አዲስ አበባ ጃንሜዳ አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ህብረት ፍሬ እና ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ኮከበ ፅባህ ትምህርት ቤት ተምረዋል። ኮተቤ መምህራን ኮሎጅ ገብተው በጂዮግራፊ መምህርነት ሰልጥነው ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂዮግራፊና አካባቢ ጥናት የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በማህበረሰብ ጥናት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በአምቦ ዩኒቨርሲቲና ሲአርዴ ትብብር የሚሰጥ የትምህርት አድል አግኝተውም በዴቭሎፕመንት ማኔጅመንት ተጨማሪ የማስተርስ ዲግሪ መስራት ችለዋል። እንዲሁም ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ በርካታ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ወስደዋል።
ለም በተባለ የመንግስት ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት በመምህርነት ያገለገሉት እንግዳችን ጥናት ላይ በሚሰሩ የግልና መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመተባበር የዳሰሳ ጥናቶችን ሰርተዋል። ከአንድ ወዳጃቸው ጋር በመሆኑም አማካሪ ድርጅት ከፍተው ህብረተሰቡን አገልግለዋል። በመቀጠልም ሲቪል ማህረሰብ ድርጅት ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመምጣት በተለይም ኤች አይቪ ኤድስ በአገሪቱ አስከፊ በሆነበት ወቅት የተለያዩ ትምህርቶችን ለህብረተሰቡ በመስጠት እንዲሁም ወጣቶች በማሰልጠን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ይህም አጋጣሚ ደግሞ ፕሮጀክቶችን የማስተባበር እድል ፈጠረላቸው። ከዚህ ባሻገር በወቅቱ የለቀቁትን ሥራ አስኪያጅ በመተካት በተጠባባቂነት እንዲሁም በዳይሬክተርነት ድርጅቱን ለስምንት ዓመት መሩ። በመቀጠልም ኤድስ ሄልዝ ኬር ፋውንዴሽን በተባለና የአሜሪካ መሰረት ባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል። በአፍሪካ ህብረት ትምህርት ዘርፍ በአማካሪነት ለአምስት ዓመት አገልግለዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትን በሥራ አስኪያጅነት እየመሩ ይገኛሉ። በምክር ቤቱ ሥራና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ስለምክር ቤቱ ዋነኛ ሥራ ምንነት ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ሄኖክ፡- ይሄ ምክር ቤት እንደሚታወቀው በአዋጅ የተቋቋመው ከአንድ ዓመት በፊት ነው። የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ በሪፎርም ከተመሰረቱ ተቋማት መካከል ነው። ይህንንም ተከትሎ አዋጅ እንዲከለስ ተደርጓል። ቀድሞ የነበረው 621 የሚባለው የሲቪል ማህበረሰቦች አዋጅ በ1113 ተተክቶ የተከለሰ ሲሆን ይሄ ምክር ቤት እንዲቋቋም በአዋጁ ላይ በግለፅ ተቀምጧል። በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የመወከልና የማስተባበር ሃላፊነት አለበት። ይህም ሲባል በፌደራል ደረጃ የተመዘገቡ ከ3ሺ700 በላይ የሲቪክ ድርጅቶን፤ የመምህራን ማህበር፤ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና የሙያ ማህበራት ፌዴሬሽን፤ አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶችንና የመሳሰሉትን በሙሉ የሚካተቱበት ምክር ቤት ነው። ከዚህም በሻገር በክልል ደረጃ ለተቋቋሙ ድርጅቶችም እንዲሳተፉ እድሉ ተፈጥሮላቸዋል።
በተጨማሪም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የመደገፍ ሚናም አለው። በተለይም ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን እንዲያስፍኑና ራሳቸውን እንዲከታተሉ የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶናል። በሌላ በኩልም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን የማማከር ሥራ ይሰራል። እንዲሁም ምክር ቤቱ እውቀትን የማደራጀት፣ የማሰራጨት፣ ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን ነገሮች በማየት የዳሰሳ ጥናት በመስራት ጠቃሚ በሆነ የልማት አቅጣጫ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ይሰራል። መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምክር ቤት በመሆኑ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ገለልተኛ ተቋም ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምክር ቤቱ አባል የሆኑ የሲቪክ ማህበራት ከተቋቋሙበት ዓላማ አንፃር ሚናቸውን ምን ያህል ተወጥተዋል ማለት ይቻላል?
