ህይወት ጥያቄ ናት፤ ጠይቆ መልስ ማግኘት ደግሞ የሰውነት ባህሪ ነው። ሰው ካልጠየቀ ጠይቆም መልስ ካላገኘ ረፍት የለውም። በዚህ ረፍት ማጣት ውስጥ ደግሞ የሚከናወኑ አያሌ ርባናቢስ ህይወቶች አሉ። እኚህ ርባና ቢስ ህይወቶች ባለመጠየቅ የሚፈጠሩ የሰውነት ጉድፎች ናቸው። ዛሬ ላይ ጉድፍ ሆነውብን እያሰቃዩን ያሉት አገራዊ ችግሮቻችን ባለመጠየቅ የጸነስናቸው፣ ጠይቀንም መልስ ባለማግኘት የፈጠርናቸው ናቸው። ዛሬ ላይ ችግር እየሆኑብን ያሉ እንከኖቻችን ባለመጠየቅ ከትላንት ወደዛሬ ያመጣናቸው ታሪኮች ናቸው። እኚህ ችግሮቻችን እልባት እንዲያገኙ በጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥና መልስ መፈለግ ያሻናል። ድጋሚ በታሪኮቻችን ላይ ነፍስ እንዳይዘሩ አድርገን በእርቅና በተግባቦት ገለን ልንቀብራቸው ይገባል። ዛሬ ላይ የአባቶቻችን ጥበብ፣ የፊተኞቻችን አስተውሎት የት እንደገባ አላውቅም። እንዳባቶቻችን የሆነ አንድም ነገር እያጣን ነው። እኔነትን ለብሰን፣ እኔነትን ተጎናጽፈን መኖርን እንደ ትልቅ ስልጣኔ በመቁጠር እየተደነቃቀፍን እንገኛለን።
እኛ እኮ ዛሬን አናውቀውም፤ በዛሬ ብርሀን ትላንትን የምንሞቅ ሞኞች ነን። ዛሬ ላይ ሆነን ወደ ትላንት እየሸሸን የነገር ቁርሾ የምንፈልግ፣ ክፉዎች ያስቀመጡልንን የውሸት ሰነድ እየበረበርን ዛሬን የምንገፋፋ መካሪ ያጣን ነፍሶች ነን። ሰው እንዴት አዲስ ታሪክ መጻፍ ያቅተዋል? ሰው እንዴት ወደፊት መሄድ ያቅተዋል? ሰው እንዴት በተሻለ ዘመን ላይ ተፈጥሮ በመነጋገር መግባባት ይሳነዋል? ሰው እንዴት ለጋራ ጥቅም ለአንድነት መተባበር ሲገባው ለመለያት ይበረታል? እኛ እንዲህ ነን። ወርቃችንን በጠጠር የቀየርን፣ እንቁአችንን በፋንድያ የመነዘርን፣ ሰላማችንን ለውሸት የሸጥን ሞኞች። እስከመች እዛው እየረገጥን እንኖራለን? እስከመች እልፍ ማለት ያቅተናል? ኧረ እንቃ!፤ ከእኛ በቀር እኮ በአገሩ ጉዳይ ያንቀላፋ የለም። ሁሉም የአለም አገራት ለጋራ አገራቸው በጋራ እየተጉ ባለበት ሰዐት ላይ የእኛ ማንቀላፋት አልገባ ብሎኛል። አለም በስልጣኔ ቀድሞ፣ በአንድነት በርትቶ የምድር ኑሮ በቃን ብሎ ጨረቃ ላይ ቤቱን እየሰራ ነው። መንግስታት በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ ልብ ሊመክሩ አለምን በግሎባላይዜሽን ስም ወደ አንድ ሊያመጣት እየሰሩ ነው። እኛ ግን በገዛ አገራችን ላይ ከገዛ ወንድሞቻችን ጋር መግባባት ተስኖናል፤ ለምን? ራሳችንን እንጠይቅ።
