ከአራት አመት በፊት የመጣው ለውጥ እንዲሳካ ማድረግ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው በሚል ጽኑ እምነት፤ ይሄን ለውጥ በጥበብና በማስተዋል ሳንጠቀምበት ቀርተን ብናባክነው ዳግም ካለማግኘታችን በላይ አገራችንን ወደለየለት የእርስ በእርስ ግጭት ይዘፍቃትና እንደ አገር እንዳትቀጥል ሊያደርጋት ይችላል በሚል ስጋት በአልጋ ቁራኛ ፣ በደዌ ዳኛ ፤ ተይዤ ጣቶቼ ብዕር ባይዙም የእጅ ስልኬ ላይ በአውራ ጣቴ በመጻፍ እንደ ስለት ልጅ የማየው ለውጥ እንዲሳካ ሌት ተቀን እዚሁ ጋዜጣ ላይ ጽፌአለሁ። በኮቪድ ቫይረስ ተጠቅቼ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለ38 ቀናት ተኝቼ ከሞት ጋር እየታገልሁ ሳለ የሰሜን ዕዝን መጠቃት ስሰማ በቁጭትና በእልህ በመነሳሳት ከሕመሜ በላይ ሕመም ስለሆነብኝ አንድ ቀን ሳላጓድል ጽፌአለሁ። የአገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚበይን የወሳኝ መታጠፊያዎች /critical junctures/ ሁሉ ወሳኝ መታጠፊያ ነው ብዬ ስለማምን ያልተገባ ነጥብ ሲጥል ያመኛል። እንደ የእግር እሳት ያንገበግበኛል።
እንግዲህ በዚህ ድባብና አውድ ላይ እያለሁ ነው የእነ ስብሀትን ክስ መቋረጥ ውሳኔ ለዛውም በዕለተ ገና ስሰማ ብዥ ያለብኝና የምይዘው የምጨብጠው የጠፋብኝ። እውነት ለመናገር በህልሜም ሆነ በእውኔ ይሆናል ብዬ ያልገመትሁትና ያልጠበቅሁት ነበር። በወቅቱ ያለጊዜውና ያለምንም ገለጻ የተላለፈው ክስ የማቋረጥ ውሳኔን አንሰላስዬ ፣ አውጥቼና አውርጄ ለመረዳት ብጥርም አልተሳካልኝም። ውሳኔው እንደ የሮኬት ሳይንስ ከብዶኝ ወይም ተወሳስቦብኝ ሳይሆን ስሜቴን መግራት፣ ተጠየቃዊና አመክኗዊ መሆን ስላልቻልሁ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጀመሪያ በጦር ግንባር ለተሳተፉ ጋዜጠኞች በተዘጋጀ የእውቅና መድረክ በኋላ በመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ጊዜ ወስደው የእነ ስብሀት ክስ የተቋረጠበትን ምክንያት በስፋት ቢያብራሩም፤ በስሜት ሀንጎቨር ላይ ስለነበርሁ በሚከተሉት ምክንያቶች የተነሳ የውሳኔውን ተገቢነት አምኖ ለመቀበል ተቸግሬ ነበር።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚያቀርበውን የውሳኔ ሀሳብ ወይም የፍትሕ ሒደቱ ውሳኔ አልያም ብያኔ እስኪሰጥ መጠበቅ የማያስችል አጣዳፊ ሁኔታ እንኳ ቢፈጠር፤ የተጠርጣሪዎችን ክስ የማቋረጥ ውሳኔ ማብራሪያውና አንድምታው ለሕዝብ ከቀረበና ግንዛቤ ከተጨበጠ በኋላ ለዛውም የሚገለጽበት ትክክለኛ ሰዓት/timing/በጥንቃቄ ተመርጦ መሆን ሲገባው የሕዝብንና የአገርን አቲት የወሰደ አድርጌ ስለተረዳሁት፤ የእናት አገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የመጦ የቁርጥ ቀን ልጆቿ በአንድነት በቆሙበት ለዛውም በገና በዓል የወረደ አስደንጋጭ ዱብ እዳ ስለነበር ውሳኔውን ከግራ ከቀኝ አመዛዝኖ ለመቀበል ተቸግሬ ነበር። በነገራችን ላይ የዛን ዕለት የአገርና የሕዝብ ስትሮክ ቢኖር ኖሮ በድንጋጤ ተዝለፍልፈው ይወድቁ ነበር ። ለነገሩ ላያስችል አይሰጥም። ሆኖም ውሳኔው የፈጠረው ሀንጎቨር ዛሬ ድረስ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም።
ከዚህ ውሳኔ በኋላ አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራባውያን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና በሒደት እየቀነሰ ከመምጣቱ ባሻገር በሁለት ቀናት እስከ 74 የሚደርሱ የተዛቡ ዜናዎችን ስለአገራችን ሲያንበለብል የነበረው የምዕራባውያን ሚዲያ ሙሉ በሙሉ ላንቃው ባይዘጋም በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። ሆኖም በእነ ስብሀት ክስ መቋረጥ ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ብዙ አውንታዊ የአጸፋ ምላሽ እጠብቅ ስለነበር ከፍ ብሎ ባነሳኋቸው ጅምር መለሳለሶች አልተደነቅሁም። አሸባሪው ሕወሓት መልሶ በአፋር ወረራ ሲፈጽም ደግሞ የእነ ስብሀት ክስ መቋረጥ እንደገና ያብሰከስከኝ ጀምሮ ነበር። ባለፈው ሐሙስ የፋና ቴሌቪዥን ዜና ላይ መክፈቻና መሪ ዜና መሆን ሲገባው በቢዝነስ ዘገባ ተወሽቆ የሰማሁት ዜና ግን የእነ ስብሀትን ክስ የማቋረጥ ውሳኔው ከአካሔዱ ባሻገር በመርህ ደረጃ ትክክል መሆኑን እንድቀበል መግፍኤ ሆኖኛል።
