ነዳጅ፣ በኢትዮጵያ ገበያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዬኖች ብር በመንግሥት ድጎማ እየተደረገበት ለተጠቃሚው በቅናሽ ዋጋ እንዲደርስ ሆኖ እስከዛሬ ዘልቋል። በዚህም ከዓለምአቀፉ ገበያ አኳያ ቀጥታ ያለው ዋጋ በሕብረተሰቡ ላይ እንዲያርፍ ቢደረግ ከፍ ያለ የኑሮ ጫና ይፈጥር የነበረበትን ሸክም መንግሥት በራሱ ተሸክሞ ሕዝቡንም አገልግሎት ሰጪውንም ሲደጉም ቆይቷል። ምንም እንኳን መንግሥታዊ ኃላፊነቱን የተወጣ ቢሆንም ለዚህ ተግባሩ ምስጋና ሊቸረው የተገባ ነው።
መንግሥት ነዳጅን በድጎማ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ በሚያደርግባቸው በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ገበያ በሊትር እስከ 30 ብር የሚሸጠው ነዳጅ ድጎማው ባይኖር ኖሮ ከሰባ ብር ይልቅ እንደነበር የተለያዩ አካላት ሲገልጹ ይደመጣል። ይህ ብቻም አይደለም፤ የኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ በብዙ መልኩ ከጎረቤት አገራት የነዳጅ ገበያ አኳያ ዝቅ ያለ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ሂደት ደግሞ የሕብረተሰቡን የኑሮ ሸክም ከማቃለሉ በተጓዳኝ፤ ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ገበያ እንዲቀርብ፤ በግልጽ ቋንቋ የነዳጅ ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ በር የከፈተ ስለመሆኑም ሲገለጽ ቆይቷል።
መንግሥት በከፍተኛ ወጪ እየደጎመ ለሕዝብ ጥቅም የሚያቀርበውን ነዳጅ በዚህ መልኩ በኮንትሮባንድ ወደውጭ ገበያ ማቅረብ ደግሞ በእጅጉ አሳፋሪ እና የሞራል ውድቀት ውጤት ሆኖ የሚገለጽ ነው። መንግሥትም ችግሩን ለማቃለል ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። ሆኖም ችግሩን በሚፈለገው መጠን መከላከል ሳይቻል አሁንም ድረስ ዘልቋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ፤ አሁን ላይ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከዕለት እለት እያሻቀበ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በአንድ በኩል የነዳጅ ኮትሮባንድ ንግዱ ሲጧጧፍ፤ በሌላ በኩል መንግሥት ለድጎማ የሚያወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ መጣ።
ለአብነት ያህል፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በታህሳስ ወር ቤንዚን በሜትሪክ ቶን 870 የአሜሪካን ዶላር እና ናፍጣ በሜትሪክ ቶን 730 የአሜሪካን ዶላር ይሸጥ ከነበረበት ሚያዚያ ወር ላይ ቤንዚን
በሜትሪክ ቶን ወደ 1028 የአሜሪካ ዶላር እና ናፍጣ ደግሞ በሜትሪክ ቶን ወደ 1138 የአሜሪካን ዶላር ከፍ ብሏል። በዚህ መልኩ የሚገለጸው የዓለምአቀፍ ገበያ ያለው የዋጋ ጭማሬ እንዳለ ቢታወቅም፤ መንግሥት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ ከታኀሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ወራት ምንም አይነት ጭማሪ ሳያደርግ ቤኒዚኒን በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 28 ብር ከ98 ሳንቲም እንዲሸጥ ወስኖ ቆይቷል።
ይህ እንግዲህ መንግሥት ሕዝቡ ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን የኑሮ ሸክም ለማቃለል ሲል የገባውና የወሰደው ከፍ ያለ ኃላፊነት ነው። ይሄን ሲያደርግ በቢሊዬኖች የሚቆጠሩ ብሮችን ለድጎማ ፈሰስ እያደረገ ነው። ይሁን እንጂ በአንድ በኩል በከፍተኛ ድጎማ የሚገባው ነዳጅ በኮንትሮባንድ ሲቸበቸብ መዋሉ፤ በሌላ በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ በመንግሥት ላይ የሚያርፈው ጫና እያደገ መምጣቱ በኢትዮጵያ ገበያ ላይም በነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ስለመሆኑ ሲነገር ቆይቷል። የትናንት በስቲያው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መግለጫም ይሄንኑ ብሂል እውነት ያደረገ ሆኗል።
