የክረምት ወቅት ብዙ መልካም ነገሮችን ይዞ የሚመጣ ስለመሆኑ ይታወቃል፤ ለአርሶ አደሩ አርሶ የሚያዘምርበት፤ ለቀጣዩ ዘመን ጎተራውን ሊሞላ በብርቱ የሚተጋበት እንደመሆኑ የአርሶአደሩ ላቅ ያለ ጥረት የሚገለጥበት ነው:: መስኩ አረንጓዴ የሚለብስበት፣ ዛፎች የሚለመልሙበት፣ አበቦች ለመፍካት የሚዘጋጁበት፣ ወንዞች ሞልተው ጉልበታቸውን የሚያሳዩበት፣ ግድቦች ጉድለታቸውን የሚሞሉበት፣ በጥቅሉ ከገጠር እስከ ከተማ በየትኛውም መልክዓ ምድር ላይ በብዙ በረከቶች የሚታጀብ ነው:: ከዚህ ሁሉ መልካምነቱ ዜጎች ሲቋደሱ፤ እንደየድርሻቸው የክረምቱን በረከት ለማብዛት ከላይ ታች ሲጥሩ ማየቱም የተለመደ ነው::
የሰው ልጆችን የነገ ሕይወት ከፍ ለማድረግ በብዙ መልኩ የሚገለጸው ይህም የክረምት ወቅት ታዲያ፤ ለብዙሃኑ መልካም ወቅት ቢሆንም፤ ለጥቂቶች ግን የስቃይና ሰቆቃ ወቅት ሆኖ ማለፉ አይቀሬ ነው:: በተለይ እንደ እኛ አገር በርካቶች በየጎዳናው በወደቁበት፤ በርካቶች ከሞቀ ቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ለተከማቹበት፤ በርካቶች በድህነት አረንቋ ውስጥ ሆነው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ያለ እረፍት በሚንከራተቱበት፤ በርካቶች አንገት ማስገቢያ ብለው የሚጠለሉባት ጎጆ ዘምማ እና ተበሳስታ ዝናብ ጠብ ሲል ቤትና ደጁ የማይለይበት ሁኔታ በበረከተባት አገርና ከተማ ችግሩ ከፍ ብሎ መገለጡ እሙን ነው::
ይህ ደግሞ እነዚህ ወገኖች ወጥተው እንደልብ ያገኙትን ሰርተው የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚቸገሩበት፤ በበጋ የጸሐይን ጨረር የሚያስቆጥረው የቤታቸው ጣሪያና ግድግዳ ከላይ ዝናብን፣ ከጎን ብርድን እያወረደ ማረፊያ የሚያጡበት፤ ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው ሸራ ለብሰው ላሉትም ከብርድና ዝናቡ ባለፈ በጎርፍ የሚቸገሩበት፤… አጋጣሚንም ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ነው:: ችግሩን የሚያከፋው ደግሞ እናቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ በህመም ከአልጋ የዋሉ ወገኖች፣ ነፍሰ ጡሮችና እመጫቶች ሳይቀሩ የዚህ ሰለባ መሆናቸው ነው::
ይህ የአገራችንም የዋና ከተማችን አዲስ አበባም ችግር ነው:: ይሄን የተገነዘቡ ጥቂት ወገኖች ደግሞ
ችግሩን ለማቃለል በጊዜ እና ሁኔታ ሳይታጠሩ ያለመታከት የሚተጉ ሲሆን፤ ብዙሃኑ ደግሞ በጊዜና በሁኔታ ተወስነው ለእነዚህ ወገኖች ለመድረስ ሲጥሩ ማየቱም የተለመደ ተግባር ነው:: በዚህ ረገድ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትና ተግባር አንዱ ሲሆን፤ ረዘም ላሉ ዓመታትም አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የአገራችን ከተሞች በወጣቶች፣ በተማሪዎች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና በሌላውም የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል::
ይህ የበጎ ፈቃደኞች የክረምት መርሃ ግብር ቀደም ሲል በአረንጓዴ ልማት በተለይም በችግኝ ተከላ፣ ውበትና ጽዳት፣ እንዲሁም በመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ብሎም በክረምት ትምህርት ተግባራት በጉልሕ የሚገለጽ ነበር:: በኋላ ላይ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን የመደገፍ፤ የምገባ እና ሌሎች ድጋፎችን ጨመረ:: በሂደት የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ተግባርን አካትቶ የበርካቶችን የዘመመ ቤት ማቅናት የተቻለበትን እድል ፈጠረ:: ይሄው ተግባር እያደገ ተቋማትን ማሳተፍ፤ ኋላም በጠቅላይ ሚንስትሩ ጭምር መከናወን ያዘ::