ባለመግባባታችን ራሳችንን ካልሆነ የምንጎዳው ማንም የለም። ባለመስማማት አገራችንን ካልሆነ የምናራቁተው ማንም የለም። ከትላንት እስከዛሬ ባለመግባባት እየተጎዳን ኖረናል። አሁን ግን እንጠይቅ፤ ጠይቀንም መልስ እናግኝ። ለአገር ሰላም፣ ለህዝቦች አንድነት ከእኔ ምን ይጠበቃል ስንል ራሳችን መጠየቅ ግድ ይለናል። ሰላም ተዐምር የለውም፤ የሰላም ተዐምሮች እኛ ነን። ሰላም በእኔና በእናተ በጎ ሀሳብ በኩል ተጸንሶ የሚወለድ፣ ተወልዶም የሚያድግ ነው። ሰላም በእኔና በእናንተ መተቃቀፍ ውስጥ የሚያብብ፣ አብቦም የሚያሸት የነፍስ ናርዶስ ነው። ሰላም በይቅርታና በፍቅር ከትውልድ ትውልድ የሚሻገር የበጎ አእምሮና ልብ ውጤት ነው። የተሸነፍነው እኛው ነን። ራሳችን ለራሳችን መሆን አልቻልንም። ሞኝነታችንን ተመልክተው ሌሎች እንደፈለጉ እያደረጉን ነው። በትንሽ ነገር እያሽከረከሩን ነው። በጣም የሚገርመው ክፉዎች መርዛቸውን የሚረጩብን በተለየ መንገድ ሳይሆን በቀላል መንገድ እኛን በመጠቀም ነው።
ይህ ማለት የእኛን አንድ መሆን የማይፈልጉ ኃይሎች እኛን ለመጉዳት ሩቅ መሄድ ሳይጠበቅባቸው እኛኑ ተጠቅመው እኛኑ ይጎዳሉ ማለት ነው። ይሄ ደግሞ የእኛን ድክመት፣ የእኛን ከሰላም ይልቅ ለነውጥ መቸኮላችንን ያሳያል። አይገርምም ግን ጠላቶቻችን እኛን ለመጉዳት እኛን ሲጠቀሙ? በአለም ታሪክ የሌለ ነገር አገራችን ውስጥ እየተፈጠረ ነው። ጠላት ከሩቅ አይመጣም እንደሚባለው እስከዛሬ በአልሸነፍም ባይነት አገራችንን ስንጎዳ የነበርነው ሌላ ሳይሆን እኛው ነን። እስከዛሬ በአንድነት ወደፊት መሄድ እየቻልን በእኔነት ስሜት ወደ ኋላ መቅረትን የመረጥንው ራሳችን ነን። ኢትዮጵያን አሁን ላለችበት የፖለቲካና የማህበራዊ ቀውስ የከተትናት እኛው ነን። እኛው ለእኛ ጠላቶች ሆነን ኖረናል፡ አሁን ግን ከዚህ አመለካከት መውጣት ይኖርብናል። ለዘመናት የትላንትን ጸሀይ እየሞቅን፣ የአምናን ዶሲ እየበረበርን ኖረናል። ለአመታት በአንድ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ አንድ አይነት ሆነን ኖረናል። አሁን ግን ከፍ እንበል። ያላየነው ሰላም፣ ያልደረስንበት የከፍታ ስፍራ አለና ወደዛ እናዝግም። ለጠላቶቻችን ግብዐት እንዳንሆን የጠላቶቻችንን ሴራ በፍቅር እናክሽፍ። በአንድነት እንስበር። በመካከላችን ክፉዎች የሰሩት ያላለፍነው ትላንትና አለ። በመካከላችን የስልጣን ጥመኞች ያበጁት ያልተሻገርነው ድልድይ አለ። በመካከላችን ክፉ ልቦች ጸንሰውት ነውረኛ እጆች የጻፉት ያልተዳፈነ ታሪክ አለ። በመካከላችን ትላንትን የሚያሳዩን ያልደፈናቸው ሽንቁሮች አሉ። እኚህ በክፉዎች ሆን ተብለው የተበጁ ነውረኛ ታሪኮች የእኔና የእናተን ዛሬና ነገ ከማበላሸት በቀር አላማ የላቸውምና በመጠየቅ፤ ጠይቆም መልስ በማግኘት እንርታቸው።
