ይሄ “የ’ኛ” የሚባል ነገር ጉድ እያፈላ ነው። በአዋጅ “የ’ኛ” የሚለው ቀርቶ በ”የ’ኔ” የተተካ እስኪመስል ድረስ “የ’ኛ” የሚለው አደጋ ላይ ወድቋል። ችግሩ “የ’ኔ” እና “የ’ኛ” ተቃርኖ መኖር ብቻ አይደለም፤ ችግሩ ሌሎችም መኖራቸው ነው። ለምሳሌ “መጤ”፣ “ነባር” አይነት ዳይኮቶሚዎች። እነዚህን የቀፈቀፈውም የዘመኑ ፖለቲካችን ነው። ለጉዳያችን መግቢያ “የ’ኛ ፖለቲካ” ብለን ስንነሳ፣ የፈጠራ መብት ባለቤትነትን ስለ ማስከበር ልናወራ ወይም፣ የራሳችን የሆነ ያለን ስለመሆኑ ለመደስኮርም አይደለም። ይልቁንም፣ ሁሌም ወደኋላ የሆነውን ጉዟችንን በተመለከተ፣ የአሁኑ ዘመን ፖለቲካ፣ ፖለቲከኞቻችንን መሬት ላይ ያለውን የእነዚህ ሁለቱን ድርብ ውጤት በተመለከተ ጥቂት ለማለት ነው።
“የ’ኛ ፖለቲካ” ስንል መርህ አለው ወይስ የለውም፤ የሚከተለው ርእዮት አለው ወይስ የለውም፤ የቆመበት መሰረትስ ቢሆን ምንድን ነው? የሚሉትን “ቀላል፣ ቀላል” ጥያቄዎች ለመመርመር፤ መርምሮም ምላሽ ለማግኘት አይደለም። ወይም፣ ፖለቲካችን እንደ ሩሲያ ኮሚኒስት ነው፤ አይ፣ እንደ ቻይናው መሰረቱን ኮንፊሺየስ ላይ የገነባ ኮሚኒስት ነው፤ አይደለም፣ እንደ ጀርመኑ ደሀን ማእከል ያደረገ የሶሻል ዲሞክራሲ ርእዮት አራማጅ ነው፣ ወዘተርፈ … እያልን አንድ የፖለቲካ ማንነት ላይ ልናቆመው፤ ያለ ባህርይው ልናስጨንቀው እና የሌለውን ልንሰጠው አይደለም።
“የ’ኛ ፖለቲካ” ያለበትን ሁኔታ፣ እየሆነ፣ እያደረገ ያለውን ተግባር፤ በተከታዮቹ ዘንድም ይሁን ሌሎች እያሰረፀ ያለውን አመክንዮ (ከተባለ)ለማሳየት፤ እንደ ዜጋ መሬት ላይ ያለውን እውነት መሰረት አድርገን ለማሄስ ነው። የእኛን ፖለቲካ በተመለከተ ብዙ ተብሏል። ተደግፏል፤ ተነቅፏልም። ይሁን እንጂ፣ በአብዛኛው ለወገነው ያደላ አስተያየት ነው ሲዘንብ የኖረ እንደመሆኑ ሲስተካከል አይታይም። አለመስተካከሉንም ከመብት ጥሰት በመጀመር ልናየው እንችላለን።
“የ’ኛ ፖለቲካ” የሰዎችን መብት ያከብራል ወይ ብሎ በመጠየቅ ጉዳዩን መጀመር ይቻላል። “አያከብርም” ካልን ማሳያዎቹ ብዙ ናቸውና እዳው ገብስ ነው ማለት ነው። ከላይ በመግቢያ አንቀፃችን ላይ ለመጠቋቆም እንደሞከርነው፣ አግላይ አስተሳሰቦች (እኔ#እነሱ፤ መጤ#ነባር …) ወደ አገራችን የተጋዙት(ኢምፖርት የተደረጉት) በፖለቲካ ፓርቲዎቻችን አማካኝነት ነው። አገራችን አለም ጉድ እስኪል ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ፣ በብሔር ፖለቲካ (ያው “እኛ” ሳይሆን “እኔ” ማለት ነው) ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን የፈሉባት ምድር ነች።
ይህ ሁሉ ይሆን ዘንድ በሩን የከፈተው የድህረ 1983 ዓ.ም “ዲሞክራሲን ያለገደብ” የተባለለት ወቅት ሲሆን፤ ያንን ተከትሎ ባልተጠበቀ ፍጥነት ቁጥራቸው መቶን የዘለለው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን (በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 111 መድረሳቸውን በአመታዊ ሪፖርቱ አስታውቆ ነበር) ዛሬም ድረስ ከ30 ምናምን አመት በኋላም ከብሄር የተላቀቀ አስተሳሰብ ብቅ ሊል አልቻለም። ለአገርና ሕዝብም ከመጠላለፍ፣ መገፋፋትና ከሴራ የተላቀቀ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊያገኙ አልቻሉም።
“የ’ኛ ፖለቲካ” አንድ ሰው መስማት ያልፈለገውን እንዳይሰማ፤ መስማት የሚፈልገውን እንዲሰማ ምንም አይነት እድል አይሰጥም፤ አፋኝ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካን መስማት እማይፈልጉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም። እነሱ አይፈልጉ እንጂ ዙሪያቸውን የከበባቸው ብሔርንና መሰል ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ ነገሮች ናቸው። አልሰማም ቢሉ እንኳን አለመስማት አይችሉም። በሌላው ዓለም ቢሆን አንድ ሰው ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ መስማት የማይፈልገውን ያለ መስማት መብቱ የተጠበቀ ነው። “የ’ኛ ፖለቲካ” ግን ይህንን አይፈቅድም። ካልሰማነው ይፈርጀናል። “የ’ኛ ፖለቲካ” እስካሁን ያመጣው፣ ሕዝብም ከ’ሱ ያተረፈው ነገር ቢኖር የእርስ በርስ ግጭትን ነው።
“የ’ኛ ፖለቲካ” ያስተማረን ቃላት (ቮካቡላሪስ) ቢኖሩ “መጨፍጨፍ”፣ “ጭፍጨፋ”፣ “ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ …”፣ “ኢሰብአዊነት በጎደለው …” የሚሉት ናቸው። በቀን በቀን በጆሯችን በመንቆርቆራቸው ምክንያት ለምደናቸው አርፈናል። ይህ ሁሉ እንግዲህ “የ’ኛ ፖለቲካ” ውጤት ነው። “የ’ኛ ፖለቲካ” ሲያስፈልገው አገርና ሕዝቡን ሁሉ ይክዳል። ይክድና ከባእድና ባንዳ ጋር ይወግናል። ይህ ጋብቻውም አገር በሰላም ውላ በሰላም እንዳታድር አድርጎ ዜጎችን ለሰላም እጦትና ሕይወት ማጣት ይዳርጋል። ከእኛ ፖለቲካ እያየን ያለነው ይህንን ነው።
ከ”የ’ኛ ፖለቲካ” ተዋንያን አገራዊ አጀንዳ ያለው የሚመስለው በጣት የሚቆጠረው ነው። ሁሌም ክርክሩም ሆነ ውዝግቡ ነጠላ ጉዳይ ላይ ነው። ሁሌም አጀንዳ ሲመዝ አንዱን ወገን አስደስቶ፤ ሌላኛውን አሳዝኖ፤ አንዱን ባንዱ ላይ ሊያነሳሳ በሚችል መልኩ እንጂ ሕዝብን የሚያሳትፍ፤ “እኛ”ን መሰረት ያደረገ አይደለም። አግላይ ነው። አንዳንዴ ይህ ተግባሩ “አቃፊነት እርሜ”፣ “አቃፊነት ለምኔ” ያለ ሁሉ ያስመስልበታል። “የ’ኛ ፖለቲካ” በዚህ ሲሉት በዚያ ነው። “አገራዊ ፖሊሲህስ?” ሲሉት፤ “እሱን አሁን አይደለም፤ ከመረጣችሁኝ በኋላ አቀርባለሁ” የሚል መልስ የሚሰጥ አላጋጭ ነው።
“የ’ኛ ፖለቲካ” አመሉ ብዙ ሲሆን፤ “ንትርክ ውስጤ ነው” ያለ ይመስል፤ ሁሌም ንትርክ፣ ሁሌም ውዝግብ ሁሌም …. ነው። ሥልጣንን እየፈለገ ገዢውን ፓርቲ ሥልጣን ላይ ሙጭጭ አለ ይላል፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚሆን አንድ ጡብ ሳያስቀምጥ ዲሞክራሲ የለም ይላል፤ ስለ ሰላም ሳያስተምር ሕዝብ ሲጋጭ ሲያይ ሕዝቡን ጨረሰው ይላል፣….። እውነታው ግን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በየክልሎችና ክልል ከተሞች በመዘዋወር ከሕዝቡ ጋር በመወያየት ያረጋገጠውና በሚዲያ ይፋ ያደረገው (በወቅቱ የኮሚሽኑ ምክትል ሊቀመንበር የትነበርሽ ንጉሴ እንደተናገሩት) ሲሆን፤ እሱም “በእኛ መካከል፣ በሕዝቡ መካከል ምንም ችግር የለም። እኛ ሁሌም አንድ ነን። እኛን የሚያጫርሱን ፖለቲከኞች ናቸው። እነሱ ካረፉ ሰላም ይሆናል።” የሚል ነበር። (በወቅቱ “የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈጠሩ 21 ግጭቶችን እያጠና መሆኑን በሚል ቀርቦ የነበረን ዜና ያስታውሷል።)
“የ’ኛ ፖለቲካ” ራስ ወዳድ ነው። ማእከል አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ሕዝብንና አገርን ሳይሆን እራሱንና እራሱን ብቻ ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ ያለንበት የከፋ የእርስ በርስ ጦርነትና ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ባልተከሰተም ነበር። “የ’ኛ ፖለቲካ” ጨካኝ ነው። አሁን በአገራችን ላይ እየደረሰ ያለውና ይደርሳል ተብሎ የሚሰጋውም ሆነ የሕዝብ መጨነቅ፤ ማዘን፤ መማረር፣… ምንም አይመስለውም። ይህ ሁሉ እሳት ሲነድ እናጥፋው ያለ ፖለቲከኛ ማግኘት አልተቻለም። ለዚህም ይመስላል አንዲት እናት “የዘንድሮ ፖለቲከኛ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም” አሉ እየተባለ ሲነገር የነበረው።
“የ’ኛ ፖለቲካ” ደም ማፋሰስ እጣ ክፍሉ ነው፤ ዜጎችን ወደ ግጭትና እርስ በእርስ ጦርነት ማሰማራት የኑሮ ዘዴው ነው፤ የዜጎችን፣ በተለይም ወጣቱን በማህበራዊ ሚዲያ ማደንዘዝ የህልውናው ጉዳይ ነው፤ ስልጣን ጥሙ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ከዚህ የፀዳና በትክክልም “የ’ኛ ፖለቲካ” የሚሉት የፖለቲካ ስሪት ያስፈልጋቸዋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲሰ ዘመን ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም