ክስተቶች የበዙበት ሳምንትን ነው ያሳለፍነው። ከጎንደሩ ክስተት ጀምሮ ወራቤ ላይ የተፈጸመውን አስከትሎ አዲስ አበባ የደረሰው ሁኔታ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ነበር። እንዲሁም ልብ የሚያደሙ እና አንገትን የሚያስደፉ ነገሮች ለበዙባት አገር የሰሞኑ ክስተት ደግሞ አዲስ ሀዘን ነበር። ብዙሃን ሞተዋል፤ የተቀደሱ የአምልኮ ስፍራዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ብዙ ንብረትም ወድሟል። የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ዙሪያ የተጣራ ማብራሪያ እስኪያቀርቡ ድረስ ጉዳዩ ይቆየንና በሰሞኑ ክስተት መሀል ያየናቸውን ብርሃናዊ ነገሮች አጉልተን እናውራ፡፡
በኢድ እለት የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሐውልት አካባቢ ትርምስ ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ወቅትም ጥቂት ግለሰቦች ስሜታዊ ሆነው አንዳንድ ያልተገቡ ተግባራትን ሲከውኑ አይተናል። በዚህ ትርምስ መሀል ግን አንድ ወንድም ህዝብን ሲያረጋጋ እና ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ ለማድረግ ሲጥር ታይቷል። በመሰረቱ ልናውቀው የሚገባ አንድ ነገር አለ። ግለሰቡ ያደረገው ነገር አዲስ አይደለም። ተአምርም አይደለም። እንደ አንድ ጥሩ አማኝ እና እንደ አንድ ሰላም ወዳድ ዜጋ ሊያደርግ የሚጠበቅበትን ነገር ነው ያደረገው። ለአንድ ሙስሊም ይህን ማድረግ የዘወትር ተግባሩ ነው ተብሎም ይታመናል። አስተምህሮውም እንደዚያ ነው። ስለዚህ ያደረገው በተለየ ሁኔታ ሊደነቅ የሚገባው አልነበረም፡፡
ይህን ሰው የምናደንቀው ግን ከምንኖርበት ዘመን አንጻር ነው። ያለፉት ጥቂት አመታት አገራችን መካሪ ሽማግሌዎቿ ያለቁባት እስክትመስል ድረስ በየቦታው ሁከት የሚፈጠርባት አገር ሆና ከርማለች። የዚህ መንስኤው ሁላችንም ከደረጃ በመውረዳችን ነው። የሰላም ሀይል የሚባል ተመናምኖ ሁሉም ወገን ወገኑን መርጦ ይዞ የሚፋጅባት አገር የሆነችው እንደዚህ ወንድም አይነት ተረጋጉ የሚል ሰው በመጥፋቱ ነው። ያሉን የሃይማኖት አባቶች በአደባባይ በቃል ከመገዘት እና ከማሳሰብ በላይ በቦታው ተገኝተው እንደዚህ እንደ ወንድማችን ወዲህ ወዲያ ተሯሩጠው እና ተናንቀው ሰላምን ማውረድ የሚችሉበት አቅም የላቸውም። አቅም ያለው በበኩሉ አንቂ እና አደራጅ ሆኖ ለሁለት እና ለብጥብጥ ሲያሰማራ ነው የሚውለው። ታዲያ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ በቦታው ላይ ተገኝቶ፤ ወዲህ ወዲያ ተሯሩጦ አደብ ግዙ ያለን ሰው ማመስገናችን በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡
ልብ አርጉ፤ ግለሰቡ ያደረገው የሚጠበቅበትን ነገር ነው። ነገር ግን በየቦታው ሁከት የበዛው ልክ እንደሱ የሚጠበቅባቸውን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ባለመኖራቸው ነው። እንዲያውም ለዚህ የሚስማማ አባባል አለ። ተናጋሪው ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው ይባላል። “The world suffers a lot. Not because of the violence of bad people but because of the silence of good people.” ይላል አባባሉ። ትርጓሜውም “ዓለም እየተሰቃች ያለችው በክፉዎች አመጽ ሳይሆን በመልካም ሰዎች ዝምታ ነው” እንደማለት ነው። እውነት ነው። በመልካሞች ዝምታ የተነሳ አመጸኞች ጉልበተኛ ሆነዋል። ይህ ወንድማችን ከመልካም ሰዎች አንዱ ነው። እሱ ዝም ቢል ኖሮ ሁከት እየፈጠሩ ለነበሩ ምንኛ ጉልበት በሆናቸው ነበር:: ነገር ግን ዝም አላለም። የአቅሙን አደረገ። ሁከቱ እንዳይስፋፋ የድርሻውን ተወጣ። ለዚህ ተግባሩ ደግሞ አክብሮት ይገባዋል። ለከርሞው ሰላሟ እንዲሰፍን ከፈለግን በየቦታው እንደሱ ያሉ መልካም ሰዎች ዝምታቸውን እንዲሰብሩ እና ከታዛቢነት እንዲወጡ ማድረግ አለብን። ያኔ ነው አገር ሰላም የምትሆነው፡፡