ባለፈው ሳምንት በዓለም ባንክና በአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም የጋራ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የፋይናንስ ሚኒስትሩ አሕመድ ሺዴና የብሔራዊ ባንክ ገዥው ዶ/ር ይናገር ደሴ ወደ አሜሪካ ያቀኑ ሲሆን፤ ከዚህ ጎን ለጎን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በጎንዮሽ ውይይቶች ላይ የሚሳተፍ ልዑክም አብሮ ተልኮ ነበር ። በፋይናንስ ሚኒስትሩ የተመራው ይህ ልዑክ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት የተነሳ ተቀዛቅዞና ሻክሮ የነበረውን ግንኙነት ለማደስ የሚያግዙና ብዥታን የሚያጠሩ ገንቢ ውይይቶችን ማድረጉ በፋና ቴሌቪዥን ዘገባ ተመልክቷል። ልዑኩ ከአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም(IMF)፣ ከዓለም ባንክ እና ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID)ጋር በመወያየት ያስመዘገበው ውጤት የእነ ስብሀት ክስ መቋረጥና መንግስት ለሰብዓዊነት ሲል የወሰዳቸው የተናጠል እርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣት መጀመራቸውን ያረጋግጣል።
እውነት ለመናገር በአራት ወራት ውስጥ ከገንዘብ ተቋማቱ ጋርም ሆነ ከአሜሪካ ጋር እንዲያ ሻክሮና እንዳልሆነ ሆኖ የነበረው ግንኙነት እንዲህ በአጭር ጊዜ ይሻሻላል ብሎ የጠበቀ አልነበረም። የዓለም ባንክ በሁለት አመታት ውስጥ 6 ቢሊዮን ዶላር በኮንሴሽንና በግራንት የፋይናንስ ድጋፍ ለመስጠት የተስማማ ሲሆን፤ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋምም(IMF) አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመደገፍ ቃል ገብቶ የነበር ቢሆንም በጦርነት የተነሳ የዘረጋውን እጅ አጥፎ ነበር። አሁን ግን ይህን የታጠፈ እጅ መልሶ ለመዘርጋት እና ተቋርጠው የነበሩ ተግባራትን እንደገና ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደርሷል። ይሄው ልዑክ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር ጋራ ባካሄደው ገንቢ ውይይት ተስተጓጉለው የነበሩ ፕሮጀክቶች እንደገና እንዲቀጥሉ መግባባት ደርሷል ።
ከሌሎች የአሜሪካ ተቋማት ጋር በተካሄደ ውይይትም ተፈጥሮ የነበረን ብዥታ ማጥራት መቻሉን የፋይናንስ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በነገራችን ላይ ይህ ታላቅ ስኬት በነጠላ ዜና ብቻ ሊታለፍ አይገባም። የመንግስት መራር ውሳኔ ያስገኘው ውጤት ከእነ ስብሀት ክስ መቋረጥና ለሰብዓዊነት ሲል መንግስት ከወሰደው የተናጠል እርምጃ ጋር አንድምታው መተንተንና መተርጎም አለበት። የመንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ሚኒስትር ከፋይናንስ ሚኒስትሩ ጋር ማብራሪያ ሊሰጡበት ይገባል። ሚዲያዎቻችንም አንድምታውን በልሒቃንን ሊያስተነትኑትና ሊያብራሩት ይገባል።
ወደ ተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ፤ የፋይናንስ ሚኒስትሩን ሰሞነኛ የአሜሪካ ቆይታቸውን ለፋና የገለጹበትን ከፍ ብሎ የዘረዘርሁትን ቃለ መጠይቅ ከተመለከትሁ በኋላ ወዲያው፤ ባለፈው ጥር መጀመሪያ አካባቢ በመከላከያ ዋና መስሪያ ቤት ሕንጻ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ንግግር ወደ ማዳመጥ ነበር የሄድሁት። የእነ ስብሀት ክስ የተቋረጠው በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ለአገር ዘላቂ ጥቅምና አንድነት ሲባል የተወሰደ መራር እርምጃ ነው ያሉት ለካ ትክክል ነበር። በወቅቱ በውሳኔው ስሜታዊ መሆኔ ምክንያታዊ ቢሆንም ትክክል ግን አልነበርሁም። እውነትም ውሳኔው ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የአገርን ህልውና ለማስቀጠል የተወሰደ ስትራቴጂካዊ፣ በማስተዋልና በጥበብ የተመራ ነበር። ሆኖም በወቅቱ ውሳኔው የፈጠረብኝን ስሜት እንደወረደ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ። የስብሀት ክስ የተቋረጠለት ብዕሬ እንዲህ ተንጨርጭራና ያዙኝ ልቀቁኝ ብላ ነበር። የተወሰኑ ናሙና አንቀጾችን እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ። ዛሬ ከስሜት ወጥታ ስትመለከተው ግን መሳሳቷ ይገባታል። ለዚህ ነው በጸሐፊው የህሊና ሚዛን ያልሁት የመጣጥፌን ርዕስ።
ሕወሓት በተደጋጋሚ የሰላምን ደጅ ዘጋ። የተዘረጉ የሰላም እጆችን ገፋ። በመጨረሻም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ውድቅት ሌሊት ለ21 አመታት ከምሽጉ ሳይወጣ የትግራይን ሕዝብ ቀን ከሌሊት ሲጠብቀው፤ በደስታው፣ በሀዘኑና በችግሩ ተለይቶት በማያውቀው ተጋብቶ፣ ተዋልዶና አበልጅ ተናስቶ በፍቅር በኖረው ሰሜን ዕዝ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ክህደት በመፈጸም በውድቅት ሌሊት ትጥቅ ፈትቶ በተኛ ሰራዊት ላይ ቦንብ በመወርወርና እሩምታ በመተኮስ ጭካኔ የተሞላበት የሚዘገን ጥቃት ፈጸመ። ይፋ ያልወጡ መረጃዎች ከ6ሺህ በላይ የሰራዊቱ አባላት በገዛ ጓደኞቻቸውና ወገናቸው እንደተፈጁ ያመለክታሉ። የዕዙ የጦር መሳሪያና ስንቅ ተዘረፈ። የሰራዊቱ የጥቅምት ወር ደመወዙና በጀቱ ሳይቀር ተወሰደ። የዚህ በእነሱ አነጋገር “መብረቃዊ ጥቃት” ግብ ሰራዊቱን በማጥቃትና በመዝረፍ የሚቆም አይደለም። እንደ ግብጽ ካሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በማሴርና በመቀናጀት የመንግስት ለውጥ በማምጣት ኢትዮጵያን ማፍረስ ነበር አላማው። የመጨረሻ ትልሙም በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ታላቋን ትግራይ መመስረት ነበር። በአገሪቱ የ3ሺህ አመት ታሪክ እንደ እፉኝቱ ሕወሓት ያለ ጠላት ገጥሟት አያውቅም የሚባለው ለዚህ ነው።
ከጥቃቱ የተረፉ የሰራዊቱ አባላት በእልህና በቁጭት እንደገና ተደራጅተው ሶስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መቐሌ በመግባት የተዘረፈውን ትጥቅ በማስመለስ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሩ ተደምስሶ እጁን የሰጠው ደግሞ ለሕግ እንዲቀርብ ተደረገ። ሆኖም ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላ በሀሰተኛ መረጃ ላይ የተመሠረተውን የምዕራባውያንን ጫና ለማስታገስ፤ ትግራዋይም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኙ፤ ገበሬውም እንዲያርስ እና በሌሎች ሰብዓዊ ምክንያቶች ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት ከትግራይ ጦሩን ሲያስወጣ እንደ ሰሞኑ ውሳኔ አስደንጋጭና ዱብ ዕዳ ነበር። ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ውሳኔው በጥርጣሪ ቢመለከተውም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በኋላ አቋሙን ለዘብ አድርጎ ነበር። ሆኖም ዛሬ ድረስ ውሳኔው ስህተት ነበር ብለው የሚሞግቱ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። በአማራና በአፋር ክልሎች የተፈጸመው ግፍ፣ ውድመትና ዘረፋ የእነዚህን አካላት አተያይ የሚያጠናክር ነው።
አፍሪካዊው ፋሽስት ወይም ናዚው ሕወሓት ግን የተናጠል የተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ፤ በሕዝባዊ ማዕበል ወደ አጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች ወረራውን አስፋፋ። የማይካድራው አልበቃ ብሎ በጋሊኮማ፣ በጭና፣ በአጋምሳ ፣ በንፋስ መውጫ ፣ በመርሳ ፣ በውጫሌ ፣ በአንጾኪያ ገምዛ ፣ ወዘተረፈ በዘር ማጥፋት ፤ በጦር ወንጀል ፤ በሰብዓዊ ፍጡር በተፈጸመ ጥቃት የሚያስጠይቀውን ወንጀል ፈጸመ። በመቶዎች በሚቆጠሩ ህጻናትና ሴቶች ላይ መነኮሳትንና አረጋውያን ጨምሮ በቡድን አስገድዶ መድፈር ፈጸመ። በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ንጹሐንን በግፍ ገደለ። ወደ 10ሺህ የሚጠጉ የጤናና የትምህርት ተቋማትን ዘረፈ። አወደመ። የመንግስትና የግል ንብረቶችን ዘረፈ። አወደመ። የወልድያ፣ የወሎና የመቅደላ ዩኒቨርሲቲዎችን አወደመ። ዘረፈ። ወደ 50 የሚጠጉ ኢንዱስትሪዎችንና ፋብሪካዎችን ዘርፎ ከጥቅም ውጭ አደረገ። ሚሊዮኖችን አፈናቀለ። እንግዲህ ሕዝብና አገር ከዚህ ትኩስና መጥፎ ትውስታ ጋር እየታገሉ፤ ሕዝቡ ከሀዘኑ ሳይጽናና፣ ከሉን ሳይቀይር ነው፤ የዚህ ሁሉ ዕልቂትና ጥፋት ስትራቴጂስት የሆነውን ስብሀት ነጋን ጨምሮ ስድስት የሕወሓት አመራሮች ለሰብዓዊነት ሲባል ከእስር የመፈታት መርዶ የተሰማው። በሀዘን ላይ ሌላ ሀዘን የፈጠረው። በበደል ላይ ሁለተኛ በደል የሆነው። የሚያሳዝነው አሸባሪው ኃይል ዛሬም ከመተናኮስ አላረፈም።
በጃዋር መሐመድና በእስክንድር ነጋ ሁለት መዝገቦች ላይ በወንጀል ተጠርጥረው በሕግ ጥላ ስር የነበሩ ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑ ደጋፊዎቻቸውን ያስደሰተ ቢሆንም፤ በተወሰነ ደረጃ ተቃውሞ ያስነሳው በሁለት አበይት ምክንያቶች ነው። የመጀመሪያው የፍትሕ ሒደቱ ተጠናቆ ውሳኔ ከተሰጣቸው በኋላ ለአገራዊ ምክክሩም ሆነ ለብሔራዊ እርቁ ሲባል በምህረትም ሆነ በይቅርታ ቢፈቱ መልካም ነበር የሚል ሲሆን። ይህ ባለመሆኑ በሕግ የበላይነቱ ላይም ሆነ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድርና የተሳሳተ መልዕክት ወይም ትዕምርት እንዳያስተላልፍ ከሚል ቅን ስጋት የመነጨ ነው። ሁለተኛው የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በባሌና በሌሎች አካባቢዎች ማንነትን ኢላማ አድርገው የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ጥፋቶችና ውድመቶች ተመልሰው ቢከሰቱ ምን ዋስትና አለን ከሚል ስጋትና ፍርሀት የመነጨ ነው። ስጋቱ ችላ የሚባል ባይሆንም የቀውስ ቀፍቃፊው ሁለቱም ክንፎች ስለተመቱ እንዲሁም የዛን ጊዜውና የዛሬው መንግስት ሕግን የማስከበር አቅም የተለያየ ስለሆነ ስጋቱ ሙሉ በሙሉ ችላ ባይባልም ያን ያህል አሳሳቢ አይሆንም። በቀጣይ አገራዊ አንድነቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ፤ እንደ ኤርትራ ካሉ ስትራቴጂካዊ አጋሮቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዳያሻክሩ ሰሞነኛ አይነት ውሳኔዎች ከመተላለፋቸው በፊት ግራ ቀኙን ማማከር ፤ ትርፍና ኪሳራውን ማስላት ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ ይገባል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ! አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝ 30 ቀን 2014 ዓ.ም