በመግለጫው እንደተመላከተውም፤ ላለፉት አራት ወራት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎ ከሚያዚያ 30 ጀምሮ በነዳጅ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። ይሁን እንጂ ይህ ውሳኔ በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በወር በአማካይ ወደ ተጠቃሚው መተላለፍ የነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዲመዘገብና በመንግሥት ላይም ከፍተኛ ጫና ማስከተሉን አስረድቷል። ለምሳሌ፣ በሚያዚያ ወር በዓለም ገበያ ነዳጅ የተገዛበት መሸጫ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ ቀጥታ ተሰልቶ ተግባር ላይ ቢውል በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ሊትር ናፍጣ መሸጫው 73 ብር እንደዚሁም የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ዋጋ 66 ብር ከ78 ሳንቲም ይሆን ነበር። ሆኖም ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከዓለም መሸጫ ዋጋ ልዩነትን 85 በመቶ የሚሆነውን ጫና መንግሥት በመሸከም ቀሪውን 15 በመቶ ለተጠቃሚው እንዲተላለፍ በመወሰን የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል።
በዚህም መሰረት ከሚያዚያ 30 ጀምሮ፣ ለምሳሌ በአዲስ አበባ፣ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ቤንዚን በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም ፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 52 ብር ከ45 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 51 ብር ከ78 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 78 ብር ከ87 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኖ ተግባራዊ ተደርጓል።
መንግሥት በዚህ መልኩ 85 በመቶውን ጫና ተሸክሞ 15 በመቶውን ወደተጠቃሚው ማውረዱ መልካም ተግባር ቢሆንም፤ በ15 በመቶውም ቢሆን የተፈጠረችውን የዋጋ ማሻሻያ ተከትሎ በሌሎች ምርትና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋት ከወዲሁ በህብረተሰቡ ላይ ማደሩ አልቀረም። ህብረተሰቡ ይሄን ቢል ካለፈው የሕይወት ልምዱ ያየውን መሰረት አድርጎ ነውና አይፈረድበትም። ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎችም እንኳን ይህችን ያህል ምክንያት አግኝተው ቀርቶ በሉ ሲላቸው ከመሬት ተነስተው ዋጋ ሰማይ ማድረሱን የተካኑበት ነው። ለዚህም ነው ሕዝቡ ከወዲሁ ለእስካሁኑም ሆነ አሁን እየተደረገ ላለው ድጎማና ድጋፍ ከማመስገን ጎን ለጎን፤ አሁናዊ ማሻሻያው በከበደው ኑሮ ላይ ሌላ የኑሮ ጫና የሚፈጥር እዳ ይዛ እንዳትመጣ መንግሥትና ባለድርሻዎችን አደራ የሚለው።
መንግሥትም ቢሆን ይሄን ቀድሞ የተገነዘበው ይመስላል። ምክንያቱም በዋጋ ማሻሻያ መግለጫው ማጠቃለያ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፤ “ይህንን መጠነኛ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ክለሳን ምክንያት በማድረግ በእቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ሰው ሰራሽ እጥረት የሚፈጥሩና በምርቶች ላይ ዋጋን የሚያንሩ ህገወጥ አካላት ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል። ለዚህም በየደረጃው ከሚገኘው የመንግሥት መዋቅር ጋር በመሆን የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ ተገቢውን ትብብር ሊያደርጉ ይገባል፤” ማለቱም ለዚሁ ይመስላል። ይህ መልካም ምልከታ ነው። ሕዝቡም የሚለው ይሄንኑ ነው። በመሆኑም ምስጋናውን ተቀብሎ ከሕዝብ የተሰጠውን የአደራ መልዕክት ወስዶ ኃላፊነትን በወጉ መወጣትም የተገባ ነው።
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም