እንኳን ለሰው ለእንስሳ እሚራራው፤ በስህተት ክበድ (እርጉዝ) በግ ካረደ ንስሃ እሚገባው፤ ሐቀኛና ባለ ኃይማኖቱ፤ ባይኖረውም ማማረር እማይወደው፤ ባለው ነገር ተመስገን ብሎ የሚኖረው፤ ካለው ደግሞ ተቋርሶ እሚበላው፤ አደራ ብትሰጠው አደራ ማይበላው፤ ‘’እውነቴን ነው ስልህ’’ ካለ ደግመህ እማታስምለው፤ ልበ ሙሉ፤ ቀጥተኛው፤ ኩርፊያውንም ደስታውንም ፊቱ ላይ የምታውቅበት፤ ወድቀህ ልትታሽ ቤቱ ብትሔድ ‘’እኔን ለኔ ያርገው’’ እያለ ቁስልህን እሚያሽልህ፤ እምነት አክባሪው ህዝቤ፤ እንግዳ መጣ ብሎ አልጋውን ለቆ ዝቅ ብሎ እግር አጥቦ የሚያስተኛ፤ ‘’እፈልግሃለሁ’’ ብለህ ተቆጥተህ ቤቱ ብትመጣ ‘’እረ መጀመሪያ እህል ካፍህ አርግ’’ ብሎ ገበታ አቅራቢው፣ ባላገሩ ገጠሬው ወገኔ ነው።
ባላገሩ ዝክሩም ምክሩም በዝናብ አብቅሎ፣ በፀሐይ አብስሎ፣ በነፋስ አድርቆ፣… ከሚመግበው ከፈጣሪው ጋር ነው። ፈጣሪውን አምኖ በሰኔ ከጎተራው ዘሩን አውጥቶ ይዘራል። ፈጣሪም “የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል እምነት ቢኖርህ ያልከው ይሆንልሃል” ብሎ በገባው ቃል መሰረት እርሱን አምኖ ከጎተራው አውጥቶ ዘሩን በማሳው ለበተነው አርሶ አደር የምህረት ዝናቡን ይልካል። ቃል ኪዳኑንም አያጓድልበትም። ባላገሩም ቢደላውም ቢከፋውም ሲነጋ ሲመሽ “ተመስገን” እያለ የፈጣሪውን ቸርነት ያመሰግናል። ሲከፋው “አንተ ታውቃለህ” ብሎ ለፈጣሪው አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ጣቱን በማንም ላይ አይቀስርም።
ታዲያ ይህ ኩሩና ኃይማኖት ወገኔ በሰኔና ሐምሌ አንደፋርሶ አርሶ፣ በነሃሴና መስከረም አሽኮትኩቶ አርሞ፣ በህዳርና ታህሳስ አበራይቶ ወቅቶ ያመረተውን ምርት “ይሄ ከኔ ወገን ነው፤ ያ ከኔ ወገን አይደለም” ሳይል ምርቱን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም አድሎ ገበያ አውጥቶ ያቀርባል። እርሱ ተጎሳቁሎ አምርቶ ሌላውን አጥግቦ ያሳድራል።
ነገር ግን ይህ ኩሩና ባለማተብ ወገኔ ጫማ ሳይለብስ እንቅፋት እየመታውና እሾህ እየወጋው ባስተማረ፤ በመርፌ የተጠቀመ (የተጣጣፈ) ልብስ ለብሶ እየሄደ “ፋሽን” እያለበሰ ባስተማረ፤ ኩርማን እንጀራ እና እፍኝ ቆሎ በልቶ እያደረ አጥግቦ ሳይማር ላስተማረ ውለታው ሲመለስለት ተወልዶ፣ ተዋልዶ፣ ታጋብቶና ታጋምዶ በሚኖርበት ቀየው ሲሳደድ፣ ሲፈናቀል፣ ሲገደል… ማየት ቅስም ይሰብራል። ከእጁ እሸት በልቶ፣ ከማጀቱ እርጎ ጠጥቶ… አድጎ በእርሱ ላይ ሰይፍ ማንሳትስ ምን አይነት የጭካኔ ጥግ ነው። ግፉስ ነገ ምን ያመጣብን ይሆን የሚለውን ሳስበው ጭንቅ ጥብብ ይለኛል።
አርሶ አደሩ ሳይማር አፈር ገፊ ሆኖ መቅረቱ ቢያንገበግበውም፤ ልጆቹ ነገ የእርሱ እጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው እና ተምረው ተመራምረው ችግሩን እንዲቀርፉለት እንዲሁም ለአገር ለወገን አለኝታ እንዲሆኑ ነው ሳይማር ያስተማረው። ነገር ግን አርሶ አደሩ “ቀለም ቆጥረው ነገ ለአገራቸው ብሎም ለወገናቸው አለኝታና ጠበቃ ይሆናሉ” ብሎ ሳይማር ያስተማራቸው ልጆቹ በጎነጎኑት ሴራ ከቀየው ሲፈናቀልና ሲገደል ይስተዋላል። ደጉ ወገኔ አምርቶ አገርን አጥግቦ እንዳላሳደረ ተፈናቅሎ በሚገኝባቸው የመጠለያ ጣቢያዎች ከዚህ ግባ የሚባል ሰባዊ ድጋፍ አጥቶ ሲራቆት ማየት ደግሞ በጣም ያማል።
ያ ባላገሩ ኩሩ ወገኔ አርሶና አርብቶ አገርን ከማብላት ውጭ የፖለቲካ ዱካውን አያውቀውም። ነገር ግን ሳይማር ያስተማራቸው ልጆቹ አንዴ የብሄር ሌላ ጊዜ የኃይማኖት፣ የቋንቋ ወዘተ. የግጭትና የልዩነት ካርድ እየመዘዙ ደጉን ወገኔን በማያውቀው ተወልዶ ባደገበት አገሩ መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተውት ይገኛሉ። እንዲሁም አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍሰው ነጻነቷን ጠብቀውና ዳር ድንበሯን አስከብረው ያቆያትን አገር፤ ዛሬ ላይ ተምረው ያልተማሩ ማህይማንና ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ፖለቲከኞች ህብረተሰቡ ለእልፍ ዘመናት የገነባውን የአንድነትና የመተባበር ድልድይ በመናድ አገሪቱን ለማፈራረስ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር እየሰሩ ይገኛሉ። ለዚህም ከሰሞኑ በአገሪቱ የሚስተዋለው በኃይማኖት ሽፋን ለዘመናት ተከባብሮ በሰላም የኖረውን ህዝብ እርስ በእርስ ለማባለት እየተደረገ ያለው የሽብር ተግባር አንዱ ማሳያ ነው።
እንደሚገባኝ፣ መማር የመጀመሪያው የባህሪ ለውጥ ማምጣት ነው። ከፍ ሲል ደግሞ የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን ገልጦ፣ ለችግሮች የመፍትሄ ሃሳብ በማፍለቅ ለአገርና ለወገን አለኝታ መሆን ነው። በዓለም ላይ በስልጣኔና በቴክኖሎጂ ማማ ላይ የሚገኙ አገራት ዜጎቻቸው ተምረው ተመራምረው ለችግሮቻቸው መፍትሄ በማበጀታቸው ነው እንደ ህዝብ ከፍ ያሉት። ነገር ግን በአገራችን ማወቅ ወይም መማር “መሰይጠን” ሆኖብን የተማረው ክፍል ሴራ እየጎነጎነ ለዘመናት ተከባብሮና ተዋዶ በሚኖረው ህዝብ ላይ የጥላቻና የመለያየት ግንብ ሲገነባ ይስተዋላል።
ተማርን የሚለው አካል፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በበሬ የሚያርሰውን አርሶ አደር ባላባት አገር “እስኪ የአርሶ አደሩን ሕይወት እናቅል” ከማለት እና ችግር ፈች ምርምር አድርጎ የወገኑን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ በሴራ ህዝብን ከህዝብ ሲለያይ ነው የምናየው። ከዚህ አኳያ ተምረናል ብለን የምናስብ ሰዎች በተማርነው ትምህርት የወገናችን ችግር መቅረፍ ቢሳነን እንኳን የችግሩ ምንጭ ግን አንሁንበት።
በአንጻሩ የመንግስት ቀዳሚና በህገ መንግስቱ የተሰጠው ዋነኛ ኃላፊነቱ ሕግን በማስከበር የህብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው። በመሆኑም መንግስት በታሪክ አጋጣሚ እጁ ላይ የወደቀችን አገር እንደአባቶቻችን ነጻነቷን ጠብቆና ዳር ድንበሯን አስከብሮ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይኖርበታል። ስለዚህ መንግስት የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን ሕግን በማስከበር የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራ ይገባል። ተልዕኮ ባላቸው ግለሰቦች በኅብረተሰቡ መካከል ሊቀሰቅሱ የሚታሰቡ ግጭቶችን ቀድሞ በማምከን የኅብረተሰቡን ለዘመናት ተከባብሮ የመኖር እሴት ሊጠብቅ ይገባል።
ሌላው መርከቧ ከሰመጠች የሚተርፍ ሰው እንደሌለ ኅብረተሰቡ ልብ ሊል ይገባል። ከዚህ አንጻር ሁሉም ዜጋ ማንንም ሳይጠብቅ የሚጠበቅበትን ለአገሩ የሚበጀውን ነገር ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ጥሩ ለመሥራት አቅም ባይፈቅድ እንኳን ለክፉ እና አገር ለሚያፈርስ አጀንዳ ተባባሪ ከመሆን መቆጠብ ይገባል። በጥቅሉ ያለ ሀጥያቱ በማያውቀው የገፈቱ ቀማሽ የሆነው ደጉና ኩሩው ባላገሩ ወገኔ ግፍና በደሉ ይበቃዋል። በሰላም ከቀየው ወጥቶ የመግባት ጥያቄው ሳይውል ሳያድር ተመልሶለት ባላገሩ እፎይ ብሎ ይኑር በአገሩ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም