ያለፈው ሳምንት እንደ አገር ብዙ ነገሮችን ያየንበት ያሳለፍንበት ብዙ ደስታዎች የኖሩ ቢሆንም በእኩይ ተግባራቸው የሰዎችን ደስታ ለማጠልሸት በሚጥሩ ሀይሎችም እዚህም እዚያም ችግሮች ሲንጸባረቁ ያለፉበት ሳምንት ነበር፡፡
እነዚህ ነገሮች ሁሉ ታዲያ እኛን እንደ አገር እንዳንቆም ከማድረጋቸውም በላይ ለጥፋት ለሚፈልጉን ሀይሎች አመቻችቶ የሚሰጠንም እንደሆነ ያስተዋለ ያለ እስከማይመስል ድረስ አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ እንድናልፍ ተገደንም ነበር፡፡ ነገር ግን ችግር ለመፍጠር የማይቦዝኑ ተላላኪዎች የመኖራቸውን ያህል በዛው ልክ ደግሞ የአገራቸው ሁኔታ የሚያሳስባቸው ህዝባቸው በሰላም ወጥቶ እንዲገባ የሚያስቡ በጠቅላላው ቅን ኢትዮጵያውያን ነገሩ ከስሩ እንዲደርቅ የራሳቸውን ሚና ተወጥተዋል፡፡ እኩይ ተግባር ፈጻሚዎቹን የምናወግዘውን ያህል እነዚህንም ሀይላት ማመስገን እንደሚገባ ደግሞ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ያም አለ ይህ ግን አሁን አገራችን ሰላም ትፈልጋለች እዚህም እዚያም በጸብ አጫሪዎች እየተለኮሶ ያሉ እሳቶች ህዝቡን ለምሬት የአገርንም ኢኮኖሚ በማሽመድመድ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ነው፡፡ በመሆኑ አሁን ለአገራችን በምድር ላይ አሉ የተባሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ መጠቀም ደግሞ የግድ የሚለን ወቅት ላይ እንደሆንን ይሰማኛል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ከላይ እንዳልኩት በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ የሠላም አማራጮች አገራችንን እስከ ታደጉልን ድረስ ብንቀበላቸው ጥሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ አጥፊዎችን ማጥፋት መረበሽ እንኳን የሚችሉት አገር ሲኖር መሆኑን ተገንዝበው ሁሉንም የሰላም አማራጮች ባይፈልጉም እንኳን እየጎመዘዛቸውም ቢሆን መቀበል አለባቸው እላለሁ። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች አንድ ቀን ልብ አግኝተው የተመለሱ እለት ዞሮ ዞሮ መግቢያቸው እምዬ አገራቸው በመሆኗ፡፡
እዚህ ላይ ምናልባት ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር ካለችበት ችግር ለማውጣት የሚመጣው የሠላም መፍትሄና የሠላም አማራጭ ከግል ፍላጎትና አቋም አንጻር ላይዋጥላቸው፣ ሊያማቸው፣ ሊጎመዝዛቸው ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያን የሚያድን እስከሆነ ድረስ እየጎመዘዘም ቢሆን መቀበል ይገባል፡፡
ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማሻገር የምናመጣው የሠላም መፍትሄና የሠላም አማራጭ ከግል ፍላጎትና አቋም አንጻር ላይዋጥልን፣ ሊያመንና ሊጎመዝዘን ቢችልም ኢትዮጵያን የሚያድንና ህዝቡን ወደ ፊት የሚያሻግር እስከሆነ ድረስ መቀበል ያለብን እውነት ሊኖር እንደሚችል ከወዲሁ መረዳት ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያውያን ሠላም እንፈልጋለን:: የሠላም እጦት መላውን ኢትዮጵያዊ አንገሽግሾታል:: በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ጽንፍ በሚከሰቱ ግጭቶች በርካታ የማህበረሰብ ክፍል እየተማረሩ እየተጎዱ ከቤት ንብረታቸው በግፍ እየተሰደዱና ላላስፈላጊ እንግልት እየተዳረጉ ነው:: ይህ ጉዳይ አሁን ላይ በቃ ካልተባለ መቼም ሊያበቃ ካለመቻሉም በላይ እንደ አገር ስለመቀጠላችን ራሱ መገመት ከባድ ነው::
ከዚህ አንጻር በየትኛውም ደረጃ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች በእነርሱ እምነት ኢትዮጵያን ወደ ፊት ያሻግራል ብለው የሚያምኑበትን የሠላም እቅድና አማራጭ ይዘው ቢቀርቡ፣ በየትኛውም ሁኔታ ሠላም እንዲሰፍን እንፈልጋለን የሚሉ ኢትዮጵያውያንም አጀንዳ እየሰጡ ከሚያባሏቸው መሰሪዎች ራሳቸውን ቢጠብቁ߹ ወጣቱም በስሜት ሳይሆን በአስተዋይነት እያንዳንዱ እርምጃው አገር ላይ ምን እንደሚያስከትል በተረዳ መንገድ ቢጓዝ በጠቅላላው አስተዋይ አርቆ አሳቢ በመሆን በብልሃት ብንጓዝ ከገባንበት ችግር ለመውጣት ቀላል ይሆናል የሚል ግምት አለኝ፡፡
አሁን አገራችን ለገባችበት ችግር በትግራይ ክልል በኩል የተነሳው ጦርነት እንደ ምክንያት ይገለጻል፤ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ኢትዮጵያ እንደ አገር እዚህ እንድትደርስ ጉልህ አበርክቶ ያለው ህዝብ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ ጉልህ አበርክቶአቸውን እንዲቀጥል፤ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ ማመቻቸት ግን ከሁላችንም የሚጠበቅ ከባድ የቤት ስራም ሆኖ ይታየኛል፡፡
እንደ ዜጋ የሽብር ቡድኑ በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች የተጎዱ አካባቢዎች በተለይ አፋርና አማራ አካባቢዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያ ሠላም እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ያ ሠላም እንዴት መምጣት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ግን ሁላችንም የራሳችንን ጠጠር መወርወር እንዳለብንም ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት መወያየትና መመካከር ይኖርባቸዋልም እላለሁ::
ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን ኢትዮጵያን እንወዳለን ማለት አንችልም፤ ይህን ጉዳይ ሁሉም ማህበረሰብና ፖለቲከኞች ሊረዱት ይገባል::በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ብቻ ናቸው::ኢትዮጵያን አልፈልግም የሚልን አካል ኢትዮጵያን ወደ ፊት እንዴት እናሻግራት በሚል ድርድርና ምክክር ወይም ውይይት ውስጥ ይካተት የሚል አቋም የለኝም::ምክንያቱም ጉዳዩ የኢትዮጵያውያን ስለሆነ::
ሕወሓት ጦርነትን የሙጥኝ በማለቱ የትግራይን ህዝብ ለከፍተኛ ስቃይና እንግልት ከመዳረጉም በላይ መከራውን ለአማራና ለአፋር ህዝብም አትርፏል። ከዚህም አልፎ መላ ኢትዮጵያውያን የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ችግሩን የከፋ የሚያደርገው ቡድኑ ዛሬም ቢሆን ከዚህ ተምሮ ለሰላም የሚዘረጉ እጆችን እየረገጠ ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የሚጓዝ መሆኑ ነው። ይህ ቡድን ከደረሰበት ኪሳራና እሱም ካደረሰው ጥፋት ሳይማር ጦርነት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ይሰብካል። ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የጦርነት ነጋሪቶችን እየጎሰመ ወጣቶችን ለጦርነት የመቀስቀስ ተግባሩን ተያይዞታል። የትግራይ እናቶችን ባዶ ቤት ለማስቀረት ወጣቶችን ወደጦርነት ለመመልመል ዛሬም አላረፈም፡፡
“በጥባጭ ካለ ማን በሰላም ይጠጣል” እንደሚባው ይህ ቡድን በመኖሩ መላ ኢትዮጵውያን ሰላም እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል። የዚህ ቡድን በሽታ እንደካንሰር በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ተሰራጭቶ የሰላም መደፍረስ መንስኤ ሆኗል። በመሆኑም ከዚህ አካባቢ ያለውን የሰላም ችግር ማጥራት ለዘላቂ መፍትሄ ወሳኝ ነው፡፡
ሕወሓት በግልጽ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ድረስ እገባለሁ የሚሉ አመራሮች ያሉበት እንደመሆኑ፤ መርዝ ቀማሚዎችን ባለ መድኃኒት አድርጎ መቀበል ስህተትም ስለሚሆን ይህ በቅጡ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ይመስለኛል::በሌላ በኩል ግን አገራችንን ለማዳን በዓለም ላይ ያሉ የሰላም አማራጮችን ሁሉ በመጠቀማችን እናተርፍ ይሆናል እንጂ አንጎዳም::
በእምነት
አዲስ ዘመን ሚያዝ 30 ቀን 2014 ዓ.ም