አቶ ሄኖክ፡- እንደሚታወቀው የአገራችን የሲቪል ማህበራት ሚና እጅግ የጎላ ነው። ዓይነታቸውም ብዙ ነው። ጤና፣ ግብርና፣ ትምህርት፣ ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ ድጋፍና የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ አሉ። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ በኢትዮጵያ ልማት ላይ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል ማለት ይቻላል። ጉዞው ግን ቀላል አይደለም። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በማደግ ላይ ያሉ አገሮች በተለይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነ ፈተና ነው ያለባቸው። ከሚጠበቅባቸው አንፃር ለመስራት እንዳይችሉ እንደአገር ዘርፉ ብዙ ችግሮች ነበሩባቸው። ለዚህ ደግሞ ምቹ ሁኔታ ያለመፈጠሩ በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው። በተለይም ቀደም ብሎ የነበረው የሲቪል ማህበረሰብ አዋጅ ለአስር ዓመት ነው የቆየ ከመሆኑም በላይ እጅግ ገዳቢ ነበር። በዚህ ምክንያት አንዳንድ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታ ስላልነበር እንዲጠፉ ሆኗል። እንኳን አዲስ ማህበራት ሊቋቋሙ ቀርተው የነበሩትም እየተዘጉ፤ እየተዳከሙ እንዲሄዱ ተደርጓል። ይህም በጣም ዘርፉን ጎድቶታል።
ምቹ ምህዳርና የሚያሰራ ህግ በሌለበት ሁኔታ ተቋማቱ የሚጠበቅባቸውን ሚና አሳክተዋል ለማለት አያስደፍርም። ይሁንና በዚያም ውስጥ ሆነው በተለይ በጤናው፤ በትምህርትና በግብርና ዘርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች የማይናቅ አስተፅኦ ነው ያበረከቱት። ህግ እንዲወጣ ከማድረግ ጀምሮ የተለያየ ፕሮግራም እንዲተገበሩና ለልማት ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይቷል። ነገር ግን ከሌሎች አገሮች አንፃር ወደኋላ እንደቀረን ይሰማኛል። በቁጥርም ቢሆን በጣም ትንሽ ናቸው። አሁን ላይ ያሉን ማህበራት አራት ሺ አይሞሉም፤ ሌላ አገራት ላይ ግን ከመቶ ሺ በላይ ማህበራት አሏቸው። በህንድን ለምሳሌ ብንወስድ ሶስት ሚሊዮን የሚደርሱ የማህበረሰብ ድርጅቶች ናቸው ያሉት። እናም ይሄ ዘርፍ ገና ብዙ መልማት አለበት ብዬ ነው የማስበው።
ከዚህ ባለፈ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚናቸውን እንዲወጡና በደንብ ግንዛቤ እንዲወሰድና ትክክለኛ ቁልፍ የሆነ የልማት አጋር ናቸው ብሎ እንዲታሰብ እንፈልጋለን። በአሁኑ ጊዜ ያንን ለማምጣት እየሰራን ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳቸው ምክር ቤት እንዲቋቋም ተደርጓል፤ ሆኖም የሚጠበቀውን ያህል የድርጅቶቹን አቅም ለማሳግ ብዙ መስራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚሰሩ ተቋማት የሕዝብን የልብ ትርታ አዳምጦ እምባን የሚያብስ ሥራ መስራት ላይ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው ይነሳል። ከዚህ አንፃር እንዳይሰሩ የነበረባቸው ተግዳሮት ምን ነበር?
አቶ ሄኖክ፡- ትክክል ነው! ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዋነኝነት ሊሰሩት የሚገባው ይህንን ነው። የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ህዝቡ ላይ የሚደርሰውን በደል በመከታተል አሰራሮች እንዲሻሻሉ ተፅዕኖ የመፍጠር ሚና አላቸው። አስቀድሜ እንደገለፅኩት ለአስር ዓመት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲህ አይነት ስራዎችን እንዳይሰሩ ተገድበው ነው የኖሩት። አገር በቀል ድርጅቶች ብቻ በተለይ በገንዘብም ተወስነው እንዲሰሩ መደረጉ እነዚህ ድርጅቶች ሃላፊነታቸውን በሚገባ እንዳይወጡ አድርጓል። በነገራችን ላይ ምቹ ምህዳር አለመኖሩ ዘርፉን ጭምር ጎድቶታል። አሁን በተሻሻለው አዋጅ እንዲሰሩ ቢፈቀድም አቅማቸውን መገንባትም አልቻሉም። ወደዚያ እንዲመጡ፤ ባለው አቅምም እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ያለው።
ሁልጊዜ የምንወስዳቸው እርምጃዎች የወደፊቱን ታሳቢ ያላደረገ ከሆነ በአገር እና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ይሄ ማሳያ ነው። አሁን ላይ እየከፈልን ያለነውም ዋጋም ከዚያ ጋር ተያይዞ ያለ ነው። ሰዎች በድርጅቶች መብት ላይ፤ በዲሞክራሲ ላይ እንዳይሰሩ ከተከለከለ ሊከሰት የሚችለው አሁን እያየነው ያለው አይነት ችግር ነው። አስር ዓመት ደግሞ በጣም ትልቅ ነው። በእነዚህ ዓመታት አብዛኞቹ ድርጅቶች ጠፍተዋል፤ ተዘግተዋል፤ አዳዲሶችም ሊቋቋሙ አልቻሉም። ይሄ በሆነበት ሁኔታ ብዙ ነገር መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን አሁን በመጠኑ ምቹ የሆነ ሁኔታ አለ፤ መስራትና ራሳቸውን ማብቃት ይገባቸዋል። በዚህ በተወሰነ ዓመታት ብቻ አዳዲስ ድርጅቶች እየተቋቋሙ ነው። የተዳከሙትም ዳግም ራሳቸውን እያጠናከሩ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- ባለፈው ስርዓት እነዚህ ድርጅቶች በአዋጅ እንዲዳከሙ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የውጭ ሃይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው የተገኙና ለአገር ደህንነት ስጋት የሚፈጥር እንቅስቃሴ ማድረጋቸው እንደሆነ ይነሳል። በእርግጥ ያ ችግር ነበር ብለው ያምናሉ?
አቶ ሄኖክ፡- አሁን ያነሳሽውን ነገር በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛ ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ንፁህ ነው ማለት አይቻልም። እንዲህ አይነት ነገር የሰሩ ምን ያህል ናቸው? ብሎ መጠየቅ ግን ይቻላል። ያለነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ የሚመራውም በኢትዮጵያውያን ነው፤ እንዲህ አይነት የህግ ጥሰት በሚፈፅሙት ላይ እርምጃ መውሰድ ይቻላል። ሁለተኛ ቁጥራቸውም ያን ያህል ብዙ ባለመሆናቸው ማስተካከል ይቻላል። በህግ ማረምና መቆጣጠር የመንግስት ስልጣን ስለሆነ የሲቪክ ማህረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙበትን ዓላማ ተከትለው መስራት ስላለባቸው ምንም ለቁጥጥር የሚያዳግት ነገር አይኖርም።
ሁለተኛው ትልቁ ክፍተት የሚኖረው ትግበራ ላይ ነው። ትግበራ ላይ ከተሰጣቸው ዓላማ ውጭ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ተብሎ ከታሰበ ያንንም መቆጣጠር ይቻላል። ምክንያቱም የመቆጣጠር ስልጣን ያለው መንግስት በመሆኑ በገሃድ ከሚሰሩት ውጭ ሲሰሩ ከተገኙ እስከመዝጋትና ፍቃዳቸውን እስከመሰረዝ ድረስ ስልጣን አለው። ነገር ግን በህግ ትልልቅ ጉዳዮችን መገደቡ ጉዳቱ በአገር ላይ መምጣቱ አይቀርም። አሁንም የምንለው ይህንኑ ነው፤ ለምሳሌ እንዲህ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ መንግስት ጋር ሳይደርስ ምክር ቤቱ ራሱ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ የስነ-ምግባር ደንብ አዘጋጅተናል። ይህም ማለት ድርጅቶች ራሳቸው ቅሬታ እንዲያቀርቡና ራሳቸውን እንዲያርሙ የሚያደርግ ነው። ምክንያቱም ከአገር ህልውና የሚበልጥ ነገር የለም።
ጥቂት ድርጅቶች እንዲህ አይነት ችግር ፈጥረው ቢገኙ እንኳን ማረም የሚቻልበት መንገድ ባለበት ሁኔታ ግን ዲሞክራሲና መብት ላይ እንዳይሰሩ በህግ መደንገግ ከዚያ ሊገኝ የሚችለውን ጥቅም ያሳጣል። ደግሞም ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ ይሆናል ብዬ አላስብም። ወደፊትም መሆን ያለበት ባልተገባ ድርጊት ውስጥ የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ድርጅቶች ቢኖሩ ይሄ ምክር ቤትም መንግስትም በጋራ ሆነን እርምጃ መውሰድ እንችላለን። በዚህ ሰበብ ግን ይደረግ የነበረው የሲቪል ማህበራትን የማስደንገጥና የማሸማቀቅ ስራ ነው። እንደሚታወቀው የእነዚህ ተቋማት አንዱ ሚናቸው መንግስትም ያለአግባብ ስልጣኑን የሚጠቀም ከሆነ ያንን መተቸና ምክረ ሃሳብ መስጠት እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳብ ማመላከት ነው። እንዲህ አይነት ተቋማት እንዳይኖር የተደረገው ጥረት ውድቀት አምጥቷል ባይ ነኝ። ህዝቡም ብዙ ተጎድቷል፤ ሲቪል ማህረሰቡ ተደራጅቶ መብቱን ለማስከበር አልቻለም ነበር። ይህንን ሰበብ በማድረግ መብትን መገደብ በአገር ልማት ላይ ትልቅ ጉዳት አምጥቷል። እሴቶቻችንን ማጎልበት አልቻልንም።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ተቋማት የፖለቲካ እና የእምነት ውግንና በማሳየትም ይታማሉ፤ ከዚህ አንፃር የነበረውን ችግር እንዴት ይገልፁታል?
አቶ ሄኖክ፡- እንግዲህ በመርህ ደረጃ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለልተኛ ናቸው። ከመንግስትም ሆነ ከሌላ አካል ውግንና ነፃ ሆነው ይሰራሉ ተብሎ ነው የሚታመነው። ሲቋቋሙም ‹‹መንግስታዊ ያልሆኑ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ነው። ይህም ምንም አይነት የፓርቲ ውግንና እንደማይኖራቸው በግልፅ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን ነው የሚያሳየን። ይሁንና ሰዎች በሃይማኖታቸው፣ በጎሳ፣ አልያም በጓደኝነት የመደራጀት መብት ህገ-መንግስቱ ሰጥቷቸዋል። ያ ማለት ውግንና ይዘው ሌላውን የሚያገል ሥራ ይሰራሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን በአገራቸው የፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ አይሰሩም ማለት አይደለም። አንዱ ብዥታ ያለው በዚህ ጉዳይ ላይ ነው። የፖለቲካ ሁኔታውንም ሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላሉ። የነበሩትን ሁኔታዎች ስናይ ከተደራጁበት አይነት አኳያ ይህንን መርህ የሚጥሱ ሊኖሩ ይችላሉ።
ይህም የሚሆነው አንደኛ ግንዛቤ ካለመኖር አንፃር ሊሆን ይችላል፤ ሁለተኛ ደግሞ ሰው በተፈጥሮ ለሆነ አካል ይወግናል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ መንግስት ጡንቻ አለው። አንዳንዶች የመንግስትን አቋም የማንፀባረቅ ነገር ታይቶባቸው ይሆናል፤ ሌሎች ለሚመስላቸው የሚወግኑበት ሁኔታ ይኖራል። ግን ይህ ውግንና በፍፁም ይሁን ብለን የምንተወው ነገር አይደለም። አሁንም ቢሆን በተለይ በመንግስት በኩል ውግንና ያላቸው ሲደገፉ እናያለን። ይሄ ለቁጥጥርም ያስቸግራል። በእርግጥ ይሄ ምክር ቤት የተቋቋመው በቅርቡ እንደመሆኑ ከዚህ በፊት የነበረውን ችግር መቆጣጠር የሚችል አካል አልነበረም። የእርምጃዎችንም ለመውሰድ አቤት የሚል የለም። እንደፈለጉ ወዲህና ወዲህ ሊያዟቸው ይችላሉ።
በአጠቃላይ የሲቪል ማህበራት የሚገባቸውን ቦታም ሆነ ነፃነት አግኝተው እስካልሰሩ ድረስ እንዲህ አይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን አሁን ይሄ ምክር ቤት ማንኛውም ድርጅት ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ እንዲሰራ ፈፅሞ አይፈቅድም። የስነ-ምግባር ደንቡም ውግንናቸውን ይዘው መስራት እንደሌለባቸው ነው የሚደነግገው። ምክር ቤቱም ከምንም ውግንና ነፃ ሆነው እንዲሰሩ ግፊት ያደርጋል። ይህንን ተላልፈው ሲገኙ ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን። በነገራችን ላይ የስነ-ምግባር ደንቡን ተፈፃሚነት የሚከታተል ኮሚቴ አለ። ይህ ኮሚቴ የሁኔታውን ደረጃ አይቶና መርምሮ ከፍ ያለ ከሆነ በህግም እስከማስጠየቅ ድረስ ሊደርስ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታስ ድርጅቶቹ ነፃነታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው?
አቶ ሄኖክ፡- እንግዲህ አስቀድመን እንዳነሳነው መንግስት ሊያደርግ የሚችለው ህግን ማሻሻል ነው። በነገራችን ላይ ገዳቢ የነበረውን ህግ ማንሳት በራሱ ትልቁ እርምጃ ነው። ይህም ማለት እንደችሮታም ባይሆንም መንግስት ግን አንድ ትልቅ ነገር አድርጓል ብለን እናምናለን። ሁለተኛው ጥሩ ነገር ደግሞ ይሄ ምክር ቤት መቋቋሙ ነው። ከዚህ ቀደም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አልተፈቀደም፤ እንዲህ አይነት ምክር ቤት እንዲኖረውም በአዋጅ ስልጣን አልተሰጣቸውም። እነዚህ ነገሮች ከህግም ሆነ ከመደላደል አንፃር ስናያቸው በጣም ትልቅ የሚባሉ ናቸው። ከዚህ በኋላ ደግሞ የታሰበውን ዓላማ ነፃና ገለልተኛ ሆነው፤ አንቺም እንዳነሳሽ ነፃነቱ ኖሯቸው ለመስራት አንደኛ ድርጅቶቹ ራሳቸው ለዚህ የነቃ ተሳትፎ ማድረግና የተሰጣቸውን መብት ተጠቅመው አሳማኝ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ራሳቸውን ማሳደግና ማጠናከርም ይገባቸዋል።
ሁለተኛ መንግስትም ሆነ ሌላ አካል እንደመንግስት ሆነው እንዲሰሩ መጠበቅ የለባቸውም። ይህም ማለት ድርጅቶቹ ነፃነቱ ከተሰጣቸው በሚሰሩበት ጊዜ ሊገጥማቸው የሚችል ተፅዕኖ መኖር የለበትም። ከዚያ ይልቅ ገንቢና ተባባሪ ሆኖ መስራት ነው ከሁሉም የሚጠበቀው።
አዲስ ዘመን፡- በስድስተኛ አገር አቀፍ ምርጫ የተሳተፉ የሲቪክ ማህበራት ምን ያህል ተልዕኳቸውን አሳክተዋል ብለው ያምናሉ?
አቶ ሄኖክ፡- ከተሳትፎ አንፃር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም በነበሩትም ምርጫዎች ብዙ ሲሳተፉ ነበር። የተሳትፏቸውን ውጤታማነትን ለመለካት ግን የተከናወኑትን ምርጫዎች ምን ያህል ዲሞክራሲያዊ ነበሩ? የሚለውን ማየት አስፈላጊ ነው። አገራችን ምን አይነትና እንዴት አይነት ምርጫ ስታካሄድ እንደነበር ለሁላችንም ግልፅ ነው። ስለዚህ አንዱ እንዲሻሻል የምንፈልገው ጉዳይ ነው። ነፃ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለአገር ያስፈልጋል ብለን ስንታገል የቆየንበት ነው። በዚህ ረገድ ከተሳትፎው ባለፈ ስር ድረስ ገብተው በትክክል ታዝበው ያዩትንና ያገኙትን ሪፖርት ያቀርባሉ የሚለው ነገር አቅም ይጠይቃል። እንግዲህ አስቀድሜ እንዳልኩሽ እንዲህ አይነቱ ጉዳይ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሰሚነታቸው እንዳይኖራቸው ተደርገው ረጅም ጊዜ ቆይተዋል። በዚያ ውስጥ ተሳትፏቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል።
በአሁኑ ምርጫ ከዚህ ቀደሞቹ በተለየ ‹‹አገር መስርተዋል›› ማለት የሚያስችል ስራ ሰርተዋል። ለምሳሌ በአሁኑ ምርጫ ከሌላው ጊዜ በተለየ የውጭ ታዛቢዎች አለመኖራቸውና በዚህ ወሳኝ ጊዜ ድርጅቶቹ ከ45ሺ በላይ የሚሆኑ ሰራተኞቻቸውን በምርጫ ትምህርት ላይ ተሰማርተው ሰርተዋል፤ ታዛቢም ሆነዋል። ይህም ማለት ፍፁም የሆነ ሥራ ሰርተዋል ማለት አይደለም። ግን ካየነው በአሁኑ ምርጫ የተሳተፈው ሰው ታዛቢም ሆነው ከዚያ በኋላም አገረ-መንግስት እንዲፀና ህዝቡም ከተለያየ ችግርና ስቃይ ከሚመጣ ብጥብጥ ለመታደግ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። ምርጫን ተከትሎ ከሚመጣ ብጥብጥ ለመታደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ከዚያም ባለፈ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲ ጠርተው እውቅና ሰጥተዋል። በሰላም በመጠናቀቁ ሁላችሁም አሸናፊ ናችሁ በማለት አመስግነዋል። በአጠቃላይ ምርጫውን ለየት የሚያደርገው በሰላማዊ መንገድ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በሰፊው መስራታቸው ነው።
አዲስ ዘመን፡- በምርጫ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ዝግጁ ያለመሆን ይስተዋላል፤ ከዚህ አኳያ ያለውን ችግር በቀጣዩ ምርጫ እንዳይደገም በምክር ቤቱ ምን ታስቧል?