በአንድነትና በጋራ ትውልድ የሚገልጠውን አዲስ ታሪክ እንጻፍ። እውነት በቃኘው፣ ፍትህ በዋጀው የመነጋገር ባህል አዲስ ነገ እንስራ። አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የሚበጃት ይሄ ብቻ ነው። ወደከፍታ ከሚወስዱን በጎ ጎዳናዎች በቀር በሁሉም ላይ ተረማምደናል..ሁሉም ጎዳናዎች ግን አደናቅፈውናል አሁን የሚቀረን ያልሄድንባቸው እነዛ የበጎነት ጎዳናዎች ናቸው። አሁን የሚቀረን ተነጋግሮ መግባባት፣ ተግባብቶ አገር መፍጠር ነው። አሁን የሚቀረን የጠላቶቻችንን ምክር የሚያሳፍር የአንድነት ሀይል ነው። አሁን የሚቀረን ከጦርነት ወደ ሰላም፣ ቤተክርስቲያንና መስኪድ ከማቃጠል ወደ መስራት መሸጋገር ነው። አሁን የሚቀረን በእኛ ክፋት፣ በእኛ አንድነት ማጣት የጠፋችውን ኢትዮጵያ ፈልጎ ማግኘት ነው። አሁን የሚቀረን በእኔነት ውስጥ የጠፋችውን ኢትዮጵያ በእኛነት ውስጥ አስሶ ማግኘት ነው።
እንደ ዜጋ ለአገራችን ያላደረግንው ብዙ ነው..ባለን አቅም፣ ባለን ወጣትነት፣ ባለን ስልጣን ለአገራችን ማድረግ ብንችል ኖሮ አገራችን በዚህ ልክ ስቃይ ላይ ባልወደቀች ነበር። ሩጫችን ሁሉ ወደ እኔነት ስለሆነ አገራችንን ለማሰብ ጊዜ አልነበረንም። ከቀሪው አለምና መንግስት የምንለየው ራስ ወዳድ በመሆናችን ነው..እመኑኝ ሲበዛ ራስ ወዳዶች ነን..ራስ ወዳድ ባንሆን ኖሮ ለሰላምና ለመነጋገር ጊዜ አናጣም ነበር። ለአንድነትና ለወንድማማችነት ቦታ አናጣም ነበር። ሰው እንዴት ራሱን ብቻ ይዞ ይኖራል? ሰው እንዴት ራሱን በቻ እያሰበ፣ ራሱን ብቻ እያፈቀረ ይኖራል? እባካችሁ ሰው እንሁን፤ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም በማፍቀር እንኑር።
እንደዜጋ ከአገራችን ከመጠበቅ በቀር ለአገራችን ምንም አድርገን አናውቅም። ከትላንት እስከዛሬ ራሳችንን ስንጦር፣ ራሳችንን ስናገለግል የኖርን ነን። ስልጣናችንን ተጠቅመን እየሰረቅንና፣ እየዋሸን፣ እየዘረፍንና የማይሆን ነገር እያደረግን የመጣን ነን። አገር ሰው ትሻለች፤ የራሱ ብቻ ያልሆነ ሰው። መቶ ሀያ ሚሊዮን ህዝብ ያላት አገር ሰው ስታጣ፣ አስታራቂ ስታጣ፣ የሰላም ሰው ስታጣ፣ ሽማግሌ ስታጣ፣ ይቅር ባይ ስታጣ፣ የተማረ ስታጣ፤ እልፍ ልጅ የወለደች አገር ተቆርቋሪ ስታጣ፣ ተነጋግሮ የሚግባባ ትውልድ ስታጣ፣ ስለሌላው ግድ የሚለው ሰውነት ስታጣ እንደምን አይገርምም?። ከዚህ በላይ አለም የሚያስገርም ነገር የላትም። ጥሩ ታሪክ ሰርተን መጥፎ ታሪካችንን እንቀይር ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። እስከዛሬ የዘጋናቸውን መንገዶች ለሌሎች እንክፈት። እስከዛሬ የዘጋናቸውን ልቦቻችንን ለትህትና እንክፈት። ተነጋግሮ መግባባት ለዚች የኋላቀርነት ፈንግል ለሚያንደፋድፋት አገራችን፣ የኋላቀርነት ቆላ ቁስል ለሚያሰቃየው ህዝባችን ፍቱን መድሀኒት ነውና የእይታ መነጽራችንን አስተካክለን ከትላንት የላቀ፣ ከዛሬ የደመቀ ነገን አሻቅበን እናይ ዘንድ ያስፈልገናል።
አለመግባባት ከጎዳን ተግባብቶ መጠቀም ለምን አቃተን? ብሄርተኝነት ካልበጀን ኢትዮጵያዊነትን መሀከል አድርጎ መኖር ለምን ከበደን? እኔነት ድልድይ ሆኖ ወንዝ ካላሻገረን እኛነትን መምረጥ ለምን ተሳነን? መጠየቅ ብንችል መልሶቻችን ቀላሎች ነበሩ። ችግሩ ግን መጠየቅ አንወድም። ብንጠይቅ ላለማመን ስለቆምን ለማመን የሚሆን አቅም የለንም። በብዙ ነገር የባከንን ህዝቦች ነን፣ በብዙ ነገር ከስልጣኔና ከዘመናዊነት የሸሸን ህዝቦች ነን። በገዛ እጃችን መድረስ ካለብን ያልደረስን ነን። በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለሰላም የሚሆኑ አማራጮችን ማየት እንጂ የትላንትን ስህተት መድግም አይኖርብንም። የቀረንን ሙጣጭ አቅም ኢትዮጵያን ለመስራት እንጠቀምበት። በአገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ ሀሳብ እናዋጣበት። አንድነትን እንገንባበት። ታሪክ ወለድ የሆኑ የእብለት ትርክቶችን እናጋልጥበት። በእናታቸው ማህጸን ውስጥ ብኩርናን ሽተው ለአንደኝነት እንደተጋፉት እንደ ርብቃ ልጆች በእኛ ግፊያ ያዘመመች ቤታችንን እንታደግበት። ከረፍታችን ለመድረስ ለራሳችን ውለታ እንዋል።
ፖለቲካችንን ብንመረምረው በርካታ ያልተጠየቁ፣ በርካታ መልስ ያላገኙ፣ በርካታ ህዝብ የማያውቃቸው ታሪኮችን እናገኛለን። ትላንትን ብንፈትሽው ህዝብ የማያውቀው፣ ትውልድ ያልደረሰበት በወንድማማቾች መካከል መቃቃርን እንዲፈጥሩ ሆነው የተቀመጡ የፖለቲካ ሴራዎችን እናገኛለን። ግን አንጠይቅም፤ ግን ለምን አንልም። ለፖለቲካ ወለድ ችግሮቻችንንም ሆኑ ለሌሎች ችግሮቻችን በመጠየቅ ውስጥ አስተማማኝ መልስን የማግኘት ባህልን ማዳበር ይኖርብናል። እኔ ግን እጠይቃለው፤ ስለ አገሬ፣ ስለህዝቤ ምንድነው ያጣነው? ስል ሁሌ ራሴን እጠይቃለው። ምንድነው የሌለን? ስል ነጋ ጠባ ራሴን አስጨንቃለው። እስከዛሬ ጠይቄ፣ እስከዛሬ ተመራምሬ እንደ አገር ያጣንውን ግን ልደርስበት አልቻልኩም። እውነት ያጣነው ምንም የለም። ከፍቅር ሌላ፣ ከትህትና ሌላ፣ ከይቅርታ ሌላ፣ ከመተው ሌላ ያጣነው ምንም የለም። በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ ተቃቅፎ የጋራ ቤት ለመስራት ከመትጋት ባለፈ ያጣነው ምንም የለም። ብዙ አገራት ምንም ሳይኖራቸው በፍቅር ብቻ ተዐምር ሰርተዋል። እኛ ብዙ እያለን ፍቅር በማጣት ብቻ ተዐምራችንን ሰውረናል። ይሄ የምንግዜም አግራሞቴ ሆኖ ልቤ ውስጥ አለ።
አገር ፍቅር ሲርቃት፣ አንድነት ስታጣ ሶርያን ናት። ህዝብ ጥላቻና መለያየት ሲበልጠው እንደ የመንና ሩዋንዳ ነው። እያየነው ካለነው አርቀን ማየት አለብን። እያሰብን ካለነው ልቀን ማሰብ አለብን። አንድነት በማጣት የፈረሱ፣ ፍቅር ርቋቸው ታሪካቸውን ያበላሹ ልንማርባቸው የሚገባን ብዙ ጎረቤት አገሮች አሉን። ከነሱ መማር አለብን። ጠቢብ ሰው በራሱ ላይ እስኪሆን አይጠብቅም፣ በዙሪያዋ ካለው የሚማር ነው። እኛ ግን ከትላንት እስከዛሬ አንድ አይነቶች ነን። ከሌሎች መማር አልቻልንም። ይሄን ሁሉ ዘመን ተዋግተን፣ ይሄን ሁሉ ዘመን ተገፋፍተን የጦርነትን አስከፊነት አልተረዳነውም። በእኛ ካልደረሰ መከራና ችግር እንዳይገባን ሆነን የቆምን ህዝቦች ነን። ፖለቲካችን ከትላንት እስከዛሬ አንድ አይነት ነው። አስተሳሰባችን ዛሬም እንደጥንቱ ነው። ዛሬም ድረስ ከጥፋት ያልዳነው፣ ዛሬም ድረስ ከብሄር ፖለቲካ ያልተለየነው እኮ ከትላንት አስተሳሰብ ስላልወጣን ነው። በልባችን ብዙ ሀሳብ ሊኖር ይችላል፣ ለአገራችን ልንሰራ፣ ለህዝባችን ዘብ ልንቆም የቆረጥን እንኖር ይሆናል ይሄ ሁሉ ብርሀናዊ ተስፋችን እውን የሚሆነው ከትላንት አስተሳሰብ መላቀቅ ስንችል ብቻ ነው።
ከትላንት የሸሸ፣ በበጎነት የገነነ፣ ስለአገሩ ግድ የሚሰጠው ዜጋ ያስፈልገናል። አገሬ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትረሳኝ፣ ብክድሽ፣ ባዋርድሽ የቆምኩባት ምድር ትፍረደኝ የሚል ትውልድ እንሻለን። አገሩን ከፊት አስቀድሞ የሚከተል እግር፣ ወገኑን ከፊት አድርጎ የሚያስብ አእምሮ ለአዲሷ ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር ነው እላለው። ስንት ጊዜ እንፍረስ? ስንት ጊዜ እንድማ? በታደሰ ልብ ወደ ፊት እንጂ ከእንግዲህ የትላንት የፖለቲካ ማህጸን የጸነሰውን የዘረኝነት ሽል ታቅፈን እዬዬ የማይታሰብ ነው። ጫንቃችን ላይ በተጫነ የእኔነትና የጎጠኝነት ደዌ መታመም ይበቃናል።
በፖለቲካ ትርፍና በእልኽኝነት የጎበጠ ጀርባችንን ሳናቀና ሌላ የነገር ቁርሾ ይዘን በቆረቆር ላይ ቁምጥና መሆን የለብንም። እኛን ሳስብ ብዙ ነገር ይገርመኛል፤ ከአግራሞቴ አንዱ በአንድ ወንዝ እየፈሰስን፣ ከአንድ ወንዝ እየተቀዳን፣ በኢትዮጵያዊነት ክርና መርፌ ተሰፍተንና ተደውረን፣ ተደባልቀንና ተቀይጠን ስናበቃ በዚህ ቁርኝት ውስጥ ሌላነትን ለመፈለግ መንፈራገጣችን ነው። ሰው እንዴት ከራሱ ጋር ይጣላል? ሰው እንዴት ከራሱ ጋር ሆድና ጀርባ ይሆናል? በኢትዮጵያ ምድር ሌላ ሰው የለም። ሌላ ብሄር፣ ሌላ ሀይማኖት የለም። ሁላችንም ኢትዮጵያን የፈጠርን፣ ኢትዮጵያን የሰራን አንድ አይነት ነፍሶች ነን። ታሪካችን፣ ባህላችን፣ ልማዳችን ተደባልቆ አንድ አይነት እኛን ፈጥሯል። አጠገባችን ያለን ሰው ስንገፋ፣ ስንጠላ፣ ራሳችንን እየገፋንና እየጠላን እንደሆነ ልናውቅ ይገባል። አገሬ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ይህ የዚህ ዘመን ብሄራዊ መዝሙር እንዲሆን እሻለው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም