በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ከህብረተሰብ ተሳትፎ ባለሙያዎች፣ ከህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችና ከተለያዩ ሚዲያዎች የተውጣጡ ጋዜጠኞች በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ አርሶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከየካቲት 13 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት በተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው ሥራ ውጤት እያመጣ እንደሆነ ተመልክተው ነበር።
በጉብኝቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ባለመሰራቱ ምክንያት በበረሃነት ተጠቅቶ በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ የተነሳ ሣርና ውሃ በማጣት በርካታ ከብቶች ይሞቱበት በነበር አካባቢ ላይ በተሰራ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ አካባቢው አገግሞ ኗሪዎች ለከብቶቻቸው ሣርና ውሃ ማግኘት መቻላቸውን ሲገልጹ ተስተውሏል። በሌላ በኩል አሁን ባለንበት የበልግ ወቅት በሀገሪቱ በርካታ አካባቢዎች የተሻለ የምርት መጠን ለማግኘት ታቅዶ በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ዝግጅት ክፍላችን በግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ አለማየሁ ጥላሁንን የበልግ ወቅት የሥራ እንቅስቃሴዎችንና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በተመለከተ አናግሯቸው ተከታዮቹን ነጥቦች አጠናቅሯል።
የበልግ ወቅት ሥራ እንቅስቃሴ የተሰጠው ትኩረት
የበልግ ወቅት ሥራ እንቅስቃሴ አንዱ የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ አካል ነው። ባለፉት ጊዜያት ለበልግ ሥራ የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎቹ የመኸርና የበጋ ሥራዎች ጋር ሲነጻጸር እኩል ትኩረት እንዳልተሰጠው ተገምግሞ ዘንድሮ ልዩ ትኩረት መሰጠት አለበት ተብሎ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚህ ዓመት በበልግ እርሻ ለመሸፈን የታቀደው የመሬት ስፋት በ 2011 ዓ.ም. ከ ሁለት ነጥብ አንድ ሄክታር ያላነሰ መሬት በበልግ እርሻ ለማልማት ዕቅድ ተይዟል።በበልግ ወቅት የሚገኘው ምርት ከአጠቃላይ የክልሎች ምርት አንጻር ያለው ድርሻ በበልግ ወቅት ከ60 በመቶ የማያንስ ሲሆን፤ አጠቃላይ የበልግ እርሻ የሚሸፍነው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ነው። ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ከአምስት እስከ ሰላሳ በመቶውን ይሸፍናሉ።
የበልግ ምርት የሚገኝባቸው አካባቢዎች
በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አካባቢዎች፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ፣ ደቡብ ወሎ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢና ሰሜን ሸዋ ዞኖች፤ በደቡብ ክልል ከፋ፣ ቤንች ማጂ፣ ሸካ፣ ዳውሮ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ጎፋ ፣ ሲዳማ፣ ጌዲዮ ዞኖችና የቄዳና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ፣ ቦረና፣ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሀረርጌ የበልግ አብቃዮች ናቸው።
የበልግ ምርት ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ሲሰላ፤ እንደ ማእከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን መረጃ የበልግ ምርት እስካሁን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ምርት ከ ዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ አለው፤ ይህ በጣም አነስተኛ ነው። በበልግ ወቅት የሚገኘው የምርት መጠን ባለፉት ጊዜያት በዋና ዋና ሰብሎች በኩንታል በዓመት ከ 18 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ሲገኝ ነበር። ዘንድሮ እስከ 29 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ በእቅድ ተይዟል።
ለዘንድሮ የበልግ ወቅት የተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች
በዘንድሮው የበልግ ወቅት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በስፋት ተሰርተዋል። ይህን የሚከታተል በኤክስቴንሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ በየጊዜው ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከወትሮ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት በመኸርና በክረምት በአየር መዛባት የሚቀንሰውን የምርት መጠን ለማካካስ እየተሰራ ነው።
የታቀደውን ያህል ምርት ለማግኘት በበልግ ወቅት የሚኖርን እርጥበትና ዝናብ በአግባቡ መጠቀም ስለሚያስፈልግ ለአርሶ አደሮች ምክርና ስልጠና በተለያዩ መንገዶች የማድረስ ሥራ እየተሰራ ነው። ክትትልና ድጋፍን በማጠናከር በተለይ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦትን ከወትሮ በተሻለ ሁኔታ የማቅረብና ውጤታማ እንዲሆኑ የመርዳት ሥራ በመሰራት ላይ ነው። በሌላ በኩል በአጭር ጊዜ ሊደርሱ የሚችሉ ሰብሎችንና ለእንስሳት የሚያገለግሉ መኖዎችን ማልማት እንዲቻል ጥረት እየተደረገ ነው። በተጨማሪም ምርጥ ዘርን በእጥፍ የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። በተለይ በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የሰብል ዓይነቶችን በጥራትና በስፋት እንዲመረቱ ትልቅ እገዛ እየተደረገ ነው።
ይኖራል ተብሎ የሚገመተው የዝናብ መጠን
ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በሰጠው ቅድመ ትንበያ ለበልግ ምርት ተስማሚ የሚሆን ዝናብ ይኖራል የሚል ግምት አለ። ምናልባት እንደተተነበየው ባይሆንና የአየር ንብረት ለውጥ ቢያጋጥም ውሃን የማስተዳደርና የማቆር ፣በተለይ ደግሞ በእርጥበት የመጠቀምና ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን የመዝራት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት፤ በየጊዜው የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲን መረጃ በመከታተል ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ለአርሶ አደሮች መረጃ እየተሰጠ ነው።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ያሉበት ደረጃ
የዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በጥሩ እየተከናወነ ነው ፤ ሥራው አልተቋረጠም። በየጊዜው ውጤት እየታየበት ያለ ስለሆነ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የልማት ዕቅድ የተያዘላቸው 7ሺ226 ተፋሰሶች ተለይተው የልማት ዕቅድ ተዘጋጅቶላቸዋል።በልማት ሥራው የተሳተፈ የሰው ኃይል ብዛት ከ 13 ሚሊዮን በላይ ሆኗል። በተጨባጭ የለሙ ተፋሰሶች ከታቀደው 7ሺ200 በማለፍ 7ሺ600 በላይ ማልማት ተችሏል።
የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች
15ሺ 111 ባለሙያዎች በተፋሰስ ልማቱ ቅየሳ ዙሪያ ስልጠና ወስደዋል። ከ299ሺ በላይ ቀያሽ አርሶ አደሮችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የክልሎች ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ በሀገር ደረጃ በተሰራው ሥራ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና በተፋሰስ ልማት እውቅና ማግኘቷ በህብረተሰቡ ውስጥ መነሳሳትን ስለፈጠረ ሁሉም ክልሎች እንደባህል አድርገው ጠቀሜታውን በመረዳት በየዓመቱ ለሰላሳ ቀናት ሰፊ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በትግራይ ክልል ከየካቲት አንድ ጀምሮ ለ30ቀናት የተቀሩት ክልሎች ደግሞ ከጥር አንድ ጀምሮ እንዲሁ ለ30 ቀናት በስፋት ተካሂዷል።
ለአርሶ አደሮችና ለግብርና ባለሙያዎች የተላለፈ መልዕክት
በመኸር ለማግኘት አቅደን ሙሉ ለሙሉ ያላሳካነውን 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማካካስ በዚህ በበልግ ወቅት የምናደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ስለዚህ አርሶ አደሮቻችን ለበልግ ሥራ እንቅስቃሴ ለየት ያለ ትኩረት በመስጠት ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ የሚያወጣቸውን መረጃዎች በመከታተል የእርሻ ሥራቸው ላይ እንዲተጉ፤ የልማት ጣቢያ ሠራተኞቻችና የግብርና ባለሙያዎች ደግሞ የክትትልና ድጋፍ ሥራዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ትኩረት እንዲደረግ ግብርና ሚኒስቴር ጥሪውን ያስተላልፋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011
የትናየት ፈሩ