አቶ ሄኖክ፡- አሁን ያነሳሽው ችግር በተጨባጭ የሚታይ ነው። በሲቪል ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በምርጫ ሃሳብ ሂደት ውስጥ በአገራችን ያለው ሁኔታ የአንድ ወቅት ስራ ነው የሚመስለው። እንዲህ አይነቱን ችግር ለመፍታት በቀጣይ በትኩረት መሰራት አለበት። አስቀድሞ ሕዝቦችን የማስተማር፣ ስለምርጫ የማወያየት ይገባል። ይሁንና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ማህበራቱ ምርጫ ሲደርስ ነው በደንብ የሚንቀሳቀሱት። ማን ምን አይነት ሃሳብ እንዳላቸው ሳናውቅ ነው ወደ ምርጫ የሚገባው። ስለዚህ ይህ አጠቃላይ ችግር ነው። እንዲህ ያሉ ነገሮች ለተሳትፎ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለምርጫ ሂደቱ በቋሚነት መሰራት እንዳለበት እናምናለን። እንዲህ ሲሆን ወደሚፈለገው ውጤት እንመጣለን። በአጠቃላይ የምርጫ ስራ የዘመቻ ስራ ሳይሆን ሁልጊዜ መሰራት ያለበት ነው። ሁልጊዜ ማህበረሰብ መንቃት፣ መረጃ ማግኘት፣ ማሰብ፣ መከራከርና መወያየት ይገባል። ይህ ሲሆን ውጤት ይመጣል፣ ያማረ ምርጫ ይኖራል፣ አገርን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል።
ብዙ ጊዜ ምርጫን ተከትሎ ብጥብጥ፣ ሁከት የሚኖረው አስቀድሞ ግንዛቤ ማስጨበጥ ባለመቻሉ ነው። ማህበረሰቡ ውዥንብር ውስጥ ይገባል፤ ያን ጊዜ ስሜት ይነዳናል። ከመጀመሪያ ጀምሮ ያየናቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሕዝቡ እያወቃቸው፣ ሃሳባቸውን እየተገነዘበ ቢሄድ ጠቃሚ ነው። ለማገዝም ሁልጊዜ ዝግጁ ነን። አንዳንዶች ‹‹የምርጫ ሥራ ሱሪ በአንገት ነው›› የሚሉት እውነታቸውን ነው። ለሲቪል ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በአንድ ወርና በ15 ቀናት በርካታ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ሲያስተዋውቁ ሕዝቡ ለመለየት ያስቸግረዋልና መሻሻል ይኖርበታል ባይ ነን።
አዲስ ዘመን፡- ከዲፕሎማሲ አኳያና በአገር ላይ ስጋት የሚደቅኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ምን አይነት ስራዎችን ነው የምታከናውኑት?
አቶ ሄኖክ፡- ምክር ቤቱ አዲስ እንደመሆኑ በዚህ ጉዳይ ብዙ አልሰራንም። ግን ከተመሰረተ ጀምሮ ባለን አቅም ዲፕሎማሲውን፣ በተለይም ትኩረት የምናደርገው ሕዝባችን እንደመሆኑ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ነገር ስለሚያሳስበን ሃሳባችንንም እንገልጻለን። በተለይም የወቅቱ ሁኔታ ላይ መግለጫዎች አውጥተናል፣ ውይይቶች አካሂደናል። ግጭቶችን ለማብረድ መንግስት እስከመጨረሻ የሰላም አማራጮችን እንዲጠቀም ምክረ-ሃሳብ ሰጥተናል። ሕዝቡ እንዲረዳዳ ተደርጓል። በውስጥ ጉዳዮቻችን በቂ መረጃ ሳይኖራቸው የሚደረገውን ያልተገባ የውጭ ጫና ተቃውመናል።
በአሜሪካ መንግስት ሊጸድቅ የቀረበው ኤች አር 6600ን የምናየው ከሕዝቡ አኳያ ነው። በአሜሪካ መንግስት በኩል ዴሞክራሲና ሰላም ለማስፈን የረቀቁ ሕጎች ቢገለፅም ይህ ህግ ከታሰበለት አላማ ወጥቶ ሕዝባችን ላይ ጫና ሊፈጥር ይችላል ብለን ገምግመናል፤ ያንጸባረቅነውም ይህንኑ ነው። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ህጎቹ ቢተገበሩ የበለጠ ያባብሱታል እንጂ መፍትሄ አይሰጡም የሚል አቋም አለን። ሌሎች መፍትሄዎችም መከተል ይገባል ብለናል። አሁን የብሄራዊ መግባባት ኮሚሽን ተቋቁሟል። እገዛ ማድረግ ይቻላል፤ በጎ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ የሚል እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ አንዴ በጎሳ፣ ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ስም በርካታ ችግሮች ሲፈጠሩ ይታያል፤ ሕዝቡ ተቻችሎ የመኖር እሴትን እንዲያጎለብት፣ አብሮነትን ለማስቀጠል ድርጅቶቹ ምን ያህል ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል?
