አንድ ወዳጄ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ያየሁት ጽሁፍ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በሶ ሲበጠብጥ እንጂ አገር ሲበጠብጥ አያምርበትም ይላል። ጽሁፉ ቀልድ አዘል ቢሆንም እውነታነት ደግሞ አለው። ምክንያቱም ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ወጣቶች ስንቃቸውን ቋጥረው፤ ቤተሰባቸውን ተሰናብተው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የገቡት ለአንድ አላማ ነው – ለትምህርት። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደግሞ ዕውቀት ሲሸምቱ እንጂ ሲረባበሹ ማየት ለማንም ጤነኛ አዕምሮ ላለው ሰው የሚያስደስት ጉዳይ አይደለም።
የሆነ ሆኖ የፖለቲካ ወላፈኑ ያረፈባቸው እና በዘረኝነት መርዝ በተበከሉ ሰዎች በሚረጩት ችግር ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ግርግሮች ሲነሱ ይስተዋላል። ከብዙ በጥቂቱ በአምቦ፣ በሐሮማያ፣ በአዲግራት እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በቅርብ ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶችን በዋቢነት መውሰድ ይቻላል።
ሰሞኑንም የበርካታ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋ ተግባር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተፈጽሞ ሦስት የወደፊት የአገር ተስፋዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ ‹‹ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል›› በሚያስመስል ሁኔታ የአሶሳው እሳት ወላፈን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ተዛምቶ ነበር። ይሁንና የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በተማሪው ጥረት መቆጣጠር መቻሉን ተማሪዎች ያስረዳሉ።
ተማሪ መሐመድ ሳኒ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው። ትውልዱ በወሎ ከሚሴ አካባቢ ነው። ጎንደርን በታሪክ ብቻ ነበር የሚያውቃት። ወጣቱ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መመደቡን ሲያውቅ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚመጡ ወጣቶች ጋር እና ከጎንደር አካባቢ ህብረተሰብ ጋር ሊኖረው የሚችለውን ጊዜ እያሰበ መደሰቱን ያስታውሳል። ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጣም ከተማሪ እስከ አገር ሽማግሌዎች በጥሩ አቀባበል አስተናግደውታል።
ጣፋጩ የዩኒቨርሲቲ ጊዜውም በትምህርት ታጅቦ በሰላም እየቀጠለ ነበር። ያለፈው ዓርብ ዕለት ግን አንድ የሆነ ሆኖ የፖለቲካ ወላፈኑ ያረፈባቸው እና በዘረኝነት መርዝ በተበከሉ ሰዎች በሚረጩት ችግር ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ግርግሮች ሲነሱ ይስተዋላል። ከብዙ በጥቂቱ በአምቦ፣ በሐሮማያ፣ በአዲግራት እና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች በቅርብ ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶችን በዋቢነት መውሰድ ይቻላል።
ሰሞኑንም የበርካታ ኢትዮጵያውያንን አንገት ያስደፋ ተግባር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተፈጽሞ ሦስት የወደፊት የአገር ተስፋዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ ‹‹ አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል›› በሚያስመስል ሁኔታ የአሶሳው እሳት ወላፈን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲም ተዛምቶ ነበር። ይሁንና የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በተማሪው ጥረት መቆጣጠር መቻሉን ተማሪዎች ያስረዳሉ።
ተማሪ መሐመድ ሳኒ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው። ትውልዱ በወሎ ከሚሴ አካባቢ ነው። ጎንደርን በታሪክ ብቻ ነበር የሚያውቃት። ወጣቱ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ መመደቡን ሲያውቅ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚመጡ ወጣቶች ጋር እና ከጎንደር አካባቢ ህብረተሰብ ጋር ሊኖረው የሚችለውን ጊዜ እያሰበ መደሰቱን ያስታውሳል። ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጣም ከተማሪ እስከ አገር ሽማግሌዎች በጥሩ አቀባበል አስተናግደውታል።
ጣፋጩ የዩኒቨርሲቲ ጊዜውም በትምህርት ታጅቦ በሰላም እየቀጠለ ነበር። ያለፈው ዓርብ ዕለት ግን አንድ ያልጠበቀው ነገር በዩኒቨርሲቲው ተስተናግዷል።
በዕለቱ በጠዋት የተሰባሰቡ ተማሪዎች ማን እንዳነሳሳቸው እና መልዕክቱን ማን እንዳስተላለፈው በማይታወቅ ሁኔታ ተገናኝተው ሰልፍ ማካሄድ እንደጀመሩ ተማሪ መሐመድ ይናገራል። እርሱ እንደሚለው፤ የአሶሳውን የተማሪዎች ሞት እያነሱ ዘረኝነት ያመጣው ጣጣ እንደ ሆነና ማንም ወገናቸው እንዳይሞት መልዕክት ያስተላልፉ ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በየማደሪያዎች ህንፃ ላይ የኀዘን መግለጫ ተለጥፎ ተገኘ። የዓርብ ዕለት ትምህርትም ሳይካሄድ ቀረ። በቀጣዩ ቀንም ሰልፉ ሲካሄድ ውሎ በግምት ከሦስት መቶ በላይ የሚጠጉ ተማሪዎች ተቀላቀሉት።
ከሰዓት ላይ ደግሞ ማን እንዳሰራጨው የማይታወቅ መረጃ በግቢው ናኘ። ሁለት ሴት ተማሪዎች በዘረኝነት መንፈስ የታጀበ አጸያፊ ንግግር እርስ በርስ መለዋወጣቸው ከተማሪው ጆሮ ደረሰ። ወዲያው ተቃውሞ እና ግርግሩ ተጀመረ። በወቅቱም ፖሊስ ግርግሩን ለማረጋጋት ወደ ግቢው ገብቶ አስለቃሽ ጭስ እስከ መጠቀም ደርሶ ነበር። ምንም የአካል ጉዳት እና ሞት ሳይከሰትም ተማሪው እርስ በርሱ ተነጋግሮ አሁን ላይ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በአሉሽ አሉሽ የተጀመረው ግርግር ወደ ዘር ጠብ መቀየሩ አግባብ እንዳልሆነ በየዶርሙ በተደረገ ምክክር የአንድ የኢትዮጵያ ልጆችን ሊበትን የመጣ የጠላት ሴራ መሆኑ ግንዛቤ በመያዙ ሁሉም ፊቱን ወደ ትምህርቱ አዙሯል።
ወጣት ብርሃኑ ገዳሙ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ነው። ግርግሩ ሲከሰት ማንም ተማሪ ወደ ዘረኝነት ችግር ይቀየራል ብሎ እንዳልገመተ ይናገራል። እርሱ እንደሚለው፤ አንድ ጊዜ ከተከሰተ በኋላ ግን ወደ መፍትሄ ለመምጣት በመጀመሪያ የተወሰኑ የህግ ተማሪዎች ለእራሳቸው የሥራ ድርሻ ሰጥተው ተማሪው ችግሩን በእራሱ መንገድ እንዲፈታ ኮሚቴ ማዋቀር ጀመሩ።
ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋር እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ድረስ ስለጉዳዩ ውይይት ተደርጎ ጉዳዩ የማንንም ሰብዕና በማይነካ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ ፍቃድ ተሰጠ። በጥቂት ተማሪዎች የተጀመረው በጎ ተግባር እየተስፋፋ በየዶርሙ እና በየትምህርት ክፍሉ ውይይቶች ተደረጉ። ማንም ተማሪውን ሊለያየው እንደማይችል በውይይቶቹ ላይ መግባባት ሲደረስም አጠቃላይ ስብሰባ ተካሂዶ ግርግሩ ሰከነ። በተማሪዎች መካከል የተፈጠረውን ችግር እራሱ ተማሪው በማስተካከልም ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አርዓያ የሚሆን ተግባር ፈጽሟል።
ወጣት ሰሚራ መሐመድ ደግሞ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ናት፤ እርሷ እንደምትለው፤ አንዳንድ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ችግር በመፍጠር እና በዩኒቨርሲቲው ሰላም እንደሌለ ለማስመሰል ይሞክራሉ። ይህም የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ አልተመቸንም በሚል ሰበብ ወደ መጡበት አካባቢ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ለመማር ፍላጎት ስላላቸው ነው። በመሆኑም ምን ጊዜም ተማሪዎች ከመነሻቸው ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲላኩ ወደ አንድ የወገናቸው ትምህርት ተቋም እንደሚሄዱ ተነግሯቸው በልበ ሙሉነት እንዲንቀሳቀሱ መደረግ አለበት።
በአንዳንድ ማህበራዊ ድረ-ገጾች እንደሚሰራጨው ግን ተመድበው በሚሄዱበት ዩኒቨርሲቲ ችግር ካለ ‹‹እኛ እንቀበላችኋለን›› የሚሉ ተቋማት መኖራቸው ነው። ይህ ደግሞ በውጤትም ሆነ በትምህርት ምርጫ ደስተኛ ያልሆነን ተማሪ ለረብሻ የሚያነሳሳ ቅስቀሳ በመሆኑ ሊቆም ይገባል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪው በችግሩ ዙሪያ እርስ በርሱ ተነጋግሮ እና እጅ ለእጅ ተያይዞ እርቅ በመፈጠሩ ትምህርት መቀጠሉን ወጣት ሰሚራ ትናገራለች። በሳል ተማሪዎች በፈጠሩት በጎ ተግባር ውይይት ተካሂዶ ስምምነት ባይደረስ ግን የከፋ ችግር ሊከሰት ይችል ነበር። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲውም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ለመፍትሄው ለደከሙ ወጣቶች እውቅና በመስጠት አርዓያነታቸውን ሊያጎላው ይገባል ባይ ናት።
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ወልደማርያም በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በአሶሳ እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ሳይዛመት መቆጣጠር መቻሉን ይገልጻሉ። በመንግሥት ደረጃ የተጀመረው የችግሩን ጠንሳሾች ለይቶ የማውጣት ሥራ በህግ ተይዞ እየታየ መሆኑን ያስረዳሉ።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የአገር ሽማግሌዎችን እና ታዋቂ ግለሰቦችን ያሳተፈ የማነቃቂያ ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ውይይቶቹ አለመረጋጋትን ሊፈጥሩ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ የመከላከል ጉዳይ ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን ነው የሚጠቁሙት። በመሆኑም በየጊዜው ክትትል እየተደረገ የዩኒቨርሲቲዎች የእውቀትና የሰላም መድረኮች እንደሚሆኑ ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2011
በጌትነት ተስፋማርያም