሉት የእምነት አባቶች በመሆናቸው ራሳቸውን በመጀመሪያ መፈተሽና ወደ ትክክለኛው ሃይማኖታዊ ልምምድ መግባት እንዳለባቸው ሳያስገነዝብም አላለፈም::
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ‹‹በሃይማኖትም፣ በፖለቲካም፣ በየትኛውም ቁመና የጽንፈኝነት ቅዱስ የለውም፤ ይህንን በአጽንኦት ማመን መቻል አለብን። በኔ ስም እንዲህ እንድታደርግ አልፈቅድልህም ብሎ መጀመሪያ ማውገዝ ያለበት የሃይማኖት ተቋማት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ናቸው›› ይላሉ::
እንደ አቶ ክርስቲያን ገለጻም፣ የሃይማኖት ተቋማት የምርምር ተቋማት መሆን መቻል አለባቸው። የምንሰማው እንደምናስተውለውና እንደምንኖረው ሁሉም ሃይማኖቶች ሠላምን፣ በጎነትን፣ ቻይነትንና ትህትናን የሚያስተምሩ ናቸው። ሁከትና ብጥብጥን የሚያበረታታን ትውልድ የሃይማኖት አባቶች በስማችን አትነግዱ ብለው ማውገዝ ይገባቸዋል::
በሃይማኖት ተቋማት ስም የሚሠራ ወንጀል ካለ የእምነት አባቶች ‹‹አልፈቅድልህም›› ማለት አለባቸው። ከሠላም እንጂ ከጠብ የሚያተርፍ ማንም የለም። ለመጾም፣ ለመስገድ፣ ለማምለክ ሠላም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ እንደ አገር በእስልምናም በክርስትና ሃይማኖትም በበጎ የምትነሳ አገር ናት። በጎ ታሪካችንን በጥላቻ እያጠፋነው ነው። ይሄ መቆም አለበት።
‹‹የፖለቲካ ፓርቲ የተመሠረተው ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንጂ ጥላቻ በመዝራት ግጭትን በመጥመቅ አሁን ካለንበት አስከፊ ሁኔታ ወደ ባሰ ሁኔታ ለማስገባት አይደለም›› ያሉት አቶ ክርስቲያን፣ ግጭትን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋልን ሊያቆሙ እንደሚገባው አፅእኖት ይሠጡታል::
‹‹ዛሬ በግጭት ስልጣን ብንይዝ ነገ በግጭት እንወርዳለን›› ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ በተለይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የማይወዱትና እንዲቀየር የሚፈልጉት ሕግ እንኳን ቢሆን የማክበር ግዴታ አለባቸው ብለዋል። ነገ መንግሥት ሲሆኑ የሚያወጡት ሕግ ሊከበርላቸው በሚፈልጉት ልክ አሁን ላይ ያለውን ሕግ ጭምር የማክበር ግዴታ አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ክርስቲያን ገለጻ፤ ለዴሞክራሲ እታገላለሁ የሚሉ፤ የዴሞክራሲ ኃይል ነን ብለው ራሳቸውን የሰየሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭትን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋልን ማቆም መቻል አለባቸው። ጨቋኝ ነው ብለው የፈረጁት አካል ሕግ እንዲያከብርም ምሳሌ መሆን መቻል አለባቸው። ሕግን እየጣሱ መንግሥት ሕግ እንዲያከብር መጠየቅ ግን ግብዝነት ይሆናል ሲሉም አመልክተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በቀጣይ ሊደረጉ ይገባል ያሏቸው አብይ ተግባራትንም አመልክተዋል:: መላከምህረት ቆሞስ አባ ጌዴዎን ብርሃነ፣ በቀታጥ ሊከወን ይገባል፣ለ ችግሩም መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን ሲጠቁሙምም፣ የሃይማኖት ተቋማት የቆሙበትን ዓላማ ብቻ ይዘው ራሳቸውን መፈተሸ አለባቸው የሚለውን ያስቀድማሉ:: መንግስት የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለአገር እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ድጋፍ ማድረግ አለበት፤ የሚለውንም ያስከትላሉ::
‹‹በመጀመሪያ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማቱ ራሳቸውን ችለው በበጎነት ግባቸው ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ነው የሚጠበቀው›› የሚሉት መምህሩ፣ ይሁንና መንግሥት ለትውልድ ቀረፃ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅትም ሩሲያን ዋቢ በማድረግ የሌሎችን አገራት ተሞክሮ ያስረዳሉ:: ይሑንና ‹‹ድጋፍ የሚደረገው ለሃይማኖቱ አይደለም፤ ሃይማኖቱ ለአገር ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ ነውም›› ይላሉ::
የሃይማኖት ተቋማት የተመሰረቱበትን ዋነኛ ተልዕኮ ከግምት ውስጥ በማስገባት ራሳቸውን ፈትሸው አገሪቱንም ከጥፋት መታደግ እንደሚጠበቅባቸው በተለይም ያሏቸውን አገልጋዮች መፈተሽ፣ ተልዕኳቸውን መሰረት በማድረግም የሚሄደውና የማይሄደውን መለየት እንዳለባቸው ነው አፅእኖት የሠጡት::
ይህንን መለየት ካልቻሉ አገርንም ራሳቸውንም ይዘው ገደል እንደሚገቡ በማሳሰብ፣ ‹‹ስልጠና ለሚያስፈልገው ስልጠና፤ የሙያ ማሻሻያ ለሚያስፈልገው የሙያ ማሻሻያ፤ ድጋፍ ለሚያሻው ድጋፍ በመስጠት፣ መባረር ያለበትንም ማባረር ይገባቸዋል›› ነው ያሉት::
ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነም፣ በቀጣይ መደረግ ስለሚገባቸው ተግባራት ሲጠቁሙም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በህዝበ ክርስቲያኑ እና ሙስሊሙ መካከል ምንም ችግር እንደሌለና ፍቅር አንድነትና መተሳሰብ ብቻ እንሚወክላቸው ይበልጥ በአደባባይ ማሳየት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ::
ከዚህ በተጨማሪ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት የቆየው መከባበርና ወንድማማችነት እንዳይቀዘቅዝ እና ጠላትም ጣልቃ እንዳይገባ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ አባቶችና መምህራን ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት ዶክተር ወዳጄነህ፣ የእምነቶቹ ተከታዮችም ችግርን ለኩሰን አገሪቱን ለችግር እንዳርጋለን» ብለው የሚያምኑ ጠላቶቻችን አሳፍሮ መመለስና ለእኩይ አላማቸው ተገዥ አለመሆንን እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተውታል::
አቶ ክርስቲያን በበኩላቸው፣‹‹የጥላቻ አበጋዞች ፖለቲካን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን እንደ ምሽግ እንዳይጠቀሙ መዝጋት ያስፈልጋል፤ እነዚህ ባዶ ሜዳ ላይ መጋለጥ መቻል አለባቸው። ይህ ሲሆን የጸጥታና የፍትሕ አካላትም እርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። ማኅበረሰቡ እነዚህን የጥላቻ አበጋዞችን ተው ብሎ መምከር፣ ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ መቻል አለበት። ይላሉ::
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ዐውድ ከበፊቱ የተለየ በመሆኑ፤ ሕዝቡም ሆነ የመንግሥትን ኃላፊነት የወሰዱ ሰዎች ይህንን ማወቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝቡት አቶ ክርስቲያን፣ ዛሬ ላይ “እስኪ እንየው” ተብለው የሚታለፉ ጉዳዮች የከፋ መከፋፈል እንዳያመጡ መጠንቀቅ ግድ ይላል፣ በዚህ ረገድ መንግሥት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ መቻል አለበት ነው ያሉት::
ከዚህ ባሻገር መንግሥት በአገር ላይ ሰላምን የማስከበር፣ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነትም ግዴታም እንዳለበት ያስገነዝባሉ:: በተለይ የጸጥታና ፍትሕ አካላትን የሚመሩ አካላት ቁርጥ ያለ ውሳኔ መወሰን መቻል እንዳለባቸውና የኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝብ ደህንነት ቀይ መስመር መሆናቸውን በሚገባ ማመን እንደሚገባም አፅእኖት ሰጥተውታል::
እንደ እርሳቸው ገለጻም፣ ሕጎች የሚወጡት ለመተግበር ስለሆነ የሕግ መተላለፍ ካለ መንግሥት የማስተግበር ግዴታ አለበት፤ ዜጎች ደግሞ በመንግሥት የሚወሰዱ ጸጥታን የማስከበርና ሠላምን የማስጠበቅ እርምጃዎች የማግኘት መብት አላቸው::
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትም፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የተዘረጋውን የአብሮነት ገመድ ለመበጠስ ያቀዱ ወንጀለኞች ብዙ ጥፋትን ለማድረስ በብርቱ የሞከሩበትም ወቅት መሆኑን መግለጫው አውስቶ፤ ይህ ውጥናቸው ባሰቡት የጥፋት ልክና ባቀዱት የወንጀል ስፋት መጠን አለመሳካቱንም አሳውቋል::
ከዚህ ባሻገር ለዜጎች በሰላም መኖር ስጋትን የሚፈጥሩ፤ በአገር ሕልውና ላይም አደጋን የሚደቅኑ አካላት ላይ መንግሥት መውሰድ የጀመረውንም እርምጃ በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚቀጥል አሳውቋል:: ከሰሞኑ በሃይማኖት ሽፋን በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶችና ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን የፌደራል ፖሊስ፣ የክልልና የከተማ አስተዳደር የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር እያዋሉ ይገኛሉ:: ተጠርጣሪዎቹም ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ይደረጋል›› ማለቱም አይዘነጋም::
አስተያየት ሰጪዎቹ ሃይማኖት የጥፋትና የክፋት እጆቻችንን እንድንሰበስብ የሚያደርግ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ያቆዩዋቸውን የመቻቻልና የመተዛዘን ዕሴቶቻችንን አጠንክረን አብሮነታችንን በማስቀጠል የጠላቶቻችንን እቅድ ማክሸፍ እንዳለባቸው አፅእኖት ሰጥተውታል::
በተለይም ወጣቶች ግጭቶች በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትሉትን አደጋ አሻግረው በመመልከት በስሜት ከመጓዝ ይልቅ ቆም ብለው ሊያስቡ እንደሚገባና፣ ከግጭቱ ጀርባ የማን እጅ ሊኖር ይችላል? ግጭቱ ምን አይነት አገራዊ ቀውስ ሊስከትል ይችላል? ምን ኪሳራ፣ ምንስ ጥቅም ይኖረዋል? የሚለውን መመርመር ግድ እንደሚላቸው አስገንዝበዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014