በዚህ መልኩ ዓመታት የዘለቀው የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባርም በርካታ እናቶችንና አቅመ ደካሞችን ከደጅ ወደ ቤት ያስገባ፤ በክረምቱ ምክንያት ሥራ አጥተው ጾም የሚያድሩ ወገኖችን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ቀምሰው እንዲያድሩ ያስቻለ፤.. በጥቅሉ ክረምት በመጣ ቁጥር ለከፋ ችግርና እንግልት ከሚዳረጉ በርካታ ወገኖች የተወሰኑትን ችግር እንዲቃለል ያደረገ ሆኗል:: ዘንድሮም የክረምቱን መግባት ተከትሎ መሰል ሥራ ሊከናወን የሚገባው፤ ይሄው እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው:: በዚህ ረገድ የተለያዩ ተቋማት፣ ወጣቶችና የከተማ አስተዳደር አካላት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸው ተሰምቷል::
ትናንት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተጀመረው ይፋዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ደግሞ ለዚህ ትልቅ አቅምና መነሳሳት የሚፈጥር ከፍ ያለ አርዓያነት ያለው ነው:: እርሳቸውም ሥራውን በይፋ በጀመሩበት ወቅት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ዓመታዊ የቤት እድሳት መርሐ ግብር በምናስጀምርበት በዚህ ወቅት ግለሰቦች፣ የንግድ ተቋማት እና የመንግሥት ተቋማት ክረምት ከመግባቱ በፊት በአካባቢያችን ላሉ በርካታ ሰዎች ምቹ እና ሰብዓዊ ክብርን መሠረት ያደረገ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር በሚደረገው ዓመታዊ ክንውን የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ። በተለይም የንግድ ድርጅቶች ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ኑሮ ማሻሻል ይችላሉ፤” ብለዋል::
እውነት ነው፤ ዛሬ የክረምቱን መግባት ተከትሎ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ኑሯቸው በስጋትና በሰቀቀን ውስጥ ገብቷል:: በአንጻሩ ጥቂቶች የተትረፈረፈ ነገርን ይዘው ለቅንጦት ነገሮች ብዙ ሃብት ሲያፈሱ ማየት የተለመደ እውነት ነው:: ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ለራሳቸው ሳይኖራቸው የተቸገሩ ወገኖቻቸው ለማገዝ የሚውተረተሩ፤ ኖሯቸውም ካላቸው ላይ አካፍለው አብሮ ችግርን ለመሻገር የሚተጉ ወገኖችን እናስተውላለን:: ይህ ደግሞ በግለሰቦች የሰብዓዊነት ሚዛን የሚታይ እንጂ በእጃቸው ወይም በካዝናቸው ባለ የገንዘብ አቅም የሚመዘን ተግባር ባለመሆኑ አንዱ ሃብቱን ለቅንጦት ጉዳይ ሲዘራ፤ ሌላው ካለውም ከሌለውም ቀንሶ በሃብቱም በጉልበቱም በጊዜውም ስለሰዎች ደስታና እርካታ መድከሙ የሚጠበቅ ነው::
ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት አገራዊ የሆኑ ችግሮች በተናጠል ሩጫና ስራ ከዳር የሚደርሱ፤ ውጤትም የሚያመጡ አይሆንም:: ውጤት የሚገኘውና ችግሩን መሻገር የሚቻለው ገንዘብ ያለው ገንዘቡን፣ እውቀት ያለው እውቀቱን፣ ጊዜም ያለው ጊዜውን፣ ጉልበት ያለውም ጉልበቱን አንድ ላይ ደምሮ ሲሳተፍ እና እነዚህን መጠቀም ሲቻል ነው:: የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክትም የሚያስገነዝበን ይሄንኑ ነው::
በመሆኑም ይህ የክረምት ወቅት ከብዙ በረከቶቹ በስተጀርባ የእነዚህን ማረፊያ ያጡ ወገኖቻችንን የስቃይ ድምጽ የሚያሰማን ወቅት እንደመሆኑ፤ በክረምቱ ምክንያት የሚሰቃዩ ወገኖቻችንን የሰቆቃ ድምጽ በቃ የምንልበት፤ ችግሮቻቸውን ተካፍለን ሕይወታቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ የምናሸጋግርበት ሊሆን ይገባል:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ሰው መሆናችንን አስበን ሃብታችንን፣ እውቀታችንን፣ ጉልበትና ጊዜያችንን አስተባብረን ክረምቱን በበጎነት ልናሳልፍ የተገባ ነው::
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2014