ሌላኛዋ መልካም እህት ደግሞ በወቅቱ ተቃውሞ እያሰሙ የነበሩ ወጣቶች ሁከትን ሳይቀላቅሉ ተቃውሞአቸውን እንዲያሰሙ ስትወተውት የነበረች ናት። ይህ ደግሞ ስልጣኔ ነው። መቃወም መብት ነው። ሁከት መፍጠር ግን መብት አይደለም። እኛ ጋር ብዙውን ጊዜ ሁለቱ ይደባለቃሉ። ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ወደ አመጽ ለመሻገር ብዙ አይፈጅበትም። ለብጥብጥ ቅርብ የሆንን ሰዎች ብዙ ነን። እርግጥ ይህ የሚሆነውና ብዙው ሰው ወደ ሁከት የሚቻኮለው ለሰልፍ የወጣበትን ጉዳይ ምንነት እና አላማ በቅጡ ስለማያውቀው ነው። ሁሉም የየራሱ ብሶት ይዞ ይወጣል። ብሶቱ የጸናበት ሰልፉን ወደ ሁከት ይለውጠዋል። ሁከት ደግሞ እንደ ሰደድ እሳት ነው። ቶሎ ይስፋፋል። በተለይም እኩይ አላማ ይዞ የሚሰራበት ሰው ሲገኝ በቶሎ ይቀጣጠላል። ያቺ እህት ይህን የተረዳች ነች። ከቤቷ የወጣችበትን አላማ ታውቀዋለች። የምትቃወመውን የምትቃወምበትን ምክንያት እና የምትቃወምበትን መንገድ አልረሳችም። ስለዚህም “የሰው ንብረት አትንኩ የፈጣሪን ስም ብቻ ጥሩ” እያለች አብረዋት ያሉት ሰዎች ያለ ምንም ትርምስ ተቃውሞአቸውን እንዲያሰሙ ለማድረግ የአቅሟን ስትጥር ነበር። እንዲህ ያሉ የሰላማዊ ትግል የገባቸው ሰዎች በአገሪቱ መበርከት አለባቸው። እንዲህ ያሉት ሲበዙ ነው ዛሬ በየስርቻው ተወሽቀው የወንበዴ ስራ እየሰሩ ነጻ አውጪ ነን የሚሉ ወሮበሎች ሊጠፉ የሚችሉት፡፡
ሶስተኛዋ ደግሞ ህግ አስከባሪ ናት። በእለቱ ለመደበኛ ተልእኮ የተሰማራች ነበረች። ከተፈጠረው ትርምስ በኋላ ብዙ ህጻናት ከወላጆቻቸው ተጠፋፍተው ብዙ ጭንቀት ተከስቶ ነበር። በዚያ ሰዓት ግን እሷ አንዲትን ህጻን አቅፋ እያረጋጋች፤ ስራዋንም እየሰራች ነበር። የሷ ስራ ህግን ማስከበር እና በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነበር። ነገር ግን ሰብዓዊነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ሲገጥማት ከስራዋ ሳትዘናጋ የሰውነት ልኳን አሳየች። ለሷ ከፖሊስነቷ በላይ እናትነቷ ፤ እህትነቷ ፤ ሴትነቷ ብሎም ሰውነቷ ቀድሟልና ሰብዓዊነትን ስራዋ አደረገች። አሁን ችግር የሆነብን ከሰው ይልቅ ብሔራቸውን፤ ሃይማኖታቸውን፤ ቋንቋቸውን፤ ብሔራቸውን፤ መሬታቸውን፤ ስልጣናቸውን የሚያስቀድሙ ሰዎች በዝተው ነው። ኢትዮጵያውያን ለሰው ቅድሚያ መስጠት ካልጀመርን ለውጥን ማምጣት እንደማንችል ማወቅ አለብን። ስለ አንዲት ነፍስ የማይጨነቅ ሰው ስለሺዎቹ ሊጨነቅ አይችልም፡፡
ስናጠቃልለው፤ ያለንበት ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ወዲያም ወዲህም ብንዞር የሚታየው እና የሚሰማው ነገር የሚያበረታ አይደለም። የሚታይ የሚሰማ በጎ ነገር ጠፍቶ አይደለም። በጎ የሚደርግም ሰው ጠፍቶ አይደለም። ይልቁንም በጎዎቹ ዝምታ ስለመረጡ ነው። ስለዚህ እንዲህ እንደጠቀስናቸው ሰዎች ያሉ በጎ የሚያስቡ እና ዝምታን ሳይመርጡ ያሰቡትን በጎነት በተግባር የሚያደርጉ ሰዎች ጥቂትም ቢሆኑ እነሱን ማመስገን አለብን። የበጎነት ትንሽ የለውም። የፈጸሙት ተግባር የተለመደ እና ምንም ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነገር ቢሆንም ዛሬ ዛሬ የተለመደ እና ማንም ጤነኛ ሰው ያደርገዋል የምንለው ነገር ሁሉ ነውና እየጠፋ ያለው እንዲህ አይነቱን ነገር ሲደረግ ማበረታታት አስፈላጊ ነው። በቀጣይ እንዲህ አይነቱ ሰው እና እንዲህ አይነቱ ተግባር ተበራክቶ አስደናቂ መሆኑ እስኪቀር ድረስ ግን እንዲህ ያሉትን በጎዎች ያብዛልን ብለን ጽሑፋችንን ቋጨን፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014