አቶ ሄኖክ፡- ለረጅም ጊዜ የሰላም ማስፈን፣ የግጭት አፈታት ስራዎችን መስራት ተገድቦ ነበር። በፊት ባህላዊ እሴቶችን የማጎልበት ስራ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰፊው ይሰሩ ነበር። ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር እንዲህ አይነት ስራ የሚሰሩ አልነበሩም። አሁን ማህበረሰቡ በሰላም ጉዳይ ካልተወያየና ካልሰራ ውጤት አይኖርም። ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህገ-መንግስቱ በሰጣቸው መብት መሰረት ተደራጅተው በእነዚህ ጉዳዩች ላይ መስራት አለባቸው። ለዘመናት ተደራጅተው ያንን መስራት አልቻሉም። እንደ አገር እሴቶቻችንን እያጣናቸው መጥተናል። የሃይማኖታዊ በጎ እሴቶቻችንን አውጥተን፣ አልምተን ባለመጠቀማችን አሁን የሚታዩ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል።
አሁንም ግን ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰላምን ነው የሚሰብኩት፣ የቆሙትም ለእዛ ነው፣ የሕዝብ ደህንነትም ያሳስባቸዋል። በመሆኑም በሰፊው ወደ ስራ መግባት አለባቸው። ያም ሆኖ ውጤት በአንድ ጊዜ የሚመጣ ባለመሆኑ በጣም ረጅም ጣልቃ ገብነት የሚፈልጉ ናቸው። የአገርን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ያስፈልጋል። ይህ የሁሉም ስራ ነው። በተለይም ሁላችንም እርስ በእርስ ተጋምደን የምንኖር በመሆኑ የተወሰኑ ማስተካከያዎች ከተደረጉና ስራዎች ከተሰሩ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ አይሆኑም። ከዚህ አኳያ ወቅታዊ ጉዳዮች ሲመጡ እንደ ምክር ቤት ቅድሚያ እንሰጣለን። አሁንም የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን ለማገዝ፣ ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰላም ለማስፈን ተቀራርቦ በመስራት ቅድሚያ ሰጥተን እየሰራን ነው። አሁን የተጀመሩ ጥረቶች አሉ። በቀጣይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት አቅጣጫ አስቀምጠናል። ምክንያቱም ግጭት ሲመጣ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ስለሚገባ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የምክክር ኮሚሽኑን የምታግዙት በምን መንገድ ነው፤ የያዛችሁት አቅጣጫ አለ?
አቶ ሄኖክ፡- ኮሚሽኑን ለማገዝ ጥርት ባለ መንገድ የኮሚሽኑን ሂደትና ሃሳብ መረዳት ቀዳሚ ተግባር ነው ያደረግነው። ከኮሚሽነሮቹ ጋር ተገናኝተን ምን ደረጃ እንዳሉ፣ ምን ሃሳብ እንዳላቸው ተወያይተናል። በቀጣይም ሲቪል ማሕበራት ድርጅቶች ምን አይነት ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ ስብሰባ በማካሄድ ውይይት አድርገናል። ግንኙነቱ ቀጣይነት ይኖረዋል። ሊያማክር፣ ሊገመግም፣ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ሚና እና ሂደቱንም የሚመረምር ቡድን እያቋቋምን እንገኛለን። የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እናካሂዳለን። የታሰበው ነገር እንዲሳካ ሚናችንን ለመወጣት እየተንቀሳቀስን ነው። ሚናችንን በመወጣት የምንሳተፍበት ሁኔታ መኖሩን ተገንዝበናል።
የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ መዋቅር አለ። መዋቅሩን በትክክል ማስተባበር፣ ማቀናጀትና የጠራ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ ከተቻለ ትልቅ እገዛ ነው ብለን እናምናለን። ማህበራቱ ገለልተኛ የሆኑና ምንም አይነት ውግንናም የሌላቸው በመሆናቸው ከብሔራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሃሳብ ጋር የሚሄድ ነው። በጣም ቁልፍ ባለድርሻ አካላት ነው የምንሆነው።
አዲስ ዘመን:- የምታመነጯቸው ሃሳቦች ለፖሊሲ ግብዓት ጠቃሚ መሆናቸው ይታመናል። የምታቀርቧቸው ምክረ ሃሳቦችን መንግስት ይቀበላቸዋል? እንደመፍትሄስ ጥቅም ላይ ይውላሉ ?
አቶ ሄኖክ፡- ይህንን ከብዙ አቅጣጫ መመልከት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ ጥናቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚደረጉ ምርምሮችን ማየት ያስፈልጋል። ከጥናቱም ባሻገር ማህበረሰቡም፣ መንግስትም ተጠቅሞባቸዋል ወይ? ይህ ባህልስ አለ? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በርካታ ጥናቶች ይደረጋሉ፤ ግን ጥቅም ላይ አይውሉም። ብዙዎቹ የሼልፍ ማድመቂያ ናቸው። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አሁን እያደረግን ያለነው እነዚህን እውቀቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መምከር ነው። ለዚህ ግን ማለማመድም ይገባል። እውቀቱን ይዞ የሚሞግትም ያስፈልጋል። ከምክር ቤት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ጥያቄ አቅርበን ተቀብለውናል። በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎ እንዲኖር ፈቃደኛ ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ጠይቀውን ተሳታፊዎችን ስም ዝርዝር ልከናል። ፖሊሲ ሲወጣ ሌሎች ተግባራትም ሲከናወኑ የመገናኛ መንገዶች ያስፈልጋሉ።
ከእዚህ ባለፈ ግን በሚወጡ አዋጆችም የነቃ ተሳትፎ አድርገናል። የምክክር ኮሚሽን ረቂቅ አዋጅ ሃሳቦቻችንን ተካትተዋል። ይህ መዳበር አለበት። እንደምናስበው ስኬታማ ባይሆንም ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። የተሰጠንም ቦታ ትልቅ ነው። እንደሲቪል ማህበራት ድርጅቶች መሳተፍ ብቻ ሳይሆን ተደማጭነትም አግኝተናል፤ ይህ ለምንሰራው ስራ ሞራል ነው። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 50 የሚደርሱ የሲቪል ማህበራት በረቂቅ አዋጆች ለማወያየት እድል አግኝተዋል። በጠቅላይ አቃቢ ህግ በኩል አፈጻጸማቸውን አብረን ገምግመናል። ሃሳባችንን ሰጥተናል፤ ይህ ጅምር ነው፤ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
እንደሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሕዝብ ጉዳይ ያሳስበናል። ልዩነቶች ሃሳቦች ወደ ጠረጴዛ መጥተው በሰላማዊ ሁኔታ የመፍታት ባህል ቢዳብር መልካም ነው። ልዩነቶች የሚፈቱበት መንገድ ሃይልና ጥፋት የተሞላበት ነው። በዚህ በጣም እናዝናለን። በየቀኑ በተለያየ መንገድ መረጃው ይደርሰናል። ዋጋ ያለው ሰው ልጅ እዚህም እዚያም ሕይወት እያጣን ነው፣ ሰው እየተፈናቀለና ንብረቶች እየወደሙ ይገኛሉ። እንደ አገር የመቀጠል ጉዳይ በጣም ያሳስበናል። የሃሳብ ልዩነቶችን ሰከን ባለ መንገድ በውይይት መፍታት ይገባል። ያለው አካሄድ መለወጥ ይገባዋል። ይህ ነገር ተለውጦ ማየት ስለምንፈልግ በዚህ ላይ መስራት አለብን። በፖለቲካ፣ በሃሳብ መሸናነፍ ያለ መሆኑን ሁሉም ማመን አለበት፣ ሰከን ማለት ያስፈልጋል። ዛሬ ከተሸነፈ አሻሽሎ ነገ አሸንፋለሁ በሚል በሰላማዊ ትግል ማመን ይገባል።
አዲስ ዘመን:- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሄኖክ፡- እኔም ለተሰጠኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም