የሰው ልጅ ሕይወት ቀጣይነት የሚኖረው የግብርና ኢኮኖሚ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጠው በመሆኑ የዓለም ሀገራት ሙሉ ኃይላቸውን በግብርና ልማት ላይ በማዋል በቂ ምርት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ይስተዋላል።ጥቂት የማይባሉ አገራትም ከራሳቸው አልፎ ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ የገቢ ምንጫቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ ተሞክሮውን በመውሰድ ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ማደግ ጥረት ብታደርግም ምርትን በበቂ ሁኔታ አምርቶ ፍላጎቷን ለማሟላት አልቻለችም። በዚህም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆኑ የእህል ዓይነቶችን ከውጭ አገራት በማስገባት ላይ ትገኛለች።
የግብርና ሚኒስቴር የቅርብ ጊዜ መረጃ እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን ሳይጨምር 123 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚጠጋ የውሃ ሃብትና ከ36 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሊለማ የሚችል መሬት ቢኖርም አገሪቱ ከተፈጥሮ ሃብቷ የምትፈልጋቸውን የሰብል ዓይነቶች ማምረት ባለመቻሏ እስካሁን የለማው መሬት 16 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው። ለአብነት ስንዴ በአገሪቱ ከጤፍ፣ከበቆሎና ከማሽላ ቀጥሎ በአራተኛ ደረጃ የሚመረት የሰብል ዓይነት ሲሆን፤ የሚለማበት መሬት ደግሞ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር ላይ ብቻ ነው።
ከዚህ መሬት አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ብቻ ነው የሚገኘው።ቀሪው የፍጆታ መጠን ከውጭ በማስገባት የሚሸፈን ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሪው ደግሞ የአገሪቱን አቅም የሚፈታተን ሆኗል።
በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሕዝብ ቁጥርና የምግብ ፍጆታ መጠን ምርትን ማሳደግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ በመሆኑ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስልቶችን ቀይሶ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በተለይም ከፍተኛ የምርት እጥረት በሚስተዋልበትና ለአገር ውስጥ ፍጆታ ሲባል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪያችንን አሟጥጦ በሚወስደው የስንዴ ምርት ላይ ትኩረት በማድረግ በአፋር ዱብቲ ወረዳ 667 ሄክታር፣ በአሚባራ 1383 ሄክታር፣ በገዋኔ 250 ሄክታር ፣በፈንታሌ 270 ሄክታር፣ በቲቢላ 440 ሄክታር መሬትን በመጠቀም ለማምረት ተችሏል። ይህ ትልቅ እመርታ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህንን ውጤታማ ሥራ ለማስፋትና ሌሎች አካባቢዎችንም ምርታማ ለማድረግ ግብርና ሚኒስቴር ከፌዴራልና ከክልል የግብርና ምርምር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ሥራውን ለማከናወን የሚያስችለውን ምክክር ማድረጉም ይታወሳል።
በግብርናው ዘርፍ ለተመዘገበው የምርት ዕድገትና የመስኖ ልማት መስፋፋት የላቀ አስተዋፅኦ ያደረገው የተቀናጀ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ በመሆኑ በአሁኑ ወቅትም ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑ አያጠራጥርም።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተገነባው ጠንካራ የልማት ሠራዊት በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ መስክ የመሬት ለምነትን የመጠበቅ፣ የውሃ አማራጮችን የማሳደግና የመስኖ ልማቶች እንዲስፋፉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።
በአገሪቱ በአብዛኛው ከፍተኛ ምርት ማምረት ይቻላል ተብሎ የሚገመትበት የክረምት ወቅት ቢሆንም በበጋው የበልግ ወቅትም ከፍተኛ ምርት ማምረት እንደሚቻል ያለፉት ዓመታት ተሞክሮ ያረጋግጣል።ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት ለበልግ ሥራ የተሰጠው ትኩረት ከሌሎቹ የመኸርና የበጋ ሥራዎች ጋር ሲነጻጸር እኩል እንዳልሆነ ተገምግሞ ዘንድሮ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በበልግ እርሻ ለመሸፈን የታቀደው የመሬት ስፋት በ 2011 ዓ.ም ከ ሁለት ነጥብ አንድ ሄክታር ያላነሰ እንዲሆን ዕቅድ ተይዟል።
በበልግ ወቅት የሚገኘው ምርት ከአጠቃላይ የክልሎች ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ከ60 በመቶ የማያንስ ሲሆን፤ አጠቃላይ የበልግ እርሻ የሚሸፍነው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ነው። ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ደግሞ ከ5እስከ ሰላሳ በመቶውን እንደሚሸፍኑ፤ በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን አካባቢዎች ፤ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ፣ ደቡብ ወሎ ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ፤ በደቡብ ክልል ከፋ ፣ ቤንች ማጂ ፣ ሸካ ፣ ዳውሮ ፣ ደቡብ ኦሞ ፣ ወላይታ ፣ ጋሞ ጎፋ ፣ ሲዳማ ፣ ጌዲዮ ዞኖችና የቄዳና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ፣ ቦረና ፣ ጉጂ ፣ ባሌ ፣ ምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሀረርጌ ሥራዎች በተጠናከሩ ሁኔታዎች ከተከናወኑ ቀደም ሲል በስንዴ ምርታማነት ላይ የታየው ዓይነት ውጤት እንደሚገኝ አመላካች መሆኑን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወቅታዊ ትኩረት ያሳያል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሕዝብ ብዛት፣ የመሬት ጥበት፣ የምርታማነት መቀነስ ፣እንዲሁም የአየር መዛባት የሚያስከትለው ተፅዕኖ ሊገታ የሚችለው የተጠናከረ የግብርና ልማት በማካሄድ በተለይ ደግሞ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሲስፋፋ በመሆኑ የጉዳዩ ባለቤት መሥሪያ ቤቶች መላ ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ወደላቀ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉት ይገባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2011